Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጨዋነት ለዘለዓለም ይኑር!

ሰላም! ሰላም! “ከእንጨት መርጦ ለታቦት፣ ከሰው መርጦ ለሹመት” እንዲል ነባሩ ብሂል፣ እኔም ወጉ ደርሶኝ በድምፄ ተወካዬን ልመርጥ ተዘጋጅቻለሁ፡፡ እናንተስ እንዳልል ውሳኔው በእጃችሁ ነው፡፡ “ተቀመጥ በወንበሬ ተናገር በከንፈሬ” የሚባለውን እንደራሴዬን የምመርጠው፣ የአገሬን ደኅንነትና ዘለቄታዊ ጥቅም አሸጋግሬ በማየት እንጂ በስማ በለው ቅስቀሳ እንዳልሆነ ስነግራችሁ ኮራ ብዬ ነው፡፡ ከቁም ነገሩ ይልቅ የወሬና የአሉባልታ መሐንዲሱ ስለባሰብን አይገርምህም/ሽም እያልን በአሉሽ አሉህ እንዳንጠመድ እንጠንቀቅ፡፡ የስማ በለው በሬ ወለደ ሳይሆን ተጨባጩ እውነታ ላይ ለማተኮር ልባችንን በሚገባ እናማክረው፡፡ በምርጫ ስሜት ውስጥ ሆኜ ይህንን እያሰብኩ ቤት ውስጥ በትካዜ ስንገዋለል፣ ማንጠግቦሽ አስተውላኝ ኖሮ ያሳሰበኝን እንድነግራት ወተወተችኝ። የማስበውን ብነግራት፣ ‹‹አይ ያንተ ነገር! ለአገር ለወገን የሚጠቅም ሥራ ከመሥራት ይልቅ፣ ለራሳቸው ደንታ ብቻ የሚጨነቁ እንዳለ ረሳኸው እንዴ? ይልቅ ተነስና አግዘኝ…›› አለችኝ እንስራ ለመሸከም እየታገለች። ስለውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ሳስብ የሚገርሙኝ ልዩ ባህሪያት አሉ። የማታይ መስላ ማየት፣ የማትሰማ መስላ መስማት፣ የማታውቅ መስላ አብጠርጥራ ማወቅ ተስጥኦዋ ናቸው። ማስተዋልን የታደለ ልቡ ሲበራለት ዕድለ ቢሱ ደግሞ ዓይኑም ዓያይ፡፡ ዓይኑ ብቻ ሳይሆን ልቦናውም ተዘግቷል፡፡ ላይ ላዩን ብቻ መውረግረግ፡፡ ‹ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም› ማለት ይኼም አይደል! 

‹‹ቀድሞ የተበላሸውን ብቻህን አታበጅ፣ ከሰው ልማት ይልቅ የሕንፃና የመንገድ ልማት በቀደመበት አገር በማይመለከትህ ራስህን አታሳምም…›› ስትለኝ፣ ‘ኧረ ምን ላድርግሽ’ እላለሁ በሆዴ። መቼም እሷን ባጣ ወይ ወደ ፈረደባት አሜሪካ አልያም ወደ ሰማይ ቤት ጥገኝነት እጠይቃለሁ እንጂ፣ መቼም እዚህ አገር አርፌ አልቀመጥም። እውነቴን እኮ ነው፡፡ መንግሥት አለልኝ እንዳትሉ ለራሱ ሥራ በዝቶበት ‘ቢዚ’ ነው። ይልቅ ከዕብድ መሀል የተገኘ ጤነኛ ከሆናችሁ፣ እያለሳለሰ የሚያቅፋችሁ የቆንጆ ልጅ ክንድ ላይ ይጣላችሁ፡፡ ታዲያ ያገኛችሁ ቀን ልማትና ትዳር አፍራሽን አለመጠጋት ነው አደራ። አንድም እኮ ከማጀት እስከ አገር የሚበጠብጠን ሲያገኙ የማይወድ፣ ሲሳካ ዓይኑ ደም የሚለብሰው ቁጥር በመጨመሩ ነው። ነገ እንዲህ ያለው ምቀኛም ተቆጥሮ ከ110 ሚሊዮን በላይ ሆናችሁ እንባል ይሆናል፡፡ ወይ ቁጥርና ሕይወት? የሚቆጨው ግን ብዙኃኑ ባለደጋግ ልቦች አንደበታቸው ተቆልፎ፣ ጥቂት መሰሪዎች አገር ማመሳቸው ነው፡፡ ወይ ነዶ!

ሰሞኑን የመንገድ ግንባታዎችን ጉዳይ አነሳስተን ከደላላ ወዳጆቼ ጋር አንዳንድ ነገሮች ስንጨዋወት ነበር። አንድ ወዳጄ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው ታዲያ? ‹‹አሁን ይህች አገር መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ስትሠለፍም ሆነ እንደሚደከምላት የሆነች ቀን በማን ስም ልትጠራ ይሆን?›› አለኝ። ምን ለማለት ፈልጎ እንደሆነ አልገባኝም። እናም ስጠይቀው፣ ‹‹አታይም እንዴ ቻይና ሁሉን ነገር እየሠራው? ቆይ የት ላይ ነው የእኛ አሻራ?›› ብሎ ሳይጨርስ አንድ ጓደኛችን ስልኩን አውጥቶ እዩ አለን። ዘመነ ኢንተርኔት በሚገባ የተጠቀሙበትን የትና የት ሲያመጥቅ፣ ያልተጠቀሙበትን የፎቶና የስላቅ ጎተራ አድርጎ በደካማ ጎናቸው ያዝናናቸዋል። የጓደኛችን ስልክ ሦስት የተለያዩ ፎቶዎችን ያሳያል። የመጀመርያው ፎቶ ላይ የሚታየው እንግሊዛዊ ሕፃን መጽሐፍ ሲያነብ ነው። ቀጥሎ ያለው ቻይናዊ ታዳጊ ትራክተር ይሾፍራል። ሦስተኛው የእኛው ጉድ በጫት ጉንጩን ወጥሮ ይታያል። አሁን የወዳጄ ጥያቄ ግልጽ ሆነልኝ። ሌላውም ጉዳይ እንዲህ ይገለጽልን፡፡ የምን መደናቆር ነው!

ከአምራቹ ይልቅ በገፍ ተመርቶ የአገር ሸክም የሆነው ዜጋ አሳሰበኝ። ዳሩ ብቻዬን አስቤ ምን አመጣለሁ? ብቻቸውን አስበው ብቻቸውን የታገሉ ሰዎች ዛሬ የት ናቸው? እሱን እኮ ነው የማወራው። ‹‹ምን እንደሆነ እንጃ የዚህችን ምስኪን አገር በትረ ሥልጣን የሚጨብጥ ሁሉ የሆነ ‘ፎቢያ’ ያለበት ይመስላል…›› ያለኝን ስሙን ለጊዜው የረሳሁትን ወዳጄን አስታወስኩ። አይገርምም? ጥቂት ቀደም ብሎ የኑሮ ጉዳይ ነበር የሚያረሳሳን። አሁን ላዩ ላይ የደኅንነት ጉዳይ ተጨምሮበት አረፈው። ፍርጃ እኮ ነው፡፡ ከሚቃለለው ይልቅ የሚደራረበው ችግር እያሳሰበኝ ወዳጄ የጠየቀኝን አሻራን የማሳረፍ ነገር ሳሰላስል፣ ለራሴ የሰጠሁት መልስ በየት በኩል የሚል ሆነ። እኮ በየት በኩል? ወደፊት እንራመድ የሚለው እንደ ጠላት፣ ወደኋላ የሚጎትተው እንደ ጀግና እየታየ ግራ ገባን እኮ፡፡ ዘመነ ግርምቢጥ!

ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ? ምን ሆነ መሰላችሁ? አንድ የውጭ ዜጋ ዘለግ ያለ ጊዜ ስለሚቆይ ደህና ቪላ ቤት እንዳፈላልግለት ይነግረኛል። መቼም ከልጅነታችን አንስቶ ፈረንጅ ስናይ ገንዘብ አፍሶ የሚበትን እየመሰለን አድገናልና አገር ምድሩን እንዴት እንዳካለልኩት አትጠይቁኝ። ዶላር ነዋ ጨዋታው፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅማ ሁኔታዬን ዓይቶ፣ ‹‹የብርን ዋጋ መውደቅ ባንተ እንዲህ ላይ ታች ማለት አረጋገጥኩ…›› ነበር ያለኝ። እሱ እንደሆነ የሚለው አያጣም። አሁን በእሱ ቤት ዘሎ ስለብርና ኢኮኖሚያችን ሊተነትን አስቦ ነው። ትንተና ከቀጭን ትዕዛዝ አዘል መልስ ጋር ይህችን ታህል በማይወዳደርበት አገር፣ በባዶ ጉንጭ ማልፋት በበኩሌ ትርፉ አይታየኝም። ባሻዬ አንድ አመሻሽ ላይ (በምን አንስተነው እንደነበር አላስታውስም)፣ ‹‹ገንዘባችን የመግዛት አቅሙ በመቀነሱ ኑሮን አልቻልነውም ስንል፣ ኑሮን እንዳልቻላችሁትማ የታሸገ ውኃ እየጠጣችሁ እያሳያችሁን ነው… ተብለን ነበር። ይህን ያሉት ቱባ ባለሥልጣን ዛሬ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ እላለሁ። ምን ዋጋ አለው የዛሬዎቹ ረስተውታል። አንበርብር የሚያሳዝነው እኮ የዛሬ ችግራችንን በዛሬ መነጽር የሚያይልን ሰው ማጣታችን እኮ ነው…›› ብለውኝ ነበር። መቼም አርቆም ሆነ አቅርቦ ማየት ማስተዋል ከሌለበት ጥበብ አይሆንም። ምርጫችንንም እንዲህ በጥበብ ብናደርገው ምን ነበረበት? ልብ የሚለው የለም እንጂ!

ለፈረንጁ ሳፈላልግ የነበረውን ቪላ ቤት አስሼ አገኘሁና ደውዬ በአስተርጓሚ ነገርኩት። የዘንድሮ ፈረንጅ እንኳን ከእኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ጋር ከተከበረው መንግሥታችንም ጋር መግባባት አቅቶታል፡፡ ፈረንጅ ሲለግም እንጂ መግባባት አቅቶት እንዳልሆነ የምትረዱት አምስት ደቂቃ አብራችሁ ስትቀመጡ ነው፡፡ ፈረንጅ የሚፈልገውን ካላገኘ ከወላድ የባሰ ምጥ ነው የሚፈጥረው፡፡ ፈረንጅ ሲደብረው ፊቱ በርበሬ እንደሚመስል ጊዜ ሲኖራችሁ በምናብ አስቡት። እናላችሁ ደቂቃ ሳላባክን ቤቱን እንዳሳየው ወትውቶኝ ይዤው ሄድኩ። በባለሙያዎች አሪፍ ሆኖ የተሠራ የሚያስመሠግን ቤት ነበር። በአንድም በሌላም ነገር ‘አይ የአፍሪካ ነገር’ ሲል የሚውልን ፈረንጅ አስደሰትኩት ብዬ በበኩሌ ኩራት ብጤ ተሰማኝ። ወዲያው ግን የመታጠቢያ ቤቱ የጉብኝት ጊዜ ደርሶ ባንቧውን ሲከፍተው ውኃ ከየት ይምጣ? ዘግቶ በድጋሚ ከፈተው። የለም! የቤቱ አከራይ ጣልቃ ገብቶ ‹‹ውኃ ኖ! ውኃ ኖ!›› ብሎ የባሰ አሸማቀቀኝ። ፈረንጁ ግራ ተጋብቶ አፍጦ ሲያየኝ፣ ‹‹የውኃ እናት ሞታለች በለውማ፣ ከእኔ አንተ ትሻል እንደሆን…›› ብሎኝ አረፈው። የውኃ ታንከር ማስገባት ሲገባው ተጎልቶ የጠበቀን አከራይ የአገሬን አፋቸው የታሰረ ዲፕሎማቶች መስሎኝ አናደደኝ። በስንቱ ነው የምንናደደው!

ፈረንጁ ግን በንዴት ይኼን እንግሊዝኛ አንበለበለው። ምኑም ባይገባንም በአጭሩ ሲፈታ ‘ያለ ውኃማ ምን ኑሮ አለ?’ እንደሆነ አውቀናል። ቤቱን ወዶት የነበረው ሰውዬ በውኃ አልባነቱ ምክንያት በአንዴ ሲያጣጥለው አከራዩ እዚያው ቆሞ እየታዘበ፣ ‹‹እንግዳ ሆኖ ይኼን ያህል መጨነቅ፣ እኛ ምን እንበል? ውኃ፣ ኔትወርክ፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ መልካም አስተዳደር… ሲጠፉብን ምን እንበል?›› ሲል ተቆጣ። ቤቱን ሊከራይ የመጣ አንድ የውጭ ዜጋ እንጂ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቡድን አባል አለመሆኑን አስረድቼ ካረጋጋሁት በኋላ ወረድኩበት። ‹‹ይህንን የመሰለ ቤት ሠርተህ ታንከር ማስገባት አቅቶህ መንግሥትን ስትወቅስ አለማፈርህ ይገርማል…›› ስለው ፈረንጁ ከት ብሎ ሳቀ። ጎበዝ ፈረንጅ እንዴት እንደሚሰልለን ገባችሁ አይደል፡፡ አዎ ይግባችሁ!

የኋላ የኋላ አከራዩ ታንከር እንደሚገዛ ምሎ ሲገዘት ፈረንጁ ቤቱን ተከራየው። አያ ፈረንጅ ምን እንደሚፈልግ ማወቅ ጥበብ ነው፡፡ ጥበብ ደግሞ ጥቅም ከማጣት ያድናል ለማለት ነው፡፡ እኔም ተጋግጬ ያገኘሁትን ኮሚሽኔን ተቀብዬ ማምሻውን ወደ ባሻዬና ወዳጆቻቸው ድግስ ቢጤ ለመታደም አመራሁ። መንገዴ ግን የዋዛ አልነበረም፡፡ ሐሳቤ የአገሬ ዕጣ ፈንታ በዚህ ምርጫ ይወሰን ይሆን ወይስ እንደተለመደው እዚያው ወከባችን ውስጥ ገብተን እንንቦራጨቅ ይሆን የሚለው ሰቅዞ እንደያዘኝ ደረስኩ፡፡ ምን ይደረግ!

እንሰነባበት መሰለኝ። እነ ባሻዬ ዘንድ ስደርስ ቤቱ በሞቀ ጨዋታ ደምቋል። የዝግጅቱ ታዳሚዎች በአብዛኛው በአንጋፋ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ አዛውንቶች ናቸው። ስለነፃነት ተጋድሎ፣ ስለዱር ገደሉ ውሎ፣ ለነፃነት ስለተከፈለ ታላቅ መስዋዕትነት… በየፈርጁ ይዘከራል። አካላቸው እንጂ ወኔያቸው ያልበረደው አዛውንቶች ጨዋታ መስጦኝ ሳለ ከዓመታት በፊት መንገድ ላይ ስጓዝ ሳላስበው የገባሁበት ሰላማዊ ሠልፍ ታወሰኝ። ሳናስበው የማንገባበት ምን ሠልፍ አለ ዘንድሮ? እዚህ ያኔ ከጣሊያን ወራሪ ኃይል ጋር ስለተደረገ ግብግብና በድል ስለተጠናቀቀ ትግል ቢወራም፣ ዛሬ ራሳችንን በራሳችን እያስተዳደርን የፍትሕና የዴሞክራሲ ጥያቄያችን እያደር ትኩስ የመሆኑ ሚስጥር ሊገባኝ አልቻለም። እናም አልገባ ቢለኝ ምሁሩን የባሻዬን ልጅ ጠየቅኩት። ‹‹አንበርብር ችግር አላላውስ ባላት አገር ውስጥ ተጨማሪ ችግር ከመጨመር፣ እንዴት ከዘመናት ችግር እንገላግላት የሚል ቀና ሐሳብና ተግባራዊ ዕርምጃ ካልኖረ ከንቱ ልፋት ነው…›› ብሎ በስጨት አለ። ስሜት በስንት ፐርሰንት እየጨመረ ይሆን? ከስሜታዊነት ይልቅ ምክንያታዊነት ቢበልጥ ኖሮ ምግብ ብርቃችን ይሆን ነበር? ሳይበሉና ሳይደርቡ በነገር መሞሻለቅ ይታክታል፡፡ ትክት ያለ ነገር!

በሰከነ ሐሳብና በደረጀ ተንታኔ እንጂ ስሜት የትም እንደማያደርስ ሲነገርም ለመስማት ፈቃደኛ አለመገኘቱ ድንቅ ይላል። እንዲህ ያለው ነገር ለምን በተማረው እንደሚብስ አላውቅም። በዚህ መሀል አንድ አዛውንት አርበኛ ልመርቅ ብለው ተነሱ። ሁላችንም ከመቀመጫችን ተነሳን። ‹‹መቼም እኛ…›› አሉ፣ ‹‹… የአገርን ዳር ድንበር በኃይል ጥሶ የመጣን ወራሪ ጠላት በምን ቸገረኝነት ተዘልለን ሳንቀመጥና ዕረፍት ሳንሰጥ ለዚህች አገር ነፃነቷን አስመልሰናል። አገር ሞታ ምን ኑሮ አለ ታዲያ?›› ሲሉ ሁሉም ‘እውነት ነው’ ይላሉ። ‹‹ታዲያ የዛሬው ትውልድ ከእኛ ገድልና ወኔ ብዙ ሊማር ይገባዋል። ግን በዛሬና በትናንት ጠላታችን መሀል ያለውን ልዩነት ካላወቀ ከፍተኛ ጉዳት አለው። የትናንቱ ባዕድ ወራሪ ሲሆን፣ የዛሬው ጠላታችን ግን እኛው ራሳችን ነን። አጉል ወኔ ያለ ብልኃት ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም… ብልኃት የሚጠቅመው ክፉና ደጉን ለመለየት ብቻ ሳይሆን፣ የነገውን አሸጋግሮ ለማየት ጭምር ነው…›› ብለው ከወቀሳው በኋላ ምርቃታቸውን አዥጎደጎዱት። እኛስ ከምርጫው ውጤት በኋላ ተመራርቀን ዓለምን ገድ ብናሰኝ? ምኞት አይከለከል!

እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንደ ተለመደው ‘አንድ አንድ’ ለመባባል ወጣ አልን፡፡ የተለመደችው ግሮሰሪ ስንደርስ ከአፍ እስከ ገደፍ ጢም ብላለች፡፡ የሐበሻ ልጆች ትናንትን ረስተው፣ ዛሬን አፍቅረው፣ ነገን እስከ መኖሩ ዘንግተው ከዋንጫቸው ይጎነጫሉ፡፡ ሁሉም በየጎራው ወጉን እየኮመኮመ መለኪያና ብርጭቆውን ያጋባል፣ የጎደለው ይሞላል፣ ያለቀው በሌላ ይተካል፡፡ የባሻዬ ልጅ ስሜታዊነቱ የለቀቀው ይመስላል፡፡ ‹‹አንበርብር!›› አለኝ ድንገት፡፡ ‹‹አቤት!›› አልኩት  ቢራዬን እየተጎነጨሁ፡፡ ‹‹ያለችን አንድ አገር ናት፣ እሷም ለሁላችንም በቂ ናት፡፡ ምንድነው የሚያተራምሰን?›› ሲለኝ ነገሩ ገባኝ፡፡ ስሜታችንን ከተቆጣጠርን ምንም የሚያተራምስ ነገር የለም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ምክንያታዊ መሆን ነው፡፡ ምክንያታዊ ስንሆን ችግሮቻችን መፍትሔ ያገኛሉ፡፡ በቃ! የእኔ መልስ ይህ ነበር፡፡ በስሜታዊነት ከመተራመስ ምክንያታዊ መሆን፡፡ አለበለዚያ አርበኛው እንዳሉት ጠላታችን ሌላ ሳይሆን እኛው ራሳችን ነን፡፡ ራስን መውቀስ ለምን ይፈራል? ራስን ፈርቶ ሌላውን ተዳፍሮ ይቻላል እንዴ? ምርጫውን አሳምረን፣ ውጤቱም አምሮበት ብንመራረቅ ምን አለበት? ሁላችንም አሸናፊ ብንሆን ምን ይጎድልብናል? ጨዋነት ያስከብራልና ጨዋ እንሁን፡፡ ጨዋነት ለዘለዓለም ይኑር! መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት