የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ የሆነውን የመስቀል አደባባይና የመኪና ማቆሚያ መሠረተ ልማት ለማስተዳደር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ስምምነት ላይ መድረሱ ተጠቆመ፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ የኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅትን በመንግሥትና በግል ዘርፍ ትብብር ማዕቀፍ አማካይነት ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ እያስተዳዳረ ነው፡፡ አደባባዩን፣ የመኪና ማቆሚያ፣ እንዲሁም ሱቆቹንና መሰል አገልግሎቶችን እንዲያስተዳድር ተወስኖ፣ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን የምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ይህንን ሥራ ለማስፈጸም ያስችለው ዘንድ፣ አዲስ መዋቅራዊ አደረጃጀት ማፅደቁን የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
የኤግዚቢሽን ማዕከሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ከመስቀል አደባባይ ፓርኪንግ ጋር ተመጋጋቢ በማድረግ፣ የፓርኪንግ መሠረተ ልማቱን ምክር ቤቱ እንዲያስተዳድረው ለማስቻል በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣ አስተዳደሩና የንግድ ምክር ቤቱ ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአንድ ጊዜ 1,400 ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግደው የመኪና ማቆሚያ፣ በአካባቢው እየታየ ካለው የንግድ እንቅስቃሴና የኩነቶች ብዛት ሳቢያ ለሚፈጠረው የፓርኪንግ ችግር መፍትሔ ይሆናልም ተብሏል።
ንግድ ምክር ቤቱ እንዲህ ዓይነት የኩነቶች ማስተናገጃ ቦታዎችን የማስተዳደር ልምዱን ተጠቅሞ፣ አደባባዩ ደረጃውንና ዘመናዊነቱን ጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑንና በተደራጀ ሁኔታ ሥራውን ለማስጀመር ዕቅድ ወጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ተሰምቷል፡፡
የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት 36 ሱቆች እንዳሉት የሚታወቅ ሲሆን፣ እነዚህን ሱቆች በማከራየት ንግድ ምክር ቤቱ አደባባዩንና የመኪና ማቆሚያውን ማስተዳደሩ የከተማ አስተዳደሩና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያላቸውን አጋርነት የሚያጠናክርና በአገሪቱና በከተማዋ ያለውን የግሉና የመንግሥት አጋርነት የሚያጠናክር ነው ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉትን የተለያዩ ስምምነቶች የተፈራረመ ሲሆን፣ ከእነዚህም ንግድ ምክር ቤቱ ከከተማዋ ኢንቨስትመንት ቢሮና ከገቢዎች ባለሥልጣን ጋር ለመሥራት የሚያስችለውን የጋራ መግባቢያ ሰነድ መፈረሙ የሚታወስ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ፣ የማዕከሉን ገቢ አሥር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከነበረው ዓመታዊ የተጣራ ትርፍ 1.8 ሚሊዮን ብር ወደ 32 ሚሊዮን ብር ማሳደጉን የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሲኤምሲ አካባቢ የሚገነባው በአዲስ አፍሪካ ኢንተርናሽናል ኤግዚቢሽን ማዕከልና በኮንቬንሽን ማዕከል ግንባታ የከተማ አስተዳደሩና ንግድ ምክር ቤቱ በጋራ የሚሠሩ ሲሆን፣ የአክሲዮን ኩባንያ ተቋቁሞ የከተማው አስተዳደር ከ50 በመቶ በላይ የአክሲዮን ድርሻ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ይህ ኮንቬንሽን ማዕከል በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ጠንሳሽነት በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ ተቋቁሞ በርካቶችን ባለአክሲዮኖች ያደረገ ሲሆን፣ አስተዳደሩ ግን ከፍተኛውን የአክሲዮን ድርሻ ይዟል፡፡
አዲሱ የመስቀል አደባባይና የመኪና ማቆሚያ የሱቅ፣ የመፀዳጃ አገልግሎት፣ ዲጂታል ስክሪን፣ መናፈሻዎችንና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጥ ነው፡፡ ለ24 ሰዓታት አገልግሎት እንደሚሰጥና ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማጠናከርም የራሱ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ መስቀል አደባባይን፣ ፓርኪንግና ተያያዥ አገልግሎቶችን ሥራ በአዲሱ በጀት ዓመት ከሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ማስተዳደር ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡