በአገሪቱ በተከሰቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የፀጥታ መደፍረስ እንዲሁም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥጋት ጋር በተያያዘ ሁለት ጊዜ ተራዝሞ የቆየው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በአብዛኛው ሰኞ በምርጫው ዕለት (ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም.) ከምርጫ ቁሳቁስ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሙሉ ለሙሉ የድምፅ መስጠቱ ሒደቱ በአንድ ተጨማሪ ቀን እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ የድምፅ መስጫ ሒደቱ ቀድሞ የሰላም መደፍረስ ሊከሰት ይችላል ተብሎ ሲጠበቅ ከነበረው ሥጋት በተቃራኒ በሰላም መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡
አገሪቱ ላለፉት 26 ዓመታት የምትተዳደርበት ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ ከዋለ ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 5 የምርጫ ዘመናት ያልነበረው የሲዳማ ክልል፣ ለመጀመርያ ጊዜ አዲስ ተሳታፊ ሆኖ የተመዘገበበት ክስተት ለ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ልዩ መገለጫው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
የሲዳማን ብሔረሰብ የሚወክለው አዲሱ አደረጃጀት በክልላዊ መንግሥትነት ራሱን ችሎ ለመጀመርያ ጊዜ ይወዳደር እንጂ፣ የሲዳማ ብሔረሰብ በቀደሙ የምርጫ ዘመናት በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግሥት ውስጥ ተካቶ ይመርጥና ይመረጥ እንደነበር ይታወቃል፡፡
የአዲስ ተሳታፊው የምርጫ ስፋት
በዘንድሮው ጠቅላላ አገራዊ የምርጫ ኩነት የሲዳማ ክልል እንደ ሌሎቹ ነባር ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የራሱ የምርጫ ክልሎችና ሰፊ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ተመድቦለት ምርጫውን በክልላዊ መንግሥት ደረጃ አካሂዷል፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚያመለክተው አዲሱ ተሳታፊና ክልል ባሉት የምርጫ ክልሎች ብዛት አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ለዘንድሮው ምርጫ 2,247 የምርጫ ጣቢያዎች በ19 የምርጫ ክልሎች ታቅፈው ድምፅ የመስጠቱ ሒደት ተከናውኗል፡፡
19ኙ የምርጫ ክልሎች የሲዳማ ክልል ዋና መቀመጫ የሆነችውን ሐዋሳን ሲጨምር፣ ከዋና መቀመጫው ውጪ ባሉ የምርጫ ክልሎች የሰኞው ዕለት ድምፅ አሰጣጥ ከድምፅ መስጫ ወረቀት እጥረት ጋር በተያያዘ የምርጫ ጣቢያዎች እስከ ቀጣዩ ቀን ማለትም ሰኔ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ረፋድ አምስት ሰዓት ድረስ የምርጫ የድምፅ መስጠት ሒደቱ እንዲቆም ተደርጓል፡፡
ምርጫ በሐዋሳ
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድምፅ መስጫ ቀን በወሰነው መርሐ ግብር መሠረት ድምፅ ተሰጥቶ ጣቢያዎቹ የተዘጉት በሐዋሳ ብቻ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በሐዋሳም ቢሆን የድምፅ መስጠቱ ሒደት በመርሐ ግብሩ መሠረት ከምሽቱ 12 ሰዓት ማጠናቀቅ ባይቻልም በቦርዱ ውሳኔ መሠረት በወረቀት እጥረት ምክንያት የተመዘገቡ ዜጎች ሳይመርጡ እንዳይቀሩ ታስቦ፣ ምርጫ ጣቢያዎች ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ ክፍት ሆነው አምሽተዋል፡፡
ሪፖርተርም በከተማዋ ተገኝቶ የምርጫ ጣቢያዎች ከተከፈቱበት ከሰኞ ሰኔ 14 ቀን እስከ ማክሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. የነበረውን ሒደት ተከታትሏል፡፡
በሐዋሳ ከተማ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች እንደ አብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ሁሉ ሰኞ ጠዋት የተከፈቱ ሲሆን፣ ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው ጣቢያዎች መራጮች ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምረው ተሠልፈው ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡
በምርጫ ቦርድ የድምፅ አሰጣጥ አፈጻጸምና ክትትል መመርያ መሠረት በሁሉም ጣቢያዎች ድምፅ መስጠት ሒደት ተከናውኗል፡፡
ሪፖርተር ቅኝት ካካሄደባቸው ጣቢያዎች ውስጥ ለአብነትም የጉዱመሌ 1 እና 5 ጣቢያዎች፣ የፒያሳ ሲቲ ሴንተር ጣቢያዎችና የሙሉ ወንጌል የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓቱ በሚገባና በተሟሏ አካሄድ እንደነበር ተስተውሏል፡፡
የየምርጫ ጣቢያዎቹ አስፈጻሚዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ ታዛቢዎች የቦርድ ታዛቢዎችና የተወዳዳሪ ፓርቲ ዕጩዎችም የድምፅ አሰጣጡ ሒደትን በጥሩ ሁኔታ፣ በሰላማዊ መንገድና ሁሉም በጠበቁት መልኩ እየሄደ መሆኑን ለሪፖርተር በድምፅ አረጋግጠዋል፡፡
በተለይም ምርጫ ጣቢያዎች ከተከፈቱባቸው ሰዓት አንስቶ እስከ እኩለ ቀን ድረስ ሁሉም ነገር በታቀደውና በሚጠቀበው መልኩ እየሄደ መሆኑ ከሁሉም አካላት ቅሬታ አለመቅረቡን ሪፖርተር በቅኝቱ ወቅት አስተውሏል፡፡
ነገር ግን በዕለቱ በጥሩ ሁኔታ ሲጓዝ ያረፈደው ድምፅ የመስጠት ተግባር በአብዛኛው ጣቢያዎች የወረቀት (ድምፅ መስጫ ሰነድ) በማለቁ መራጮች ወረቀት እስኪመጣ በትዕግሥት እንዲጠብቅ አልያም ከሰዓታት በኋላ ተመልሰው በመምጣት ድምፅ እንዲሰጡ በምርጫ አስፈጻሚዎች ተነግሯቸዋል፡፡
ለአብነትም ከምርጫ አስፈጻሚዎች መረዳት እንደተቻለው ከጠዋቱ 5 ሰዓት በድምፅ መስጫ ወረቀት ማለቅ ምክንያት ድምፅ መስጠቱ ሲቋረጥ በተወሰኑ ጣቢያዎች እንዲሁ 6 ሰዓት ላይ መራጮች ድምፅ ሳይሰጡ እንዲቆዩ መደረጉን በጣቢያዎቹ ሪፖርተር ተመልክቷል፡፡
የጉዱማሌ ምርጫ ጣቢያ 5 እና 1 ኃላፊዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት ድምፅ መስጠቱ እንዳቆመ አረጋግጠዋል፡፡ ወደ ምርጫ ማስተባበሪያ ማዕከላት በሰዓት ሪፖርት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ የሁለቱም ጣቢያ ኃላፊው ከማስተባበሪያ ማዕከላት የድምፅ መስጫው በሰዓታት ውስጥ በሔሊኮፕተር እንደሚላክላቸው ተነግሮናል ብለው ነበር፡፡
ነገር ግን በሐዋሳ ሁሉም ጣቢያዎች በሔሊኪፕተር ይላካል የተባለው ወረቀት መድረስ የቻለው ምርጫ ጣቢያዎቹ ይዘጉበታል በተባለው ሰዓት ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ነው፡፡
ይህንኑም የቁሳቁስ እጥረት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዕለቱ ምሽት በላይ ያረጋገጠ ሲሆን መራጮች በተመዘገቡበት መሠረት የጣቢያዎቹ የመዝጊያ ሰዓት እስከ ምሽት ሦስት ሰዓት ተራዝሟል፡፡
ነገር ግን በሐዋሳ ብቻ መራጮች በተመረጠው የሰዓት ገደብ ውስጥ ድምፅ ሰጥተው ቢዘጉም፣ በሲዳማ ክልል ውስጥ ያሉት 19ኙም ክልሎች በዕለቱ የድምፅ መስጫው ሰነድ ባለመድረሱ ምርጫ ቦርድ ጣቢያዎቹ ማክሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲከፈቱ በወሰነው መሠረት ከረፋዱ 5 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ ተመዝጋቢዎች ድምፃቸውን ሰጥተዋል፡፡
በጣምራነት የሲዳማና የደቡብ ክልሎች የምርጫ ቦርድ አስተባባሪው ፍሬው በቀለ ለሪፖርተር እንደገለጹት በዕለቱ ከድምፅ መስጫ ወረቀት እጥረት ጋር በተያያዘ ለሁሉም የሲዳማ 19 የምርጫ ክልሎች ከ900 ሺሕ በላይ ተመዝጋቢዎች ድምፃቸውን ማክሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሰጡ አረጋግጠዋል፡፡
የሐዋሳው በጎ አካሄድ ምንም እንኳ እንደሌሎቹ የክልሉ ምርጫ ጣቢያዎች ሁሉ የቁሳቁስ በተለይም የድምፅ መስጫ ወረቀት እጥረት ሒደት እክል ቢገጥመውም አጠቃላይ የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓቱ የአስፈጻሚዎች አተገባበር እንዲሁም ከድምፅ መስጫ ድንኳኖች ውጭ ያለው አካባቢያዊ ሁኔታና ዝግጅት ሪፖርተር በሐዋሳ ያስተዋለው አጠቃላይ ሁኔታ በአገሪቱ ከዚህ በፊት ከሚስተዋሉ የቀደሙ ክስተቶች የተሻለ ዝግጅት መደረጉን አስተውሏል፡፡
የምርጫ አስፈጻሚዎች ምርጫውን ተቀብለው የሚያስተናግዱበት ቅልጥፍና፣ መራጮችን በሚገባ ስለድምፅ አሰጣጡና የኮሮጆ አጠቃቀም፣ ሠልፉን የሚያስተናግዱበትና አያያዝ እንዲሁም በድምፅ መስጫ ድንኳኖች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከል ባማከለ ሁኔታ የተዋጣለት ዝግጅትና የተሻለ የአፈጻጸም ብቃት የታየበት ነው ማለት ይቻላል፡፡
በዚህም ረገድ ሪፖርተር በራሱ ካስተዋለው ባሻገር በየጣያዎቹ የተገኙ የብልፅግና፣ የኢዜማ፣ የመኢአድ፣ የሲዳማ አንድነት ፓርቲና ሌሎች ተወካዮች አረጋግጠዋል፡፡ በተጨማሪም ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የድምፅ መስጫ ዕለት በአዲስ አበባ የታየው ረዣዥም ሠልፍና መንቀራፈፍ በሐዋሳ አልታየም፡፡
በሐዋሳ የአዲስ ከተማ ምርጫ ጣቢያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሲቪል ማኅበራት ጥምረትን በመወከል በታዛቢነት የተገኙት አቶ ቻለው በዛብህ እንደገለጹት፣ ‹‹ከዚህ በፊት ካሉኝ ልምድ አንፃር በሐዋሳ ተዘዋውሬ ማስተዋል እንደቻልኩት ያየሁት ነገር ቢኖር በከተማዋ የሚታየው የማስፈጸም ብቃትና ጥራት ለመላው ኢትዮጵያ ሞዴል ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ ሪፖርተር በራሱ ካስተዋለው ባሻገር በየጣቢያዎቹ የተገኙ የብልፅግና፣ የኢዜማ፣ የመኢአድ፣ የሲዳማ አንድነት ፓርቲና ሌሎች ተወካዮች ይኽንኑ አረጋግጠዋል፡፡
ይህንንም የምርጫ ሒደት ቅልጥፍናና ስኬታማ አተገባበር በተመለከተ ብልፅግናን በመወከል በጉዱማሌ ጣቢያ ዕጩ ሆነው የቀረቡትና ድምፃቸውን ሲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቀድሞው የአዋሳ ከንቲባና የአሁኑ የአዲስ አበባ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ይገኙበታል፡፡
አቶ ጥራቱ አጠቃላይ ሒደቱ ለአገራችን ጥልቅ ተስፋ ድጋሚ እንዲፈነጥቅ ያደረገ አርኪ የማስፈጸም ብቃት የታየበት ነው ሲሉ አወድሰውታል፡፡ አቶ ጥራቱ በከተማዋ የታየው አጠቃላይ በጎ ዝግጅትና አርኪ ያሉት አፈጻጸም፣ ባለፈው ዓመት በሐዋሳና በሌሎች ሥፍራዎች በተካሄደው የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ምርጫ ጋር ተያይዞ የመጣ ልምድ ከመሆኑ ጋር አያይዘውታል፡፡
በሐዋሳ ሰኞ የተካሄደው ድምፅ የመስጠት ተግባር በዕለቱ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ትናንት ማክሰኞ በሁሉም ጣቢያዎች ውጤት ይፋ ሆኗል፡፡ በየምርጫ ጣቢያዎች የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተወካዮች የአስመዘገቧቸው ውጤቶች በተለጠፉት የውጤት ማሳወቂያ ቅፆች ላይ ተገልጧል፡፡
ማክሰኞ ድረስ የተራዘሙ ከአዋሳ ውጪ ያሉ ሁሉም ጣቢያዎች ማክሰኞ ድምፅ ሰጥተው በዕለቱ አጠናቀዋል፡፡ ሪፖርተር ይህን ዘገባ እስካጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ለየጣቢያዎቹ ይህ ነው የተባሉ ችግሮች አልተሰሙም፡፡ የምርጫ ውጤቶቹም እስከ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 16 ቀን ድረስ ይፋ ይሆናሉም ተብሏል፡፡
6ተኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁን ተከትሎ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ (ረዳት ፕሮፌሰር) ለመላው የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ‹‹አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በከተማችን ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም በመጠናቀቁ እንኳን ደስ ያለን! እንኳን ደስ አላችሁ!›› ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።
የዘንድሮው ምርጫ በከተማችን ፍፁም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ በምርጫው ሒደት ‹‹ተዋናይ የነበራችሁ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የከተማችን ነዋሪዎች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የፀጥታ አካላትና የሚዲያ አካላት እንዲሁም ከቀበሌ ጀምሮ ያላችሁ የከተማው አመራሮች በምርጫው ሥነ ሥርዓት ውጤታማነት ለነበራችሁ አስተዋጽኦ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ›› ያሉት ከንቲባው ኢትዮጵያ ብዙዎች እንዳሟረቱባት ሳይሆን በዜጎቿ የተባበረ ክንድና አገር ወዳድነት ስሜት 6ኛውን አገራዊ ምርጫ በሐዋሳ ከተማ ውስጥ ያለ ምንም የፀጥታ ሥጋት በሰላም ማጠናቀቅ መቻሉንና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ምን ያህል ረዥም ርቀት መጓዝ እንደሚያስችል አመላካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡