ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምፅ ለመስጠት የወሰዱት ካርድ ዋጋ ስላለው ለመምረጥ ወጥተናል ያሉት የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች፣ በማለዳው የምርጫ ጣቢያ ድንኳኖችን በረዥም ሠልፎች አጥለቅለቀውታል፡፡ በዕለቱ በአካባቢው ካፊያ የነበረ ቢሆንም መራጮችን ሊያቆማቸው አልቻለም፡፡ አዋቂዎች፣ እናቶች፣ አራሶች፣ አርሶ አደሮች፣ ሥራ አጦች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እንዲሁም በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሁለት አቅጣጫ ተሠልፈዋል፡፡
በዕድሜ ጎልማሳ የሆኑት አቶ አድማሱ ሹሜ በወልቂጤ ከተማ አዲስ ሕይወት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ በመንደራቸው በሚገኘው አዲስ ሕይወት ቁጥር-3 የምርጫ ጣቢያ የተገኙት ከንጋቱ 12፡30 ሰዓት ላይ ነው፡፡ ምርጫው ከመድረሱ በፊት በተለያዩ ሚዲያዎችና በአንዳንድ ግለሰቦች የሚሰሙት ወሬ፣ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ ላይከናወን ይችላል የሚል ሥጋት እንዳሳደረባቸው ለመደበቅ አልፈለጉም፡፡ በምርጫው ዕለት ሁከት ይፈጠራል የሚል ግምትም ነበራቸው፡፡ ሆኖም ካሰቡት በላይ ሰላማዊ ሆኖ ስላገኙት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ማንም ቢመረጥ የእሳቸው ዋናው ዓላማ አገሪቱን የሚጠቅም ፓርቲ መሆኑ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም እንዳሳቸው የመረጡ ግለሰቦችም ሆኑ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለድምፅ መስጠቱ ትኩረት እንደሰጡት ሁሉ የምርጫውንም ውጤት በዚያው ልክ ተረጋግተው እንዲጠባበቁና የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በጉራጌ ዞንና የም ልዩ ወረዳ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከአሥር በላይ የግል ተወዳደሪዎች ለሕዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤቶች ተፎካክረዋል፡፡ ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ ሪፖርተር ባደረገው ቅኝት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ እንዲሁም የብልፅግና ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ምሥል የያዙ ባነሮችን በስፋት ለዕይታ ውለው የተመለከተ ሲሆን፣ ቅኝት በተደረገባቸውም የምርጫ ጣቢያዎች በፓርቲ ታዛቢነት የምርጫውን እንቅስቃሴ ሲከታተሉ የነበሩ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጨምሮ የሁለቱን ፓርቲዎች ታዛቢዎች መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ነበር፡፡
በየምርጫ ጣቢያዎቹ የተመደቡት ወጣት አስፈጻሚዎች ለመራጩ ኅብረተሰብ የድምፅ አሰጣጡን የተመለከቱ መግለጫዎችን ያለ መሰልቸት ሲሰጡ፣ ከተመዘገቡበት ጣቢያ ውጪ የመጡ መራጮችን በትህትና ወደ ተመዘገቡበት ጣቢያ እንዲሄዱና እንዲመርጡ ሲያስረዱ፣ የተበላሹ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ታዛቢዎችን እያሳዩ ሲያስወግዱ ለማየት ተችሏል፡፡ መስጠት የሚፈቀድላቸውን መረጃ ለመገናኛ ብዙኃንና ለሲቪክ ማኅበራት ታዛቢዎች ያለ ማንገራገር ይሰጡም ነበር፡፡
በጉራጌ ዞንና የም ልዩ ወረዳ በጠቅላላው 13 የምርጫ ክልሎችና 923 የምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ በጣቢያዎቹም ከ630 ሺሕ በላይ ሕዝብ ለመምረጥ ተመዝግቦ እንደነበር፣ ከዞኑ የምርጫ ቦርድ አስተባባሪ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ሪፖርተር ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ ወልቂጤ ከተማን ማዕከል አድርጎ በዞኑ የሚገኙትን የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች የምርጫ ሒደት ተከታትሏል፡፡
በቅኝቱም ከምልከታ አንስቶ መራጮችን ስለምርጫው ሰላማዊነት፣ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ስለምርጫው ሒደትና ተግዳሮቶች፣ አስፈጻሚዎችን ስለሁነቱ ተዓማኒነት፣ እንዲሁም የምርጫ ክልል ኃላፊዎችን ስለቅኝታቸውና የቀረቡ ቅሬታዎችን በማስመልከት ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡
በወልቂጤ ከተማ በአምስት ቀበሌዎች በሚገኙ ከአሥር በላይ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ቅኝቶች የተደረጉ ሲሆን፣ ከተማው ውስጥ የሚገኙት መናኸሪያ፣ ሰላም በር፣ አዲስ ሕይወት፣ ዕድገት በር፣ ዕድገት ጮራ ጣቢያዎችን፣ በቀቤና ወረዳ የሚገኙትን ርሙጋና ፍቃዶ ቀበሌ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን በአካል በመሄድ፣ እንዲሁም በቀቤና ወረዳ ዘቢሞላና ወሸርቤ ጣቢያዎች፣ በቸሃ ወረዳ እምድብር የምርጫ ክልሎች ውስጥ ስለሚገኙት አሙርና እናቴ ጣቢያዎች በተገኙ ጥቆማዎች ጥያቄዎችን ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ምላሾች ተሰጥተውባቸዋል፡፡
ሪፖርተር ወልቂጤና አካባቢው ያለውን የምርጫ እንቅስቃሴ በመዘገብ ሒደቱ ውስጥ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ከምርጫው ሥነ ሥርዓት ውጪ የተፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራትን የተመለከቱ ቅሬታዎች ይደርሱት የነበረ ሲሆን፣ የተወሰኑትን በቦታው ድረስ በመሄድ የተቀሩትን ደግሞ ቅሬታ ለተነሳባቸው የምርጫ ጣቢያ የምርጫ ቦርድ አስተባባሪዎች በማቅረብ ምላሾችን አግኝቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) የጉራጌ ዞን አስተባባሪና በወልቂጤ ከተማ ተዘዋዋሪ ታዛቢ አቶ ታኖ ገትር፣ እንዲሁም በቸሃ ወረዳ እምድብር የምርጫ ክልል ፓርቲውን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት አቶ የወንደሰን አውላቸውና የክልል ምክር ቤት ዕጩው አቶ አዲሱ እጥፉ አቤቱታቸውን ካቀረቡት ውስጥ ይገኙበታል፡፡
በቀቤና ወረዳ-1 ርሙጋ ጣቢያ-1 የኢዜማ ታዛቢዎች እንዲመለሱ መደረጉን፣ እንዲሁ በቀቤና በወሸርቤ ጣቢያ ታዛቢዎችን የማንገላታት እንቅስቃሴ እንደነበር፣ በእምድብር ምርጫ ክልል ውስጥ በሚገኙ ጣቢያዎች አካባቢ የምርጫ ቅስቀሳ እንቅስቃሴ እንደነበር፣ እናቴ የምርጫ ጣቢያ አቅመ ደካሞችን እንረዳለን በሚል ሰበብ ድምፅ የማስቀየር እንቅስቃሴ ከቀረቡት ቅሬታዎች ተጠቃሾቹ ሲሆኑ፣ ፓርቲው ለመገናኛ ብዙኃን ካቀረበው አቤቱታ ባሻገር ለምርጫ ክልሎቹ ቅሬታውን በጽሑፍ አቅርቧል፡፡
የጉራጌ ዞንና የየም ልዩ ወረዳ የምርጫ ቦርድ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አሳልፈው መኩሪያ በተነሱት ቅሬታዎች ላይ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አዛውንቶችና የአካል ጉዳት ያለባቸው መራጮች በየምርጫ ጣቢያዎቹ በፓርቲ ታዛቢዎች ሳይሆን በሲቪክ ማኅበራትና በሌሎች ታዛቢዎች እንዲታገዙ መደረጉን፣ የፓርቲ ታዛቢዎች እንዳይገቡ ተከለከሉ በተባሉ ጣቢያዎች ሪፖርቱ እንደቀረበ በመሄድ ታዛቢዎች በምርጫ ቦርድ አስተባባሪዎች ፊት እንዲገቡ ለማድረግ ጥረት እንደተደረገና ሆኖም ቅሬታ አቅራቢው ፓርቲ ታዛቢዎቹ ተመልሰዋል የሚል ምላሽ እንደሰጠ ገልጸዋል፡፡
ሁሉም በዕለቱ ሊመርጥ የወጣ ዜጋ መርጦ እንዲመለስ በማሰብ ሠልፎች ረዥም በሆነባቸው አካባቢዎች ሦስት የነበሩ የድምፅ መስጫ መከለያዎችን ወደ አራት ከፍ እንዲሉ መደረጉን ያስታወቁት አቶ አሳልፈው፣ የአስፈጻሚነት ገለልተኝነት ጥያቄ በተነሳባቸው ግለሰቦች በተጨባጭ በተወሰደ ዕርምጃ ከአስፈጻሚነት የተሰረዙ እንዳሉም ገልጸዋል፡፡
የእምድብር ምርጫ ክልል አስተባበሪ የሆኑት አቶ እንግዳ ዘውዱ ቅሬታ በቀረበባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ቅኝቶች መደረጋቸውን፣ ቅስቀሳ ነበረ ለሚለው የምርጫ ቦርድ አስተባባሪዎች የተባሉት ቦታዎች ሲደርሱ አለመመልከታቸውን፣ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ እንሰጣለን በሚል የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲቆም መደረጉን፣ በተለይ ከፍተኛ ፉክክር በሚያደርጉት የኢዜማና የብልፅግና ታዛቢዎች መካከል መተማመን ባለመኖሩ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ጥያቄዎች ይነሱ እንደነበረ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምፅ ይሰጥበታል ከተባለው መደበኛው የምርጫ ሰዓት እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ መራጮች እንዲመርጡ በተደረጉባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ቅኝቶች ተደርገዋል፡፡ በመጨረሻም በበኩር ወረዳ ዕድገት በር ቀበሌ መርካቶ ቁጥር-2 ጣቢያ በመገኘት፣ ከፓርቲና ከሲቪክ ማኅበራት ተወክለው ከመጡ ታዛቢዎች ጋር በመሆን የድምፅ ቆጠራ ሒደቱን ለመታዘብ ተችሏል፡፡
ሰኔ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠዋት ሪፖርተር በአሥር የምርጫ ጣቢያዎች ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቶችን ማየት የተቻለ ሲሆን፣ በስምንቱ ጣቢያዎች በር ላይ ውጤቶች ተለጥፈው ነበር፡፡ በሁለት ጣቢያዎች እስከ ጠዋቱ አራት ሰዓት ድረስ የተለጠፈ ውጤት አልነበረም፡፡