Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናምርጫ በባህር ዳርና አካባቢው

ምርጫ በባህር ዳርና አካባቢው

ቀን:

በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከፍተኛ ፉክክር ይደረግባቸዋል ተብለው ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ትልልቅ ከተሞች ውስጥ አንዷ ባህር ዳር ነች፡፡ በባህር ዳር ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫው ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፣ በባህር ዳርና በሁለት የገጠር ቀበሌዎች ደግሞ ከ137,778 በላይ መራጮች ድምፅ ለመስጠት ተመዝግበዋል፡፡

በከተማዋ ለፌዴራል ፓርላማና ለክልል ምክር ቤት ዕጩዎቻቸውን በማቅረብ ተወዳደሪ የነበሩት ዘጠኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብልፅግና፣ አብን፣ ኢዜማ፣ እናት ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጀት፣ የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ፣ ኅብር ኢትዮጵያ፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ናቸው፡፡

በከተማዋ እነዚህ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ውድድር በተለየ ሁኔታ እንዲታይ ያደርገዋል ተብሎ የተገመተው፣ ፓርቲዎቹ የባህር ዳር መራጮች ይመርጧቸው ዘንድ በተለይ በጎዳና የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ ራሳቸውን በይበልጥ ያስተዋውቃሉ የሚል ግምት ቢኖርም፣ በምርጫው ዋዜማ የሪፖርተር ዘጋቢ ከተማዋን ተዘዋውሮ ሲመለከት እነዚህ ፓርቲዎች ምርጫውን የሚያመላክቱ የመራጮችን ምሥልና የመወዳደሪያ ምልክቶቻቸውን የሚያሳዩ የጎዳና ላይ ማስታወቂያዎች በባህር ዳር ከተማ ጎዳናዎች ላይ አይታዩም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ አዲስ አበባ ካሉ ከተሞች አንፃር ሲታይ በባህር ዳር ፓርቲዎች በጎዳና ላይ የሚታይ ‹‹ምረጡኝ›› የሚል የማስታወቂያ ሰሌዳ የላቸውም፡፡ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ከዚህ አንፃር በተወሰኑ ቦታዎች የፓርቲውን ዓርማ ከማኖር ውጪ፣ ሌሎች ፓርቲዎች ይኼ ነው የሚባል የቅስቀሳ ማስታወቂያዎቻቸውን አለማኖራቸው ትንሽ ግርታ መፍጠሩ አይቀርም፡፡

ይህም ቢሆን ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የታየው የምርጫ ሒደት ግን አስደማሚ በሚባል ሁኔታ በከተማው ጠንከር ያለ ውድድር እንደሚኖር መገንዘብ የሚቻለው፣ መራጮች ገና ጎህ ሳይቀድ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች መትመም በመጀመራቸው ነው፡፡ ከሌሊቱ 11፡30 ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ሪፖርተር ባደረገው ቅኝት መታዘብ እንደተቻለው፣ ከምርጫ አስፈጻሚዎችና ከታዛቢዎች በፊት መራጮች ቀድመው የተገኙበት ነበር፡፡

ሪፖርተር በአንድ የምርጫ ጣቢያ ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ወደ ምርጫ ጣቢያ የወጡ ሁለት ጎረቤታሞችን አግኝቶ አነጋግሯቸዋል፡፡ እነዚህ መራጮች በሌሊት መጥተው ያሻቸውንና ይበጀኛል ያሉትን ለመምረጥ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ በሌሊት የመጡት ሁለቱ መራጮች ማንም ሳይቀድማቸው በምርጫ ጣቢያው ተገኝተው፣  ከምርጫ ጣቢያው ድንኳን ውጪ ባገኙት ወንበር ተቀምጠው የሌሊት ቁሩን ችለው ምርጫውን ለማካሄድ ሰዓታት መጠበቅ ነበረባቸው፡፡

ነገር ግን እነዚህ ሁለቱ ጎረቤታሞች በዚያን ሌሊት መጥተው ድምፃቸውን ሰጥተው ለመመለስ ግን የግድ 12፡00 ሰዓት መሙላት ነበረበት፡፡

የጣቢያው አስመራጮችና ታዛቢዎች የመጡት ደግሞ ከ12፡00 ሰዓት በኋላ በመሆኑ፣ ሁለቱ ጎረቤታሞችም ሆኑ ከዚያ በኋላ የመጡት መራጮች መርጠው ለመሄድ ተጨማሪ ደቂቃዎች መጠበቅ ነበረባቸው፡፡ ምክንያቱም አስመራጮች ልክ ምርጫው መጀመር በነበረበት ሰዓት ከመጡ በኋላ ምርጫውን ለመጀመር መሰናዳት ስለነበረባቸው፣ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ሠልፍ የያዙ መራጮች መምረጥ የጀመሩት ከንጋቱ 12፡40 ሰዓት በኋላ ነበር፡፡ ይህም በመሆኑ መራጮች ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ተደምጧል፡፡

እንዲህ ያለው የመራጮች ትጋት በብዙዎች የባህር ዳር የምርጫ ጣቢያዎች ታይቷል፡፡ የግሽ ዓባይ 12/1 የምርጫ ጣቢያ ደግሞ ምርጫው ከአንድ ሰዓት በኋላ መጀመሩ በመራጮች ላይ ቅሬታ እንዲያሰሙ አድርጓል፡፡

ከዚህ ውጪ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ሲካሄድ ለመመልከት ተችሏል፡፡  መራጮችና ታዛቢዎች ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡ በጣና ምርጫ 2 ‹ሀ› የምርጫ ክልል ድምፃቸውን የሰጡት የአብን ምክትል ሊቀመንበር ከምርጫ ድምፅ አሰጣጡ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ከምርጫው ሒደት ጋር ተያይዞ የታየው ሁኔታ በተመሳሳይ በድምፅ ቆጠራም ላይም ከተደገመ፣ የዘንድሮን ምርጫ በተለየ ሁኔታ እንዳየው ያደርገኛል፤›› ብለዋል፡፡ ተዘዋውረን በተመለከትናቸው ምርጫ ቦታዎች ሁሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ታዛቢዎቻቸውን ያስቀመጡ ሲሆን፣ የሲቪክ ማኅበራትና የዓለም አቀፍ ታዛቢዎችም የነበሩበት ምርጫ ነበር፡፡

የዘንድሮውን ምርጫ በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው መራጮችና የፖለቲካ ፓርቲ ታዛቢዎች የምርጫ ሒደቱ መልካም መሆኑን፣ ከበፊቶቹ ምርጫዎች አንፃር ሲታይም በብዙ ሁኔታ የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ በምርጫው ዕለት ያዩት የመራጮች ፍላጎትና የምርጫ ሒደቱ የተለየ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ በተለይ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር መካሄዱ ትልቅ ነገር ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በምርጫው ዕለት ጠዋት ላይ የምርጫ ጣቢያ ለክልል ምክር ቤት ከሚወዳደሩ ዕጩዎች መካከል መምረጥ የሚቻለው ሁለት ሆኖ ሳለ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ‹‹ግን አራት መምረጥ ትችላላችሁ›› ብለው ገለጻ በማድረጋቸው አንዳንድ መራጮች በዚሁ መሠረት አራት መርጠው በመሄዳቸው ድምፃቸው እንዲበላሽ ሆኗል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በሌሎች ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንደገጠሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአብን ታዛቢ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እሳቸው ታዛቢ በሆኑበት የምርጫ ጣቢያ በሆኑበት የምርጫ ጣቢያ ለምክር ቤት ‹‹አራት መምረጥ ትችላላችሁ›› የሚለው ማብራሪያ ትክክል አለመሆኑን በመግለጽ ማስተካከያ እንዲደረግበት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ መራጮች በተባሉት መሠረት አራት መርጠው መሄዳቸውን አልሸሸጉም፡፡

ለዘንድሮ ምርጫ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው፣ ምርጫው ቀደም ብለው ከገለጹት ግድፈት ውጪ ምንም ዓይነት ችግር ያልተስተዋለበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በምድረ ገነት አንድ ‹‹ለ›› የምርጫ ጣቢያ ያገኘናቸው የአብን ታዛቢ አቶ ጌታቸው ገነቱ በምርጫው ዕለት ጠዋት ላይ የብልፅግና ፓርቲ አባላት ተደጋግሞ ሲታዩ እንደነበር፣ የፓርቲ አባላት በምርጫ ጣቢያው አካባቢ መገኘታቸው ሕገወጥ በመሆኑ ከአካባቢው እንዲርቁ አቤት እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባት የፀጥታ ኃይሎች እነዚህን ያላግባብ በምርጫው ጣቢያ የተገኙ ግለሰቦች ከአካባቢው እንዲርቁ አድርገናል ብለዋል፡፡  

በባህር ዳር ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ አብዛኛው መራጭ መርጦ ሄዷል፡፡ ከቀትር በኋላ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ከተመለከታቸው ስድስት ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ አራቱ በምርጫ ጣቢያዎቹ ከተመዘገቡ ከ70 በመቶ በላይ መምረጣቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ በአንድ የምርጫ ጣቢያ 1,062 መራጮች የነበሩ ቢሆንም፣ ከ750 በላይ የሚሆኑት ከዘጠኝ ሰዓት በፊት መምረጣቸው ነው፡፡

በዚህ ምርጫ ለየት ብለው ከታዩ ክስተቶች ውስጥ በምርጫ ጣቢያዎቹ ሁሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች ወጣቶች መሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በዘንድሮ ምርጫ የተለየ ተብሎ የሚጠቀሰው የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች ዘምነው መገኘት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎች አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ማሃባው ለዚህ ምስክር ነኝ ይላሉ፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት የነበሩ የምርጫ ማስፈጻሚያ ቁሳቁሶች ከአሁኑ ጋር ሲነፃፀር እጅግ የተለዩ ሆነዋል፡፡ ምርጫ አስፈጻሚዎችን፣ መራጮችንም ሆነ ታዛቢዎችን የማያሰለች ሆኖ የተዘጋጀ ነው፡፡ ዘመናዊ አሠራር ያመጣም ነው፡፡ ከዚህ በፊት አሰልቺ የነበሩ አሠራሮችንም የለወጠ በመሆኑ የዘንድሮን ምርጫ ልዩ ያደርገዋል፤›› ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በባህር ዳር የተደረገው ምርጫ እስከ ምሽት 12፡00 ሰዓት ድረስ በሰላማዊ መንገድ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡  በምርጫው ዕለት ምሽት ላይ የመጨረሻውን ቅኝት የተደረገበት የጣና 2 ‹‹ሀ›› የምርጫ ጣቢያ ነው፡፡ የምርጫ መዝጊያውንና የቆጠራ ሥርዓቱን ለመከታተል በምርጫው ጣቢያ ሪፖርተር የደረሰው 11፡55 ሰዓት ላይ ነበር፡፡

ልክ 12፡00 ሰዓት ሲል የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ሰዓት መድረሱንና መራጮች ቢመጡ ማስተናገድ ማቆማቸውን ካስታወቁና 12፡00 ሰዓት ላይ በምርጫ ጣቢያው የተሠለፈም ባለመኖሩ፣ ታዛቢዎችም ተስማምተው ድምፅ የመስጠቱ ሒደት ቆሞ ወደ ቆጠራ ለመግባት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

እዚህ ውሳኔ ላይ እስኪደርስ ድረስ በዚያ ጣቢያ ከተመዘገቡ 1,200 መራጮች ውስጥ 954 የሚሆኑ ድምፅ መስጠታቸውን፣ 168 ደግሞ ካርድ ወስደው ለምርጫ ያልወጡ መሆናቸው ተገለጿል፡፡ 12፡30 አካባቢ ሲሆን፣ ምርጫው እስከ ሦስት ሰዓት መራዘሙን የሚገልጽ መረጃ ደረሰ፡፡ በዚህ ጊዜ ተከፍቶ ሊቆጠር የነበረው የመራጮች ድምፅ እንዲዘገይ ተደርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለቱ የድምፅ መስጫ ሳጥኖች ቁልፍ እንደገና እንዲከፈት ተደርጎ የሚመጡ መራጮች ካሉ ተብሎ ሲጠበቁም ሪፖርተር አስተውሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...