Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየምርጫ ጎዳና

የምርጫ ጎዳና

ቀን:

ዞሲማስ ሚካኤል በጎልማሳ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት (1923-1967) ፍጻሜ ዋዜማ  ለሕግ መወሰኛና የሕግ መምርያ ምክር ቤቶች እንደራሴዎች ምርጫ ውድድር ሲካሄድ በለጋ ዕድሜው ተመልክቷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ መካከለኛ ወረዳ ግዛት፣ በካዛንቺስ አጥቢያ ተወዳዳሪ የነበሩት አቶ ግርማቸው ፊሊክስ የምርጫ ቅስቀሳቸውን ከግንፍሌ ድልድይ አጠገብ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተነስተው፣ የብራዚል ሥሪት በሆነችው ፎልስቫገን መኪናቸው ሆነውና አስፋ ወሰን ትምህርት ቤቱ ደጃፍ ቆመው ‹‹ምረጡኝ›› እያሉ ሲቀሰቅሱ ያስታውሳል፡፡

የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ዘውዱን በገለበጠ በ13ኛው ዓመት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን (ኢሕዲሪ) የሚመሠረትበት የብሔራዊ ሸንጎ ምርጫ ሲካሄድ በሙሉ ቁመናው አይቶታል፡፡ ለሸንጎው አባልነት ዝሆን፣ አንበሳና ጎሽ የምርጫ ምልክት ሆነው የተደረገውን የ1979 ዓ.ም. ምርጫ ላይም ተሳትፏል፡፡ ታዋቂው ገጣሚና የሥነ ጽሑፍ መምህሩ ደበበ ሰይፉ የካዛንቺስ ተወካይ ሆኖ በዝሆን ምልክትነት ለብሔራዊ ሸንጎ ሲመረጥም እማኝ ነበር፡፡ ኢሕዲሪ ለሁለተኛ ዙር የሸንጎ ምርጫ ሳይበቃ፣ የሪፐብሊኩ 4ኛ ዓመትም ሳይጠናቀቅ፣ ሥርዓቱ እንደ ዘውዱ ሁሉ ሲያከትምም እማኝ ነበር፡፡

ደርግ አክትሞ ሕወሓት መሩ ኢሕአዴግ፣ በምሕፃሩ ኢፌዴሪ የተባለውን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን ከመሠረተ በኋላ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ አምስት ዙር ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡

በዘመነ ኢሕአዴግ ከተካሄዱ አምስት ምርጫዎች መካከል ‹‹ትንግርታዊ›› የተሰኘው የግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. ምርጫ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ነበር፡፡ የምርጫ ውጤቱን ተከትሎ ‹‹ተጭበርብሯል››፣ ‹‹አሸንፌያሁ – አላሸነፍክም›› ውዝግብ የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈ ለአካል ጉዳት ያበቃ ጽልመትም የተስተናገደበት ነበር፡፡

ልዩ ክስተት የነበረው ምርጫ 97 በተቃዋሚዎችና በገዥው ፓርቲ መካከል የተደረጉ የቀጥታ ሥርጭት ክርክሮች፣ ከመገናኛ ብዙኃን ባሻገር በሞባይል ቴሌፎን በአጭር የጽሑፍ መልዕክት (ኤስኤምኤስ) ጭምር ቅስቀሳው ተጧጥፎበታል፡፡ የዘንድሮው የሰኔ 14ቱ ምርጫ 2013 ሞባይልን እንደ መቀስቀሻ በአገልግሎት ላይ ባይውልም፣ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ግን ከወርኃ ሚያዝያ ጀምሮ እያሰለሰ ‹‹ለምርጫ ተመዝገቡ፣ መሪዎችሽን ምረጪ…››፣ እያለ የተለያዩ መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ ሰንብቷል፡፡

በዘመነ ኢሕአዴግ ከነበሩት ምርጫዎች ከዋና ዋና ተቀናቃኞች መካከል የሚጠቀሱት ገዥ ፓርቲው ኢሕአዴግ የምርጫ ምልክቱን ‹‹ንብ›› ሲያደርግ፣ ተቃዋሚው ቅንጅት ደግሞ ባለ ሁለት ጣት ‹‹V›› ምልክት ነበረው፡፡ በዘንድሮ ምርጫ ከኢሕአዴግነት ወደ ‹‹ብልፅግና›› የተለወጠው ገዥው ፓርቲ አዲስ የምርጫ ምልክት አበጅቷል፡፡ የቀድሞውን ቅንጅት ምልክትን ግን ሌላ ፓርቲ ወስዷል፡፡

የምርጫ ሥነ ቃል ትውስታ

በምርጫ 97 ሒደት ከቅድመ ምርጫው ከሚያዝያ ወር እስከ ድኅረ ምርጫ ሰኔ ወር ድረስ በኅብረተሰቡ ዘንድ በቃል ግጥሞች፣ በቀልዶች፣ በኃይለ ቃሎች፣ በዘፈን ግጥም የታጀቡ ሥነ ቃሎች መታየታቸውና መደመጣቸው አይዘነጋም፡፡ ከእነዚህም መካከል ሪፖርተር በሚያዝያ 16 ቀን 1997 ዓ.ም. ዕትሙ ያወጣው የሠዓሊ ሮማን ካሳ የካርቱን ሥዕሎች ዓውደ ርዕይ ዘገባ ላይ የሠፈረው ቀልድ ይገኝበታል፡፡

‹‹ሁለት ሴቶች ተጣልተዋል፡፡ ለገላጋይ አስቸግረዋል፡፡ ከመሐል አንዱ ጎረምሳ ገብቶ ግራና ቀኝ ለይቶ ይገላግላቸዋል፡፡ ሴቶቹ ግን አምረዋል፤ በተለይ አንዷ ስድቧን ታንበለብለዋለች፡፡ ገላጋዩም ተቸገረ፡፡ እንዲህም አለ፡፡

‹‹አንቺ! ምን አለበት ስድቡን ብተይው?››

እርሷም መለሰች፤

‹‹ባክህን ወደዛ! እንኳን እኔ ፓርቲዎችም አልተባሉም፣ እሺ፡፡››

በሌላ አጋጣሚ የቀረበውም ቀልድ ይህን ይመስላል፡፡

‹‹ከበርቴው ሼክ መሐሙድ አልአሙዲ፣ የበላይ ጠባቂ የሆኑለት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ሊገነባው ላሰበው አዲስ ስታዲየም 80 ከመቶ ወጪውን እንደሚሸፍኑ በገለጡበት መድረክ ለብሰው የተገኙት ‹‹ንብ›› ያለበት ካኔቴራ ነበር፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የክለቡ ደጋፊዎችና ከንቲባ አርከበ ዕቑባይ ተገኝተዋል፡፡ ከበርቴው የኢሕአዴግን የምርጫ ዓርማ ያለበት ቲሸርት ከማድረጋቸውና ‹‹የምረጡ ቅስቀሳ›› በድምፅ አልባ ማድረጋቸው ሳያበቃ፣ ‹‹የጊዮርጊስን V ዓርማ የወሰዱትን እናስመልሳለን›› በማለት፣ ቅንጅት በእጅ ጣት ምልክት መጠቀሙን ይኮንናሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አንዱ የጊዮርጊስ ደጋፊ ‹‹እንዴ ሼኩ ‹‹V›› አስመልሳለሁ ብለው ከፎከሩ አየር ኃይልም ኢሕአዴግ የወሰደውን ዓርማዬን ንብ ካልመለሰልኝ እደበድባለሁ፡፡ እንዳይል እሠጋለሁ፤›› አለ፡፡ የአየር ኃይል የእግር ኳስ ክለብ መጠርያ ንብ እንደነበረ ልብ ይሏል፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫ ከድሮ እስከ ዘንድሮ

በዘውዳዊ ሥርዓት /1923-1967 ዓ.ም./

በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ድረ ገጽ እንደተዘገበው፣ በዘመናዊት ኢትዮጵያ በ1923 ዓ.ም. የመጀመሪያው የተጻፈ ሕገ መንግሥት ተረቆ የንጉሠ ነገሥቱን የማይገሰስ ሥልጣንን፣ የዘውድ አወራረስና የፓርላማ ማቋቋሚያ አዋጅ ይዞ በይፋ ወጣ፡፡ በዚህም ሕገ መንግሥት ተመሥርቶ የመጀመርያው ፓርላማ ተቋቋመ፡፡

 የፓርላማው ይዘት እኩል የአባላት ቁጥር ያላቸው ሁለት ምክር ቤቶች ማለትም የሕግ መወሰኛ ክር ቤት እና የሕግ መምሪያ ክር ቤት ተብለው ተቋቁመው ነበር፡፡ ፓርላማውም 1924 እስከ 1928 ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የተጠቀሱት ክር ቤቶች አባላትንም የሚመርጧቸው ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው ነበሩ፡፡ ምክንያቱም 1923  የተዘጋጀው ሕገ መንግሥት ‹‹ሕዝቡ ራሱ መምረጥ እስከሚችል ድረስ የምክር ቤቶቹ አባላት በንጉሡና በመኳንንቱ ይመረጣሉ›› የሚል አንቀጽ ስለነበረበት ነው፡፡ ይህ ፖርላማ በጣሊያን ወረራ ምክንያት እስከ 1935 ዓ.ም. ድረስ ተዘግቶ ነበር፡፡

ከነፃነት በኋላ 1935 ዓ.ም. የተቋቋመው ፓርላማም እንደፊተኛው የሕግ መምርያና የሕግ መወሰኛ  ምክር ቤቶች ነበሩት፡፡ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላትም በንጉሠ ነገሥቱ የተመረጡ ሲሆን የሕግ መምሪያ አባላት ግን እንደቀድሞው በንጉሡና በባለሟሎቻቸው አማካይነት የተመረጡ መሆናቸው ቀርቶ የአገር የሽማግሌዎች በየወረዳቸው ተሰብሰበው የሚመርጡዋቸው ባላባቶች እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ እነዚህ የምርጥ ምርጥ ተወካዮች 1935 እስከ 1948 ዓ.ም. ድረሰ ሳይለወጡ ለአሥራ አምስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡

1948 ዓ.ም. ጀምሮ ሕዝቡ ራሱ እንደራሴዎቹን በቀጥታ እንዲመርጥ ተፈቀደ፡፡ 1948-1967 ዓ.ም. በየአራት ዓመቱ አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ በወቅቱም ምርጫውን የሚያካሂደው የምርጫ ቦርድ የተቋቋመ ሲሆን፣ ከአገር ግዛት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ይሠራ ነበር፡፡

የመራጭነት መስፈርቱም ኢትዮጵያዊ መሆን፣ ዕድሜ 21 ዓመትና ከዚያ በላይ፣ በአካባቢው ለአንድ ዓመትና ከዚያ በላይ የኖረ፣ ጤነኛ አእምሮ ያለው የሚል ሲሆን የተመራጭነት መስፈርት ደግሞ ኢትዮጵያዊ መሆን፣ ዕድሜ 25 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ፣ ጤነኛ፣ በአካባቢው አንድ ዓመት ወይም ከአንድ ዓመት በላይ የኖረ፣ ሁለት ሺሕ ብር የሚገመት ተንቀሳቃሽ ንብረት ወይም አንድ ሺሕ ብር የሚገመት የማይንቀሳቀስ ንብረት ያለው መሆን ነበረበት፡፡ 

በዘመነ ደርግ  /1967-1983 ዓ.ም./

ዘውዳዊ ሥርዓቱን በ1967 ዓ.ም. በማስወገድ «ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ» በሚል ስም ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግሥት፣ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትን ያበጀው ሥልጣኑን በጨበጠ በ13ኛው ዓመት ላይ ነው፡፡

1979 ዓ.ም. 835 አባላት ያሉት የሥራ ዘመናቸውም አምስት ዓመት የሆኑ ባለ አንድ ሸንጎ ምክር ቤት በምርጫ ተሰየመ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን (ኢሕዲሪ) በ1980 ዓ.ም. ወርኃ መስከረም ዕውን አደረገ፡፡ በወቅቱ ለመራጭነት የሚያበቁ መስፈርቶችም የመራጭ ዕድሜ 18 ዓመትና በላይ፣ አዕምሮው ጤነኛ፣ በፍርድ ቤት ቅጣት ውስጥ ያልሆነ የሚል  ነበር፡፡

 በዘመነ ሽግግር መንግሥት /1983-1987 ዓ.ም./

ሕአዴግ በትጥቅ ትግል በሥልጣን ላይ የነበረውን ኢሕዲሪን ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ካስወገደ በኋላ በተካሄደው የልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ስብሰባ የሸግግር  መንግሥት ተመሠረተ፡፡ በሽግግር ወቅቱም እንደ ሕገ መንግሥት የሚያገለግል ቻርተር ፀደቀ፡፡ በቻርተሩ መሠረት 86 አባላት ያሉት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የተሳተፉበት የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ተመሠረተ፡፡ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 11/1984 ዓ.ም. በሽግግር ወቅቱ ምክር ቤት ተዘጋጅቶ በየካቲት ወር 1984 ዓ.ም. የወረዳና የቀበሌ ጊዜያዊ አስተዳደር አካላት ምርጫ ተደረገ፡፡ ብዙ ሳይቆይ በዚሁ ዓመት በግንቦት ወር 1984 ዓ.ም. የብሔራዊ፣ ክልላዊ፣ የዞን እና የወረዳ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ተካሄደ፡፡

በዘመነ ኢፌዴሪ /1987-2007 ዓ.ም./

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 102 መሠረት ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የተቋቋመ ሲቪል ተቋም ነው፡፡

የሽግግሩ መንግሥት የምርጫ ኮሚሽን ሥራውን አጠናቆ ሲጨርስ፣ በምትኩ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 64/1985 ዓ.ም. መሠረት ተቋቋመ፡፡ ቦርዱ ከተሰየመበት ከኅዳር 1986 ዓ.ም. ጀምሮ የምርጫ አዋጁ ስድስት ጊዜ ተሻሽሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከተቋቋመ ጀምሮ ያካሄዳቸው ጠቅላላ ምርጫዎች አምስት ሲሆኑ (19871992 19972002) ሁሉም በግንቦት ወር ውስጥ ተካሂደዋል፡፡ ስድስተኛው ምርጫ ደግሞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም.  የሚካሄድ ሲሆን በተወሰኑ አካባቢዎች ግን ጳጉሜን 1 ቀን እንደሚከናወን ቦርዱ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...