Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትነገ ዝም ብሎ ሌላ ቀን አይደለም!

ነገ ዝም ብሎ ሌላ ቀን አይደለም!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የምርጫ 2013 ዓ.ም. ድምፅ መስጫ ቀን የኋሊት እየተቆጠረና በጣም እየገሰገሰ መጥቶ፣ በዚህና በሌሎች ብዙ ውጣ ውረዶች፣ ፈጣንና ተለዋዋጭ ሁነቶች መካከልም የድምፅ መስጫ ቀኑን ለሁለት ከፍሎ፣ እነሆ ነገ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. አብዛኛው የተመዘገበ ድምፅ ሰጪ ወደ ምርጫ ጣቢያ የሚሄድበት፣ መሄድም ያለበት ቀን ነው፡፡ የነገው የድምፅ መስጫ ቀን በራሱ፣ እንዲሁም ቀስ ብለን፣ እያወቅንበት ከሄድን ቀስ ብሎ የሚደርሰው (ወይም እየተምዘገዘገ ከተፍ የሚለው) ሌላው ድምፅ መስጫ ቀን ማለትም ጳጉሜን 1 ቀን ከፍተኛ ጥንቃቄ፣ ኃላፊነትና ባለቤትነትን የሚጠይቅ ከፍተኛ የአገር ግዳጅ፣ የአገር አደራ ቀን ነው፡፡ ይንንን የምለው በነገውና በጳጉሜን 1 ቀን የድምፅ መስጠት ሒደት ውጤት መሠረት የአገሪቱን ሕዝቦች ልዕልና መወከል የተዋጣለትና የሠመረለት ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ይደራጃል ብዬ አይደለም፡፡ ደርግም (በ1980 ዓ.ም)፣ ኢሕአዴግም (በ1987 ዓ.ም.) የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አቋቋምን ብለው ለኢትዮጵያና ለዓለም ሁሉ አውጀው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን የፈቃዱ ውጤት የሆነ መንግሥት በምርጫ አቋቁሞ አያውቅም፡፡

የዚህ ምክንያት ሥልጣን አያያዝን ኢትዮጵያ ውስጥ ሥርዓታዊ ያላደረግነው በመሆኑ ነው፡፡ ዋናው ችግር ያለው ለጊዜው ሕገ መንግሥትና ከእሱም የተወለዱ ሕጎች ላይ አይደለም፡፡ በጣም መሻሻል የሚገባቸው የሕግ ድንጋጌዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሕጎች ቢኖሩም ለአሁኑ እጅ ከወርች ያሰረን ያለውን ሕገ መንግሥትና የምርጫ ሥርዓት መኗኗሪያ ማድረግ አለመቻላችን ነው፡፡ መንግሥትን በኃይል የመጣልና የመተካት ታሪክና አሠራር መቆም አለበት፣ ያለውን ሕገ መንግሥትና የምርጫ ሥርዓት/ማለትም (በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው ለሚለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9/3 ድንጋጌ ተገዥና ታማኝ መሆን)፣ ሁሉም የእኔ ብሎ ይቀበለው ማለት ነውርም ስህተትም አይደለም፡፡ ይህንን ያለውም ትናንት ከ27 ዓመታት በፊት ኢሕአዴግ ብቻ አይደለም፡፡ ብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ በታኅሳስ 4 ቀን 1953 ዓ.ም. ድርጊታቸው (ፈጸሙት በተባለው ድርጊት) የተከሰሱት የዚያን ጊዜውን የ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 252 ተላልፈው፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማፍረስ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ነው፡፡ በየትም አገር በሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኃን ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፣ ወንጀልም ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ማቋቋሚያ ሰነድም ይህንን ያካትታል፡፡

ዋናው ጥያቄ ግን ሕገ መንግሥቱንና የምርጫ ሥርዓቱን የመቀበልና ያለ መቀበል ጉዳይ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱንም ሆነ የምርጫ ሥርዓቱን የተቀበለም ሆነ መለወጡን የሚፈልግ ሁሉ ፍላጎቱን ይዞ ለመታገልና ለመወዳደር ያስፈልጋል ብሎ የሚያምንበት፣ ያስፈልጋል ተብሎ የሚታመንበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ የመኖርና ያለ መኖር ጉዳይ ነው፡፡ ላለፉት አምስት ምርጫዎች መከራ ያየነው ይህ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ በሌለበት የአፈናና የጥርነፋ አገዛዝ ሥር ሆነን ነው፡፡ ብዙ ገንዘብ የሚከሰከስበት፣ በየአምስት ዓመቱ የሚደረገው የእስከ ዛሬው ‹‹ምርጫ›› ሕወሓት በኢሕአዴግ ስም መንግሥትነትን የሚሾምበት ግርግርና ሥነ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ በተለይ እየቆየ ሲገባን እንደተረዳነው ራሱ ዓምደ መንግሥት እየሆነ የሚታደስበትና ራሱ አገረ መንግሥት ሆኖ የሚፀናበት አሠራር ነበር፡፡

ይህንን ነገ ብዙዎቻችን ድምፅ የምንሰጥበትን ምርጫ ልዩ የሚያደርገው (ቀደም ሲል እንደተባለው በዚህ የነገ ድምፅ መስጠት ውጤት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲ ስለምናዋልድ ሳይሆን)፣ በለውጡ ውስጥ የተፈጠረውን የዴሞክራሲ አየርና ሽታ ተቋማዊ የምናደርግበት የመጀመርያው ድኅረ ለውጥ ምርጫ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ድኅረ ለውጥ የመጀመርያው ምርጫ መደረግ ያለበት ወይም ሊደረግ የሚገባው መቼ ነው የሚለው ጥያቄ በገዛ ራሱ፣ ወደ ምርጫ በሚወስደው የለውጥና የሽግግር ጎዳና ውስጥ የሁሉንም፣ ቢያንስ ቢያንስ የአብዛኛውን ስምምነትና መግባባት ማግኘት ነበረበት፡፡ የዛሬው ዋና ጉዳያችን እሱ ባይሆንም ምን ዓይነት መሰናዶና እንዴት ያለ ዝግጅት አድርገን ወደ ምርጫ እንግባ በሚለው የአገር የለውጥና የሽግግር አደራ ላይ ከመነጋገርና ከመግባባት ይልቅ፣ ሠርቶ በማያውቅ ሕገ መንግሥት የአምስት ዓመት የምርጫ ቀጠሮ ላይ ሞተን እንገኛለን አልን፡፡ ድንገት ኮቪድ-19 መጥቶ ምርጫ 2012 ከማለት ድነንና ተርፈን ምርጫ 2013 ማለት ውስጥ ገባን፡፡ ነገ ድምፅ የምንሰጥበት ምርጫ ከዚህም የበለጠና አንዳንዴም የከፋ ከባቢ፣ አካባቢያዊ ሁኔታ ውስጥ የሚካሄድ ነው፡፡

የነገ ድምፅ የምንሰጥበት (ጳጉሜን 1 ቀን ቀጠሮ ከተያዘላቸው የምርጫ ክልሎች በስተቀር) ምርጫ ለአንዴ፣ ለመጀመርያና ለመጨረሻ ጊዜ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 8 (የሕዝብ ሉዓላዊነትን) ድል የምንጎናፀፍበት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት በሕዝብ ድምፅ ተቋቁሞና ኖሮ አያውቅም፣ መንግሥታዊ ሥልጣን ከሕዝብ ሿሚነትና ጠያቂነት ጋር ተገናኝቶ አያውቅም፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ ስምንት እንደሚደነግገው ወይም የሚደነግገው፣ የሕዝቦች እንደራሴያዊ ዋና ባለሥልጣንነት ሊረጋገጥና ሊዘልቅ የሚችለው መጀመርያ መንግሥታዊ አውታራት (ምርጫ ቦርድ፣ ፍርድ ቤት፣ መከላከያ፣ ደኅንነት፣ ፖሊስ፣ ሲቪል ሰርቪስ ወይም የመንግሥት አገልግሎት) ከየትኛውም ዓይነት የፖለቲካ ቡድን ታማኝነት፣ ባለቤትነት፣ ተቀፅላነት ነፃ ሆነው እስከታነፁ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ምርጫ ውስጥ የገባነውና የመጀመርያውን ምርጫ የምናካሂደው ይህ ገና ያልተከፈለ ዕዳ፣ ቢጀመርም ጨርሶ ያልተጠናቀቀ የጋራ የቤት ሥራ እያለብንና እሱንም እያደረግን ነው፡፡ መንግሥታዊ አውታራትን ከፓርቲያዊ ወገንተኛነትና ባለቤትነት የማፅዳቱና የማላቀቁ ሥራ፣ በአገርና በሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ላይ ክፍተትና ግርታ ሳይፈጠር መካሄድ የመቻሉ ጉዳይ ራሱ አንድ የአገር ግዳጅ ሆኖ ሳለ፣ በዚህ ላይ አገር በዋና ዋና መንግሥታዊ አውታሮቿ ላይ ከሁሉም በላይ ደግሞ በመከላከያው ላይ የደረሰው ጥቃት ሁኔታችንን መጠነ ሰፊና ባለብዙ መከራ አድርጎታል፡፡

የመንግሥታዊ አውታራትን ገለልተኛነት የማነፅ ሥራ ሳይከናወን የምርጫ መብታችን ራሱ ትርጉም ያለው አይሆንም፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተለመደው ዓይነት ሐሳዊ ይሆናል፣ የሕዝብ ልዕልና መወከል የተሳካለት ሪፐብሊክ ልናቋቁምም አንችልም፡፡ ይህ ምርጫ ይህንን ሁሉ ማለትም የመንግሥት አውታራትን ገለልተኛነት ካረጋገጥን በኋላ የሚደረግ ሳይሆን፣ ይህንን ማድረግ በተግባር የምንማርበትና የምንለማመድበት ነው፡፡ ፋይዳውም ድሉም በዚሁ ጎዳና መጓዙ ነው፡፡ የገዥ ቡድን/ፓርቲ ተፈሪነትና የሕዝቡ ፈርቶና ሠግቶ አዳሪነት መለወጥ የሚችለው፣ በዚህም አማካይነት በሕገ መንግሥቱ የተዘረዘሩትን የመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ድንጋጌዎች እስትንፋሳችንና መኗኗሪያ ማድረግ የሚያበቃ ድል የምናስመዝግበው፣ ይህንን ምርጫ የዚሁ ትግል አካል ስናደርገው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ከሁሉም በላይና ከማንኛውም ነገር አስቀድሞ ዴሞክራሲ በቅድመ ሁኔታነት የሚፈልገውን የመንግሥት አውታራት ገለልተኛነት የማነፅ ሥራና ሒደት የሕዝብን፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ የአባሎቻቸውን፣ እንዲሁም የእያንዳንዱን ዜጋ ተሳትፎና አመኔታ የግድ መቆንጠጥና ከዚያም በላይ መቀዳጀት አለበት፡፡ ፓርቲዎች የሚሰጣቸውን ድምፅ ከወዲሁ የሚያዩትና የሚቆጥሩት፣ መራጩም ሕዝብ ድምፁን ሲሰጥ (ፍርዱን ሲሰጥ) በዚህ ሒሳብ ነው፡፡ ዴሞክራሲ የሚፈልገውን የተቋማትና የመንግሥት አውታራት ገለልተኝነት በማነፅ ሒደት ውስጥ ተሳትፎን እያስመዘገበ ነው፡፡

እስኪሰለች ድረስ ዴሞክራሲ ገለልተኛ አውታረ መንግሥት ይጠይቃል፡፡ የመንግሥት ዓምዶችን ገለልተኛ አድርጎ የማነፅ ሥራ የዴሞክራሲ ቅድመ ሁኔታ ነው ብለናል፡፡ ምርጫው ራሱ ገለልተኛ አጫዋች ይፈልጋል፡፡ ምርጫ ቦርድን ገለልተኛ አድርጎ የማነፁ ሥራ የሚያበረታታ የዕድገት ደረጃ ላይ ቢሆንም፣ ገና አሁንም በመከናወን ላይ ያለና በመካሄድ ላይ ያለ ግዙፍ ሥራ ነው፡፡ የመንግሥትን፣ ከመንግሥት የሥልጣን አካላት ከየትኛውም ክፍል ባለሥልጣን፣ ከገዥው ፓርቲ (ከገዥው ፓርቲ ማለት የፌዴራልም የክልልም አለ)፣ ከአባላቱና ከካድሬዎቹ የሚመጡ ግፊቶችን አንጥሮ የመመለስ ብቃት በአንድ ጊዜ የሚገነባ ወይም ተሰጥቶ የሚገኝ ባህርይ አይደለም፡፡ የገዥው ፓርቲ ካልሆኑ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ከክልል በታች ካሉ የዞን፣ የወረዳ አካላት፣ ምርጫው ውስጥ ከሌሉ ፖለቲከኞች የሚፈልቀው፣ የሚሰነዘረው ግፊትና ተፅዕኖ ራሱ ለእኛ ከሩቅ ለምናየው እንኳን፣ ‹‹አሁን ማን ያውቀዋል የምርጫ ቦርድን መከራ!›› የሚያሰኝ ነው፡፡ ከሩቅ ሆኜ ሳየው ምርጫ ቦርድ፣ ባለሥልጣናትና ሠራተኞች ጫማ ውስጥ ሆኜ የእነሱን ችግርና ቁስል ይዤ ሳየው፣ ያለፈው ሳምንት (ከሰኔ 7 ቀን እስከ ሰኔ 13 ቀን ድረስ የነበረው ሳምንት) የምርጫው አስፈጻሚ የሥልጣን አካል ባለሥልጣናት ኑሮ፣ ኑሮ የሚባል አይደለም፡፡ የምርጫ ቦርድ ተግባርና ኃላፊነት በጭራሽ የሚቀናበትና የሚያስቀና አይደለም፡፡ ጭራሽ ‹‹እግዜር ፅናቱን ይስጣችሁ›› የሚያሰኝ ነው፡፡

ይህንን የምለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እስኪ ምሥሉን ተመልከቱት፡፡ የሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ሁለተኛው ሳምንት (ከሰኔ 7 እስከ ሰኔ 13 ቀን ድረስ ያለው ጊዜ) ከምርጫው ቀን በፊት ያለው የምርጫው ዓመት የመጨረሻው አጥቅ ነው፡፡ ይህ አጥቅ ወይም ከድምፅ መስጫው ቀን በፊት ያለው የመጨረሻው የጊዜ ጉማጅ ሁለት የተለያዩ ነገሮች የተደባለቁበት ወቅት ነው፡፡ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየጊዜ እየተሻሻለ የመጣ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የካቲት ሁለተኛ ሳምንት ላይ የጀመረውና እስከ ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. (ረቡዕ) ድረስ ያለው ጊዜ የምረጡኝ ቅስቀሳ/የምርጫ ዘመቻ ቅስቀሳ ጊዜ ነው፡፡ ሰኔ ሁለተኛ ሳምንት ላይ የምርጫ ቅስቀሳው የቀረው ጊዜ የሦስት ቀናት (ሰኞ፣ ማክሰኞና ረቡዕ) ዕድሜ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ እስከ ድምፅ መስጫው ሰኔ 14 ቀን ድረስ ያለው የአራት ቀናት ጊዜ (ከሰኔ 10 እስከ 13) የምርጫ ቅስቀሳ የማይካሄድበት፣ የሕግ ክልከላ ያለበት የዝምታ/የጥሞና ጊዜ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለይም የአገራችን የምርጫ ፖለቲካ ይህን ሕግ፣ በዚህ ሕግ የተወሰነውን ልዩነትና ክልከላ ያውቀዋል ወይ ብሎ ጥያቄና መልስ፣ ይህን የመሰለ ሕግ የማስፈጸም ሕግ የማስከበር ግዴታ ያለበት የመንግሥት የሥልጣን አካል ብቻ ሳይሆን የሁላችንም፣ የዜጎችም ራስ ምታት ነው፡፡

እሑድ ሰኔ 6 ቀን በተከናወነው የመስቀል አደባባይ – ማዘጋጃ ቤት ፕሮጀክት ምርቃት ላይ፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ባደረጉት ንግግር ስለተመረቁ 2,500 ፕሮጀክቶች ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ ቁጥር በለውጡና በሽግግሩ ወቅት የተመረቁትን አጠቃላይ የኢትዮጵያ ይሁን ወይም በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አላውቅም፡፡ ያም ሆኖ ግን መላው የምርጫ ቅስቀሳ የአምስት ወራት ያህል ጊዜ በሙሉም ባይሆን፣ በተለይም የመጨረሻዎቹ ወራት ከሁሉም በላይ ደግሞ የግንቦት ወር የገዥው ፓርቲ የሥራ  አፈጻጸም ሆኖ እንዲመዘገብ የተፈለገ የሥራ ውጤት ሁሉ ለምርቃት የቀረበበት ጊዜ ነው፡፡ ይህን ያህል ገና ከድጡና ከማጡ አልወጣንም፡፡ ይህን ያህል ገና በጨዋታው ሕግ ላይ አልተስማማንም፡፡ ይህ ነው ዴሞክራሲ የሚፈልገውን የመንግሥት አውታራትን ገለልተኛነት የማነፅ ሒደት ውስጥ ገና አልገባንም፣ ያ ማለት ምን እንደሆነ ገና አልተገለጸልንም የሚባለው፡፡

እግረ መንገዴን አንድ ሌላ ነገር ላንሳ፡፡ በተጠቀሰው የመስቀል አደባባይ – ማዘጋጃ ቤት ፕሮጀክት ምረቃ ላይ (ዕጩ ተወዳዳሪ) አዳነች አቤቤና ዓብይ አህመድ ንግግር ማድረጋቸውን የሰማ የሆነ የቁንጫ ሌጦ የሚያወጣበት የፕሮቶኮል (ይድረስ እከሌ ወይም እከሌ ሆይ ብሎ የጠራበት) ቅደም ተከተል መኖሩ፣ መቼም ለአዲስ አበቤ ‹‹የሚሳነው›› አይመስለኝም፡፡ እኔ ግን ከዚህ የፕሮቶኮል የስም አጠራር መዘበራረቅና ቅደም ተከተል ይልቅ ዛሬም ነውር ያላደረግነው አንድ ትልቅ የገለልተኛነት ጉዳይ ሲበዛ ያሳስበኛል፡፡ ላብራራ፡፡

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ (ዶ/ር) ዓብይን የጋበዙበትን ንግግር ሲያደርጉ መግቢያቸው ላይ በቅደም ተከተል ክቡር/ክብርት እከሌ እያሉ የዘረዘሩት መጀመርያ ከዓብይ (ዶ/ር) ጀምረው ነው፡፡ ከዚያ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትን ስም አስከተሉ፡፡ ለጥቀውም ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)ን ጠሩ፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) ደግሞ ይህን ቅደም ተከተል ሆን ብለው ቀያየሩት፡፡ ወይም ሆን ብለው እንደቀያየሩት መረዳት አያዳግትም፡፡ መጀመርያ ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)ን አስቀደሙ፣ ቀጥለውም ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን ጠሩ፡፡ የእኔ ሕመም፣ የእኔ ጭንቀት ትክለኛውና ተገቢው ‹‹ፕሮቶኮል›› የቱ ነው የሚለው የአቀማመጥም ሆነ የአጠራር ቅደም ተከተልና ክብር አይደለም፡፡ የአሁን ጭንቀቴ ዴሞክራሲ የሚፈልገውን የመንግሥት አውታራት ገለልተኛነትን ከማነፅ የአገር ሕመምና መድኃኒት አንፃር አሳሳቢው ጉዳይ፣ የአንድ አገር ርዕሰ ፈታሂ ፕሮቶኮልና ቦታ ቅደም ተከተል ሳይሆን የእሳቸው እዚያ ቦታ አስቀድሞ ነገር መገኘት ልክነትና አስፈላጊነት ነው፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢም ሆነ ወኪል ወይም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሰብሳቢ እዚያ ቦታ ቢገኙስ ኖሮ ጉዳዩ ራሱ አያስደነግጥም ነበር? በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ፕሮጀክት ምረቃ የዚህ ሰኔ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚውልበት የምርጫ ቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ መከናወኑ የማይገባ/ያልተገባ የምርጫ ቅስቀሳ የሚባል መሆኑ፣ በዚህ የፓርቲ (የመንግሥት መደበኛ ሥራ አይደለም) የቅስቀሳ ዝግጅት ላይ የሚገኘውን ወይም የማይገኘውን፣ የሚጠራውንና የማይጠራውን ለይቶ ማወቅ አለመቻል፣ ይህንን ቢያንስ ቢያንስ ነውር አለማድረግ ዴሞክራሲ የሚፈልገውን የመንግሥት አውታራትን ገለልተኛነት በማነፅ ሒደት ውስጥ ያለብንን ችግር የሚያመላክት መሊኪያ ነው፡፡

ፍርድ ቤት እንኳን ከፓርቲ ከመንግሥትም ተገቢውን ርቀት መጠበቅ አለበት፡፡ እንኳንስ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት፣ በመደበኛውም የዘወትር የሥራ ዕቅድ ውስጥ መንግሥትና ፓርቲን መለየት፣ በእነሱ መካከል ልዩነት ማበጀት አለበት፡፡ ይህ ሳይደረግ ቀረ ተብሎ እንዲታማ በጭራሽ ሰበብ መፍጠር የለበትም፡፡ ይህንን ደግሞ በሕግና በደንብ ዳር ድንበሩን በማበጀት መጀመር አለበት፡፡ ዝም ብሎ ልጥቅም ዝም ብሎ ምንጥቅም ሥርዓት የመገንባት ትግል አካል አይደለም፡፡ የዚህ ዓይነት ትንሽ፣ ጥቃቅን የሚመስሉ ጉዳዮችን አደገኛነትን መዘንጋት፣ ላለመዘንጋትም በህሊናና በሥርዓት ግንባታችን ሒደት ውስጥ የ‹‹ተጠንቀቅ›› ምልክት አለመትከል ነፃ ተቋማት የመገንባት ሥራችን ላይ ተፅዕኖ ያመጣል፡፡ መንግሥታዊ አውታራትን ከቡድን ታማኝነት የማላቀቅ የለውጥና የሽግግር ሥራችንን ለሚያሰናክል ግዴለሽነት ይዳርጋል፡፡

ነገ ወደ የምርጫ ጣቢያዎች የምንሄደው በዚህ ግብ ማዕቀፍ ውስጥ፣ ለውጡንና ሽግግሩን ከክሽፈት በማዳን ሰፊ ማ”ዕቀፍ ውስጥ የምርጫውን ሕጋዊነትና ሰላማዊነት ለመጠበቅ ዘብ በመቆም መንፈስ ነው፡፡ ለዚህ ዓላማ ሲባል ማንም በመራጭነት የተመዘገበ ኢትዮጵያዊ የድምፅ መስጫ ካርዱን/የመራጭነት መብቱን በጭራሽ ማቃጠል የለበትም፡፡ እከሌን ይምረጥ እከሌን ግን አይምረጥ አልልም፡፡ ያንን ለገዛ ራሱና በዕውቀት ላይ ለተመሠረተ የህሊና ፍርድ ይስጥ፡፡ ድምፅ መስጠት ማለት በዕውቀት ላይ የተመሠረተ፣ ለጭፍን ጥላቻም ለጭፍን ፍቅርም ያልጎበረ ፍርድ ነውና፡፡

ዴሞክራሲን የማደላደልና የመገንባት ሥራ ከየትኛውም ቡድን ታማኝነት፣ ተቀፅላነት፣ ፀድቶ የታነፀ ተቋም የመገንባት ሥራም ሆነ ተራ የሚመስለው ድምፅ የመስጠት (በመራጭነት ተመዝግቦ፣ የመራጭ ካርድ አግኝቶ፣ ይህንንም ወደ የመምረጫ ወረቀት ለውጦ ድምፅ የመስጠት የነገው ዕለት የጥቂት ጊዜ) ተግባር ራሱ ከፈቃደኝነት፣ ጊዜን ከመሰዋት የዘለለ የአቋሞች ብዙነት፣ ፀብና ጥል የለሽ ውድድር ያለበት፣ መብቶችና ኃላፊነቶች የተግባቡበት የአዲስ ሕይወትና የአዲስ ባህል ግንባታ ሥራ ነው፡፡ የሐሳብ ውድድሮችን የማስተናገድ ልምምድ ባልነበረው የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ውስጥ የነገው ድምፅ የመስጠት የዜግነት መብት፣ ሕገ መንግሥቱ በተለይ በአንቀጽ 38/1/ሀ እንደሚለው፣ ‹‹በቀጥታና በነፃነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካይነት በሕዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ መብት›› ይህንን መብት ትርጉም ያለው መኗኗሪያ የማድረግ ግዳጅና ግዴታ አለበት፡፡ ይህ ግዴታ ደግሞ በሰላምና በሕግ ውስጥ ሰላማዊና ሕጋዊ ሆኖ መከናወን አለበት፡፡ የምርጫውን በተለይም ከዚህ በኋላ በዋነኛነት የቀረውን የድምፅ መስጠቱን፣ ወዘተ (የድምፅ ቆጠራውን የውጤት አገላለጽን) ሒደት ሰላማዊነት፣ ሕጋዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነትና ተዓማኒነት ዘብ ቆሞ የመጠበቅ ጉዳይ በዚያው በሰላማዊነትና በሕጋዊነት ማዕቀፍ ውስጥ መከናወን አለበት፡፡ ሕገወጥነትን የመከላከል፣ ሕጋዊነትን የማስከበር፣ የግለሰብ ዜጋም ሆነ የመንግሥት የሕግ አስከባሪዎች ተግባር ግን የራስን የሕግ አክባሪነት የውኃ ልክ ከማስገመት መነሳት የለበትም፡፡

በተለይም መንግሥትና የመንግሥት የሥልጣን አካላት የድምፅ መስጠት ሒደቱ የፀብ ደጋሾች የመጫወቻ ሜዳ እንዳይሆን፣ ከማንምና ከምንጊዜም የበለጠ ግዴታ አለባቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰኔ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ከፌዴራልና ከክልል፣ ከደኅንነትና ከፀጥታ ተቋማት ተውጣጥተውና ተሰባስበው መግለጫ የሰጡት አመራሮችና እነሱም በበላይነት የሚመሯቸው ተቋማትና የሚያሠማሯቸው ሕግ አስከባሪዎችና የሕዝብ ደኅንነት ጥበቃ ሠራተኞች የጥበብ መጀመርያ መንግሥትንና ፓርቲን ለያይቶ ከማየት መነሳት አለበት፡፡ ምርጫና የምርጫ ሒደት በሚባለው ግጥሚያና ጨዋታ ውስጥ ተጋጣሚው ወይም ተወዳዳሪ ተጫዋች በመሆንና ሕግ አስከባሪ ወይም ገለልተኛ አጫዋች በመሆን መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ፣ ይህንንም የአገርና የሕዝብ ግንዛቤ አድርጎ መነሳት የመጀመርያው ታላቅ መነሻ ዕርምጃ ብቻ ሳይሆን ረዥም ጉዞ ጭምር ነው፡፡

ገለልተኛ ሆኖ መታነፅ በቀረው አገዛዝ ባለበት፣ ዴሞክራሲ የግድ የሚፈልገውን ገለልተኛ የመንግሥት አውታራት የማነፅ ውዝፍ ገና ተከፍሎ ያላለቀ ዕዳ ባለበት አገር ውስጥ፣ የነገው ውሏችን የድምፅ መስጠቱን ሒደት ሰላማዊነት፣ ሕጋዊነትና እኩል ተወዳዳሪነት ከማረጋገት በላይ መሄድ አያሻውም፡፡ በዚህ ላይ በአገር ውስጥ ምርጫውን፣ ከለውጡና ከሽግግሩ ጋር ፋይዳ ቢስ አድርጎ የማዋደቅ፣ በምርጫው የማኩረፍ ዝንባሌና አቋም አለ፡፡ የምርጫ ሐደቱን አበላሽቶና አኮላሽቶ ኢትዮጵያን ለማነቅ ምክንያት ሲፈልጉ የቆዩ ኃያላን አሁንም ገና ከአናታችን አልወረዱም፡፡ ነገ ዝም ብሎ ሌላ ቀን አይደለም የምንለው፣ ነገን በቅጡ ተጠቅመን የአገር የአርበኝነት ግዳጃችንን የምንወጣበት ቀን መሆን አለበት እያልን የቆየነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...