Thursday, July 25, 2024

​​​​​​​በምርጫው ማግሥት የአገር ሙሉ ትኩረት ለኢኮኖሚው ይሁን!

ምርጫውን በሰላም አጠናቆ ፊትን ወደ ኢኮኖሚው ማዞር አጣዳፊ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ የኢኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ ለምትገኘው ኢትዮጵያ ለፖለቲካው ብቻ የሚባክነው ዕውቀት፣ ጉልበት፣ ጊዜ፣ ሀብትና ሕይወት ገታ ተደርጎ የኢኮኖሚው ጉዳይ ይታሰብበት፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ፣ ሰፊ ለም መሬት፣ በርካታ የውኃ ምንጮች፣ ተስማሚ የአየር ፀባዮች፣ በርካታ ማዕድናት፣ የቱሪዝም መስህቦችና የተለያዩ የተፈጥሮ ፀጋዎችን የታደለችው ኢትዮጵያ ፅኑ ድህነት ቁምስቅሏን እንደሚያሳያት ዓለም የሚያውቀው አሳዛኝ ገጽታዋ ነው፡፡ ለአብዛኛው ሕዝብ ዛሬም በልቶ ማደር ቅንጦት ነው፡፡ መጠለያ ጎጆ ማግኘት ብርቅ ነው፡፡ በሕክምና ሊድኑ በሚችሉ በሽታዎች መሞት አሁንም ያልተገላገሉት መከራ ነው፡፡ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ረምና አድካሚ ጉዞ ይፈልጋል፡፡ ትርፍ ስንዴ አምርታ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚገባት አገር ዛሬም ትመፀወታለች፣ ወይም ጨረታ እያወጣች በከፍተኛ ወጪ ትገዛለች፡፡ የምግብ ዘይት ብርቅ ሆኖባት በውጭ ምንዛሪ ለጤና ጠንቅ የሆነ የረጋ ፓልም ዘይት ብታግበሰብስም ቅም አይላትም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ፖለቲከኞች በቀሰቀሷቸው ግጭቶች ሳቢያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች ሜዳ ላይ ተበትነው የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ጠባቂ ሆነዋል፡፡ የአገሪቱ በጀት ሩብ ያህሉ በብድርና በዕርዳታ ካልተደገፈ፣ እንደ ሰደድ እሳት የሚንቀለቀለው የኑሮ ውድነት የሚሊዮኖችን ሕይወት ለማጨለም ተዘጋጅቷል፡፡ ዜጎች ገቢያቸው እያሽቆለቆ የኑሮ ውድነቱ እየተተኮሰ ነው፡፡ በምርጫው ማግሥት ፊትን ወደ ኢኮኖሚው መመለስ ካልተቻለ መጪው ጊዜ ከባድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለረዥም ዓመታት ብዙዎችን የሚያስፈራ በመሆኑ ‹‹ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ›› የተባለለት ተወዶ አይደለም፡፡ ያለፉትን ሃምሳ ዓመታት የፖለቲካውን ውጣ ውረዶች በወፍ በረር ለመቃኘት ሲሞከር፣ በ1953 ዓ.ም. የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት በደም መፋሰስ መክሸፉ ያስከተለው ጦስ አይዘነጋም፡፡ ከ13 ዓመታት በኋላ በ1966 ዓ.ም. በግብታዊነት የፈነዳው አብዮት የደም ባህር ሆኖ የፈጠረው ምስቅልቅልና ዕልቂት መቼም የሚረሳ አይደለም፡፡ የቀይና የነጭ ሽብር ዕልቂት፣ እስር፣ ስደት፣ የእርስ በርስ ጦርነትና ሌሎች ተያያዥ ቀውሶች የአብዮቱ ማግሥት መዘዞች ነበሩ፡፡ በግንቦት 1983 ዓ.ም. ኢሕአዴግ መላ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ለ27 ዓመታት የታዩት ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው መከራዎች የትናንት ትዝታዎች ናቸው፡፡ ግድያዎች፣ እስራቶች፣ ዘረፋዎች፣ ማሳደዶችና ሌሎች ለጆሮ የሚከብዱ ሰቆቃዎች ብዙ ተብሎባቸዋል፡፡ ያለፉት ሦስት ዓመታት ማንነትን መሠረት ያደረጉ የንፁኃን ግድያና ጭፍጨፋ፣ ማፈናቀልና አረመኔያዊ ድርጊቶች በስፋት ይታወቃሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ወጀብ ውስጥ ያለፈች አገር ሕዝብ ዕድሜውን ሙሉ በችጋር እየተቆራመደ በድህነት መማቀቁ ያስቆጫል፡፡ ከአገር በፊት የሚቀድም ምንም ስለሌለ ምርጫውን በሰላም በማጠናቀቅ ለአገር ልማት መነሳት ተገቢ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ከአፍሪካ አንደኛ ሆና ሥጋ፣ ወተትና እንቁላል ለሕዝባችን ብርቅ ናቸው፡፡ በርካታ ወንዞች፣ ሐይቆችና ባህሮች እያሉ ዓሳን የዘወትር ምግብ ማድረግ አልተቻለም፡፡ ጥራ ጥሬ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬና ሌሎች አልሚ ምግቦችን ማግኘት እንደ መርግ የከበደ ነው፡፡ መደበኛ የሆኑት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎና የመሳሰሉት ከአቅም በላይ እየሆኑ ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በቀን ሦስቴ ለመመገብ ባለመቻሉ፣ የምግብ ዋስትና ጉዳይ አሁንም ሆድ የሚያስብስ አጀንዳ ነው፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች ከሴፍቲኔት ዕርዳታ ሳይላቀቁ፣ በየቦታው ማንነትን መነሻ በሚያደርጉ ጥቃቶች ምክንያት ከቀዬአቸው የሚፈናቀሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ የዕለት ደራሽ ምግብ ጠባቂ ናቸው፡፡ ቀሪው አብዛኛው ሕዝብ ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ኑሮ መግፋት አቅቶት በኑሮ ውድነት ይጠበሳል፡፡ የመኖሪያ ጉዳይ ከተነሳ ደግሞ እጅግ አሳዛኝ ሕይወት ነው የሚመራው፡፡ በከተሞች በተፋፈጉና ፈፅሞ ለኑሮ በማይመቹ ጎስቋላ መንደሮች ውስጥ ሚሊዮኖች ፍዳቸውን ያያሉ፡፡ ንፁህ ውኃ፣ መፀዳጃ፣ ኤሌክትሪክና መሰል መሠረተ ልማቶችን ማሰብ ይከብዳል፡፡ በዚህ ዘመን በገጠር የሰው ልጅና እንስሳት ደሳሳ ጎጆ ውስጥ አንድ ላይ መኖራቸው ሌላው እንቆቅልሽ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ አስመራሪ የድህነት አዘቅት ውስጥ ሆኖ አገርን ጤና መንሳት ነውር መሆን አለበት፡፡ አገር ከማንም በላይ ናትና፡፡

ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅና ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ የብዙዎች ጉጉት ነበር፡፡ በንግዱም፣ በማኅበራዊ ግንኙነቱም ሆነ በሌሎች መስተጋብሮች ‹‹እስኪ ይህ ምርጫ ይለፍ›› የሚሉ ቀጠሮዎች መብዛታቸው በቀላሉ የሚታይ ሥጋት አልነበረም፡፡ ሰዎች በፖለቲካው ተዋንያን አለመግባባት ምክንያት ሕይወታቸው ለአደጋ እንዳይዳረግ ሥጋት ቢያድርባቸው፣ ሥራ ላይ መዋል የሚገባውን ገንዘብ ለማንቀሳቀስ ቢፈሩና በአጠቃላይ ምን እንደሚፈጠር ስለማያውቁ ተጠራጣሪ ቢሆኑ አይፈረድባቸውም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰው ጉዳት በጣም ከባድ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለምርጫው ቅስቀሳ ሲባል ገዥውም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያፈሰሱት የአገር ሀብት ከፍተኛ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ አገር ለምታና ዜጎች ደልቷቸው ቢሆን ኖሮ ወጪው አይቆጭም፡፡ ስለዚህም በከፍተኛ ውጣ ውረድ ውስጥ የተከናወነው ምርጫ ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ አለበት፡፡ የሚልሱትና የሚቀምሱት የሌላቸው ምንዱባን በበዙበት አገር ውስጥ፣ የምርጫ ውጤትን የግጭት መቀስቀሻ ማድረግ በታሪክ የሚያስጠይቅ በደል ነው፡፡

ኢትዮጵያን ለአገራቸው ህልውና ሲሉ ትዕግሥትን፣ ማስተዋልንና ጥንቃቄን ምርኩዛቸው አድርገው የሚፈልጉትን መርጠዋል፡፡ ፖለቲካን በዕውቀት፣ በጥበብና በብልኃት ለመምራት የሚያስችል አቅም ባልተገነባበት አገር ውስጥ፣ ምርጫን የሁሉም ነገር መጨረሻ ግብ አድርጎ ለመውሰድ መሞከር ፋይዳ እንደሌለውም ይረዳሉ፡፡ ምርጫ ዴሞክራሲን ለመለማመድ ከሚደረጉ መሣሪያዎች አንዱ እንጂ በራሱ ግብ እንዳልሆነም ይገነዘባሉ፡፡ ከምርጫ በኋላ ሕይወት መቀጠሉ አይቀርም፡፡ የፖለቲካው ተዋንያን ከምርጫ በኋላ በሚያገኙት ውጤት ከመጠን ያለፈ የደስታ ስካር፣ ወይም ለመግለጽ የሚያስቸግር ቁጣ ውስጥ ሆነው ወትሮም እንደነገሩ የሆነውን የፖለቲካ ምኅዳር የሚያበላሹት ከሆነ ኪሳራው ለአገር ነው፡፡ በምርጫው ድል የቀናው ተፎካካሪውን አክብሮ አሳታፊ ለሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ካልተዘጋጀ፣ ያልቀናው ደግሞ አኩርፎ ራሱን ለአመፅና ለሁከት ካዘጋጀ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከአዙሪት ውስጥ አይወጣም፡፡ በመሆኑም ለአገር እናስባለን የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ፣ ከምርጫው ማግሥት ጀምሮ ለአገር ልማትና ዕድገት ማቀድ ይጀምሩ፡፡ የፖለቲካ አጀንዳቸው ማዕከላዊ ነጥብ ከሥልጣን በፊት የኢትዮጵያዊያንን ሕይወት ለመቀየር ይሁን፡፡ ማኒፌስቶአቸው ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ከማስከበር ጎን ለጎን፣ ለአገር ልማትና ዕድገት በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ዕቅድ ይካተትበት፡፡

የፖለቲካው ቀውስ በሚያስከትለው መዘዝ ምክንያት ግጭት ሲፈጠርና በዜጎች ላይ ግድያ፣ ዘረፋ፣ ማፈናቀልና ሌሎችም ስቃዮች ሲያጋጥሙ፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ከየአቅጣጫው ሲግተለተል በተደጋጋሚ ለመታዘብ ተችሏል፡፡ በምርጫ 97 ማግሥት በተፈጸሙ ግድያዎች፣ የጅምላ እስሮችና በሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሳቢያ ምዕራባውያን የቀጥታ በጀት ድጋፍ አቋርጠው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ አሁን ደግሞ በትግራይ ክልል በተደረገው ጦርነት ሳቢያ በዜጎች ላይ በደረሱ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት፣ ምዕራባውያን አገሮች የኢኮኖሚ ማዕቀብ ለማድረግ እየተዘጋጁ ከመሆናቸውም በላይ፣ ስማቸው ይፋ ባልተደረገ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ የአሜሪካ መንግሥት የቪዛ ክልከላ አድርጓል፡፡ የኢኮኖሚ ማዕቀቡ የዓለም ባንክን፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅትን (አይኤምኤፍ) እና ሌሎች ለጋሽና አበዳሪ አገሮችንና ተቋማትን የሚያስተባብር ሊሆን ስለሚችል ጫናው ከባድ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ የውጭ ምንዛሪ ድርቅ ሲያጋጥም ነዳጅና ሌሎች በርካታ ምርቶችን ከውጭ ለምታስገባ አገር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ፀጋዎች በመጠቀም ለማንም ተፅዕኖ አለመንበርከክ የሚቻለው፣ ዘመኑን ከማይመጥን የፖለቲካ ሽኩቻ ውስጥ በመውጣት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ ሀብታቸውንና ጉልበታቸውን ለአገር ልማትና ዕድገት ለማዋል ተባብረው ይነሱ፡፡ በምርጫው ማግሥት የአገር ሙሉ ትኩረት ለኢኮኖሚው ይሁን

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእንቆቅልሽ ጨዋታ ውስጥ ውጡ!

በወርኃ ሚያዝያ ተካሂዶ የነበረው ውይይት ቀጣይ ነው የተባለው መድረክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደገና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አገናኝቶ ነበር፡፡ መንግሥትን የሚመራው...

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...