Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ​​​​​​​መሬትን ለፖለቲካ መሣሪያነት መጠቀም ይብቃ!

​​​​​​​መሬትን ለፖለቲካ መሣሪያነት መጠቀም ይብቃ!

ቀን:

በሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)

መሬት እንደ ሁኔታው የግል፣ የሕዝብ የመንግሥት ተብሎ ሊመደብ ሲችል በእኛ አገር ማንኛውም መሬት የመንግሥት ነው፡፡ ከዚያ እልፍ ሲልየብሔር/ብሔረሰቦችየጋራ ሀብት ነው ይባላል፡፡ ይህ በጣም አስቂኝና አስገራሚ የሆነ ነገር የተፈጠረው በኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲከኞች ሴራ ነው፡፡ በአገራችን መሬት በተለይም የአርሶ አደር የነፍስ ወከፍ መሬት ከኢኮኖሚ መሣሪያነት ይልቅ፣ የአገር ውስጥ ፖለቲካ መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ተደርጎ ቆይቷል፡፡መሬት አይሸጥም አይለወጥም” በሚል ጉንጭ አልፋ የመድረክ ላይ ክርክር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ሲጨቃጨቁ እሰማለሁ፡፡ ይህ ሁሉንም የመሬት ተጠቃሚ ዜጋ  የሚመለክት አጀንዳ ወደ መሬት ወርዶ የጉዳዩ ባለቤት በሰፊው እንዲከራከርበት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የጠቁሙ ጥቂቶች ናቸው፡፡

አጀንዳው ስለመሬት ጉዳይ መወያየት አስፈላጊ በሚሆንበት ወቅት ብቻ ልክ እንደ ክት ልብስ እየተቆጠበ፣  በፖለቲካ ፓርቲዎች ጎራ በጥንቃቄና በብልጠት ተይዞ ወደ መድረክ ብቅ እንዲል ይደረጋል፡፡  ፓርቲዎቹ መሬት መሸጥ መለወጥ ስለማይኖርበት ምክንያት መያዣ አድርገው የሚያቀርቡት ይበልጥ አርሶ አደሩን ነው፡፡አርሶ አደሩ መሬቱን ከሸጠ ከቦታው ላይ ተነቅሎ ይሰደዳልየሚል ሟርት ያስቀድማሉ፡፡ የቀድሞውን የመሬት ከበርቴ ሥርዓት ለመመለስ የአርሶ አደር መሬት በግዥ የሚሰበስቡ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች መጡብህ  በማለት፣  ጥያቄው በአርሶ አደሩ  አዕምሮ ውስጥ ፍርሃት እንዲያነግስ ያደርጋሉ፡፡  ይህ የፖለቲካ ሥልት ብዙኃኑን ሕዝብ በተለይም ደሃውን አርሶ አደር በፖለቲከኞች ጫማ ሥር ደፍቆ ለመያዝ ያገለግላል፡፡

እኛ የአርሶ አደር  ወገኖች ነን በማለት የውክልና ፈቃድ በስሙ ያወጡ በመምሰልየአዞ እንባ እያፈሰሱተቆርቋሪ መስለው ለመቅረብ የሚሞክሩ አሉ፡፡አዛኝ ቅቤ አንጓችማለት እንዲህ ነው፡፡  የሚፈልገውን ነገር አጥቶ የሚያለቅስ ሕፃን ልጅን ፍላጎት ማስተናገድ ያልቻሉ ወይም ያልፈለጉ ወላጆች ሕፃኑን ዝም ለማሰኘት  “አው…ው…ውጅቡ መጣብህ…እንደሚሉት ዓይነት ማለት ነው፡፡ የመሬትን ጥቅምና የበሬን ውለታ ከአርሶ አደር በላይ የሚያውቅ የለም፡፡ ሰዎቹ አርሶ አደር የሰብል መሬቱንና የቀንበር በሬውን በዋዛ ፈዛዛ ለማጣት አንደማይፈልግ ማወቅ ይሳናቸዋል፡፡

ከመሬት ከበርቴዎች ማቆጥቆጠጥ ተከላከልንልህ የሚለው አካል በቀጥታ መንግሥት ለማለት ነው፡፡ መሬትን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከዜጎች እየቀማ በመሬት ሊዝ እንደፈለገ ይሸጣል፡፡ ዜጎች የመሬት መሸጥ መብት ተነፈጉ እንጂ መሬት ከመሸጥ አልዳነም፡፡ ከግለሰብ በመግዛት የመሬት ከበርቴ የሚሆኑ ሰዎች ዕድል ተዘግቶ ይሆናል እንጂ፣ መሬትን ከመንግሥት በመግዛት አከማችተው የመሬት ከበርቴ የሚሆኑ ዜጎች አልታጡም፡፡ አርሶ አደሩን ከመሬቱ በማፈናቀል በግብርና እንቨስትመንት ስም ሰፋፊ ቦታዎችን አጥረው የሚያስቀምጡና በሪል ስቴት ስም የሚቆጣጠሩ በርካታ ሰዎች የሉምን? ዜጎችን የመሬት ሙሉ የባለቤትነት መብት በማሳጣት በመሬቱ ላይ ቋሚ ንብረት እንዳያደርጉ፣ በማሳ ላይ የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብትን እንዳይንከባከቡ፣ የመሬት ለምነትን በዘላቂነት ባለማስጠበቅ ለሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ወጪና ጉዳት ዳረገ እንጂ፣ ዜጎችንና መሬትን በአግባቡ አላገናኘም፡፡
የዜጎች የመሬት ባለቤትነት ሙሉ መብት መነጠቅ የዜጎችን ዘላቂ ሕይወት ይጎዳል፡፡ መንግሥት መሬትን በዝቅተኛ የጉዳት ካሳ ክፍያ ከዜጎች ወስዶ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ዋጋ ለደንበኞቹ ይሸጣል፡፡ ይህን ማድረግ ያስቻለውም በሕገ መንግሥቱ ላይ ስለመሬት የተቀመጠው አንቀጽ ነው፡፡ መንግሥት መሬትን በሸጠበት ዋጋ ዜጎች በቀጥታ ቢሸጡ ማግኘት ይችሉ የነበረውን ገቢያቸውን በሕግ አግባብ አታልሎ ይቀማቸዋል፡፡ መንግሥት ከዜጎች ላይ በርካሽ ዋጋ ወስዶ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ሽጦ ለዘለዓለሙ ይነቅላቸዋል፡፡ ከተሸጠው መሬት የተገኘውም ገቢ የአካባቢውን ሕዝብ እንዴት እንደጠቀመ ለሕዝቡ ግልጽ አይደረግም፡፡ ታዲያ ዜጎችን ማን ነቀለ ሊባል ይችላል?

በመንግሥት ለሚገነቡ ተቋማትና ለግል ኢንቨስተሮች ሲባል ከዚህ ቀደም ከእርሻ መሬታቸው ላይ እንዲነሱ የተደረጉ ቤተሰቦች፣ አሁን ከሚገኙበት የከፋ የኑሮ ሁኔታ ለዚህ በቂ ማስረጃ ይገኛል፡፡ የተሰጣቸው የዓመት ቀለብ የማይሸምት የካሳ ግምት ከጎዳና ተዳዳሪነት አላዳናቸውም፡፡ 

መንግሥት በመሬት ባለቤትነት ላይ ባለው የጠቅላይነት ሚና አዲስ በሚመሠረቱ የገጠር ከተማ ማዕከላት ዙሪያ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ይበልጥ የጉዳቱ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፡፡ የንዑስ ከተሞች ማዘጋጃ ቤቶች የአርሶ አደሩን እርሻ ቀስ በቀስ በሊዝ ሥርዓት ውስጥ እያስገቡ ስለሚሄዱ፣ አርሶ አደሩ መሬቱን እንዲያጣና አማራጭ በሌለው ሁኔታ ከግብርና ሥራ  ለዘለቄታው  እንዲፈናቀል የማድረግ ሥጋት ደቅነውበታል፡፡  ይህ በአርሶ አደር ቤተሰብ ደረጃ ሊስተካከል የማይችል አደገኛ የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጥ ነው፡፡ የከተማ ንዑስ ማዕከላቱ የአርሶ አደሩን መሬት በከተማ መሬት አስተዳደር ሥር ለማስገባት የሚያደርጉትን ዕቅድ ለመቅደም አርሶ አደሩ በግብርና ሥራ የሚተዳደርበትን መሬት ቤት ለሚሠሩ ወገኖች ቀድሞ  በዝቅተኛ ዋጋ ስለሚሸጥ፣ መሬቱ ከግብርና ሥራ ውጪ ይሆናል፡፡

በገጠር ንዑስ የከተማ ማዕከላትና በአቅራቢያቸው በሚገኝ መሬት ላይ የሚስተዋለው የቤት ሥራ መስፋፋት መንስዔ ይህ  የአርሶ አደሩ የመሬት ሙሉ የባለቤትነት መብት አለመከበር  የፈጠረው ሥጋት ነው፡፡ ይህ በሥጋትና በመጠራጠር ላይ የተመሠረተ የኑሮ ሁኔታና የዜጎች ንብረት የማፍራት ችግር  አርሶ አደሩንና የአገራችንን ኢኮኖሚ በሁለት መንገድ ጎድቶታል፡፡ አንደኛ መሪ የከተማ ፕላን ገና ባልወጣላቸውና የከተማ ኢኮኖሚ ሕይወት ባልተጀመረባቸው የገጠር ንዑስ ማዕከላት፣ እንዲሁም በነባር ከተሞች ጥግ የቤት ግንባታ የሚያጧጡፉ ዜጎች ትርፍ በማይኖረው የቤቶች ግንባታ ላይ ያላቸውን ጥሪት በማፍሰስ ለረዥም ጊዜ ባዶ ቤት በኪሳራ ሲጠብቁ እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ ሁለተኛ ለግብርና ሥራ መዋል የሚገባውን ለም መሬት ከምርት ኃይል በመቀነስ፣ የግብርና ምርት ውጤትም ቀንሶ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገው የቤተሰብም ሆነ አገራዊ ጥረት እንዲዳከም ሆኗል፡፡  

በነባር ከተሞች ያለው ችግርም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለግንባታ ሥራ የሚውል መሬት ለማግኘት ሲባል የከተማ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ሠፈራቸውበመልሶ ልማትስም ሲነሱ፣ የዜጎች የወደፊት የኑሮ ሁኔታ ተቀባይነት ባለው መንገድ ታሳቢ አይደረግም፡፡

በከተሞች የሚኖሩ ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆነ ዜጎች የዚህ ችግር ሰለባዎች ናቸው፡፡በልማት ሰበብ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ሰፈር በአደገኛ ሁኔታ እንዳይፈናቀሉ የሚያደርግ ዜጋ ተኮር የልማት ዕቅድ አይዘጋጅም፡፡ መፈናቀል ከቀድሞ መኖሪያ ሠፈር በአካል መነሳት ብቻ ሳይሆን ከሠፈሩ ያገኝ ከነበረው ማንኛውም አገልግሎት፣ ከለመደው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ሕይወት እንዲለይ መደረግም ጭምር ነው፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በትልልቅ ከተሞች የተደረጉ ሰፋፊ የመልሶ ማልማት ጥረቶች  ይህን ዜጋ ተኮር ልማት ታሳቢ አላደረጉም፡፡የልማት ተነሺዎችኃላፊነት በጎደለው መንገድ  ተጠራርገው  በከተማ ጥግ አዲስ በተከፈቱ፣ አገልግሎት ገና ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች የትም ይጣላሉ፡፡
ዜጋ ተኮር ልማት የመልሶ ማልማት ተግባር  በሚካሄድበት ቦታ ለሚገኙ ቀደምት ነዋሪዎች የኑሮ ዋስትና እንዲሰጥ የሚያደርግ፣ ከአዲሱ ልማት ጋር በተጓዳኝ የሚታቀድ የመልሶ ማቋቋም የፕሮጀክት ፓኬጅ እንዲኖር ግድ ይላል፡፡የልማት ተነሺዎቹለረዥም ጊዜ ከኖሩበት የትውልድ ቀዬአቸው ርቀው እንዳይሰደዱ  መንደር ተሠርቶላቸው በአዲስ ሁኔታ በጎን እንዲኖሩ መደረግ ይቻላል፡፡ ዳሩ ግንበሰው ቁስል እንጨት ስደድበትእንዲሉ  የልማት ተነሺዎችን የሚታደግ የረባ ተጓዳኝ ዕቅድ አይያዝም፡፡ የዚህ ጭካኔ  የተሞላው ነባር ቦታዎችንና ነዋሪዎችን ከኖሩበት ቦታ የማፈናቀል  እንቅስቃሴ  ከኢኮኖሚያዊናማኅበራዊ ዓላማው ይልቅ ፖለቲካዊ ዓላማው ያመዘነ ነበር፡፡ 

በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከተውን የኅብረተሰብ ክፍል ትውልድና የአገራችንን የረዥም ዘመን የታሪክ አሻራዎች አዳክሞ በማጥፋት፣ በምትኩ የወቅቱን ገዥ መደብ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ፍላጎት በልማት ስም ለማሳካት ጥረት ተደርጓል፡፡

የዚህ የችግር አቆራኝ ቀለበት የኢሕአዴግ [ብልፅግና ፓርቲ?] የሚከተለው በሕገ መንግሥት የተቸነከረ አጉል የመሬት ፖሊሲ ነው፡፡መሬት አይሸጥም አይለወጥም” በማለት አርሶ አደርን ከመሬትና ከሕይወት አፈናቅሎ ለአርሶ አደር ጠበቃ ነኝ የሚል ፓርቲና መንግሥት ቆም ብሎ ማሰብ አለበት፡፡መሬት አይሸጥም አይለወጥም” የሚለው የሕገ መንግሥት አንቀጽየአዛኝ ቅቤ አንጓችአስተሳሰብ፣ የአርሶ አደሩን ደም በመምጠጥ በብልጣ ብልጥነት ለዘለዓለም ለመኖር እንዲያስችል በጥንቃቄ የተዘጋጀ ነው፡፡ አርሶ አደሩን አስሮ የሚይዝና ዜጎችን ከመሬት የለያየ መሰሪ አንቀጽ  መሻሻል አለበት፡፡የዜጎች የመሬት ባለቤትነት ሙሉ መብት ተረጋግጧልበሚል ቢስተካከል ለአገራችን ዘላቂ ዕድገትና ሰላም አስተዋጽኦ የሚያደርግ ይመስለኛል፡፡

በመሬት ላይ ሙሉ መብት መኖር አለመኖሩ ቀድሞ ሳይጠቀስ ስለመሸጥ አለመሸጥ መጠቀሱ የሕፃን ልጅ ማስፈራሪያ ዓይነት ነገር ነው፡፡  ከላይ እንደተገለጸው ሕፃኑ የሚፈልገውን ነገር ለመከልከል አባት/እናትአው…ው…ውጅቡ መጣብህ…እንደሚሉት ይመስላል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክሩንእዚያው ዘንቦ እዚያው እንዲያባራከማድረግ ይልቅ፣ ወደ ታች ወርዶ ጥቅሙም ሆነ ጉዳቱ በቀጥታ ለሚመለከታቸው ዜጎች ደርሶ በቀጥታ በሚደረግ ሕዝባዊ ውይይት እንዲወሰን ይደረጋል ቢሉ መልካም ነው፡፡ እየተዳደርን ያለነው በወያኔያዊ ሕገ መንግሥትና ዝርዝር ሕግ ስለሆነ፣ ከምርጫው በኋላ በሚቋቋመው በሕዝብ በተመረጠ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ መሻሻል ያለባቸው  በርካታ ሕጎችና መዋቅሮች አሉ፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ፉክክር ውይይት ወቅት ወሳኝ ጉዳዮችን አረንጓዴ መብራት  አሳይቶ አለመዝጋት፣ ሕገ መንግሥቱም ሆነ በዚህ ላይ የተመሠረተው ሕግና መዋቅር ሁሉ ወደፊትም ባለበት እንደሚቀጥል አመላክተው እንዳለፉ ይቆጠራል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የዲፓርትመንት ኃላፊ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...