Wednesday, February 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​​​​​​​ምርጫው ሰላምን የምንሸምትበት ይሁን!

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ነገ ይካሄዳል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመራቸውን ፓርቲ ይመርጣሉ፡፡ እንደ አገር የዚህ ምርጫ አስፈላጊነት እንዲህ በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ከቀደሙት ምርጫዎች የተሻለ እንደሚሆን የታመነበትና ተስፋም የተጣለበት ይህ ምርጫ፣ ለኢትዮጵያም ትልቅ ትርጉም ያለው ተደርጎም ስለሚወሰድ የምርጫው በሰላም መጠናቀቅ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡

እንከን የለሽ ምርጫ ይሆናል ተብሎ ባይታሰብም፣ የተሻለ ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉ ቅድመ ምርጫ ክንውኖች የታየበት በመሆኑ የምርጫ ሒደቱም በተመሳሳይ ይከናወን ዘንድ የሁሉም ምኞት መሆን አለበት፡፡  

የምርጫው ሒደት በተደላደለ መንገድ እየተጓዘ የምርጫው ቀን ላይ ደርሰናል ብለን አፍን ሞልተን መናገር ባንችልም፣ የተሻሉ ነገሮች የታዩበት ስለመሆኑ በማሰብ ፍፃሜውም እንዲያምር የሁሉም ኃላፊነት የተሞላበት አካሄድ ወሳኝ ነው፡፡

ከ37 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለመምረጥ ካርድ ወስደው፣ ያሻቸውን ለመምረጥ ነገን እየጠበቁ ሲሆን፣ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን በማድረግ ረገድም ሁሉም ዜጋ በኃላፊነት መንቀሳቀስ አለበት፡፡

በሰላማዊ መንገድ መምረጥና ማስመረጥ ያስፈልጋል፡፡ ሥልጣን በምርጫ ብቻ የሚገኝ ስለመሆኑ አምኖ፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት መሞከር፣ ባስ ያለ ነገር ከገጠመም በሕግ መፍታት እንደሚቻል ተገንዝቦ ከአመፅና ከግርግር ራስን በማራቅ ለምርጫው ሰላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት ሁሉም የየበኩሉን ይጠበቅበታል፡፡

የትኛውም ተወዳዳሪ ፓርቲ ለዚህች አገር ኃላፊነት አለበትና የምርጫው ሒደትም ሆነ በአጠቃላይ ከዚሁ ጋር የተያያዙ ግድፈቶች ቢያጋጥሙ የሕዝብን ድምፅ በመቀበል አንደኛው ለሌላኛው፣ ‹እንኳን ደስ አለህ›፣ ‹እንኳን ደስ አላችሁ› በመባባል አዲስ ታሪክ ለማጻፍ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡

ምርጫው በሰላም ተጠናቆ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲረከብ የምንሻውም፣ እስካሁን የመጣንበትን ብዙ ስንክሳር የበዛባት ጉዞ አርሞ የተሻለ ለመጓዝ ተስፋ የተጣለበት በመሆኑ ነው፡፡

በነገው ምርጫ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ መንቀሳቀስ፣ የተሻለ አገር እንዲኖረን ማድረግም ነው፡፡ በተለያዩ ትርክቶች፣ እርስ በርስ የምንባላበትን ታሪክ ለመቀየር መንገድ ይከፍታል ተብሎ ስለሚታመንም ነው፡፡

በዚህ ምርጫ አብላጫ ድምፅ ያገኘው ፓርቲ መንግሥት ሊመሠርት የሚበቃበት ቢሆንም፣ አሸናፊው ሁሉም ስለመሆኑ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት አገርን መታደግ ያስፈልጋል፡፡ ያሸነፈችው ‹ኢትዮጵያ ናት›፣ ያሸነፈው፣ ‹ሕዝቧ ነው› ብለን ለመግለጽ በፍፁም ጨዋነት ይህንን ምርጫ ማጠናቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ይህ ምርጫ እንደ አገር ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በሰላም ተጠናቆ፣ ሁሉም ተመሠጋግኖ እንዲያልፍ፣ ዜጎች የተሻለ አየር እንዲተነፍሱና የተሻለ ነገን እንዲጠብቁ ለማድረግ ደግሞ ሁሉም ፓርቲዎች በሰከነ መንገድ መጓዝ አለባቸው፡፡ በቅድመ ምርጫ ሒደቱ ያየናቸው መልካም ተግባራት የምርጫው ውጤት እስከሚገለጽና ከዚያም በኋላ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ይህ ኃላፊነት ደግሞ ለአንድ ወገን የሚተው አይደለም፡፡

በተለይ ከምርጫ ውጤት መገለጽ ጋር ተያይዞ መተማመን እንዲኖር በብርቱ መሠራት አለበት፡፡ ድምፄ ተጭበርብሯል ያለ ፓርቲ ወይም ያልተገባ ተግባር ተፈጽሟል የሚል አካል ካለ ጉዳዩን በሕግ ብቻ መፍታት አለበት፡፡ ችግር አለ ያለ አካል ችግሩን የሚፈታው በአመፅና በብጥብጥ ባለመሆኑ፣ በዚህ ምርጫ በሕግ መዳኘት ቀዳሚ ምርጫዬ ነው ማለት ያስፈልጋል፡፡

እንደ አገር የገጠሙንን ተደራራቢ ችግሮች ለማለፍ በተለይ ኢኮኖሚውን ለማሳደግና ገበያውን ለማረጋጋት ከተፈለገም በምርጫ ወቅት በተለይም ከምርጫው በኋላ ችግሮች ቢኖሩ በሕግ አግባብ ለመፍታት የሚኬድበት መንገድ ወሳኝ ነው፡፡

የፖለቲካ ትርምስ ባለበት ሁኔታ ሥልጣን በምርጫ ብቻ የሚገኝ ስለመሆኑ ማስተማሪያም ስለሚሆን ይህን ምርጫ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

የነገው ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን መንግሥት፣ የፀጥታ ኃይል፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎችና አመራሮች፣ ታዛቢዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች ለመምረጥ ካርድ የወሰዱም ሆነ ያልወሰዱ ሁሉ ለዚህ ምርጫ በአግባቡ መጠናቀቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

መጠቀስ ያለበት ሌላው ጉዳይ ደግሞ በዚህ ምርጫ ማንም ያሸንፍ ማን ከዚህ የተሻለ ምርጫ ለማካሄድ ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን ነው፡፡ ቀጣይ ምርጫዎችን የተሻለ ለማድረግና አሁን ታዩ የተባሉ ግድፈቶቻችን አርሞ የተሻለ አፈጻጸሞችን ይዞ ለመቀጠል የሚረዳ ስለመሆኑም ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡ በተለይ ምርጫው ከተጠናቀቀና አሸናፊው ፓርቲ ከታወቀ በኋላ፣ ፓርቲዎች አብሮ የመሥራት ልምዳቸውን ማዳበር፣ ከዚያም አልፎ ለቀጣይ ምርጫዎች መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ምርጫ ሲደርስ ብቻ አለን ከሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመላቀቅ ከተፈለገም ሁሉም ከነገዋ ዕለት ጀምሮ ለቀጣይ ምርጫ አሻግሮ ማየት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ጠንከር ያሉ ፓርቲዎች እንዲወጡ ያስችላል፡፡ ስለ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የምናወራው አገር ሰላም ስትሆን ነውና፣ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫን ሰላም የምንሸምትበትና ለወደፊት አብሮ በሰላም ለመኖር የምንችልበት ይሆን ዘንድ ሁሉም ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት