Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር​​​​​​​እንደ በሬ ከአራጃችን ጋር ባንውል ይመረጣል!

​​​​​​​እንደ በሬ ከአራጃችን ጋር ባንውል ይመረጣል!

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ

ሞኞች የዕለቱን እንጂ ዘለቄታውን የማይገነዘቡ፣ ተምረው ካልተማረ አባታቸው ያልተማሩ፣ የተጠነሰሰላቸውን ያልተገነዘቡ፣ ለጊዜው ሹመትና ጥቅም የሚሯሯጡ የዘመኑ ፖለቲከኞች የምዕራባዊያንን ተንኮልና ሚስጥር ያውቁ ይሆን? እንግሊዝና ፈረንሣይ ወዳጅ መስለው ጠላት በመሆን የሠሩትን እናስታውስ ይሆን? አውሮፓዊያን አፍሪካን ሲወሩ፣ ጣሊያን ወዳጅ መስላ ውስጣችንን ስትሰልልና ወገንን ስታታልል ኖራ በመጨረሻም እንግሊዝንና ፈረንሣይን አስተባብራ በኢትዮጵያ ላይ ስትነሳ፣ ለፈጸመችው ወረራ በመጀመርያ ዕውቅና የሰጡት ሁለቱ እንደነበሩ ታሪክ ምስክር ነው።

ይሁን እንጂ አምላኳ የማይረሳት ኢትዮጵያችን እርስ በርሳቸው እንዲባሉ አድርጎ፣ እንግሊዝም ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ አዙራ ከጀርመንና ከጣሊያን ሴራ በማምለጥ፣ እኛም ለነፃነት መብቃታችን ታሪክ የሚመሰክረው ሀቅ ነው።                                                                                             ዛሬ ነፍጠኛ ተብለው የሚኮነኑት ወገኖቻችን በዘርና በሃይማኖት ሳይሆን፣ ለአንድ አገር ለአንድ ሕዝብ ሲሉ በባዶ እግር ዘምተው፣ በአንድ እፍኝ በሶ ወይም ደረቅ ቂጣ በቀንድ በያዟት ከብርጭቆ ባነሰች ውኃ ተቃምሰው፣ አገር ወይም ሞት ብለው ነፃነት ጠብቀውና አስጠብቀው ያቆዩትን አገር፣ የዛሬው ትውልድ እንደ ዋዛ በዘርና በሃይማኖት እየተለያየ ለጠላት መንገድ ከፍቶ አልፎም መርቶ ሊያስገባ እየቃጣው ነው።

ጎበዝ ወደ ኋላ መለስ ብለን እንግሊዝና ፈረንሣይ ያደረጉንንና ሊሸጡን የተስማሙበትን እንመልከት። ባለማወቅ የምናደርገውን መለስ ብለን እናጢን። ሹመት፣ ሀብትና ታላቅነት አገር ሲኖር መሆኑን ተገንዝበን ይሆን? ወገኖቼ ሊያስማሙን ሳይሆን ሊያለያዩን፣ ሊያቀራርቡን ሳይሆን ሊያራርቁን፣ አዛኝ ቅቤ አንጓች ሲሆኑ እያየን በጭፍን ራሳችንን አሳልፈን እንዳንሰጥ እንጠንቀቅ። ያለ መግባባት እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ዛሬ የመጣ ታሪክና ወግ አይደለም፡፡ ሁሌም ያለ ነው፡፡ ነገር ግን ማንነትን አውቆ ከባዕድ ወጥመድ ውስጥ ላለመግባት በአንክሮ ማስተዋል እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሳንገነዘብ፣ በእልህና በቁጭት ያለ አዋቂ ሥራ ሠርተን የጠላት ማሾፊያ እንዳንሆን በአንክሮ እንመልከት፣ እናጢን።

ወገኖቼ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳችው ታላቋ ብሪታኒያ ያጠመደችው ወጥመድ የጥቁርን ሕዝብ ብቻ ለማጥፋት ካልሆነም ንብረቱን ቀምታ የዘለዓለም ባሪያዋ ለማድረግ ያቀነባበረችውን ውጥን፣ እኛ ዛሬ እንዳናሳካለት እንጠንቀቅ፡፡ እነሱ                                                                   ጥቁርን ለማጥፋት ሽር ጉድ ሲሉ ምነው ማስተዋል አቃተን ብዬ ራሴን ስጠይቅ፣ እኔ ተሳስቼ እንጂ መቼ ነው እጅ ሰጥተን የምናውቀው ብዬ ለራሴ መልሼ አሁንም ኩራት ይሰማኛል።

የመውረርና የመውረስ ዘይቤያቸውን ትንሽ ላመላክትና ልብ ብንገዛ ላሳስብ ወደድኹኝ። ዘመኑ እ.ኤ.አ. በ1497 ነበር፡፡ ንጉሥ ሔንሪ ሰባተኛ መርከቡን ወደ ዛሬዋ ሰሜን አሜሪካ ወደ ተባለችው ወደ ቀይ ህንዶች አገር የላከው፡፡ ያ መልዕክት ባላገሮቹን ቀይ ህንዶች ሲያፈናቅል፣ በጦር መከራቸውን ሲያሳይ፣ ንብረታቸውን ሲያፈርስና ከቦታ ቦታ እየተንከራተቱ ከመቶ ዓመታት በላይ ሲታገሉ ቢቆዩም፣ የኋላ ኋላ ተሸንፈው የአዲሶቹ መጤዎች ተገዥ ሆኑ። የኋላ ኋላ ግን እንግሊዝ በምታደርገውና በአስተዳደር ሁኔታዋ ባለመስማማት የራሷ ሰዎች የጀመሩት የመለያየት ቁርሾና ቁጭት መሠረቱን ይዞ፣ በመጨሻም እ.ኤ.አ. ሐምሌ 4 ቀን 1784 አሜሪካ ራሷን የቻለች አገር መሆኗን አወጀች።  ከእንግሊዝ ተለይታም ለዓለም ምሳሌና ታላቅ አገር ለመሆን በቃች።                                                                               

እንግሊዞች ቀጥለው ደግሞ እንደ ልማዳቸው ታላቁን ንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስን እያባበሉ እጃቸው ሊያስገቡና ቀይ ህንዶች (Red Indian) ላይ የፈጸሙትን በተመሳሳይ ለማድረግ አስበው ሳይሳካ ቀረ። እንግሊዝ ሁኔታው ሊሳካላት ሳይችል ቢቀርም፣ ሁሌም ለአጭር ጊዜ ሳይሆን ለመቶ ዓመታት የምትሠራውን ፕላን አቆብቁቦ ሲጠባበቁ እ.ኤ.አ. በ1974 ሊይዝላት ተቃርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊ እርስ በርሱ ይጣላ እንጂ አገሩን አሳልፎ ስለማይሰጥ ተዋጋም ተጋደለ ራሱንና ክብሩን ሳይሰጥ ቆይቷል። የዛሬው ሁኔታ ቢያሠጋንም “ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይስትም” እንዲሉ፣ ዛሬም ትናንትም የነበረውና ያለው ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ተጠናክረን ለነፃነታችን እንደምንቆም አልጠራጠርም።

ወገኖቼ ነጭ ጥቁርን ለማጥፋት የቦዘነበት ዘመን የለም፡፡ ከአንዳንድ ከተሞች ጥቁሮችን ለማጥፋት ዘመቻ ሲካሄድም እያየን ነው። ለጊዜው የት እንደሆነ ራሳችሁ ካወቃችሁት መልካም፣ ካልሆነም ውሎ አድሮ ታገኙታላችሁ። ነባርና አንድ አካል፣ አንድ አምሳል የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፉት 40 ዓመታት በተፈጠሩት ተውሳካዊ ችግሮች ተሰቃይቷል፡፡ እርስ በርሳችን ልዩነት ፈጥረን ሊያጠፉን ለሚፈልጉን መንገድ ከመክፈት ይልቅ፣ እንዲያውም የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና መላው የአፍሪካ ሕዝብ በአንድነት ተነሳስተው ቸሩ ፈጣሪ የሰጣቸውን የተፈጥሮ ሀብት በመተባበርና በቴክኖሎጂ በመጠቀም ራስን ችሎ ለሌላው መትረፍ እንጂ የምን ነፃ አውጪነት ነው? ከማንስ ነው ነፃ የምንወጣው? ማን ገዛንና? ወደ ልቦናችን እንመለስና እናስተውል።

በአሜሪካ 330 ሕዝብ ከየአገሩ ተሰባስቦ በሁሉም ባይስማማም በሰላም ሠርቶ መኖር ሲችል፣ ለዘመናት አብሮ የኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባልተጠበቀና ባልታሰበ ጊዜ እርስ በርስ መጋጨት፣ መለያየትና መፈነቃቀልን ሥራዬ ብሎ ሲያያዝ የአርሲ፣ የባሌ፣ የሶዶ፣ የጎጃም፣ የጎንደር፣ የትግራይ፣ የወላይታ፣ የከፋና የሌሎችም ሽማግሌዎች ምን በላቸው? ወይስ ሁሉን አውቃለሁ ባዩ የዘመኑ ግንፍል ወጣት አላስጠጋ አላቸው? ወገኖቼ ባህል የሌለው ሕዝብ ምንም ቢሠለጥንና በሰማይ ቢበርም፣ ከእንስሳ ሳይሻል ኖሮ የሚያልፍ መሆኑን መረዳትና መገንዘብ ተገቢ ነው። ከተሳሳትኩ ይቅርታ፡፡

ነጭ ለጥቁር የማይተኛ መሆኑን ትንሽ ግንዛቤ ልስጥና ልለፍ። ታላቁ 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብረሃም ሊንከን ባሪያ ነፃ ሊያወጣ መታገሉንና ለሰው አዛኝ መሆኑ ከታሪክ ሰምተናል። ቀጥሎ ሥልጣኑን የተረከበው አንድሪው ጆንሰን እጅግ በጣም ደሃ አባቱ የሦስት ዓመት ዕድሜ እያለው ሞተበት፡፡ እናቱ ለግርድና እንኳ በቂ ችሎታ ያልነበራትና ልጆቿን የምታበላው እንኳ የሌላት ደሃ በመሆኗ፣ ከራሊህ ሰሜን ካሮላይና ወደ ዋሽንግተን ይዛቸው ሄደች፡፡ በዚያው የሟችን ልጆች በማሳደግ ላይ እንዳለች ትንሹ አንድሪው አንድ ልብስ ሰፊ ዘንድ በዘምዛሚነት ተቀጠረ፡፡ ትምህርት ቤት ገብቶ አያውቅም፡፡ እዚያው ትንሽ ማንበብ እንደተለማመደ ጌታውን በጣም ጠላውና ለማንም ሳይናገር ከተማውን ጥሎ ወደ ጋርንቪል ቴኔሲ ጠፍቶ ሄደ። በዚያን ጊዜ 16 ዓመቱ ነበር።

አንድሪው በዚያው በለመደው የስፌት ሥራ ተሰማርቶ እየሠራ ማንበብና መጻፍ ለመደ። ዕድሜው 18 ዓመት ሲሞላ ኤሊዛ ማካደል የምትባል ወጣት አገባ፡፡ ከእሱ የተሻለ የተማረች ነበረችና ማበብና መጻፍ በይበልጥ አስተማረችው፡፡ ትምህርት ቤትም ገባ፡፡ አፈኛና ጮሌ ስለነበረ የተማሪዎች ክርክር በሚደረግበት ጊዜ ከእሱ የተሻሉት የእሱን አንደበት በመፍራት ውድድር ውስጥ ሳይገቡ እሱ ተመረጠ፡፡ 5ኛ ክፍል እንኳ ያልደረሰ ወጣት ለከተማው አማካሪነት የዴሞክራት ፓርቲ መረጠው፡፡ ይህ ሰው ባሪያ ለመግዛት ቀርቶ ከባሪያ ያልተሻለ ኑሮን እየገፋ መጥቶ እዚህ የደረሰና እጅግ በጣም ወደ ታች ዝቅ ካለ ደሃ ቤተሰብ የመጣ ሰው፣ የአብረሃም ሊንከንን የባሪያ ነፃነት እምነት በማጉደፍ የባርነት ሕግ እንዲፀድቅ አጥብቆ በመከራከሩ ሪፐብሊካን ያልሆነን የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባል የነበረን አንድሪው ጆንሰን፣ አብረሃም ሊንከን ለሁለተኛ ጊዜ ሲመረጥ ምክትል ሆኖ እንዲሰየም ሪፐብሊካኖች ድጋፍ አድርገውለት በከፍተኛ ድምፅ ሊመረጥ ቻለ።

ይህንን ታሪክ ለምንድነው ያቀረብኩት ባሪያ ሊያስተዳደር ቀርቶ አባቱ ከለማኝ ያልተሻለ ደሃ፣ በዘሩ ከነጭነት ሌላ ምንም የሚያጣቅሰው የባሪያ ባለንብረት ያልሆነ ሰው፣ በቀለሙ ብቻ በመመካት የባሪያን ነፃነት በመቃወሙ ነጭ ምን ጊዜም ለጥቁር የማይተኛ መሆኑን ለማስገዘብ ነው። አንድሪው ጆንሰን የነጭ የበላይነት አቀንቃኝ የሆነው ነጭ በመሆኑ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ግን መናጢ ደሃ ነበር፡፡

ወገኖቼ ታሪክን ከመሠረቱ ብንመለከት ታሪካችን የጋራችን እንጂ የግል አይደለም፡፡ ዛሬ ወዳጅ መስለው ሊያሽሞነሙንን ላይ ታች የሚሉ ነገ ዞር ብለው ሊያዩን የማይፈልጉ መሆናቸውንም እንገንዘብ። አገራችንን በቴክኖሎጂና በኢንዱስትሪ አስቀድመን የዓለም ቁንጮ ለመሆን መሞከር ሲገባን፣ በሆነ ባልሆነው ስንነታረክ ጊዜ ባናጠፋ የተሻለ ነው እላለሁ። አይመስላችሁም? ሁሉን አሟልቶ ሰጥቶን ያንን ለመጠቀም፣ ሕፃን አዝላ የምትለምነዋን ወጣት ከልመና ሳናላቅቅ፣ ሥራ ባገኝ ብለው ወደ ዓረብ አገሮች ሲሄድ ባህር ላይ ወድቀው የዓሳ ነባሪ ምሳና እራት የሚሆኑትን ወጣቶች ከችግርና መከራ ሳናላቅቅ፣ ለአገሩ በዱር ገደሉና በጦር ሜዳዎች አጥንቱን ከስክሶ ደሙን አፍስሶ በመጨረሻ መልካም ጡረታ ሲገባው ዳቦ መግዣ አጥቶ እየለመነ፣ እኛ ዛሬ ለሹመትና ላልተገባ ጥቅም የምንሯሯጠው ተገቢ ይሆን? ሹማምንት ካጠፉ ሥርዓት ይዘው እንዲመሩ ማድረግ መልካም ነው፡፡ ሹማምንቱም አንዴ ከተሾምኩ የሚል ትዕቢት ውስጥ ከገቡ ያለፉት ኃያላን እንዴት እንደ ወረዱ ማስታወስ እንጂ፣ በወሬ ጋጋታ አገርን ሰላም መንሳት አይበጅምና ይታሰብበት። 

የአሁኖቹ የምርጫ ተወዳዳሪዎችም ያለውን መውቀስ ብቻ ሳይሆን፣ ለአገር ልማት፣ ሰላምና አንድነት ቢያስቡ መልካም ይሆናል። የተሠራውን ማመሥገንም መኮነንም ይቻላል፡፡ ግን መጪውንስ የትኛው ልምድና የሠራው ነው ይህንን ያህል የሚያናግረው? አሁን ያለው መልዓክ ነው ማለቴ ሳይሆን ለመኮነንም ሆነ ለማመሥገን ያለን ልምድ አናሳ በመሆኑ፣ አሁን ደግሞ ከላይ እንደጠቀስኩት አቆብቁበው የሚጠባበቁን ብዙ ጠላቶች ስላሉን ሁሉንም በየፈርጁ እንየው ለማለት ነው።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...