Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየጌርጌሴኖን ተስፋ

የጌርጌሴኖን ተስፋ

ቀን:

ሁሉም በየፊናቸው ቁጭ ብለዋል፡፡ አንዳንዶቹ ከራሳቸው ጋር ሙግት ይዘዋል፡፡ ከሌላ ሰው ጋር መግባባት የቸገራቸው መኖራቸውን መታዘብ ይቻላል፡፡ ፊታቸው ላይ ጉስቁልና፣ ጭንቀትና ፍርኃት የሚነበብባቸውም አሉ፡፡

ብዙዎቹ ራሳቸውን ማስተዳደር የሚችሉ አይደሉም፡፡ የአዕምሮ ሕመማቸው ኑሮዋቸውን አመሳቅሎታል፡፡ ጫት፣ ሲጋራ፣ ሀሺሽና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን መጠቀማቸው እንዲሁም የኑሮ ውጣ ውረድ የፈጠረባቸው ጭንቀት ለአዕምሮ ሕመም እንዳጋለጣቸው ከማዕከሉ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

በሕመም፣ በእንግልትና በመከራ ውስጥ ያለፉትን ሕሙማን፣ የጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማኅበር እየታደጋቸው ይገኛል፡፡  ማኅበሩ ከየጎዳናው ሰብስቦ ወደ ማዕከሉ ካስገባቸው ውስጥ የበርካቶቹ ሕይወት እየተለወጠ ይገኛል፡፡

- Advertisement -

ከሕመማቸው አገግመው መደበኛ ሕይወታቸውን መምራት የጀመሩም አሉ፡፡ በማኅበሩ ውስጥ አገልግሎት አግኝተውና ከበሽታው ተላቀው የራሳቸውን ሕይወት መኖር ከጀመሩት ውስጥ  አፎሚያ አሰፋ አንዷ ናት፡፡

 ከዚህ በፊት በሜክሲኮ አካባቢ ከልጇ ጋር ጎዳና ላይ ሸራ ወጥራ ትኖር እንደነበር የምትናገረው አፎሚያ፣ ጎዳና ከመውጣቷ በፊት ዓረብ አገር እንደሠራችና ከዚያም እንደተመለሰች ከቤተሰቦቿ ጋር የተመቻቸ ኑሮ እንደነበራት  አስረድታለች፡፡

ነገር ግን ባገኘችው ጥሪት ‹‹ጭፈራ ቤት አሸሼ ገዳሜ›› ትል እንደነበርና ለተለያዩ ሱስ አማጭ ዕፆች ተጋልጣ እንደነበር ያስታወሰችው አፎሚያ፣ ባልታሰበ ሰዓት ራሷን ጎዳና ላይ ማግኘቷን ተናግራለች፡፡

የምትጠቀማቸው አደንዛዥ ዕፆች ለአዕምሮ በሽታ እንዳጋለጧት፣ ከዚያም አልፎ በጎዳና ላይ እያለች የምትመገበው ምግብ መርዟት ለተለያዩ በሽታዎች ተጋልጣ እንደነበር ገልጻለች፡፡

ጥሪትና ገንዘብ በነበራት ጊዜ የተለያዩ ሱስ አማጭ ዕፆችን መጠቀሟ ብቻ ሳይሆን እሷ ‹‹ባለመጠንቀቄ›› በምትለው የአንድ ልጅ እናት መሆኗ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባት ነበር፡፡

የልጇ አባት ማርገዟን ባወቀ ጊዜ ልጁን ትቶባት እንደሄደ፣ ይኼም በኑሮዋ ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳደረሰባት አስታውሳለች፡፡ ከልጇ ጋር ሆነው በሜክሲኮ አካባቢ ለአራት ዓመታት ያህል ጎዳና ላይ መኖራቸውን ብርድና ዝናብ ረሃብ ጭምር እንደተፈራረቀባቸው ትናገራለች፡፡

በጊዜው በደረሰባት ጫና ምክንያት የአዕምሮ ሕመምተኛ ልትሆን እንደቻለች፣  በአንድ አጋጣሚ ወደ ጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማኅበር እንደተቀላቀለችና በማዕከሉ በሚደረገው እንክብካቤ ከዕለት ወደ ዕለት የመኖር ተስፋዋ እንደጨመረ አስረድታለች፡፡ በማዕከሉም በቂ የሕክምና አገልግሎት በማግኘቷ ወደ መደበኛ ሕይወቷ ተመልሳለች፡፡

ማዕከሉ ውስጥ አራት ዓመት ያህል ጊዜ እንደቆየችና በዚህም የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዳገኘች፣ አሁን ላይ መልካም ሕይወት እየኖረች መሆኑን ተናግራለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በማኅበሩ ውስጥ በእንግዳ ተቀባይነት እየሠራች ሲሆን፣ በኑሮዋም መለወጥ ችላለች፡፡

ልጇ ማኅበሩ ውስጥ በገባችበት ወቅት እንደተለያትና ዘውዲቱ መርሻ ድርጅት ውስጥ ገብቶ ትምህርቱን እየተከታተለ መሆኑን፣ አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም አክላለች፡፡

ገደላማ ቦታ ላይ የሚገኘው ጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማኅበር ክረምት በመጣ ቁጥር ለሁሉም ሥጋት ነው፡፡ ዝናብ ሲሆን መውደቅም የተለመደ ነው፡፡ ይህ ለአፎሚያና በውስጡ ለሚገኙ ከ400 በላይ ሕሙማን ብቻ ሳይሆን ለማኅበሩ መሥራቾችም ሥጋትና ችግር ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን ችግሩን የሚቀርፍ ዕርምጃ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል ተወስዷል፡፡ ማኅበሩ ለዓመታት ሲጠይቅ የነበረውን  ለማዕከል ግንባታ የሚሆን መሬት  ከአስተዳደሩ ተረክቧል፡፡

ቅዳሜ ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. የተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በተገኙበትም የማዕከሉ ግንባታን መጀመር የሚያበስረው የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

የመሠረት ድንጋዩ በተቀመጠበት ወቅት የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን መለሰ አየለ እንደገለጹት፣ የከተማ አስተዳደሩ ለማዕከሉ ግንባታ የሚውል ሦስት ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ሰጥቷቸዋል፡፡

ለማዕከሉም ግንባታ 150 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የገለጹት ሊቀ ኅሩያን መለሰ፣ የሕንፃው ግንባታ 2500 ካሬ ሜትር ላይ እንደሚያርፍ አስረድተዋል፡፡

ማዕከሉም የራሱ የሆነ የገቢ ምንጭ እንደሌለው፣ ግንባታውንም ማኅበረሰቡን በማስተባበር እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት በኩል በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ሦስት ሺሕ የሚሆኑ የአዕምሮ ሕሙማንን ከጎዳና ለማንሳት ዕቅድ እንደተያዘ፣ በአሁኑ ወቅትም 450 የሚሆኑ ሕሙማን በማዕከሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ሕሙማኑ ከሚገለገሉበት ማዕከል ውጭ የሕክምና ማዕከል ለመገንባት የከተማ አስተዳደሩ ቃል እንደገባላቸው፣ ይኼም ሕሙማኑን ለመርዳትና ወደ ቀደመው ሕይወታቸው ለመመለስ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አክለዋል፡፡

ወደ ማዕከሉ የሚገቡ ሕሙማን አስታዋሽና ምንም ዓይነት ረዳት፣ ወገንና ዘመድ የሌላቸው የአዕምሮ ሕሙማን በመሆናቸው፣ ከጎዳና የማንሳት ሥራው የሚከናወነውም ማኅበሩ ባወጣው መሥፈርት መሠረት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ ውስጥ በሚቆዩበት ጊዜ በጤናቸው ላይ ለውጥ ካላመጡ ከማዕከሉ እንደማይወጡ፣ በጤናቸው ላይ ለውጥ ያመጡትን ቀጥታ ከቤተሰብ ጋር ለማገናኘት  እንደሚሠራ፣ ቤተሰብ ለሌላቸው ደግሞ የሥራ ዕድል ተመቻችቶ ክትትልና ቁጥጥር ይደረግላቸዋል፡፡

በማዕከሉ 13 ቋሚ የሕክምና ባሙያዎች እንደሚገኙና ከአማኑኤል ሆስፒታልና ከጤና ሚኒስቴር ጋር ተቀናጅተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

ጌርጌሴኖን የአፅምሮ ሕሙማን መርጃ ማኅበር ከተመሠረተበት ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ የአዕምሮ ሕሙማንን ከጎዳና እና ከሃይማኖት ተቋማት በር ላይ በማንሳት ለ15 ዓመታት ያህል ሕሙማንን በኪራይ ቤት ሲያስታመምምና ሲንከባከብ ቆይቷል፡፡

የማኅበሩ አሁናዊ ጥሪ

 ‹‹መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ›› የሚል መሪ ሐሳብ ያለው ጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማኅበር፣ በጎ አድራጊዎችና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሁሉ ተቋሙን በተለያዩ መንገዶች ማለትም በጉልበትና በዕውቀት፣ በገንዘብና በቁሳቁስ እንዲረዱ ጥሪውን አቅርቧል፡፡ የዕርዳታ አሰጣጡንም እንደሚከተለው አብራርቶታል፡፡

‹‹በጉልበት ስንል፡ የተረጂዎችን ልብሳቸውን፣ ሰውነታቸውን በማጠብ፣ ምግብ በማጉረስና ፀበል በማስጠመቅ መርዳት ነው፡፡

‹‹በዕውቀት ስንል፡ ለተረጂዎችም ሆነ ለማኅበሩ ዕድገት ጠቃሚ ምክሮችን በመስጠት፣ በሕክምና መርዳት፣ ለማኅበሩ የገቢ ምንጭ ሊያስገኙ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና ሰዎች ይህንን በጎ ዓላማ በመደገፍ ለዘላቂ ዕርዳታ እንድንነሳ በማስተባበርና በሚችሉት ሙያመርዳት ነው፡፡

‹‹በገንዘብ ስንል፡ አንድ ሰው ከላይ የተዘረዘሩትን ችግሮች ተገንዝቦ በገንዘብ ለመርዳት ቢፈልግ በማኅበሩ ስም ጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማኅበር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ቁጥር 1000156009478 አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ብለው ማስገባት ይችላሉ፡፡ ወይም ከማህበሩ ሕፈት ቤት ድረስ በመምጣት በደረሰኝ መስጠት ይችላሉ፡፡ በቦታ ርቀት ወይም በሥራ ምክንያት የማይችሉ ከሆነ ያሉበት ድረስ በመምጣት የምንቀበል ይሆናል፡፡

‹‹በቁሳቁስ ስንል፡ ለእነዚህ ችግሮችና ሚስኪኖች ብርድ ልብስ፣ አንሶላ፣ የተለያዩ አልባሳት፣ ሳሙና እና የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በመስጠት ማገዝ፡፡

የጌርጌሴኖን የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልእንጦጦ  መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መንገድ፣  ቁስቋም 17 ቁጥር አውቶቡስ  ማዞርያ እንደሚገኝ ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...