ሰኞ ሰኔ 14 ቀን ጠዋት የሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ያለ ጸጥታ ችግር እንዲከናወን ኋላፊነት የወሰዱ የጸጥታ ኃይሎች በምርጫው ዋዜማ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ቅኝት እያደረጉ ነው።
በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የፌዴራል ፖሊስ ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት እና የሪፐብሊክ ጋርድ (ጥበቃ) አባላት በተለያዩ ተሽከፍካሪዎች ላይ ሆነው ቅኝት ሲያደርጉ ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ ተስተውለዋል።
በምርጫው ዋዜማ እሁድ የጸጥታ አስከባሪዎች ቅኝት በሰፊው የተስተዋለ ሲሆን ፤ ለወታደራዊ እንቅስቃሴ ምቹ እና ፈጣን የሆኑ ባለአራት እግር ሞተር ሳይክል ተሽከርካሪዎች ላይ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልቡ የሪፐብሊክ ጥበቃ አባላት በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በሽሮሜዳ ፣ ስድስት ኪሎ ፣ ፒያሳ አካባቢዎች ሲዘዋወሩ ተስተውለዋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ብርቱካን ሚደቅሳ ቅዳሜ ሰኔ 12 ቀን ለጠቅላይ ሚንስትሩ በጻፉት ደብዳቤ አስተዳደራቸው ቀዳሚ ትኩረቱን በምርጫ ጸጥታ ጉዳይ ላይ እንዲያደርግ እንዲሁም የአየር ትራንስፖርትን ያካተተ የትራንስፖርትና የሎጀስቲክስ አቅርቦት ለአስቸኳይ ሁኔታዎች ዝግጁ እንዲሆን ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እሁድ ሰኔ 13 ቀን ብሔራዊ የምርጫ ደህንነት እዝ አባላትን በመሰብሰብ የተደረገውን ዝግጅት እንደገመገሙ የጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት መረጀ ያመለክታል።
በዚህ ግምገማም ከጽጥታ ኃይሎች ስምሪት በተጨማሪ ፤ በድሮን እና በሳተላይት የታገዘ የምርጫ የደህንነት ቅኝት በመላ የሀገሪቱ እየተከናወ ስለመሆኑ ገለጻ መደረጉን የጽ/ቤቱ መረጃ አመልክቷል።