የበሻሻ ከተማ የሃሮና የሰኮቴ የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ መስጫ ሳጥንና የቁሳቁስ ዝግጅት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሌሊቱ 11:30 ጀምሮ መካሔድ መጀመሩን ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ መመልከት ችሏል። የምርጫ ጣቢያዎቹ ጎን ለጎን ይገኛሉ።
የምርጫ ጣቢያዎቹ በድምሩ 2289 መራጮችን የተመዘገበ ሲሆን፣ ከንጋቱ 12:00 ሰዓት ላይ ድምፅ መሰጠት ጀምረዋል። የመጀመሪያውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር) መራጭ በሆኑበት የሃሮ የምርጫ ጣቢያ 1,500 መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፣ በሰኮቴ 789 መራጮች ተመዝግበዋል።
ድምፅ ለመስጠት የተመዘገበው መራጭ ከ 11:30 ሰዓት ቀደም ብሎ ሰልፍ መያዝ የጀመረ ሲሆን፣ ለፓርላማ ዓቢይ (ዶ/ር) ብልፅግና ፓርቲን፣ አቶ ካሊድ ጀማል ኢዜማን፣ እንዲሁም አቶ ዳግም ዋሪሶ እናት ፓርቲን ወክለው ይወዳደራሉ።
ለጨፌ ኦሮሚያ የክልሉ ምክር ቤት ግን ብልፅግና ፓርቲ ብቻውን ይወዳደራል።
ሪፖርተር ቅዳሜ ሰኔ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ 10 ሰዓት ገደማ በጅማ ከተማ በዞኑ ከሚገኙ የምርጫ ክልሎች በአንዱ ባደረገው ጉብኝት በምርጫ ክልሉ ለሚገኙ 89 የምርጫ ጣቢያዎች ተጨማሪ ሁለት ሁለት የምርጫ አስፈፃሚዎች ውል ገና እየተገባ ነበር። የዚህ ተግባር ትዕዛዝ ከማዕከል የምርጫ ቦርድ ዘግይቶ ለቅዳሜ አጥቢያ አርብ ምሽት ከነ ስም ዝርዝሩ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል ።
እሁድ ሰኔ 13 ቀን 2013 ዓ. ም. በጅማ ከተማ ሦስት የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁስ ረፋዱ ላይ የምርጫ ቁሳቁስ ገና አለመድረሱንና የድንኳን ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ለማየት ተችሏል።
ይሁንና የዞኑ የምርጫ አስተባባሪ እሁድ ከሰዓት ቁሳቁስ ሙሉ በሙሉ ተሰራጭቶ አልቋል ብለዋል።
- Advertisement -
- Advertisement -