የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ባለፈው ሳምንት መጀመርያ በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ፣ ማኅበሩ በታዛቢነት ባሰማራቸው 13 ሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃቶች መፈጸማቸውን አስታወቀ፡፡
ማኅበሩ ሐሙስ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ በተለይም ወሲባዊ ትንኮሳ፣ ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጥቃት በታዛቢዎች ላይ መድረሱን የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሪት ሌንሳ ብየና ተናግረዋል፡፡
በምርጫው ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመታዘብ 369 የምርጫ ጣቢያዎችን በ130 ታዛቢዎች መሸፈን እንደቻለ ማኅበሩ በመግለጫው ወቅት አስታውቋል፡፡
በዚህም ታዛቢዎች ምልከታ ባደረጉባቸው ጣቢያዎች ውስጥ የሴቶች ውክልና አናሳ እንደነበረ፣ የምርጫ ጣቢያዎቹ 82 በመቶ ወንድ ኃላፊዎች እንደነበራቸው፣ 18 በመቶ የሚሆኑት በሴት የሚመሩ እንደነበሩ ወ/ሪት ሌንሳ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ዕገዛ የሚያስፈልጋቸው የማይመስሉ ሴት መራጮች በምርጫ አስፈጻሚ አካላት ዕገዛ እንደተደረገላቸው፣ ለመምረጥ መሥፈርቱን ያላሟሉ ወንዶች ድምፅ እንዲሰጡ መደረጉ፣ በምርጫ ጣቢያዎቹ መገኘት ያልተፈቀደላቸው ሰዎች በጣቢያ እንደተገኙና ምርጫውን የመታዘብ ሥራ እንዲያከናውኑ የታዛቢዎች መብት መነፈጉን መታዘባቸውን የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር አክለው ተናግረዋል፡፡
ማኅበሩ መንግሥት በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመመርመርና በዳኝነት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሕግ አስፈጻሚ አካላት፣ ለፖሊስ፣ ለሌሎች ሕግ አስከባሪ አካላት ሥነ ፆታ ተኮር ሥልጣን እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቅበታል በማለት አሳስቧል፡፡
በተመሳሳይ ሴት የምርጫ አስፈጻሚና አስተባባሪ ሠራተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ ይረዳ ዘንድ፣ የሴት የፀጥታ አስከባሪዎች ቁጥር ከፍ ማለት አለበት ሲሉ ዋና ዳይሬክተሯ ጠይቀዋል፡፡