Wednesday, February 1, 2023

ምርጫ በየካ አራዳና ቂርቆስ ክፍላተ ከተማ አካባቢዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአንድ ዓመት ተራዝሞ የነበረው የኢትዮጵያ ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤት ምርጫ በዕለተ ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ተካሂዷል። ዓምና መካሄድ የነበረበት ምርጫ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ ዓመት እንዲራዘም ሲደረግ ቀጠሮ በተያዘለት ቅዳሜ ግንቦት 28 ቀን ያልተካሄደው፣ በቁሳቁሶች አቅርቦት (ሎጂስቲክስ) እና ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት ነበር፡፡

ኅብረተሰቡ ባለፉት አምስት ዙር የኢፌዴሪ ምርጫዎች ድምፁን በዕለተ ሰንበት እሑድ ቢሰጥም፣ ዘንድሮ ግን በአዘቦቱ በዕለተ ሰኞ ድምፁን መስጠቱ ብቻ ሳይሆን ወሩም ከግንቦት ወደ ሰኔ መሻገሩ ምርጫውን ልዩ አድርጎታል፡፡

የሪፖርተር ዘጋቢ ቅኝት ባደረገባቸው የየካ፣ አራዳና ቂርቆስ ውስን የምርጫ ጣቢያዎች አዲስ አበቤዎች ማልደው ነበር ከየምርጫ ጣቢያዎች የተገኙት፡፡

የመዲናዪቱ ነዋሪዎች ምርጫ “97 በጣለው ግርዶሽ ሳቢያ ከስድስት ዓመት በፊት በተካሄደው 5ኛው ዙር ምርጫ፣ እንደ ሁሉም ክልሎች በእኩል ጊዜ ሁለቱንም ማለትም የክልልና የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ በተመሳሳይ ለማካሄድ ባይታደሉም ዘንድሮ ግን ተሳክቶላቸዋል፡፡ በዕለተ ሰኞ ሰኔ 14 ቀን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባልነት ይመጥናሉ የሚሏቸውን ፓርቲዎች ሲመርጡ ውለዋል፡፡

 ከ2007 ምርጫ ጋር ሲነፃፀር በዛ ያለ የሕዝብ ቁጥርና ሠልፍ የታየበትም ነው፡፡ የሕዝብ መነቃቃት እንደነበረው የሚገልጹት በየካ 07 ምርጫ ክልል 16 ያገኘናቸው አቶ ተረፈ ዓለሙ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ በ2007 ዓ.ም. የነበረው ምርጫ ከዘንድሮው ቀልጠፍ ያለ እንደነበር ያስታወሱት አስተያየት ሰጪው፣ ያሁኑ ምርጫ ለከተማው ምክር ቤት 14 ሰዎች የሚመረጡበት በመሆኑ የድምፅ መስጫውን ጊዜ እንዳራዘመው ይሰማኛል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ምርጫ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው በአራዳ ክፍለ ከተማ ምርጫ ጣቢያ 007/2ሀ ነው፡፡ ጎህ ከቀደደበት አንስቶ በሁለት ረድፍ የተሠለፉት በርካታ መራጮች ድምፅ መስጫ ሰዓት እስከሚደርስ ይጠባበቃሉ፡፡ በድምፅ መስጫ ክፍል ውስጥ ሁለት አስፈጻሚዎች፣ አንድ አጋፋሪና ዘጠኝ የምርጫ ታዛቢዎች ባሉበት መራጮች ከ12 ሰዓት ከሩብ ጀምሮ ድምፅ ሲሰጡ ነበር፡፡ ለአረጋዊውያንና ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ ሲሰጥ ነበር፡፡

በዚህ የምርጫ ጣቢያ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ምክትል መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌ ከረፋዱ 3:15 ላይ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

‹‹አሁን እኔ ለመምረጥ በመጣሁበት ሰዓት ሁኔታው የተረጋጋ ነው፡፡ ስለአጠቃላይ ምርጫው ማውራት አልችልም፡፡ ገና ሒደቱ መጀመሩ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ምን ይሆናል፣ ማታ ምን ይሆናል፣ መናገር አልችልም፡፡ የራሴን ምርጫ ግን በትክክል መርጫለሁ፤›› በማለትም የኢዜማ ምክትል መሪው አቶ አንዱዓለም ተናግረዋል፡፡

በዚሁ ምርጫ ጣቢያ ድምፅ ሰጥተው ሲወጡ ያገኘናቸው አንድ አካል ጉዳተኛ የተረጋጋና ሰላማዊ መሆኑን ለአገር የሚበጁትን መምረጣቸውን ተናግረዋል፡፡ ምርጫው እንደሚናጠቀቅም እምነታቸው መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ ያስተዋልነው ቢኖር፣ አንዲት ሸምገል ያሉ እናት ለመምረጥ በመቸገራቸው በምርጫ አስፈጻሚው ፈቃድ በረዳታቸው ተደግፈው በአሻራቸው ድምፅ ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡

ከተዘዋወርንበት ምርጫ ጣቢያ አንዱ የካ 06 ነው፡፡ ድምፅ ወደሚሰጥበት አዳራሽ ለመግባት መንገድ ላይ ከተተከለው ድንኳን ውስጥ ተቀምጠው የነበሩና 11 ሰዓት አካባቢ ያገኘናቸው ሁለት ጎልማሶች፣ ‹‹የምርጫው ሰዓት የሚራዘም ከሆነ ተመልሰን እንመጣለን›፤›› ብለው ከድንኳኑ ወጥተው ሲሄዱ አስተውለናል፡፡

 በየካ 06/29 ምርጫ ጣቢያ ያገኘናቸው ወ/ሮ አልማዝ ኃይለ የመምረጫ ስፍራው ጠባብነት ድምፃችንን በጊዜ እንዳንሰጥ አድርጎናል ብለዋል፡፡

በየምርጫው ጣቢያ የድምፅ አሰጣጡ በመጓተቱ ለመምረጥ የመጡት ሲያማርሩ፣ የሰው ኃይል ቢጨምሩ፣ ተጨማሪ ድምፅ መስጫ ቢያዘጋጁ ያሉም አልታጡም፡፡

ድምፅ መስጠቱ እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት ቢራዘምም መራጩ በመብዛቱ ከሰዓት ገደቡ አልፎ ድምፅ የሰጡ ሲኖሩ፣ ሳይመርጡ የሄዱም አሉ፡፡

ከተዘዋወርንባቸው የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ሲመዘገቡና ድምፅ ሲሰጡ በፎቶና በቪዲዮ ለመቅረፅ የምናደርገውን ጥረት ያደናቀፉ ሁለት ጣቢያዎች  በየካ አጋጥመውናል፡፡  በተለይ የየካ 07 ክልል 16 ምርጫ ጣቢያ ንጹሕ ሰሎሞን፣ ፎቶም ሆነ ቪዲዮ መቅረፅ የሚቻለው ከደጅ እንጂ፣ ሰው ድምፅ ሲሰጥ አይደለም ብለዋል፡፡ ይኸም በተሰጠን ሥልጠናና የበላይ ኃላፊችን የተነገረን ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

በምርጫው ማግስት የምርጫ ውጤቱን ለማየት በማለዳ ብንደርስም ገና ቆጠራ ላይ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ እስከ እኩለ ቀንም አልተገለጸም፡፡

የሐረሪ ክልል ምርጫ በመዛወሩ ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ሐረሪዎች ለክልልና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ድምፅ የሚሰጡት ጳጉሜን 1 ቀን ይሆናል፡፡ ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ በአዲስ አበባ ከተማ ከ1987 ዓ.ም. የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ጀምሮ እንደሚመርጡ ይታወቃል፡፡

ታሪካዊ ዳራ

ኢትዮጵያ የፓርላማ ምርጫ ማድረግ የጀመረችው የዘውድ ሥርዓቱ የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት በነበሩት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) ዘመን በ1948 ዓ.ም. ነበር፡፡ በዘመነ ዘውድ እስከ 1965 ዓ.ም. ድረስ አምስት የፓርላማ ምርጫዎችን ተካሂደዋል፡፡

 የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በ1967 ዓ.ም. ሥልጣኑን ከጨበጠ ከ12 ዓመት በኋላ፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) የተመሠረተበትን የብሔራዊ ሸንጎን ምርጫ በ1979 ዓ.ም. አካሂዶ ሕዝባዊ ሪፐብሊኩ በ1980 ዓ.ም. ዕውን ሆኗል፡፡ የአምስት ዓመት ዘመነ ሥልጣኑን ሳይፈጽም በ1983 ዓ.ም. አክትሟል፡፡

 የሦስት ሥርዓተ መንግሥትን ምርጫዎች ያሳለፈችው አዲስ አበባ ከተማ፣ ከሽግግር መንግሥት (1983-1987) በኋላ የተመሠረተው ኢፌዴሪ አምስት የፓርላማ ምርጫዎችን (1987-2007) ከከተማ ምክር ቤት ምርጫ (በአራቱ) ጋር አስተሳስራ አከናውናለች፡፡ የዘንድሮው የሰኔ 14 ቀን ምርጫዋ ስድስተኛዋ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -