በየካ ምርጫ ክልል 28 ምርጫ ጣቢያ 7 ስር ለተቋቋመው ንዑስ የምርጫ ጣቢያ የተመደቡ ምርጫ አስፈጻሚዎች እስከ ቀትር ድረስ ባለመገኘታቸው በድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ መስተጓጎልን ፈጥሯል።
የሪፖርተር ምርጫ ዘገባ ቡድን ያነጋገራቸው የምርጫ ጣቢያው አስተባባሪ አቶ አዲስ ዳምጤ እርሳቸው በሚመሩት ምርጫ ጣቢያ 7 ስር 1700 መራጮች መመዝገባቸውን ነገር ግን የመራጮች ቁጥር በመጨመሩ ንዑስ ጣቢያ እንደተቋቋመ ገልጸው ለንዑስ ጣቢያው አምስት ምርጫ አስፈጻሚዎች የተመደቡ ቢሆንም በድምጽ መስጫው ቀን ሳይገኙ ቀርተዋል።
በዚህ ምክንያትም እርሳቸው ለሚያስተባብሩት ምርጫ 7 የተመደቡትን ምርጫ አስፈጻሚዎች ለሁለት በመክፈል የምርጫ ሂደቱን ረፋዱ ላይ እንዳስጀመሩ ገለጸዋል።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን የዚህ ንዑስ ምርጫ ጣቢያ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እንደከን አላጣውም። ለንዑስ ምርጫ ጣቢያው የተላከው የድምጽ መስጫ ወረቀት ከመራጮች ቁጥር በእጅጉ ያነሰ ሆኖ መገኘቱን አቶ አዲስ ለሪፖርተር ገልጸዋል።
በንዑስ ምርጫ ጣቢያው የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 481 ቢሆንም ከምርጫ ቦርድ የተላከው የድምጽ መስጫ ወረቀት ግን 250 ብቻ እንደሆነ የተናገሩት አቶ አዲስ ፤ ጉዳይን ለምርጫ ቦርድ የበላይ አመራሮች በማሳወቅ ተጨማሪ የድምጽ መስጫ ወረቀት እንደሚላክላቸው መልስ አግኝተው ይህንኑ እየተጠባበቁ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚህ ምርጫ ጣቢያ እጩ ተመራጭ የሆኑት የዳቆን ዳንኤል ክብረት የምርጫ ወኪል ችግሩ መከሰቱን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል።