Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  ምርጫ በርዕሰ ብሔሯ በፖለከቲከኞችና በታዛቢው ዕይታ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ስድስተኛው አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ካከናወኑ አካባቢዎች አንዷ በሆነችው አዲስ አበባ መራጩ ሕዝብ ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያዎቹ ተሠልፎ ታይቷል፡፡ የምርጫ ሒደቱ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ አመሻሽ 12 ሰዓት ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ በአብዛኞቹ ጣያቢዎች አልተሳካም፡፡ በአንዳንዶቹ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁስ መዘግየትና መቀያየር፣ በአንዳንዶቹ ጣቢያዎች የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎች አለመገኘት እክል ሲፈጥር ተስተውሏል፡፡

  ሆኖም ምርጫ ቦርድ ችግሮችን ከሥር ከሥር እየፈታ ምርጫው ተከናውኗል፡፡ በዕለቱ ሪፖርተር ከተዘዋወረባቸው ጣቢያዎች አንዱ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ምርጫ ክልል 23 ጣቢያ 5 ይገኝበታል፡፡

  በዚህ ጣቢያ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ  ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ድምፅ ሰጥተዋል፡፡  

  በዚህ ምርጫ ጣቢያ 12 ሰዓት ላይ ምርጫ ይጀመራል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም፣ በተፈጠረ የምርጫ ወረቅት መቀያየር ምክንያት የመጀመርያዋ መራጭ ድምፅ የሰጡት 2፡39 ሰዓት ላይ ነበር፡፡ በሥፍራው ቅድሚያ ለአዛውንቶችና ለአካል ጉዳተኞች የተሰጠ ሲሆን፣ ምርጫው ባለመጀመሩ ብቻ ከሁለት ሰዓት በላይ ከምርጫ ጣቢያ ውጪ ቆመው ወረፋ ሲጠብቁ ለነበሩ መራጮች ወንበር ተሰጥቷል፡፡ በሥፍራው ድንኳን አለመኖሩ መራጮች ንጋት ላይ ለብርድ፣ ረፈድ ሲል ለፀሐይ እንዲጋለጡ አድርጓል፡፡ ብዙዎቹ ምርጫ አጀማመሩ በመዘግየቱ ቅሬታ ያሰሙ የነበረ ቢሆንም፣ ተስፋ ሳይቆርጡ ወረፋቸውን ሲጠባበቁ እንደነበር ታዝበናል፡፡

  በኮልፌ ቀራንዮ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶና በቂርቆ ክፍለ ከተማ የተወሰኑ ጣቢያዎች በአብዛኛው የታዘብነው ይህንኑ የመራጮች ረዣዥም ሠልፍ ነው፡፡ መራጮች በትዕግሥት ወረፋ ሲጠብቁ ቆይተዋል፡፡

  በምርጫው ሒደት መጓተት ምክንያት ምርጫ ቦርድ የመፈጸሚያ ሰዓቱን እስከ ምሽት ሦስት ሰዓት የገፋ ቢሆንም፣ ምርጫ ጣቢያዎቹ ተራቸውን በመጠባበቅ ላይ የነበሩትን ሁሉ ከሦስት ሰዓት በኋላም አስተናግደዋል፡፡

  ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ድምፅ በሰጡበት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ምርጫ ጣቢያ 4 እና 5፣ እሳቸው ከቀኑ 5፡20 አካባቢ ከመኪናቸው ሲወርዱ ጀምሮ መራጩ ሕዝብ በዕልልታ፣ በፉጨትና በጭብጨባ ተቀብሏቸዋል፡፡

  በሥፍራው የአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድንን የሚመሩት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡

  ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው ሥፍራዎች ያገኘናቸው ዕጩዎችና ኦባሳንጆ ምን አሉ?

  ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ

  ‹‹የዜግነት ግዴታዬን ስለተወጣሁ ደስ ብሎኛል፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ ጊዜ ውጭ ስለኖርኩ ድምፅ ስሰጥ የመጀመርያ ጊዜዬ ነው፡፡ ፓርላማ ስከፍት ባደረግኩት ንግግር ኢትዮጵያ ውስጥ የምናደርገው ምርጫ ካለፈው የተሻለ እንዲሆን እያሻሻልን መሄድ ይኖርብናል ብዬ ነበር፡፡ አሁንም ይህ ምርጫ እዚያ ውስጥ እንደሚገባ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በሕዝቡ በብዛት መውጣትም በጣም ነው የተደነቅሁት፡፡ ሕዝቡ የራሱን መብት ለማስከበርና የራሱን ድምፅ ለማሰማት ቆርጦ እንደተነሳ ያሳያል፡፡ ምርጫ በዴሞክራሲ ሒደት ላይ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን የዴሞክራሲ ሒደት አንድ ክፍል ነው፡፡ ምርጫ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ እናም ምርጫን የሁሉም ማዕከል አድርገን የምንኖርበት አይደለም፡፡ ይህ ምርጫ ካለቀ በኋላ ሌላ ቀን ይመጣል፡፡ ለዚህ ኢትዮጵያውያን በሙሉ መተባበር አለብን፡፡ ኢትዮጵያ ላሉባት ጉዳዮች ማድረግ የሚጠበቅብን ከምርጫ በላይ ነው፡፡››

  ‹‹ስለዚህ ኢትዮጵያውያን አንድ ላይ ሆነን ያሉብንን ችግሮች የምንፈታበት፣ አንድ ላይ ለሁላችንም የምትመች አገር የምናደርግበት ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ዛሬ የመጣው ሕዝብ ‹ኑሮዬ ይሻሻልልኛል ብዬ ነው የመጣሁት› የሚሉና ሌሎችንም የሚናገሩ መሆናቸውን በመገናኛ ብዙኃን አይቻለሁ፡፡ ይህ ለሚመረጠው አካል ትልቅ ኃላፊነት እየሰጠ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህንን ሁሉ ለማድረግ ኢትዮጵያውያን አንድ መሆን አለብን፡፡ በምርጫ ማሸነፍ አለ፣ መሸነፍ አለ፡፡ መሸነፍ ማለት ለሌላ ጊዜ መዘጋጀት ማለት እንጂ ከጨዋታ መውጣት አይደለም፡፡ አንድ ላይ ሆነን የምንሠራበት ነው፡፡››

  ‹‹እንዲያውም ሌሎች አገሮች የሚጠባበቅ መንግሥት ይሉታል፡፡ ብዙ አገሮችን አይቻለሁ፡፡ በምርጫ ታዛቢ ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡ የምርጫ ዕርዳታም አስተባብሬያለሁ፡፡ ምርጫ ከአገር ዓውድ ውጭ ሊታይ አይችልም፡፡ እናም የምንችለውን ነው የምናደርገው፡፡ እኔ እንደምለው ነገ ይነጋል፣ ፀሐይ ትወጣለች፣ መተባበር አለብን፡፡ የሚያሸንፈውም ይህንን እንደሚይዝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የሚሸነፍ ደግሞ በፀጋ መቀበል ነው፡፡  አይሆንም ከተባለ ደግሞ ሕግ የሚፈቅደው አካሄድ አለ፡፡ ትምህርት ነው፡፡ ከዚህ ጥሩ እንማር፡፡ ለሚቀጥለው እግዚአብሔር ፈቃዱ ከሆነ ስንገናኝ የተሻለ ነገር ለማሳየት እንጣር፡፡ ምርጫ ሒደት ነውና፡፡››

  የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድንን የሚመሩት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ

  ‹‹የአፍሪካ ኅብረት ታሳቢ ቡድን የምርጫ ዝግጅቱን፣ ምርጫውን ለማየትና ምርጫው ሲካሄድ ለመታዘብ ሞክሯል፡፡ እኔ ከአምስት ቀናት በፊት ነው የመጣሁት፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን አመራርን፣  የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ ለምርጫ ዝግጅቱ የሚመለከታቸውን አካላት ምርጫ ቦርድ፣ ሕግ አውጭውን፣ ፖሊስ፣ ደኅንነት፣ ከመከላከያ ሚኒስቴርና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን አግኝቻለሁ፡፡ አንዳንድ ችግሮች መኖራቸውን ተገንዝቤያለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎችም የምርጫ ተሳትፎ ላይ የተሻለ ዕድል መከፈቱን አይቻለሁ፡፡ ከችግሮቹ የደኅንነት ሥጋት፣ የኮቪድ-19ወረርሽኝ፣ በቁሳቁስ አቅርቦት በኩል የተወሰነ ችግር፣ በምርጫ ጣቢያዎች አንዳንዶቹ ይከፈታሉ ከተባለበት ሰዓት ዘግይተው መጀመር ታይተዋል፡፡ ነገር ግን የምርጫ ዝግጅቱ ከእነዚህ ካየናቸው ክፍተቶች በስተቀር ጥሩ ነው፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ የሚገኙ የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎችን አይቻለሁ፡፡ እናንተም እዚህ እንደምታዩት አንዳንድ መራጮች ከ12 ሰዓት በፊት እና 12 ሰዓት የመጡ ናቸው፡፡ ትዕግሥተኛ ናቸው፣ በዕድሜ የገፉም አሉ፡፡ ያገኘኋቸው የፓርቲ ታዛቢዎች ደስተኛ ናቸው፡፡ ለእኔ በነገሩኝ ሰዓት (ከእኩለ ቀን በፊት የነበረ ቃለ መጠይቅ ነው) ቅሬታ አልነበረም፡፡ የእኛ ታዛቢዎች በክልሎችም አሉ፡፡ ሆኖም ሁሉንም የምርጫ ጣቢያዎች መታዘብ አንችልም፡፡ እኛ ታዛቢ ነን እንጂ ተቆጣጣሪ ቡድንም አይደለንም፡፡››

  ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)   

  ‹‹እስካሁን ይህ ነው የሚባል የፀጥታ ችግር አልሰማንም፡፡ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ችግሮች እንዳሉ እንሰማለን፡፡ አብዛኞቹ ከምርጫ ቁሳቁስና ከአሠራር ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ የቁሳቁስ አቅርቦት ችግር በብዙ ቦታዎች ብናይም፣ ሆን ብሎ ምርጫውን ለማበላሸት እስካልሆነ ድረስ ችግሮች ይጠበቃሉ፡፡ ዋናው ሰው ምርጫውን በሰላም ያለ ምንም እንቅፋት ማድረጉ ነው፡፡ የምርጫውን የመጨረሻ ውጤት ተዓማኒነት ያለው ምርጫ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህ የመገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡››

  አንዳንዶች የተለያዩ ችግሮች ባሉበት ምርጫ የማድረግ ፋይዳው ምንድነው ይላሉ? እርስዎ ምን ይላሉ የተባሉት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹እንዲህ የሚሉ ሰዎችን የምጠይቃቸው ስለዚህ ምን ይሁን? ነው››፡፡ ምን እናድርግ ለአገሪቱ መረጋጋት በሕዝብ ውክልና ያለው መንግሥት ይኑር እያልን ነው፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው በምርጫ ነው፡፡ ችግሮች አሉ፡፡ ግን አንዱ የዚህ የምርጫው ውጤት የሚሆነው ሕጋዊ የሆነ መንግሥት መጥቶ እነዚህን ችግሮች በተረጋጋ መንገድ እንዲፈታው ማድረግ ነው፡፡ ይህ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡ ይህ ምርጫ ከዚህ ቀደም ከነበሩት አምስቱ የተለየና ትርጉም ያለው ነው፡፡ ተዓማኒና የብዙኃኑን ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ማለት ችግር የለም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ያሉት ችግሮች በጉልህ ውጤቱን የሚቀይሩት ዓይነት አይደሉም፡፡ ዋናው ሊሆን የሚችለው ነገር ምርጫው የሚያንፀባርቀው የሕዝቡን ፍላጎት ነው፡፡ ይህ እኛ የምንፈልገውና ተስፋ የምናደርገው ነው፡፡››

  የ1997 ዓ.ም. ምርጫን አስመልክተውም፣ ‹‹የ1997 ዓ.ም. ምርጫ የተበላሸው ምርጫው ከተሰጠበት ጊዜ አንስቶ እንጂ በቅድመ ምርጫው አልነበረም፡፡ ከምርጫው ቀን ጀምሮ ነው ሳጥን ግልበጣ የተደረገው፡፡ አሁን ይህ ይደረጋል ብለን አናምንም፡፡ ከምርጫው በፊት ችግሮች ነበሩ፡፡ ዛሬም ታዛቢዎች እንዳይገቡ የተከለከሉባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ዋናውን የምርጫ ውጤት የሚቀለብሱ ናቸው ወይ? የሚለው ላይ ነው ማተኮር ያለብን፡፡ ይህ አይሆንም ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡››

  የአውሮፓ ኅብረት ፍትሐዊነት በሌለበት የምርጫ ታዛቢ አልክም ብሏል፣ ይህን እንዴት ያዩታል? የተባሉት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹የምርጫው ተዓማኒነት የሚመረኮዘው እኛ በምንሠራው ላይ እንጂ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ ወይም ሌላ አገር በሚሠራው አይደለም፡፡ እኛ ይህ ምርጫ ተዓማኒነት እንዲሆን ለራሳችን ደኅንነት ስንል ሠርተናል፡፡ ይህን ያደረግነው ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ስንል አይደለም፡፡ መጥተው ቢሆን በተወሰነ ደረጃ ለምርጫው ተዓማኒነት ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን የሚከታተሉ ሌሎች አካላት አሉ፡፡ የሲቪል ሶሳይቲ ተወካዮችና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች አሉ፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች በሌሉበትም የእኛ ምርጫ ተዓማኒነት ኖሮት ማንም ያሸንፍ ማን የኅብረተሰቡን ስሜት የሚገለጽ እንዲሆን ነው የምንፈልገው፤›› ብለዋል፡፡

  ወ/ሮ አዳነች አቤቤ

  ‹‹ምርጫ ለውጥ ነው፡፡ በአንድ እጃችን ዴሞክራሲን እየተከተልን በሌላ እጃችን ችግኝ እየተከልን አገራችንን ማልበስ አለብን፡፡ አገራችን ቀድሞ የነበራትን ደን ለመመለስ ጥረት ተደርጓል፡፡ ዛሬ በአንድ እጃችን ዴሞክራሲን በምንተክልበት ቀን በሌላ እጃችን ችግኝ መትከላችን ከዓለም የምርጫ ሒደቶች ልዩ ያደርገናል፡፡ የራሳችን የሆነ የዴሞክራሲና የሥራ ባህል እየተከተልን እንደሆነ እያየንበት ነው፡፡ በዚህ ታሪካዊ ሒደት ውስጥ ተካፋይ መሆን በራሱ ዕድለኛነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡››

  ‹‹በተለያዩ መዘግየቶች፣ የድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ አለመፍጠን፣ የመሳሰሉ ችግሮች አሉ፡፡ ሕዝባችን በትዕግሥት በየምርጫ ጣቢያ እንደሚታየው ድምፁን ሰጥቶ ተግባራዊ ማድረጉ ነገ ለሚጠይቀው ጥያቄና የሚመኛትን ኢትዮጵያ ለመመልከት ዋናውና ትልቁን መሠረታዊ ሥራ እየሠራ እንደሆነ አውቆ ይህንን ሒደት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ፣ ነፃና ተዓማኒ በሆነ መንገድ ብቻ መብቱን በተግባር እንዲያውል በሰላማዊ ሒደት  ለእኛ አዲስ ታሪክ ነው፡፡ ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ በሆነ ምዕራፍ ላይ ይህንን ማየታችን ፈጣሪም ረድቶናል፣ ሕዝባችንም ጽናት አሳይቶናል፡፡››

  ‹‹ዴሞክራሲን እንተክላለን ማለት ለማሸነፍ ብቻ አይደለም፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ዕጩ ራሱን ማዘጋጀት ያለበት ሒደቱ ዴሞክራሲያዊ እስከሆነ ድረስ፣ ሰላም እስከሆነ ድረስ ዴሞክራሲን በመትከል ትልቅ ርቀት መሄዳችንን ነው፡፡ ሁላችንም አሸናፊዎች ነን፡፡ አገራችን ነች የምታሸንፈው፣ ኢትዮጵያ ነች የምታሸንፈው የምንልበት ዋናው ምክንያት በዚሁ ወሳኝ በሆነ ጊዜ ውስጥ ሕዝባችን ድምፁን ሰጥቶ መሪውን መምረጥ መቻሉን ነው፡፡ አገራችን በውስጥም በውጭም ካለባት ተግዳሮት አንፃር አሸናፊ ትሆናለች፡፡ ስለዚህ ባሸንፍም እሰየው ደስ ይለኛል፡፡ ባላሸንፍም አገሬ በዴሞክራሲ ሒደት መሪዋን ስለምትመርጥ ታሸንፋለች፡፡ እጅግ ደስተኛ ሆኜ እቀበላለሁ፡፡ ሁሉም ዕጩ በዚህ መልኩ ይቀበላል ብዬ አምናለሁ፤›› ብለዋል፡፡

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -