Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናምርጫ በአምቦና ጊንጪ

ምርጫ በአምቦና ጊንጪ

ቀን:

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በአምቦና አካባቢው የተደረገው ምርጫ የብዙኃኑን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡ በተለይ ባለፉት የምርጫ ጊዜያት ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት አካባቢ ስለነበር፣ የበርካቶች ዓይንና ጆሮ ወደዚህ አማትረዋል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ኢሕአዴግ ትግል በሚያካሄድበት ወቅት በ1983 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ያደረገውን ግስጋሴ፣ በአምቦ አካባቢ ድጋፍ የነበረው ወታደራዊ ደርግ የኢሕአዴግን ጥቃት መመከት ችሎ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት የአምቦና የአካባቢው ሕዝብ ከደርግ ጋር ተባብሮ በፅናት መዋጋቱ ይነገር ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ኢሕአዴግ አገሪቱን ተቆጣጥሮ ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባካሄዳቸው ምርጫዎች፣ አብዛኛውን ጊዜ በአምቦ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲያሸንፉ ወይም ከፍተኛ ፉክክር ሲያደርጉ ማስተዋል የተለመደ ነበር፡፡ በተለይ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ የነበራቸው በመሆኑ፣ ቀደም ሲል ይመሩት የነበረው  የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) በምዕራብ ሸዋ ዞን በማሸነፍም በመፎካከርም ይታወቃል፡፡

ምንም እንኳ መረራ (ፕሮፌሰር) በአካባቢው ኅብረተሰብ ተወዳጅ ሆነው ክፍተኛ ድጋፍ ሲያገኙ ቢስተዋልም፣ በምርጫ 2002 እንዲሁም በምርጫ 2007 መሸነፋቸው አይዘነጋም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ባለፉት የምርጫ ጊዜያት የተለያዩ ውዝግቦች የማያጡት የምዕራብ ሸዋ ዞን ከተሞችና የገጠር ወረዳዎች፣ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ሕዝባዊ ተቃውሞች ሲያስተናግዱ ቆይተዋል፡፡ በተለይ ከ2008 ዓ.ም. ወዲህ የነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ በመላ አገሪቱ ለነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ የአንበሳውን ድርሻ እንዲወስድ አድርጎታል፡፡

አምና በሰኔ ወር የአምቦ ከተማ ተወላጅ በሆነው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመው ግድያ፣ በአካባቢው ከፍተኛ ቁጣን መፍጠሩ ይታወሳል፡፡ ሰኞ  ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ስደስተኛው አገር አቅፍ ምርጫ በተደረገበት ወቅትም የድምፃዊውን የአንደኛ ዓመት ሙት ዓመት መታሰቢያ ወቅት ስለነበር፣ በዞኑ የተደረገውን ምርጫ ውጥረት ውስጥ የከተተ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር በአካባቢው የሚወዳደረው ብልፅግና ፓርቲ ያለ ምንም ተቀናቃኝ በመቅረቡ ምርጫውን የበለጠ ተጠባቂ አድርጎታል፡፡

የምርጫ ዋዜማ

 በምርጫው ዋዜማ እሑድ ሰኔ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. የአምቦ ከተማ ሕዝብ የተለመደውን የዕለት ተዕለት ኑሮውን በማካሄድ ላይ ነበር፡፡ በከተማው የተጠናከረ ጥበቃ መኖሩ ታይቷል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ ቀይ መለዮ ለባሾች፣ የከተማዋ ፖሊሶችና ሚሊሻዎች ጭምር በፒካአፕ ተሽከርካሪዎች በከተማዋ ሲዘዋወሩ ተስተውለዋል፡፡

በመውጫና በመግቢያ እንዲሁም ከአምቦ 33 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ጊንጪ ከተማ ድረስ የተጠናከረ ጥበቃ በሁሉም የፀጥታ ኃይሎች ሲደረግ ነበር፡፡ በተለይ የሃጫሉ ግድያ ብጥብጥ መፍጠሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታን ስለነበር፣ የከተማው ወጣቶች ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ግብ ግብ ይፈጥራሉ የሚል ጥርጣሬ በመኖሩ፣ በከተማዋ ስድስቱም ቀበሌዎች ውስጥ ለውስጥ ሳይቀር ጥበቃው የተጠናከረ ነበር፡፡

በአምቦ ከተማ በምርጫው ዋዜማ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በሬስቶራንትና በመጠጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች በሰጡት አስተያየት፣ ከምርጫ መካሄድ ወራት በፊት በባጃጅ አገልግሎት ላይ የሰዓት ገደብ ስለተጣለ ሥራቸው መቀዛቀዝ ማሳየቱን አስረድተዋል፡፡

በተለይ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ አብዛኛው የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያ ቤቱ በመግባታቸው ኢትዮጵያ ሆቴል፣ አበበች መታፈሪያ፣ ደራራ ሆቴል አንድና ደራራ ሆቴል ሁለትን ጨምሮ በጣት የሚቆጠሩ እንግዶችን ነበር የሚያስተናግዱት፡፡ ሪፖርተር ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ባደረገው ቅኝት ጥቃቅን ምግብ ቤቶች፣ ግሮሰሪዎችና  ሱቆች ተዘግተው ቤታቸው መክተማቸውን ታዝቧል፡፡

የምርጫ ዝግጅት

እሑድ ሰኔ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ የአምቦ ምርጫ ክልል አንድ ለምርጫ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን በ94 ምርጫ ጣቢያዎች ማሠራጨት ጀመረ፡፡ የምርጫ ቁሳቁስ የተከፋፈለባቸውን ቶርበን ኩታዬ የምርጫ ጣቢያ፣ እንዲሁም በኪሶሴ ኦዳ ሊበን ቀበሌዎች ሥር የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ በመገኘት ቁሳቁሶቹ መዳረሳቸውን ለማየት ተችሏል፡፡

በከተማው የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በፓርቲ ተወካዮችና በከተማው ወጣቶች ትብብር አማካይነት ዳስ መሥራት፣ አካባቢውን ማፅዳትና መብራት እንዲገባላቸው ተደርጓል፡፡

የምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ አንድ ምርጫ ክልል አስተባባሪ አቶ መለሰ መረራ፣  በምዕራብ ሸዋ አምቦ አንድ ለምርጫ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 69,696 ናቸው ብለዋል፡፡ በአምቦ ምርጫ ክልል አንድ 94 የምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ በዚህ የምርጫ ክልል አንድ ፓርቲ ብቻ የተወዳደረ ሲሆን፣ ለተወካዮች ምክር ቤት አንድ፣ እንዲሁም  ለክልል ምክር ቤት ሦስት፣ በድምሩ አራት ዕጩዎች ተመዝግበዋል፡፡ ከዕጩዎች ውስጥ ሁለቱ ሴቶች ናቸው፡፡

ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 121 ኪሎ ሜትር ላይ ርቀት ላይ የምትገኘው የአምቦ ከተማ ስድስት ቀበሌዎች ሲኖሯት፣ ከ100 ሺሕ በላይ ሕዝብ እንዳላት ይገመታል፡፡ በአምቦ ከተማ 31 የምርጫ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ በአምቦ ከተማ 29,669 ነዋሪዎች በመራጭነት ተመዝግበዋል፡፡

የምርጫ ዕለት አምቦና ጊንጪ

ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የአምቦና የጊንጪ ከተማ ነዋሪዎች ከሊሌቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያው ተሠልፈዋል፡፡ በተለይ የአምቦ ከተማ ነዋሪወች በነቂስ ወጥተው ለመምረጥ ሠልፍ ይዘው ተስተውለዋል፡፡

በአምቦ ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሒደቱ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት መጀመሩን ተመልክቷል፡፡ በየምርጫ ጣቢያው አምስት ታዛቢዎች የድምፅ አሰጣጡን ሒደት ከመጀመሩ አስቀድሞ ተገኝተዋል፡፡ በምርጫ ጣቢያዎቹ ከአምቦ ሴቶች ፊዴሬሽን፣ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ፌዴሬሽን፣ ከአምቦ ወጣቶች ማኅበር፣ እንዲሁም ከብልፅግና ፓርቲ ተሰይመዋል፡፡

በአምቦ ከተማ እያንዳንዱ ጣቢያ የተመዘገበው ሕዝብ በአማካይ ከ700 እስከ 1,033 ነው፡፡ የምርጫ አስፈጻሚዎች በሚገባ የሠለጠኑ ቢመስሉም፣ በተለይ የምርጫ አስተባባሪዎች ላይ ፍራቻ ይስተዋል ነበር፡፡ ይኼም ፍራቻ የመጣው በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የሚነገርለት ኦነግ ሸኔ ምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ ዛቻ ሲያደርግ እንደነበር በከተማዋ የሚኖሩ ሰዎች ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ማለዳ በአምቦ ከተማ ሪፖርተር ከደረሰባቸው በርካታ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል ሆራ አይቶ 01-ሐ፣ 02-ሀ-2፣ 04-ሐ 2፣ 03-04 ለ-2 እና በሌሎችም ጣቢያዎች መራጩን ሕዝብ በተቀላጠፈ ሆኔታ ሲያስተናገዱ ታይተዋል፡፡ በአንፃሩ ከማለዳው ታይቶ የነበረው ሠልፍ ከአራት ሰዓት በኋላ እምብዛም ነበር፡፡

በምርጫ ጣቢያ መራጮች ድምፅ ከመስጠታቸው በፊት ማብራራያ ሲደረግላቸው ነበር፡፡ ዕድሚያቸው ገፋ ያሉ እናት ግን ካርዱን እንዴት አድርገው ድምፅ መስጠት እንዳለባቸው ግራ ሲጋቡም ተስተውሏል፡፡

በአምቦ ከተማ 04-ለ-2 ድምፃቸውን ሲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የ78 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ አቶ አበበ ዘለቀ በድምፅ አሰጣጡ ደስተኛ መሆናቸው ገልጸው፣ ከዚህ ቀደም በተሳተፉበት ምርጫ ማዋከብ እንደነበርና በዘንድሮ ምርጫ ግን ሁሉም ነገር በግልጽ እንደተስተናገደ አስረድተዋል፡፡

ሌላዋ የ04-ለ-2 ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ጥሩዬ ካሳዬ ምንም ሳይደናገሩ ያመኑበትንና ለውጥ ያመጣል ያሉትን ፓርቲ ያለ ማንም ጫና መምረጣቸውን ተናግረዋል፡፡

በምርጫው ዕለት ከቀትር በኋላ በአገሪቱ እየተካሄደ ስላለው ጠቅላላ የምርጫ ክንውን በተመለከተ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ተከትሎ፣ በከተማዋ በነበረ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ድንጋጤ ተፈጥሮ ነበር፡፡

በአምቦ የምርጫ ክልል አንድ ጣቢያ አስፈጻሚዎች በደረሳቸው መረጃ ተደናግጠው ከአካባቢው ገለል ማለታቸውን፣ ነገር ግን ምርጫውን እናስቀጥላለን ብለው ነበር፡፡

በአምቦ ከተማ 31 ጣቢያዎች የተጠቀሰው ችግር ባለማጋጠሙ በምርጫ አስፈጻሚዎች ዘንድ መደናገጥን የፈጠረ አጋጣሚ ሆኖ ማለፉን ሪፖርተር መታዘብ ችሏል፡፡ ሆኖም ችግር ተፈጠረ የተባለበት በምዕራብ ሸዋ ዞን ሊበን ጀዊ ወረዳ አገር ጉቦ ቀበሌ የኦነግ ሸኔ ኃይል በምርጫው ጣቢያ ተኩስ መክፈቱ ተነግሯል፡፡ ከዚህም ባሻገር በተመሳሳይ ዞን የገጠር ወረዳ ድሬ ጪኒ የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁስ ይዞ ሲጓዝ የነበረ አምቡላንስ ላይ ተኩስ ተከፍቶ ሾፌሩንና አንድ የፀጥታ አስከባሪን ጨምሮ ሦስት ሰዎች መሞታቸውም ተገልጿል፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን 22 ወረዳዎች እንዳሉ፣ በ20ዎቹ ወረዳዎች ምርጫው በሰላም መጠናቀቁን የገለጹት የምራዕብ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምርያ ኃላፊ ኮማንደር አደሬ ቶላ ናቸው፡፡

ከአምቦ ከተማ ወጣ ብሎ ጊንጪ ከተማ 3፡00 ሰዓት ላይ ሪፖርተር ሲደርስ፣ በደንዲ ሁለት የምርጫ ክልል ጊንጪ 01 አስተዳደር አዳራሽ ውስጥ መራጮች ሠልፍ ይዘው ሲመርጡ ተመልክቷል፡፡ በምርጫው ወቅትም ዕድሜያቸው ጠና ያሉና በርካታ ወጣቶች ድምፃቸውን ሲሰጡ ነበር፡፡ ጊንጪ ከተማ እንደ አምቦ በከፍተኛ የፀጥታ አስከባሪዎች ተሞልታ ነበር፡፡

በዚህ ምርጫ ጣቢያ 1,100 መራጮች ተመዝግበዋል፡፡ የምርጫ አስተባባሪው አቶ ጌቱ ተመስገን ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ በአካባቢው በሰባት ምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ድምፃቸውን እየሰጡ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳም ብልፅግና ፓርቲን ወክለው ለጨፌ ኦሮሚያ ድምፃቸውን በደንዲ ሁለት ምርጫ ክልል 01 ሰጥተዋል፡፡

ቆጠራ

በአምቦ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከ12 ሰዓት ጀምሮ በራቸውን ዘግተዋል፡፡ በአንፃሩ 02-02 ሆራ አየቶ ምርጫ ጣቢያ 11፡30 አካባቢ ቆጣራ ሲጀመር ሪፖርተር ተገኝቷል፡፡ ቆጠራው በሚከናወንበት ወቅት አንድ የከተማ ፖሊስ ቆጠራውን በቅርበት ቆሞ ሲመለከት ተስተውሏል፡፡ በተጨማሪም በግንደ ያሂ ገዳ 02-04-ሀ-2 ምርጫ ጣቢያ ሁለት የከተማ ሚሊሻዎች ቆጠራውን ሲመለከቱ መታዘብ ተችሏል፡፡

በምርጫው ዋዜማና በምርጫው ቀን ፀጥ ረጭ ብላ የነበረችው አምቦ ከተማ ማክሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ሙለ በሙሉ ወደ መደበኛ የዕለት ተለዕለት ኑሮዋ ተመልሳለች፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...