Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዳዲስ ባንኮች ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል እየገጠማቸው ያለው ፕሬዚዳንት የመሰየም ተግዳሮት 

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱን የባንክ ኢንዱስትሪ ለመቀላቀል የሚያስችላቸውን ምሥረታ ያካሄዱና ለማካሄድ እየተሰናዱ ያሉ አዳዲስ ባንኮች ይፈተኑበታል ተብሎ ከሚጠበቀው ተግዳሮቶች ውስጥ አንዱ፣ ባንኮቻቸውን የሚመሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይም ፕሬዚዳንቶችን መሰየም ነው፡፡

በኢንዱስትሪው ውስጥ ካለው የባለሙያዎች እጥረት አኳያ ብቁና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚጠይቀውን መሥፈርት አሟልተው የሚገኙ የሥራ መሪዎች ለመሰየም ሁሉም በየፊናቸው ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ይህንንም ለማግኘት ዓይናቸውን የጣሉት፣ አሁን በሥራ ላይ በሚገኙ ባንኮችና በተለያዩ ባንኮች ውስጥ በፕሬዚዳንትነት አገልግለው የነበሩት ላይ ነው፡፡

በዚሁ መሠረት ይመጥናሉ ያሏቸውን በማጨት ላይ ናቸው፡፡ እስካሁን ባለው ሒደትም ወደ ሥራ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ ባንኮች ውስጥ አምስት ባንኮች በፕሬዚዳንት ወይም በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ያገለግሉናል ያሉትን ከተለያዩ ባንኮች በመውሰድ ይፀድቅላቸው ዘንድ ያመለከቱ ሲሆን፣ የአንድ ባንክ ፕሬዚዳንትነት ሹመት ደግሞ ፀድቋል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንዳመለከቱት፣ እነዚህ የባንኮች የመጀመርያዎቹ ፕሬዚዳንቶች ወይም ሥራ አስፈጻሚዎች እንዲሆኗቸው ያጯቸውን የሥራ መሪዎች ለብሔራዊ ባንክ ያቀረቡት ፀሐይ፣ አማራና አሃዱ ባንኮች ናቸው፡፡ ከዚህም ቀደም ብሎ ሒጅራ ባንክና ጎህ ቤቶች ባንክ በዕጩነት ያቀረቧቸውን ፕሬዚዳንቶች ለማፀደቅ ለብሔራዊ ባንክ ማመልከታቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ፣ አሃዱ ባንክ የባንኩ ፕሬዚዳንት አድርጎ ያጫቸው የቀድሞ የቡና ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ እሸቱ ፋንታዬን ነው፡፡ ፀሐይ ባንክና አማራ ባንክ ደግሞ የባንካቸው ፕሬዚዳንቶች ይሆናሉ ብለው ያቀረቧቸውን የሥራ መሪዎች ያገኙት በአሁኑ ወቅት በዳሸን ባንክ በምክትል ፕሬዚዳንትነት እያገለገሉ ያሉ ናቸው ተብሏል፡፡ በዚህ መረጃ መሠረት ሦስቱ አዳዲስ ባንኮች ያቀረቧቸውን ዕጩ ፕሬዚዳንቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያፀድቅላቸው ዘንድ በማመልከት ምላሽ እየተጠባበቁ ነው፡፡  

ከእነዚህ ሦስት ባንኮች ሌላ ቀደም ብሎ ደግሞ ጎህ ቤቶች ባንክ በተመሳሳይ መንገድ በፕሬዚዳንትነት እንዲያገለግሉት በጎህ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ የታጩት የቀድሞው አቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አስማረ ሹመት በብሔራዊ ባንክ የፀደቀ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት ሥራ መጀመራቸው ታውቋል፡፡ ሒጅራ ባንክም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን እያገለገሉ ያሉትን አቶ ዳዊት ቀኖ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ በማጨት ለብሔራዊ ባንክ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ እየጠበቀ ቢሆንም፣ ሹመቱ እስኪፀድቅ በታጩበት ኃላፊነት ሥራ ጀምረዋል፡፡  

እንደ እነዚህ ባንኮች ሁሉ የምሥረታ ጉባዔውን ያካሄደውና በቅርቡ ሥራ የጀመረው ዘምዘም ባንክም፣ የባንኩን የመጀመርያ ፕሬዚዳንት በማድረግ የሾመው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩትን ወ/ሮ መሊካ በድሪ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

ለባንክ ፕሬዚዳንትነት የሚታጩ የሥራ መሪዎችን በማፈላለግና በመሰየሙ ሒደት የብሔራዊ ባንክ መመርያንና መሥፈርት ማሟላት ይጠበቃል፡፡ አሁን ባለው መሥፈርት መሠረት የአንድ ባንክ ፕሬዚዳንት ለመሆን በአንድ ባንክ ውስጥ ቢያንስ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ለአሥር ዓመት ያገለገሉ የሚለው መሥፈርት አንዱ ነው፡፡ በቅርቡም አምስቱ ባንኮች ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ ያደረጓቸውንና በብሔራዊ ባንክ ሹመታቸው ከፀደቀላቸው የሥራ መሪዎች ውስጥ ሁለቱ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ ናቸው፡፡ ሁለቱ ደግሞ የዳሸን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን እየሠሩ ያሉ ሲሆን፣ ሁለቱ የአቢሲኒያና የቡና ባንክ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡

በቅርቡ ሥራ የሚጀምሩትና የባንኮቻቸውን ፕሬዚዳንቶች ሹመት ያፀደቁትና በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት ባንኮች በአጠቃላይ ከ220 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ያሏቸው ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የተከፈለ ካፒታላቸው መጠን ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ከእነዚህ ባንኮች ከፍተኛ የተባለውን ካፒታል የያዘው አማራ ባንክ ነው፡፡ አማራ ባንክ በስድስት ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ምሥረታውን ያካሄደ ሲሆን፣ በአገሪቱ የአክሲዮን ኩባንያዎች ታሪክ ከፍተኛ የተባለውን ከ184 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖችን በመያዝ ኢንዱስትሪውን የሚቀላቀል ይሆናል፡፡

አሃዱ ባንክ ደግሞ 580 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ ምሥረታውን አካሂዷል፡፡ ከ2.9 ቢሊዮን ብር በላይ የተፈረመ ካፒታልና ከ734.7 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል በመያዝ ምሥረታውን ያካሄደው ፀሐይ ባንክ ደግሞ ያሉት ባለአክሲዮኖች 373 ብቻ ናቸው፡፡ በቅርቡ ወደ ሥራ ለመግባት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መገኘቱን ያሳወቀው ጎህ ቤቶች ባንክ፣ ያሰባሰበው የተከፈለ ካፒታል ከ530 ሚሊዮን ብር በላይ ሆኖ የባንኩን ምሥረታ ማካሄዱ ይታወሳል፡፡ ሒጅራ ባንክም 560 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና 1.2 ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል ይዞ ምሥረታውን ያካሄደ ሲሆን፣ ሁለተኛ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች