Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየተናጠል ሥልጠናና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ዝግጅት

የተናጠል ሥልጠናና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ዝግጅት

ቀን:

በሦስት ምዕራፍ ተከፋፍሎ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን የቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት አሁን ላይ ሦስተኛውንና የመጨረሻውን የዝግጅት ምዕራፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይሁንና ወሳኝ የብሔራዊ ቡድኑ አንዳንድ አትሌቶች ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ጋር በአንድ ማዕከል ዝግጅት እያደረጉ እንዳልሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን ሸቦ የ10,000 እና የ5,000 ሜትር ዋና አሠልጣኝ ናቸው፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ምክትልና ዋና አሠልጣኝ በመሆን በአምስት ኦሊምፒኮች ላይ ተካፍለዋል፡፡ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ከዝግጅትና መሰል ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በተለይም በተናጠል የሚደረጉ ዝግጅቶች እንዳሉ የሚነገረውን አስተያየት ይጋራሉ፡፡ እንደ ዋና አሠልጣኙ ከሆነ ይህ ክፍተት ከወዲሁ መፍትሔ ካልተበጀለት በቀጣይ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ትልቅ ተግደሮት መሆኑ እንደማይቀር ያምናሉ፡፡ በእነዚህና ሌሎችም ጉዳዮችን በተመለከተ ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡     

ሪፖርተር፡- የቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት በዓይነቱ የተለየ ሆኖ ነው የተጀመረው፡፡ የስምንት ወር ዝግጅት አድርጋችኋል፡፡ በተለየ ጠቅሞናል ብለው ሊነግሩን የሚችሉት ምን አለ?

ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን፡- ዝግጅቱ እንደተባለው ከኅዳር ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከወትሮው ለየት ባለ አካሄድ በመጀመርያው የዝግጅት ምዕራፍ ተጀምሮ እስካሁን እንደቀጠለ ነው፡፡ የመጀመርያው የዝግጅት ምዕራፍ ጣፎ በሚገኘው ጥሩነሽ ዲባባ ሆቴልና በአሰለፈች መርጊያ ሆቴል በመሰባሰብ የተደረገ ሲሆን፣ ሁለተኛውንና ሦስተኛውን የዝግጅት ምዕራፍ ደግሞ በአዲስ አበባ ሌክሰስ ሆቴል በማድረግ ቀጥለናል፡፡ ዝግጅቱ ወቅቱ የሚጠይቀውን ሥልጠና  ጠዋትና ከሰዓት በመስጠት እንደቀጠለ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ያለው ነገር በአካልም ሆነ በአዕምሮ ጥሩ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡– ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም ከአትሌቶች ምርጫ ጋር ተያይዞ የሚነግሩን ካለ?

ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን፡- ምርጫውን በተመለከተ ሁሉም እንደሚያውቀው ለመጀመርያው የዝግጅት ምዕራፍ ለእያንዳንዱ የውድድር ዓይነት ቁጥራቸው በርከት ያሉ አትሌቶች በምርጫ ተካተው ነበር፡፡ በየዝግጅት ምዕራፉም የተለያዩ ማጣሪያዎች ተደርገዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የኦሊምፒክ የመጀመርያና የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሻምፒዮናና የመጨረሻውና የቶኪዮ ኦሊምፒክ ምርጫ ከሳምንት በፊት ያደረግነው የሔንግሎ ማጣሪያ ይጠቀሳል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ለእያዳንዱ የውድድር ዓይነት ሦስት ሦስትና አንድ ተጠባባቂ በመያዝ የመጨረሻው የዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡ ክትትልና ድጋፉም ከሞላ ጎደል ጥሩ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በሦስቱ የዝግጅት ምዕራፎች አትሌቶቹ በሥነ ልቦናውም ሆነ በአካል ብቃቱ ረገድ የሚገኙበትን ሁኔታ እንዴት መግለጽ ይቻላል?

ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን፡- አትሌቶቻችን በሁሉም ረገድ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የሔንግሎን ጨምሮ ከሰሞኑ በተከናወኑት ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ምስክር ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ዝግጅቱ እርስዎም ሆኑ ፌዴሬሽኑ እንዳላችሁት ከወትሮው በተለየ መልኩ መደረጉ ይነገራል፡፡ ነገር ግን ደግሞ ኮቪድን ምክንያት በማድረግም ሊሆን ይችላል አትሌቶች ሆቴል ከገቡ በኋላ እንደገና እንዲወጡ የተደረገበት አጋጣሚ በመኖሩ ዝግጅቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደነበር የሚናገሩ አሉ፡፡ በዋናነትም በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን፡- በእርግጥ እንደ አንድ አሠልጣኝ በተለይ የሁለቱ ተቋማት አለመግባባት የፈጠረብን ተፅዕኖ አልነበረም ለማለት ይቸግረኛል፡፡ በተጨባጭ ያ ሁኔታ ባይፈጠር በግሌ እመርጥ ነበር፡፡ ምክንያቱም አትሌቲክስ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መልካም ገጽታ ግንባታ ነው፣ ፍቅር ነው፣ ወንድማማችነትና የአብሮነት መገለጫ ነው፡፡ ሲጠቃለልም ሰላምና ውጤት ነው፡፡ አትሌቲክስ በኢትዮጵያ ካሉት ስፖርቶች በውጤት ሲለካ የመጀመርያው ቁንጮ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስተዋወቀ ብቸኛው ስፖርት ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይህን ስፖርት አንድ ሆነው ተንከባክበው ክብርና ዝናውን ጠብቀው ማቆየት እንደሚጠበቅባቸው ይሰማኛል፡፡ ይህም ሆኖ ችግሩ በሥልጠናው ረገድ ያን ያህል የከፋ ተፅዕኖ አሳድሮብን ነበር ማለት ባልችልም እንደ አጠቃላይ ሰላም ቢፈጠር ብዙ ነገር ማግኘት እንደሚቻል ነው መውሰድ የሚገባን፡፡

ሪፖርተር፡- በሥልጠናው ረገድ ያን ያህል ተፅዕኖ አላሳደረብንም ሲሉ ግልጽ ቢያደርጉልን? ምክንያቱም  ችግሩ በተከሰተበት ወቅት የስፖርቱ ሙያተኞችን ጨምሮ በርካቶች የጉዳዩን አሳሳቢነት ሲገልጹ የተደመጡበት አጋጣሚ ነበርና ነው?

ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ለአንድ ነገር ውጤታማነት ሰላም መሠረታዊ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰላም የብዙ ነገር መገለጫ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ተፅዕኖ አልፈጠረብን ለማለት የቻልኩት በሥልጠናው ረገድ እንጂ በሥነ ልቦናው ረገድ አይደለም፡፡ ሥልጠና ላይ ችግር ሊፈጥር የሚችለው በአሠልጣኞችና በአትሌቶች እንዲሁም ተዛማጅነት ባላቸው ሙያተኞች መካከል ችግሩ ሲከሰት ነው፡፡ አሁን ባለው በአሠልጣኞችና በአትሌቶች መካከል ያለን ግንኙነት ሰላማዊ ነው፡፡ ግን ደግሞ ችግሩ ባይኖር ኖሮ የበለጠ በሆነ ነበር፡፡ በእኛ እምነት ስፖርቱን የሚመሩ ሁለቱ ተቋማት ቀርቶ ከሌላውም አካል ድጋፍ በምንፈልግበት በዚህ ሰዓት ላይ ችግሩ መፈጠሩ በአንድም ሆነ በሌላ ለአትሌቲክሱ ጉዳት አለው ብሎ መውሰድ ግን ይቻላል፡፡ የሆነ ሆኖ ችግሩ ተፈጥሯል፡፡ ግን ደግሞ መፍትሔ እንደሚያገኝ እምነት አለኝ፡፡ እስከዚያው ግን እኛም ሆነ የአትሌቶቻችን ድርሻ ዝግጅታችንን በተሰጠን ፕሮግራም መሠረት ማከናወን ስለሆነ ያንን እያደረግን ነው፡፡ ለዚያም ነው በኢትዮጵያ ሻምፒዮናም ሆነ ሔንግሎ ላይ ያንን የመሰለ ውጤት ሊመዘገብ የቻለው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሆቴል ገብተው ዝግጅት እያደረጉ ካሉት 36 አትሌቶች 30ዎቹ የራሳቸው ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ የቻሉ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ አትሌቶች መካከል በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለወትሮው የሚታወቁበት የአብሮነት መንፈስ አሁን የለም፡፡ ብዙዎቹ ዝግጅት ሲያደርጉ የሚታዩት በተበታተነ ሁኔታ ነው፡፡ እርሶ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ነዎትና የፈጠረብዎት ችግር የለም?

ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን፡- በአባባልም ከተናጠል ይልቅ አብሮነት የሚፈጥረው የመንፈስ ጥንካሬ ይኖራል፡፡ ከዚህ አኳያ የተናጠሉ አካሄድ አይጠቅምም፡፡ እንደዚያም ሆኖ አሁን ላይ በተለይም ሌክሰስ ሆቴል ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ አትሌቶች አንድ ላይ ተሰባስበዋል፡፡ ነገር ግን ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገው ቀድሞ የ10,000 እና 5,000 አትሌቶች በአንድ ማዕከል ሆነው በአንድ ዋናና ምክትል አሠልጣኞች ነበር የሚሠሩት፡፡ ይህ በማራቶንም ሆነ በመካከለኛ ርቀት ተመሳሳይ ነበር፡፡ ይህ አሁን ላይ የለም፡፡ በግል የሚሠለጥኑ አትሌቶች መበራከት ይታያል፡፡ አንዳንድ አሠልጣኞች አንድ አትሌት ብቻ ይዘው የሚሠሩ አሉ፡፡ አንድ አሠልጣኝ ሁለትና ከዚያም በላይ ይዞ የሚያሠራበት ሁኔታ አለ፡፡ 20 እና ከዚያም በላይ አትሌቶችን ይዞ የሚያሠራበትም አጋጣሚ አለ፡፡ የራሴን ተሞክሮ ባነሳ በእኔና በረዳቴ ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ የሚሠለጥኑ አትሌቶች በብሔራዊ ቡድኑ ከሚገኙት 28 ሲሆኑ፣ የቀሩት ግን በግል የሚሠለጥኑ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዮሚፍ ቀጀልቻና ሙክታር እድሪስ እንዲሁም ለተሰንበት ግደይና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ወደ ማራቶን አካባቢም በተመሳሳይ በሦስት አሠልጣኞች በሐጂ አዴሎ፣ በገመዶ ደደፎና በጌታነህ ተሰማ የሚሠለጥኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደነዚህ የመሰሉ አካሄዶች ጥሩ እንዳልሆኑ ሊወሰድ የገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ለችግሩ መከሰት ምክንያት የሚሉት ምንድነው?                 

ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን፡- በእኔ እምነት ወቅቱ ያመጣው ካልሆነ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ ለዚህ መፍትሔው ከብሔራዊ አሠልጣኞች ጭምር በተለይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንደ ብሔራዊ ተቋም ደንቦችና መመርያዎችን በትኩረት መመልከት ይኖርበታል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ልክ እንደ ቀድሞ በአንድ ማዕከል ሆኖ ሥራውን እንዲሠራ ማድረግ ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ የደረሰን ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህን ማድረግ የሚያስችል አሠራር በተለይ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል የሚታይ ቁርጠኝነት አለ?

ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን፡- እስካሁን ባለው ቁርጠኝነቱ ያን ያህል አጥጋቢ አይመስለኝም፡፡ ለዚህም ነው በጥቂት አትሌቶች የተጀመረው የተናጠል ሥልጠና አሁን ላይ እየባሰበት ካልሆነ ሊሻሻል ያልቻለው፡፡ እንዲያውም ከቡድን ይልቅ የተናጠል ሥልጠናው አፉን እየከፈተ የመጣበት ሁኔታ ነው የሚስተዋለው፡፡

ሪፖርተር፡- በእርሶ እምነት የችግሩ ምንጭ የቱ ላይ ነው? ይህ ዓይነቱ አሠራር ለምን ሊፈጠር እንደቻለ የሚነግሩን ይኖራል?

ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን፡- ሁሉም ሊያውቀው የሚገባው ብሔራዊ ቡድን የሚባል ነገር ከጠፋ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አሁን ላይ የምናየው ችግር ሊፈጠር የቻለውም ለዚያ ይመስለኛል፡፡ የሚገርመው ብሔራዊ ቡድን የሚባለው ነገር እንደፈረሰ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ብሔራዊ ቡድን የሚመስል ነገር ከሪዮ ኦሊምፒክ ጀምሮ ለመሥራት የቻልነው እኔና ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ ነን፡፡ ምናልባትም ለዛሬው ብሔራዊ ቡድን መነሻ የሆነን በዚያን ወቅት ያስቀመጥነው እርሾ ነው፡፡ ችግሩን አሁን ያለው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ሆነ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ወደ ነበረበት ሊመልሱት አልቻሉም፡፡ ይህ ነገር ለወደፊቱ ምናልባትም ከቶኪዮ ኦሊምፒክ በኋላ ለቀጣዩ ኦሊምፒክ በተቻለ መጠን በችግሩ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ነበረበት የሚመለስበት ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል፡፡ ችግሩን ሙሉ በሙሉ መቅረፍ ባይቻል እንኳ ለብሔራዊ ቡድን ተቀራራቢ የሆነ የአሠራር ሥርዓት ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ይህ የማይደረግ ከሆነ ግን ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የወደፊት ትልቅ ፈተና ሊሆን እንደሚችል አልጠራጠርም፡፡ በእርግጥ ስፖርቱ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ አንጻር ልክ እንደ ቀድሞ ሁሉም አንድ ላይ መሥራት አለባቸው የሚል ድርቅ ያለ እምነት የለኝም፡፡ እንደ ኦሊምፒክ የመሰሉ አገራዊ ተሳትፎዎች ሲመጡ ግን ብሔራዊ ቡድን ብሎ መጥራት የሚያስችል የአንድነት ስሜት ያለው ቡድን መገንባት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም አገሮች ያለ የሚኖርም ነው፡፡ ቁርጠኝነቱ ካለ ማቀራረብ ይቻላል፡፡ ዓለም ላይ ያለው የሥልጠና ዘዴም ነው፡፡ በዚህ መልኩ የምንሠራ ከሆነ በሺሕ የሚቆጠሩ ጥራትና ብቃት ያላቸው አትሌቶች ማፍራት ቀላል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ማረጋገጫ የሚሉት ካለ ቢነግሩን?

ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን፡- ቀደም ባሉት ዓመታት የነበረውን ትተን በቅርቡ ሔንግሎ ላይ በተደረገው ማጣሪያ ላይ መመልከት ብንችል፣ ከእኛ ጋር ከመጀመርያ ጀምሮ በሆቴል ተሰባስበው ሲሠሩ ከነበሩትና አቅም አለን ብለው በተናጠል ሥልጠና ሲሠሩ ከነበሩት አትሌቶች በቁጥርም ሆነ በውጤት የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡት በቡድን ሆነው ሲሠሩ የነበሩት ናቸው፡፡ በአሥር ሺሕ ወንዶችና በአምስት ሺሕ ሴቶች ከአንደኛ እስከ አምስተኛ የወጡት እነዚሁ ልጆች ናቸው፡፡ ይህም በማዕከል የሚሰጥ ሥልጠና ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው ይነግርሃል፡፡ በጋራ በሚሰጥ ሥልጠና አንዱ ከሌላው የተለየ ምን ዓይነት ጥንካሬ እንዳለው፣ ሌላው ከዚህ ተሞክሮ የሚያገኝበት ሰፊ ዕድል ጭምር ይፈጥራል፡፡ አሁን ላይ እርስ በርስ ለመወዳደር ሳይሆን ከዓለም ጋር ለመወዳደር ነው ዝግጅት የምናደርገው፡፡ በዋናነትም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአትሌቲክሱ ጥሩ አቅም እየፈጠሩ ከመጡት ከእነ ኡጋንዳና ከሌሎችም የዓለም ታላላቅ አትሌቶች ጋር ለመወዳደር ነው፡፡ በዚህ ሁሉ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት መሥራት የሚጠበቅብን የእነዚያን አትሌቶች የአሯሯጥ ዓይነትና የአጨራረስ ብቃት እንዲሁም ጥንካሬያቸው ዙር ላይ ወይስ የመጨረሻው የሚለውን በመቀመር እየሠራን ቢሆንም የአትሌቶቻችን የተበታተነ አካሄድ ግን ማስቀረት ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቶኪዮ ኦሊምፒክ ምን እንጠብቅ?            

ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን፡- ካለፉት ኦሊምፒኮች የተሻለ ውጤት እናስመዘግባለን፡፡ በተለይ በእኔ ሥር የሚገኙት አምስትና አሥር ሺሕ በሁለቱም ጾታ በሥነ ልቦናውም ሆነ በአካል ብቃት ጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ የሔንግሎ ማጣሪያ ጥሩ ማሳያ ሆኖናል፡፡

ሪፖርተር፡- በሴቶች አምስትና አሥር ሺሕ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰንን የያዘችው ለተሰንበት ግደይ በቶኪዮ በሁለቱም ርቀት መሮጥ እንዳለባት የሚናገሩ አሉ፣ እንደ ዋና አሠልጣኝ በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?

ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን፡- በእኔ በኩል ይህን አልመክርም፡፡ ምክንቱያም ቶኪዮ በጣም ሞቃታማ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ውድድሮቹ የሚደረጉበት ሰዓትና ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ልዩነት አለ፡፡ ለምሳሌ 5,000 ሴቶችና 10,000 ወንዶች ውድድሩ የሚደረገው በመጀመርያዎቹ የመክፈቻ መርሐ ግብሮች ላይ ነው፡፡ ለዚህ ውድድር አትሌቶች ወደ ጃፓን ጉዞ የሚያደርጉት ከመርሐ ግብሩ አምስትና ስድስት ቀን ቀደም ብለው ነው፡፡ 10,000 ሴቶች ውድድራቸውን የሚያደርጉት ወደ መጨረሻዎቹ ቀኖች ላይ ነው፡፡ በዚያ ላይ የኮቪድ ፕሮቶኮል ውድድሮቻቸውን የሚያጠናቅቁ የየአገሮቹ አትሌቶች ከቶኪዮ ቶሎ እንዲለቁ ያስገድዳል፡፡ ሌላውና ዋናው ነገር እንዲሁም ሁሉም ሊያውቀው የሚገባው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁሉም የውድድር ዓይነት የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገብ የሚችል አቅም ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ በ10,000 ሴቶችና ወንዶች የብቃት ችግር የለብንም፡፡ በ5,000 ሜትርም እንደዚሁ በሁለቱም ጾታ የብቃት ችግር የለብንም፡፡ የሁሉም ሰዓት ማክሮ ሰከንድ ካልሆነ ይህን ያህል ልዩነት የለውም፡፡ አንዳንዶቹ ጠዋት ማጣሪያ ተሩጦ ከሰዓት ፍጻሜ የሚሆንባቸው ውድድሮችም አሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት አንድ አትሌት በሁለት ርቀት የሚለውን አልደግፈውም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...