Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባው የከሰል ፋብሪካ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ እስካሁን ሲንቀሳቀስባቸው ከነበሩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በተጨማሪ፣ በማዕድን ልማት ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችለውን የድንጋይ ከሰል ፋብሪካ ሊገነባ ነው፡፡

ሰንማይኒንግ የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ እህት ኩባንያ፣ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለውን የከሰል ፋብሪካ የሚገነባው በጉራጌ ዞን ነው፡፡

የዚህ ፋብሪካ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ሰኔ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር አቶ ታከለ ኡማና የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው በተገኙበት ተቀምጧል፡፡

ሰንሻይን አዲሱን ኢንቨስትመንት በተመለከተ በላከው መግለጫ አገራችን በተለያዩ መአድናትና የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች ቢሆንም እስካሁን ድረስ በበቂ ሁኔታ ይህን እምቅ ሀብት መጠቀም አልተቻለም፡፡ ከእነዚህ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል የድንጋይ ከሰል አንዱ በመሆኑ በዚህ ኢንቨስትመንት መሰማራት ጠቀሜታው ታይቶ ሊገባ መቻሉን የሚጠቁም ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ የተፈጥሮ ሀብት ብትታደልም እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት የድንጋይ ከሰልን ለሲሚንቶ ፋብሪካ ሲሚንቶ ለማምረት ሒደትና ለኢነርጂ ማመንጨት ለመጠቀም በየዓመቱ ከውጭ የምታስገባ መሆኑን የሚያመለክተው የሰንሻይን መረጃ የዚህ ፋብሪካ መገንባት ለድንጋይ ከሰል የምታወጣውን ወጪ ይቀንሳል፡፡

ይህንም ሁኔታ በመገንዘብ፣ በመአድንና ነዳጅ ሚኒስትር በተደረገለት ግብዣና በራስ ፍላጎት የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ በጉራጌ ዞን ለመትከል ሙሉ የአዋጪነት ጥናት በማከናወንና የድንጋይ ከሰሉን በማጠብ የተሻለ የጥራት ደረጃ ለማድረስ የሚረዳ የእጥበት ደረጃ ማረጋገጫ ወደ ደቡብ አፍሪካ በመላክ ያስመረመረን ሲሆን በዚሁ መሠረት የፋብሪካ ዲዛይን በማሠራት ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡

ሰንማይኒንግ በጉራጌ ዞን ሊተክል ያቀደው የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ፋብሪካ በዓመት የማምረት አቅሙ 800 ሺሕ ቶን የታጠበ የድንጋይ ከሰል ሲሆን፣ ለዚሁ የሚያስፈልገውን አንድ ሚሊዮን ቶን ያልታጠበ የድንጋይ ከሰል ከጉራጌ ዞን ከተረከበው የድንጋይ ከሰል መአድን ማውጫ ሜዳና በአካባቢው ከተደራጁ የድንጋይ ከሰል አውጪ የኅብረት ማኅበራት በግዥ በመረከብ የሚሠራ ይሆናል፡፡ ለፋብሪካው ተከላ የሚያስፈልገውን የ23.3 ሔክታር የመሬት ፈቃድ ከጉራጌ ዞን ተረክቦ ዛሬ ይፋዊ ሥራውንም መጀመሩን ኩባንያው አስታውቋል፡፡

ፋብሪካው ሥራውን ሲጀምር ከሰል ማውጫን ጨምሮ በጠቅላላው ለ500 የአካባቢው ነዋሪዎችና ከ1‚500 በላይ ለሆኑ ለተደራጁ ማኅበራት የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡

የፕሮጀክቱ ጠቅላላ የኢንቨስትመንት ወጪ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ይሚያመለክተው ይኸው መረጃ ከዚህ ውስጥ ለፋብሪካው ማሽነሪ ግዥ እስከ 190 ሚሊዮን ብር ወጪ ያደረጋል፡፡ ፋብሪካው ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ ተከትሎ የተሠራ ስለሚሆን በአካባቢው ምኅዳር ላይ በተቻለ መጠን ለውጥ የማያመጣ ይሆናል ተብሏል፡፡

የዚህ ፋብሪካ ምርት በዋናነት የሚውለው ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ግብዓት ሲሆን፣ እስካሁን ከውጭ በማስመጣት ሲጠቀሙ ነበር፡፡ አሁን ግን ፋብሪካው መገንባቱ አገሪቱ ለድንጋይ ከሰል ግዥ የምታወጣውን እስከ 67.5 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት ያስችላል ተብሎ ታምኗል፡፡  

እንደ ሰንሻይን ማይኒንግ መረጃ የፋብሪካው ግንባታ በአሥራ አንድ ወራት ይጠናቀቃል፡፡ በፕሮጀክቱ ጥናት ላይ እንደተመለከተው፣ የፋብሪካውን ግንባታ ለማጠናቀቅ 11 ወራት የሚፈጅ ሲሆን፣ በተያዘለት ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሰንማይኒግና ትሬዲንግ ኩባንያ የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ እህት ኩባንያ ሲሆን፣ በሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን፣ በመንገድ ሥራ፣ ሆቴሎች ሥራና በመሳሰሉት ግዙፍ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት ይታወቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ናሽናል ኦይል (ኖክ) ኩባንያ በተመሳሳይ መንገድ የድንጋይ ከሰል ማምረቻ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡ በአሶሳ ከተማ ሰኔ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ በተቀመጠበት ወቅት እንደተገለጸው ግንባታው በሁለት ቢሊዮን ብር ካፒታል የሚካሄድ ነው፡፡

900 ሺሕ ቶን የድንጋይ ከሰል ማምረት አቅም ይኖረዋል የተባለው የዚህ ፋብሪካ ግንባታው በ11 ወራት ተጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡

ኖክ በሚገነባው ፋብሪካ የድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ ሥርዓት ላይ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ዶ/ር) እና የቤንሻንጉል ጉምዝ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ተገኝተዋል፡፡

በድንጋይ ከሰል ምርትን በተመለከተ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ተጨማሪ የድንጋይ ከሰል ማምረቻዎችን በቀጣይ ቀናት በተመሳሳይ መንገድ ግንባታቸውን ለማስጀመር መታቀዱን ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች የሚገነቡ የድንጋይ ከሰል ማምረቻዎች በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም ይኖራቸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች