Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹ምርጫው በውጭና በውስጥ የተፈጠረውን ተፅዕኖና የተጋረጡትን ተግዳሮቶች ለመፍታት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል››

  ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት

  ኢትዮጵያውያን ነገ ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር ይጠይቃል፡፡ በሰላም መጠናቀቁም ለኢትዮጵያውያን ከምንም ነገር በላይ ድል ነው፡፡ ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ምርጫው በሰላም መጠናቀቅ በሚኖረው ፋይዳ ዙሪያ ከታደሰ ገብረ ማርያም ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- ሥልጣን ላይ መውጣት በምርጫ ብቻ ነው ቢባልም በኢትዮጵያ የተደረጉ ምርጫዎች እክል አላጣቸውም፡፡ የምርጫ ፋይዳው እስከ ምን ድረስ ነው?

  ልጅ ዳንኤል፡- የምርጫ መኖር ዴሞክራሲን እንድንለማመድና በበለጠ እየተጠናከርን እንድንሄድ ያደርገናል፡፡ ሕዝብም መብቱን በመጠበቅ የሚያስተዳድረውን አካል ያለምንም ጣልቃ ገብነት በነፃ የሚመርጥበትን ሥርዓት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡  ይህም ሥርዓት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያችን እንደምትታወቀው አምስት ዙር ምርጫ አሳልፋ ስድስተኛውን ዙር እያስተናገደች ነው፡፡ በአምስተኛውና በስድስተኛው ዙር መካከል ብዙ የታሪክ ወጣ ገባዎችን አሳልፋለች፡፡ አንድ ሰው የሚፈልገውንና የሚያስተዳድረውን ሰው እስካልመረጠ ድረስ በምንም ዓይነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይኖራል ተብሎ አይታመንም፡፡ በሠለጠነው ዓለም እንደምናየው ኅብረተሰቡ በሰፊው እንዲሳተፍበት ከተፈለገ ዋነኛውና ትልቁ መሣሪያ ሰላም ነው፡፡ ሰላም የተጠበቀባት አገር የሚኖሩ ሕዝቦች ደግሞ የተለያዩ ሐሳቦችን በነፃነትና ሥርዓት ባለው መልኩ ሊያንሸራሽሩ፣ ተፎካካሪዎች የሚያንፀባርቁትን ሐሳብ ያለ ምንም ተፅዕኖ ሊያዳምጡና የራሳቸውን ውሳኔና የሐሳብ ቅቡልነትን ሊያረጋግጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲሠራበት ይታያል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፋንታ ላይ ለማሳረፍ የወጠኗቸውን ሐሳቦች በመገናኛ ብዙኃን በየዕለቱና በየሳምንቱ በተያዘላቸው ፕሮግራም መሠረት ለኅብረተሰቡ ሲያስተላልፉ ቆይተዋል፡፡  

  ሪፖርተር፡- በዚህ ዓይነቱ ፕሮግራም ላይ ምን ታዝበዋል? ስድስተኛው ምርጫስ ከበፊቶቹ ምርጫዎች በምን ይለያል?

  ልጅ ዳንኤል፡- ቀደም ሲል በተካሄዱት ምርጫዎች ላይ በተደረጉ ፕሮግራሞች በተደጋጋሚ ሕዝቡ ተታሏል ማለት ይቻላል፡፡ በጋዜጣም ሆነ በቴሌቪዥን እንዲህ እናደርግልሃለንና እኛ እንሻልሃለን እያሉ ሕዝቡን ግራ አጋብተውታል፡፡ ወከባና ውዥንብር ውስጥ ከተውታል፡፡ በዚህም የንፁህ ወጣቶች ደም እንደ ጅረት የፈሰሰበት የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ አሁን ግን ሕዝቡ እንደ ቀደመው አይደለም፡፡ ነቅቷል፡፡ ምን እንደሚፈልግ በግልጽ ያውቀዋል፡፡ ገዥው ፓርቲም የቀድሞዎቹን አካሄድ እርግፍ አድርጎ ትቶ ግልጽነት ባለው መልኩ ወደ ኅብረት ቀርቧል፡፡ እኔን ብቻ ምረጡኝም አላለም፡፡ ከእሱ ጋር የሚፎካከሩትን ፓርቲዎች የሚያያቸውም እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ አንድ አጋር ነው፡፡ ይህንንም እኔ በበኩሌ የማየው ለሕዝቡ እንደ አማራጭ ተድርጎ እንደቀረበለት ነው፡፡ በፊት ግን የሚደረገው ከመንግሥት ፍላጎት ውጭ ፖለቲካ የሚናገሩት ሁሉ የመንግሥት ወይም የሥርዓቱ ጠላት ተብለው ይፈረጁ እንደነበር ነው፡፡ ሕዝቡ በጎሳና በዘር መከፋፈሉ እንዲወናበድና እንዲደናገር መንገድ ከፍቷል፡፡ ስድስተኛው ምርጫ ከሌሎቹ የሚለየው በዋነኛነት ሕዝቡ መንቃቱ ነው፡፡ አሸናፊው ፓርቲ ሕዝቡ ላይ እንደበፊቱ እየፈነጨና እየጨቆነ እንዳይሄድ በማድረግ ረገድም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ፡፡  

  ሪፖርተር፡- መራጩ ሕዝብ ድምፅ በሚሰጥበት ጊዜ ምንድነው መገንዘብ ያለበት?

  ልጅ ዳንኤል፡- አሁን እኛ ያየነው በከተሞች የሚካሄደውን እንጂ ወደ ገጠሩ ዘለቅ ብለን ያየነው ወይም የዳሰስነው ነገር የለም፡፡ በዘውድ ሥርዓቱ ወቅት ምርጫ ሲደረግ እኛ አንዴ አፄ ኃይለ ሥላሴን  መርጠናል ሌላ ምን ያስፈልጋል? ተብሎ ይነገርበት የነበረው ዘመን አልፏል፡፡ ይህንን ያነሳሁበት ምክንያት የተጠቀሰው የዱሮ ዓይነቱ አመለካከትና ሐሳብ አሁንም አይጠፋም ብዬ ነው፡፡ ሰው በቅርብ የሚያውቀውንና ያበላውን ሰው ነው መምረጥ የሚፈልገው፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ የሚከሰተው ትምህርት በሌለበት ወይም ባልተስፋፋበት ቦታ ነው፡፡ በሌላ ዓለም ያየን እንደሆነ ሕዝቡ ሰውዬውን አይደለም የሚመርጠው፡፡ የሚመርጠው አስተሳሰቡን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜም ለምርጫ የቀረበውን ሰው ሐሳቡን አስተሳሰቡንና ራዕዩን ማየት ለድምፅ መስጫ ጊዜ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንዴት ነው የምትንቀሳቀሰው? የአገሪቱን ዓመታዊ በጀት እንዴት እያበቃቃንና እያከፋፈልን ሥራ ላይ እናውለው? ምን ዓይነት አካሄድ ብንከተል ነው ከቀረው ዓለምና ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የሚኖረን? ይኼስ በምን መልኩ የተመሠረተ መሆን አለበት? የሚሉትና ሌሎች ነጥቦች የትኛው የፖለቲካ ፓርቲ ነው የሚያንፀባርቀው የሚሉትንና ሌሎችንም ሁኔታ ማየት በድምፅ አሰጣጡ ላይ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው መራጩ ሕዝብ ከወዲሁ ሊገነዘበው ይገባል፡፡ 

  ሪፖርተር፡- የፊታችን ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. መራጩ ሕዝብ ድምፅ እንዲሰጥ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም የሚያስፈልገው ዝግጅት በተቻለ መጠን ዳር እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ ከሕዝቡና ከፀጥታ አስከባሪዎች ምን ይጠበቃል? ምን ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው ይላሉ?

  ልጅ ዳንኤል፡- በመጀመርያ ሕዝቡ በጊዜ ወጥቶ ድምፁን ያለምንም ተፅዕኖ መስጠት አለበት፡፡ ይህም መከናወን ያለበት እርስ በርስ በመከባበርና በመረዳዳት ነው፡፡ ይህም ማለት ድምፅ ለመስጠት በሠልፍ ወረፋ በሚያዝበት ጊዜ በተቻለ መጠን ለአረጋውያን፣ ለነፍሰ ጡሮች፣ ለአካል ጉዳተኞችና የተለያዩ የጤና ችግር ላለባቸው ሰዎች ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ ሊበጅላቸው ይገባል፡፡ የምርጫው በሰላም መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል መሠረት መኖሩን ያሳያል፡፡ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ ኢትዮጵያ ውስጥ  የሚካሄደው ምርጫ በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በምሥራቅ አፍሪካ፣ ከደቡብ አፍሪካና ከጋና በስተቀር በሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ዘንድ በአርዓያነትና በሞዴልነት ይታያል የሚል የፀና እምነት አለኝ፡፡ ይህንን የምልበት ምክንያት ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያን እንደ ታላቅ ወንድም ወይም እንደ አባትና እናት ስለሚያዩዋት ነው፡፡ ለነሱ ነፃነት አስተዋጽኦ ያደረገች አገር ከመሆኗ ባሻገር ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖት ያላት መሆኗን በመገንዘባቸው ነው፡፡ አሁን የምናደርገው ምርጫ በሰላም ይጠናቀቃል፡፡ ኢትዮጵያንም በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ አንድ ትልቅ ደረጃ ላይ ያወጣታል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት አልፎ አልፎ ተከስቶ የነበረው መፈናቀልና አለመረጋጋት ሊረግብ የቻለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የበሰለ ወይም የሰከነ አስተሳሰብና ዕይታ ስላለው ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- የድምፅ መስጫው አካባቢ ድባብ ምን መሆን ይኖርበታል?

  ልጅ ዳንኤል፡- በድምፅ አሰጣጥ ወቅት ሳልገልጸው እማላልፈው ነገር ቢኖር የድምፅ መስጫ ቦታ ወይም አካባቢ ከምንም ዓይነት ተፅዕኖ የፀዳ፣ ነፃ፣ ሰላምና ፀጥታ የሰፈነበት መሆን አለበት፡፡ ለዚህም የፀጥታ ኃይሉ በቦታው ወይም በአካባቢው ተገኝቶ ሥነ ሥርዓቱን ማስከበር ይገባዋል፡፡ ለመረበሽ ሲባል ሰካራም ወይም የአዕምሮ ሕመምተኛ ሆኖ ብቅ ሊል ይችላል፡፡ በዶላር ተገዝቶ ለመምረጥ ወረፋ ይዞ የሚጠባበቀውን ማኅበረሰብ ሊያውክ ይችላል፡፡ ስለዚህ የተለዩ እንቅስቃሴዎችን የፀጥታ ኃይሉ በትኩረትና በጥንቃቄ ሊያየው ይገባል፡፡ ሰው ሊረጋጋ ይገባል፡፡

  ሪፖርተር፡- የምርጫ ውጤቱ ተዓማኒነት ወሳኝ ነው፡፡ እዚህ ላይ ምን ይላሉ ቀኑም የሥራ ቀን ነው?

  ልጅ ዳንኤል፡- የትኛው ሥራ ነው? ከዚህ የበለጠ ምን ሥራ አለ? ዛሬ እኮ እየበላን፣ እየጠጣንና በሰላም ተኝተን የምንነጋረው ሰላም ስላለ ነው፡፡ አሁን ደግሞ እየሆነ ያለው የበለጠ ሰላም ለማግኘት፣ ኢትዮጵያ ምን እንደሆነች ለዓለም ለማሳየት ነው፡፡ በምርጫ ወቅት የማወናበዱ ነገር ልዕለ ኃይል በተባለችው አሜሪካም ተደርጓል፡፡ ትራምፕ እንዲመረጥ ያልፈነቀለው ወይም ያልሞረከው ነገር አለ እንዴ? በኢትዮጵያ ደረጃ ግን በአሁኑ ጊዜ ይህ ዓይነቱ አሳፋሪና አስነዋሪ ነገር ይሞከራል ብዬ አላስብም፡፡ ሰዎች ግን ድክመት አለብን፡፡ ይኼም የሚሆነው ራሳችንን ከመውደድና ለአገሪቷ ዕድገት ካለማሰብና ከመስገብገብ የሚመጣ ነው፡፡ አሁን ግን እንዲህ ዓይነቱ እኩይ ተግባር እንዳይፈጸም ካለፉት ምርጫዎች የተማርን ይመስለኛል፡፡ በዚያን ዘመን ያልተሸፈኑ ቀዳዳዎች አሁን ይሸፈናሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ምርጫው የድምፅ ካርድ ከመስረቅ በፀዳ መልኩ ይካሄዳል የሚል የፀና እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ ምርጫ ማጭበርበር ውስጥ የምትገባው መውደቅህን አስቀድመህ ስትረዳና የሚመርጥ ክፍል አነስተኛ መሆኑን ስትገነዘበው ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- አሜሪካ ምርጫውን ብትቀበልም ሥጋት አለኝ እያለች ነው፡፡ ሥጓቷ ከምን ይሆን? በዚህ ላይ ያልዎትን አስተያየት ቢያካፍሉን?

  ልጅ ዳንኤል፡- ሥጋቷ (ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥት ትሆናለች) የሚል ነው፡፡  አፄ ቴዎድሮ እኮ ራሳቸውን ሲገሉ የአገሪቱን ጥንካሬ ነው ያሳዩት፡፡ አፄ ዮሐንስ አንገታቸውን  በመቀላት መስዋዕት የሆኑት የኢትዮጵያን ትልቅነት ለማሳየት ነው፡፡ አፄ ምኒልክም እንዲሁ፡፡ በአብዮቱ ዘመን አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ ባህር ማዶ በመሸሽ ሕይወታቸውን ማትረፍ ይችሉ ነበር፡፡ (ለአገሬ ሠርቻለሁ እናንተ ደግሞ ከእኛ የበለጠ እንሠራለን ካላችሁ መልካም ነው) በሚል ነው ሥልጣናቸውን የለቀቁላቸው፡፡ (ያስተማርናቸው ከእኛ የተሻለ እንዲሠሩ እንጂ ልንገላቸው አይደለም ነው) ያሉት፡፡ ከዚህ አንፃር በእጅ አዙር የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት ያፈረሱት ፈረንጆቹ ናቸው፡፡ ያን ጊዜ ባለሀብቶች ወደ ሰፋፊ የእርሻ ልማት ገብተው ነበር፡፡ ኢኮኖሚውም የመነቃቃት ባህሪ አሳይቶ ነበር፡፡ ይኼ ነገር ካደረና ከዋለ አይመለስም፣ ለእኛም አይታዘዝም፣ በሚል መንፈስ ፈረንጆቹ ሥርዓቱ እንዲፈርስ ምቹ ሁኔታ ፈጠሩ፡፡ በአሁኑ ሥርዓትም እየተፈለገ ያለው ተመሳሳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ መልካም ግንኙነት ደግሞ አካባቢውን ወይም የምሥራቅ አፍሪካ ግንኙነትን ሁሉ ያጠናክረዋል፡፡ ስለሆነም ምርጫውን አስመልክቶ ፈረንጆቹ በጣም የሚያሠጋቸው አንድም ከቻይና ጋር ያለን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት አሜሪካ ፓይንት ፎር፣ ሚሊታሪ አሲስታንስ አድቫይዘሪ ግሩፕ (ማግ)፣ የአሜሪካው ሀይዌይ ወዘተ. እየተባለ 500,000 ብር ይሰጡንና በምትኩ 1,000,000 ብር ይወስዱብን ነበር፡፡ አሁን ግን ቻይና መጣችና ነገሮችን ሁሉ እንዲለወጥ አደረገች፡፡ ስለሆነም በአጠቃላይ ምዕራባውያን የሚፈልጉት ጠንካራ ሳይሆን ደካማ መንግሥት፣ ለማኝና ደሃ ሕዝብ፣ ሁልጊዜ በእነሱ ሥር እየለመነ የሚኖር ነው፡፡ የአሁኗ ኢትዮጵያ ግን ከዚህ እየወጣች ነው፡፡ በአጠቃላይ ፈረንጆች የኢትዮጵያን ትልቅነት ማየት አይፈልጉም፡፡

  ሪፖርተር፡- የድምፅን ውጤት በፀጋ ለመቀበል ምን መደረግ አለበት?

  ልጅ ዳንኤል፡- ማሸነፍ እንዳለ መሸነፍም አለ፡፡ አንድ ፓርቲ ከተሸነፈ ከሽንፈቱ መማር አለበት፡፡ እኔ አሁን እንደማየው ተወደደም ተጠላም ምርጫው ፍትሐዊና ትክክል አይደለም የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? ለምንድነው ይኼንን ያሉት? የሚለው መታየት ይኖርበታል፡፡ ዋናው ነገር አሸናፊ ይሆናል ተብሎ የተረጠረጠው ፓርቲ (በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተመካክረንና አብረን እንሠራለን) በሚል ቃል ገብቷል፡፡ ይህንን እስካደረገ ድረስ ምርጫው ትክክል አይደለም የሚሉ ሁሉ ይሰክናሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ሕገ መንግሥቱን ወደ ማሻሻል፣ የሰንደቅ ዓላማውን ወደ መለወጥና ኢኮኖሚውን ወደ ማሻሻል እንቅስቃሴ ይገባል፡፡

  ሪፖርተር፡- ሰንደቅ ዓላማው የመለወጥ ሲሉ መሀል ያለውን ምልክት ነው? ወይስ አጠቃላይ ነው?

  ልጅ ዳንኤል፡- አጠቃላዩን መለወጥ እኮ አፍሪካን እንደመለወጥ ይቆጠራል፡፡ ይህ ሳይሆን ይለወጥ የሚል ሐሳብ እየቀረበ ያለው ሰንደቅ ዓላማው መሀል ያለውን ምልክት ነው፡፡ በዘውድ ሥርዓቱ ወቅት ‹‹ሞአ አንበሳ ዘ እምነ ነገደ ይሁዳ›› የሚለው ጽሑፍና አንበሳ ምሥል ያለበት ሰንደቅ ዓላማ በንጉሠ ነገሥቱ መኪናና በቤተ መንግሥቱ ይውለበለብ ነበር፡፡ በተረፈ ዋናው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በአግድም አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ነው፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ መሀሉ ላይ አሁን ያለው ምልክት የሚታይበት ሰንደቅ ዓላማ ፈጠረ፡፡ አሁን ያለው የሰንደቅ ዓላማ ዓርማ እንዲለወጥ የሕዝቡ ጥያቄ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡-  ከውጤቱ መገለጽ በኋላ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ ምን ዓይነት ጥንቃቄ መወሰድ አለበት? ኢትዮጵያ ከፊቷ የተደቀኑባትን ተግዳሮቶች ማለፍ፣ በትግራይ ሕግ የማስከበር፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና ሌሎችም ከምርጫው ውጤት ጋር ተያይዞ እንዴት ያዩታል?

  ልጅ ዳንኤል፡- አንድ ሰው በእግሩ መንቀሳቀስና ጥሩ ማሰብ እስከቻለ ድረስ ችግርን መፍታት ይችላል፡፡ ጥሩ የሚያስብ ኅብረተሰብ የሚፈጠረው በሥነ ምግባርና በትምህርት ሲታነጽ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሕግ አስከባሪዎች በድምፅ መስጫ ወቅት ድምፃቸውን ለመስጠት ተሠልፈው ወረፋ በመጠበቅ ላይ ካሉ ሰዎች መካከል ሥርዓት የሚያበላሹ ወይም የሚያውኩ ቢገኙ፣ በሥርዓት ተይዘው ወደ ሚመለከተው መቅረብ፣ አለበለዚያም መምከር እንጂ ዘለው ዱላ ባያነሱ መልካም ነው፡፡ ይህንን ካደረጉ ሥጋት አለን እያሉ ለሚያላዝኑት ፈረንጆች እንደፈራነው የሰብዓዊ መብት እየተጣሰ ነው በሚል ውጤቱን እንዲያንቋሽሹ በር ይከፍትላቸዋል፡፡ ስለዚህ ይህ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተረፈ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ማድረግ አገሪቷ ከተጋፈጠቻቸው ተግዳሮቶች ሁሉ በተሻለ ሁኔታ ለመወጣት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

   

   

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  የክልሎችን አንደኛ ደረጃ ትምህርት መማሪያ መጻሕፍት ለማሳተም 29 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተባለ

  ለብሔራዊ ፈተና የሚያገለግሉ አንድ ሚሊዮን ታብሌቶች በአገር ውስጥ ሊመረቱ...

  በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት መምህራን አያስፈልጉም ተባለ

  የትምህርት ሚኒስቴር አካሄዱኩት ባለው የዳሰሳ ጥናት፣ በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ካገኘሁት ገቢ ላይ ግብር መክፈል አለብኝ የሚለው አስተሳሰብ ብዙ ይቀረዋል›› አቶ ሙሉጌታ አያሌው፣ የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት

  የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ያለና በመንግሥትና በንግዱ ማኅበረሰብ መካከል ከታክስ ጋር በተያያዙ የሚነሱ አመግባባቶችን የሚመለከት ተቋም ነው፡፡ ግለሰቦችና ነጋዴዎች...

  ‹‹የእኛ ብሔርተኝነት የበሰለና ዴሞክራሲያዊ ነው›› አቶ በቴ ኡርጌሳ፣ የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር

  ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ፣ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ፣ ከአርሲ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፣ እንዲሁም ከኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርሲቲ በሄልዝ ኦፊሰርነት ተመርቀዋል፡፡ ገና ባህር ዳር...

  ‹‹የሰላም ስምምነት ተደረገ ማለት በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይታለፋሉ ማለት አይደለም›› ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር

  ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ በአዳማ ዳኞች መታሰራቸው ከሰሞኑ ትልቅ መነጋገሪያ የፈጠረ ጉዳይ ነበር፡፡ በሐዋሳ ፈጣን መንገድ ላይ ጭምር ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑና በኦሮሚያ ክልል ያለው የፀጥታ...