Sunday, November 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜና‹‹ቀኑ ለመራጮችና ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ለአገራችንም ጥሩ ነው›› ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣...

  ‹‹ቀኑ ለመራጮችና ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ለአገራችንም ጥሩ ነው›› ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሠብሳቢ

  ቀን:

  የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እኩለ ቀን ላይ ምርጫውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ቀኑ ለመራጮች፣ ለፓርቲዎችና በአጠቃላይ ለአገራችን ጥሩ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመጀመርያው ዙር የምርጫ ሒደት እስካሁን አንድም የፀጥታ ችግር አልገጠመንም፡፡ አምቦ አንድ ጣቢያ ላይ ምንም የተፈጠረ ነገር ሳይኖር ለአስፈጻሚዎች በደረሳቸው መረጃ በመደናገጥ ለጊዜው ገለል ብለዋል፡፡ ነገር ግን እናስቀጥለዋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከባድ ችግር የለም፡፡ ምርጫው መደረግ ባለባቸው ሁሉም ሥፍራዎች እየተካሄደ ነው፡፡ ዜጎችም እየመረጡ ይገኛሉ፡፡ ምርጫው መደረግ ባለባቸው ጣቢያዎች በአብዛኛው በሚባል ሁኔታ በሰዓቱ ከፍተው መራጮችን ሲያስተናግዱ ቆይተዋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ 9 ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ኃላፊነት የጎደላቸው አስፈጻሚዎች በቦታቸው ባለመገኘታቸው ጣቢያዎቹ ሳይከፈቱ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ቦርዱ ወዲያው መፍትሔ ወስዷል፡፡ በዘጠኙ ጣቢያዎች የተፈጠረውን ክፍተት በመሙላት 27 አስፈጻሚዎች ቃል ገብተው ተሰማርተዋል፡፡ ምርጫውም እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ 

  የመዝገብ መጥፋት 

  አዲስ አበባ ላይ አንድ የመራጮች መዝገብ የጠፋ ሲሆን፣ ይህንን እናጣራለን ያሉት ወ/ሪት ብርቱካን፣ ይህ መራጮችን ችግር ውስጥ እንደማያስገባና በአፋጣኝ መዝገብ ተልኮ ካርዳቸው እየታየ የምርጫ ሒደቱ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ 

  የቁሳቁስ እጥረት

  በአንዳንድ ቦታዎች የቁሳቁስ እጥረት ገጥሟል፡፡ ይህ አታሚው ከተሰጠው ትዕዛዝ ውጪ በ50/50 ያሸጋቸው የመራጮች ወረቀቶች መኖራቸው ችግር ፈጥሮ ነበር፡፡ የታዘዘው 100/100 አንድ ላይ ተጣብቆ እንዲመጣ ነበር፡፡ ይህ ችግር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ አልተከሰተም፡፡ ችግሩ የተከሰተው በክልል ላይ ሲሆን፣ የጎላው ደግሞ አሶሳ ላይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የድምፅ መስጫ ወረቀቱ ስላለቀባቸው በአየር ኃይልና በኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፋጣኝ አሶሳ እንዲደርስ እናደርጋለን ብለዋል፡፡ 

  አሶሳ ላይ ለተፈጠረው የመምረጫ ወረቀት እጥረት መራጮች ላይ ለሚፈጠረው እንግልት ይቅርታ እንጠይቃለን ሲሉም ወ/ሪት ብርቱካን ተናግረዋል፡፡ 

  የሲቪል ሶሳይቲ ታዛቢዎች

  የሲቪል ሶሳይቲ ታዛቢዎች በየቦታው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ አረጋግጠናል፡፡ አንድ ሁለት ቦታ ላይ ግን ታዛቢዎችን አናስገባም ብለው ያለመቀበል ሁኔታ በቦርዱ አስፈጻሚዎች ታይቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ለዚህ መፍትሔ ተሰጥቶ እየታዘቡ ነው፡፡ 

  ያልተከፈቱ ጣቢያዎች 

  በደቡብ ኡባ ደብረፀሐይ በተባለ የምርጫ ክልል አንድ ሰማያዊ ምርጫ መስጫ ሳጥን ተሰርቋል፡፡ ይህንን ፖሊስ እያጣራ ነው፡፡ ብብርና አግሊቾ ምርጫ ክልሎች ላይ (የክልል ምክር ቤት) ምርጫ ክልሎች ሆነው፣ የተወካዮች ምክር ቤትንም ይመርጣሉ፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ሰነድ ምንም ችግር ባይኖረውም፣ የደቡብ የምርጫ ክልሎች ዲዛይን ውስብሰብ በመሆኑ አንዱ መሄድ የነበረበት ለሌላው ሄዷል፡፡ ነገር ግን ምርጫው ሳይስተጓጎል እየተከናወነ ነው፡፡

  እዚህም እዚያም የምርጫ ወረቀት ያነሳቸው የምርጫ ጣቢያዎች አሉ፡፡ ከሥር ከሥር ለማድረስ የሚያስፈልገው ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን፣ መግለጫው ከተሰጠበት እኩለ ቀን አንስቶ የጎደለው እንደሚሟላ ተገልጿል፡፡  

  ቦርዱን ያሳሰበው ጉልህ ችግር 

  በየምርጫ ጣቢያው የፖለቲካ ፓርቲዎች ወኪሎቻቸውን አስቀምጠው ጉዳዩን የመታዘብ፣ የማየት፣ ችግር ከጋጠመ አስመዝግበው ወደ ሕግ የመውሰድ መብት አላቸው፡፡ ይህን በተመለከተ በአብዛኛዎቹ ክልሎች ጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው ማለት ቢቻልም፣ 3 ክልሎች ላይ በተለይ በሁለቱ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ሥጋት ታይቷል፡፡  በአማራና በደቡብ ክልሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ወኪሎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ፣ እየተደበደቡና ባጅ እየተቀሙ እንደሆነ፣ የገዥው ሲቀር ከሁሉም ፓርቲዎች አቤቱታ ተቀብለናል ያሉት ወ/ሪት ብርቱካን፣ ይህ እንዲፈታ ለክልሉ አስተዳዳሪዎቸ መናገራቸውን ተስተካክሎ የፓርቲ ወኪሎች በቦታቸው ካልተገኙ የምርጫውን ተዓማኒነት አደጋ ላይ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ 

  ማስተካከያ በአፋጣኝ ማድረግ እንዳባቸው፣ የታችኛው ክፍልና አንዳንዴ የሕግ አስፈጻሚዎች ተግባሩን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ ቦርዱ እንደሚያሳስብና ይህንን የሚያደርጉ አሁኑኑ መታቀብ እንዳለባቸው ቦርዱ ያሳውቃል ብለዋል፡፡

  በዕጩዎች ወኪሎች ላይ የሚደረግ ሕገወጥ ተግባራት በውጤቱ ላይ ችግር ስላለው፣ ይህንን የመንግሥት አካላት ተገንዝበው ችግሩን የሚፈጽሙትን ዛሬ የሥራ ቀን ስላልሆነ ወደ ቤታቸው እንዲገቡ እንዲያደርጉ የጠየቁት የቦርድ ሰብሳቢዋ፣ ይህ ችግር በመለስተኛ ደረጃ በአፋርም ታይቷል ብለዋል፡፡ 

  በአዎንታዊ መታየት ያለበትና ለሕዝቡም ለቦርዱም ትልቅ ድል ነው የሚባለው በአብዛኛው ጣቢያዎች ከጥቂቱ በስተቀር በሰዓት ተከፍተው በሰላም ምርጫው እየተከናወነና ዜጎችም እየመረጡ መሆኑን ነው፡፡ 

  የቁሳቁስ እጥረት ያለበት ሳንካ ቢሆንም፣ የማይፈታ ችግር ስላልሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይስተካከላል፣ ቀጣዩን መግለጫ ስንሰጥ ችግሮቹ ይፈታሉ ብዬ አስባለሁ ብለዋል፡፡ ከሁሉም በላይ የፓርቲ ወኪሎች በየቦታው እየተገኙ ኃላፊነታችን እንዲወጡ አስቻይ ሁኔታ እንዲጠር ጠይቀዋል፡፡ አክለውም ችግሩ በስፋት የታየበት አዲስ አበባ፣ ደቡብ ክልል በሥራቸው የሚተዳደሩ ሠራተኞቻቸውን፣ አስተዳዳሪዎቻቸውንና ተወዳዳሪዎቻቸውን ጨምሮ ከማሰናከል ተግባር እንደታቀቡ እንዲያደርጉ ቦርዱ ጥሪ ያቀርባል ብለዋል፡፡ 

  የፍርድ ውሳኔ ያላረፈበት ጉዳይ ያላቸው በርካታ ሰዎች እስር ቤት ቢኖሩም፣ በእስር ቤት የተቋቋመ ጣቢያ ስለሌለ ማንም እስረኛ ሊመርጥ የሚችልበት ሁኔታ እንደሌለ፣ አዲስ አበባ ላይ ለገጠመው ክፍተት እንዲሟላ ተደርጎ ምርጫው እየተካሄደ መሆኑን፣ ዘግይተው የጀመሩ ጣቢያዎችን በተመለከተ ቦርዱ ውሳኔ ማሳለፍ ስለሚችል ዓይቶ ሰዓት የሚራዘምበት ሁኔታ ላይ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ በመግለጽ ወ/ሪት ብርቱካን የእኩለ ቀን መግለጫቸውን አጠናቀዋል፡፡ ቀጣይ መግለጫ ከሰዓታት በኋላ ይሰጣሉ፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...