የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ ከተደረገው ምርጫ በኋላ በርካታ አቤቱታዎች እንደተቀበለ፣ ከእነዚህም ውስጥ ውጤት ሊያስቀይሩ ይችላሉ የተባሉ አቤቱታዎችን በጥልቀት እየመረመረ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሐሙስ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል ለአገር ውስጥና ለውጭ የመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ምርጫው ከተደረገበት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ብዙ ፓርቲዎች በርካታ አቤቱታዎችን ለምርጫ ቦርድ አቅርበዋል፡፡
አቤቱታዎቹ ተጠቃለው በዓይነትና በይዘታቸው ከውጤቱ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ለማየት እየተሞከረ እንደሚገኝ ያስታወቁት ሰብሳቢዋ፣ ‹‹አንዳንዶቹ አቤቱታና ቅሬታዎች በምርጫ ቦርድ ደረጃ ሊታዩ የማይችሉ እንደሆነ ገና ከጅምሩ ለመረዳት ተችሏል፤›› ብለዋል፡፡
ከቀረቡት አቤቱታዎች ዝርዝር የሚጎድላቸው፣ የምርጫ ጣቢያዎች ያልተገለጹበት፣ ትክክለኛ ያልሆነ ድርጊት ፈጸመ የተባለው አካል ሳይገለጽ ቅሬታ የቀረበባቸው እንደሚገኙ ያስታወቁት ወ/ሪት ብርቱካን፣ ‹‹ሆኖም ከቀረቡት አቤቱታዎች ከምርጫው ውጤትና ይዘት ጋር በጣም የተቆራኙትን ቦርዱ ውጤቶችን በሚያፀድቅበት ጊዜ ለማፅደቅ ወይም ላለማፅደቅ፣ ወይም ለሚሰጠው ውሳኔ እንደ መሠረት ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉትን አንዳንድ አቤቱታዎች ተመልክቶ ምላሽ ይሰጥበታል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
እንደ ሰብሳቢዋ ገለጻ፣ ከምርጫው ዋዜማ አንስቶ የምርጫ ተወካዮች ችግር በሚገጥማቸው ወቅት ለቦርዱ ሪፖርት የሚያቀርቡበት ቋሚ የቅሬታ መቀበያ ዴስክ ተቋቁሞ ነበር፡፡
በፓርቲዎቹ የቀረቡ ቅሬታዎችን የምርጫ ቦርድ መመለስ የሚገባቸውን ጉዳዮች ከማረጋገጥና የመጨረሻውን ውጤት ከመግለጽ ጋር አብረው የሚታዩ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ሆኖም በምርጫው ሒደት ላይ ወቅታቸውን ያልጠበቁ ጥያቄዎችን ቦርዱ እንደማይመለከት አስታውቀዋል፡፡
በጣቢያዎች ውጤቶችን በመደመር ወቅት ችግር የተስተዋለባቸው የምርጫ ጣቢያዎች እንደነበሩ ያልሸሸጉት ሰብሳቢዋ፣ ከግንዛቤ ጉድለት ወይም ከነበረው ረዥም የምርጫ ዕለት እንቅስቃሴ ስልቹነት የተነሳ በጥቂት የምርጫ ጣቢያዎች ትክክለኛ ያልሆኑ የአሠራሮች የተስተዋለባቸው እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ በአንድ የምርጫ ጣቢያ የተደባለቀ ድምፅ መስጫ ተሠራጭቶ ድምፅ ሲሰጥበት እንደዋለ ያስታወቁት የቦርድ ሰብሳቢዋ፣ በቆጠራው ጊዜ እስከ ግማሽ ድረስ እንደተቆጠረና ሆኖም ስህተት መሆኑ ሲታወቅ ‹‹ኳራንታይን›› እንደተደረገ ገልጸዋል፡፡
በመራጮች ምዝገባ ሒደት ድምፅ ለመስጠት የተመዘገቡና በምርጫው ዕለት ለመመዝገብ የመጡት ሰዎች ቁጥራቸውን ማመሳከር እንደሚገባና ይህም በመመርያ የሚታወቅ እንደሆነ ያስታወቁት ወ/ሪት ብርቱካን፣ ለድምፅ መስጫ ወደ ጣቢያዎች የመጣው ወረቀትና በሳጥኑ ውስጥ የተገኘው፣ እንዲሁም ተበላሽቶ የተመዘገበው ድምር ትክለለኛነት የማረጋገጥ ሒደት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ በደሴ ከተማ በአሥር ያህል ጣቢያዎች ይህንን አሠራር ሳይተገብሩ ወደ ምርጫ ክልል ስለላኩት ቆጠራው ድጋሚ መከናወን ነበረበት ያሉት ሰብሳቢዋ፣ የምርጫ ክልሉ ለጊዜው ‹‹ኳራንታይን›› አድርጎ ሳጥኖቹን አስቀምጦ ስለነበረ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በሐሰት ሲሽከረከር እንደነበረ በመግለጫው ወቅት ገልጸዋል፡፡
ከላይ የቀረቡት ዓይነት መሰል መጠነኛ ስህተቶችና በምርጫው ውጤት ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ የምርጫ ጣቢያዎች በቁጥር በጣም አነስተኛ ናቸው ያሉት ሰብሳቢዋ፣ የቀረቡ ሪፖርቶችን መሠረት በማድረግና ቃለ ጉባዔ በመያዝ ድጋሚ ቆጠራና መሰል ውሳኔዎች የሚሰጡባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ዝርዝር ሪፖርቶችን ቦርዱ ከክልሎች እየተቀበለ እንደቆየ ያስታወቀ ሲሆን፣ እንደ አንድ ግድፈት ተፈጽሟል ብሎ የወሰደው ነገር ቢኖር በአሮሚያ ክልል በነገሌ የምርጫ ከልል የተፈጸመው ጉዳይ ነው ብሏል፡፡
በነገሌ ምርጫ ክልል ለምርጫው አንድ ቀን ሲቀር የታተመው ድምፅ መስጫ ወረቀት በሕጉ መሠረት ተመዝግቦ የነበረን የግል ተወዳዳሪ ያላካተተ እንደሆነ በመረጋገጡ፣ በምርጫ ክልሉ ድምፅ መስጠት እንደሌለበት ከላይ እስከ ታች ትዕዛዝና መረጃ ተላልፎ እንደነበር ተገልጾ ነበር፡፡ ሆኖም ማንነቱ በመጣራት ላይ ያለ አንድ የመንግሥት ይሁን የምርጫ ክልል ኃላፊ ሒደቱ ይቀጥል በማለቱ ከመቶ በላይ በሚሆኑ ጣቢያዎች ምርጫው ሲከናወን እንደቆየ፣ ይህም ሕገወጥ በመሆኑ ለፌዴራል ፖሊስ ለማሳወቅ ጥረት የተደረገ መሆኑን፣ ጥፋተኛው በሕግ እንዲጠየቅ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን፣ የተከናወነው የድምፅ አሰጣጥም ምንም ዓይነት የሕግ ውጤት እንደማይኖረው የቦርድ ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል፡፡