Tuesday, November 28, 2023

ምርጫ በሰሚትና ቦሌ አካባቢ ጣቢያዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በዮሐንስ አንበርብር 

በሰሚት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሰሚት ለስላሳ ፋብሪካ ጀርባ በሚገኝ የኮንዶሚኒየም ግቢ ውስጥ በሚገኘው የምርጫ ጣቢያ ድምፅ ለመስጠት የአካባቢው ነዋሪዎች ከሌሊቱ 11:30 ጀምሮ በመገኘት፣ ረዥምና መንታ ሠልፍ ይዘው ተራቸውን ሲጠባበቁ ይስተዋሉ ነበሩ።

የሪፖርተር ዘጋቢ በሥፍራው ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላይ የተገኘ ሲሆን፣ በወቅቱም የምርጫ አስፈጻሚዎችና የፓርቲ ወኪሎችና ታዛቢዎች በተገኙበት ድምፅ አሰጣጡን ለማስጀመር የመጨረሻ ዝግጅት ማለትም ከአሥር በላይ ለሆኑ መራጮች ድምፅ አሰጣጡን የተመለከተ ገለጻ እያደረጉ ነበር። 

የሪፖርተር ዘጋቢ ለድምፅ መስጫነት ከተሰናዳው የኮንዶሚኒየም ግቢው የጋራ መጠቀሚያ ሕንፃ በመውጣት በውጭ ተሠልፈው ተራቸውን የሚጠብቁ መራጮችን ፎቶግራፍ በማንሳት ሒደት ላይ በነበረበት ወቅት ግን፣ መለያ ባጅም ሆነ ጋዋን ያላደረገ አንድ የምርጫ አስፈጻሚ ነኝ ያለ ወጣት ፎቶ ማንሳት እንደማይቻል ለመከልከል ሞክሯል።

ክልከላ የሚያደርገው ወጣት ማን እንደሆነምርጫ አስፈጻሚ ከሆነ ከምርጫ ቦርድ የተሰጠውን መታወቂያ እንዲያሳይ ሲጠየቅ ከወረዳው መምጣቱን ገልጿል። 

የወረዳ ኃላፊዎችም ሆኑ ማንኛውም የመንግሥት አመራር በምርጫ ጣቢያዎች 200 ሜትር ርቀት ውስጥ መገኘት እንደሌለባቸው በምርጫ ቦርድ ሕግ የተከለከለ መሆኑ በዘጋቢዎቹ ሲገለጽለት፣ ‹‹ከወረዳ ብመጣም አመራር አይደለሁም›› የሚል ምላሽ በመስጠት ለመከልከል ያደረገውን ሙከራ ትቶ ወደ መጣበት አካባቢ የተመለሰ ቢሆንም፣ 200 ሜትር ርቀት ርቆ አልሄደም።

በዚሁ ጣቢያ ሥራውን በመሥራት ላይ የነበረ የሪፖርተር የፎቶ ጋዜጠኛም ተመሳሳይ ክልከላ በሌላ አንድ ወጣት የደረሰው ሲሆንምርጫ ቦርድ ለጋዜጠኞች የሰጠውን የይለፍ መታወቂያ በማሳየት መከልከል እንደማይችል ሲገልጽለት ስልኩን በማውጣት ወደ አንድ ቦታ በመደወል፣ ‹‹ጋዜጠኞች እያስቸገሩ ነው መግባት ይችላሉ ወይ?›› በማለት ይጠይቃል።

የስልኩን መልዕክት ልውውጥ እንዲሰማ አድርጎ ንግግሩን የቀጠለ ሲሆን፣ ከሌላኛው ጫፍ የሚመጣው ድምፅ ‹‹አይችሉም!›› የሚል ነበር። 

ይህ ወጣት ማንቱን እንዲያሳይ ሲጠየቅ ፈቃደኛ ያልነበረ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ከሰላም ሚኒስቴር እንደመጣ ገልጿል። ነገር ግን የሪፖርተር ባልደረቦች መታወቂያውን አሳይቶ ማንነቱን እንዲያረጋግጥ ሲሞግቱ ያወጣው መታወቂያ የሰላም ሚኒስቴር በጎ ፈቃደኛ የሚል ሆኖ ተገኝቷል። 

ወጣቱ ጋዜጠኞች ላይ ክልከላ መጣል እንደማይችልና በምርጫ ጣቢያ ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን መምራትና መወሰን የሚችለው የምርጫ ጣቢያው አስተባባሪ እንደሆነ ይህም ቢሆን ፈቃድ ያገኙ ጋዜጠኞች ሥራቸውን እንዳይከውኑ መከልከልን እንደማይመለከት ጋዜጠኞቹ ሲከራከሩ ምላሽ ሳይሰጥ ጀርባውን ሰጥቶ ተመልሷል።

የሪፖርተር የምርጫ ዘጋቢዎች ከጠዋቱ 1:30 ሰዓት ላይ በተለምዶ ሰሚት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው  የካ ምርጫ ክልል 28 ምርጫ ጣቢያ ሰባት በደረሱበት ወቅት፣ እስከ አምስት መቶ መራጮች ተሠልፈው እጅግ አዝጋሚ በሚባል ሒደት ወስጥ ድምፅ ሲሰጡ ተመልክተዋል።

 

አንዳንዶችም ተሰላችተው ሠልፉ ሲቀል መመለስ ይሻላል እያሉ ከሠልፉ ሲወጡ ነበር። በዚህ ምርጫ ጣቢያ በመራጮች ምዝገባ ወቅትም ቢሆን ከፍተኛ ሕዝብ የተመዘገበ እንደሆነ የገለጹት የምርጫ ጣቢያው አስተባባሪ አቶ አዲስ ዳምጤበዚህም ምክንያት ንዑስ ምርጫ ጣቢያ መቋቋሙን አስረድተዋል።

በምርጫ ጣቢያ ሰባት ሥር ብቻ 1,700 የተመዘገቡ መራጮች መኖራቸውን የገለጹት የምርጫ አስተባባሪውበንዑስ የምርጫ ጣቢያው ደግሞ 481 መራጮች እንደተመዘገቡ አስረድተዋል።

በዚህ የምርጫ ጣቢያ ድምፅ ለመስጠት የተገኙት መራጮች ቁጥር በዝቶ የሚታየውም፣ ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች በአንድነት በአንድ ቦታ ድምፅ የሚሰጡ በመሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የድምፅ አሰጣጥ ሒደቱን የበለጠ ያዘገመ እንዲሆን ያደረገው ዋናው ምክንያት፣ ለንዑስ ምርጫ ጣቢያው በአስፈጻሚነት ከተመደቡ የምርጫ አስፈጻሚዎች መካከል አምስቱ በዕለቱ በተመደቡበት ቦታ ሳይገኙ በመቅረታቸው እንደሆነ ጠቁመዋል። 

በዚህም ምክንያት በንዑስ ጣቢያው የተመዘገቡ መራጮች የሪፖርተር ዘጋቢዎች በሥፍራው እስከ ነበሩበት 2:30 ሰዓት ድረስ ድምፅ መስጠት አልተጀመረም ነበር።

በቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 6 የተገኙት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (/ር) ድምፃቸውን ሲሰጡ ተስተውለዋል።

እሳቸው በተወዳደሩበት የምርጫ ጣቢያ የተገኘው የመራጮች ቁጥር ከፍተኛ የነበረ ሲሆን፣ እንደ ሌሎቹ ሁሉ በዚህም ምርጫ ጣቢያ የድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ ፈጣን ባለመሆኑ መራጮች ተሰላችተው ይታዩ ነበር። 

በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የነዋሪነት መታወቂያ ያልያዙ መራጮችን በጊዚያዊ የምርጫ መዝገብ (በጊዜያዊነት በፖስታ) ድምፅ ሲሰጡ ተስተውለዋል። ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው የቦሌ ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ካርድ የያዙ፣ ነገር ግን የነዋሪነት መታወቂያቸውን እንደጠፋባቸው የገለጹ የተወሰኑ መራጮች በጊዜያዊ ድምፅ መስጫ ሥርዓት ድምፅ ሲሰጡ እንደነበር ለመታዘብ ተችሏል።

የሪፖርተር ዘጋቢዎች በየካ ምርጫ ክልል 28 ምርጫ ጣቢያ ሰባት ሥር ቀትር ላይ በድጋሚ በተመለሰበት ወቅት፣ ቀደም ሲል የተገለጹት የንዑስ የምርጫ ጣቢያው ምርጫ አስፈጻሚዎች አሁንም በምርጫ ጣቢያው አለመገኘታቸው ተረጋግጧል።

ይሁን እንጂ የምርጫ ጣቢያ ሰባት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አዲስ ዳምጤ፣ ከምርጫ ቦርድ የበላይ አመራሮች ጋር በመመካከር እሳቸው ከሚመሩት 1,700 ከተመዘገቡበት የምርጫ ጣቢያ የተመደቡ ምርጫ አስፈጻሚዎችን ለሁለት በመክፈል፣ በንዑስ የምርጫ ጣቢያው ድምፅ መስጠት ሥርዓቱ እንዲጀመር ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በድምፅ መስጫው ዕለት ቀትር ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች የተመደቡ ምርጫ አስፈጻሚዎች በተመደቡበት ቦታ ሳይገኙ መቅረታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፣ በእነዚህ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ ምርጫ አስፈጻሚዎች ምክንያት የድምፅ አሰጣጡ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች መስተጓጎል ገጥሞት እንደነበር ገልጸዋል።

ነገር ግን አሁንም ቢሆን የዚህ ንዑስ ምርጫ ጣቢያ የድምፅ አሰጣጥ ሒደት እንከን አላጣውም። ለንዑስ ምርጫ ጣቢያው የተላከው የድምፅ መስጫ ወረቀት ከመራጮች ቁጥር በእጅጉ ያነሰ ሆኖ መገኘቱን አቶ አዲስ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

በንዑስ ምርጫ ጣቢያው የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር 481 ቢሆንም፣ ከምርጫ ቦርድ የተላከው የድምፅ መስጫ ወረቀት ግን 250 ብቻ እንደሆነ የተናገሩት አቶ አዲስጉዳዩን ለምርጫ ቦርድ የበላይ አመራሮች በማሳወቅ ተጨማሪ የድምፅ መስጫ ወረቀት እንደሚላክላቸው መልስ አግኝተው ይህንኑ እየተጠባበቁ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህ ምርጫ ጣቢያ ዕጩ ተመራጭ የሆኑት የዲያቆን ዳንኤል ክብረት የምርጫ ወኪል ችግሩ መከሰቱን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል።

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -