የአረጋውያን ማኅበር ሁለገብ ማዕከል ሊያሠራ ነው
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ለአረጋውያን ጥበቃ ለማድረግ የቀረፁትን የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር የአፍሪካ አረጋውያን ፕሮቶኮል አፀደቀች፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር የአፍሪካ አረጋውያን ፕሮቶኮልን በአዋጅ ቁጥር 1182/2012 ማፀደቋና የማስፈጸም ኃላፊነቱንም ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሰጠቱ፣ የኢትዮጵያ ጡረተኞችና አረጋውያን ብሔራዊ ማኅበር የአባላቱን ፍላጎት ዕውን ለማድረግ የሚወስደው ሕጋዊ ዕርምጃ ቅቡልነት እንዳለው ማሳያ መሆኑን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አባሙዳ አበበ ኃይሉ ጐበና እንዳሉት፣ ፕሮቶኮሉ ከማንኛውም መድልኦ ነፃ የመሆን፣ እኩል የፍትሕና ሕግ ጥበቃ የማግኘት፣ የራሳቸውን ደኅንነት አስመልክቶ ካለማንም ጣልቃ ገብነት ውሳኔ የመወሰን መብትን ይሰጣል፡፡
አቅማቸውን ያማከለ የሥራ ዕድል ማግኘት፣ ማኅበራዊ ደኅንነት ጥበቃ፣ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲሁም የጤና አገልግሎት የማግኘት፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች፣ በባህል በመዝናኛና በስፖርታዊ ዝግጅቶች ላይ የመሳተፍ መብቶችን የያዘ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል፡፡
ፕሮቶኮሉ በልዩ ሁኔታ ለሴት አረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኛ፣ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ ሥጋት ባለባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ አረጋውያን ልዩ ልዩ ጥበቃዎችን የሚያስቀምጡ ድንጋጌዎችን ያካተተ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ጡረተኞችና አረጋውያን ብሔራዊ ማኅበር አዲስ አበባ ውስጥ ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኘው 6,900 ሜትር ካሬ ቦታ ላይ የአረጋውያን ሁለገብ ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል ዲዛይን በማሠራት ላይ መሆኑንም ፕሬዚዳንት ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አባሙዳ አበበ እንዳሉት፣ ለግንባታው ማከናወኛ የሚሆን ገንዘብ የማፈላለጉ እንቅስቃሴ ከዲዛይኑ ሥራ ጎን ለጎን አብሮ እየተከናወነ ነው፡፡ የማመቻቸቱም ተግባር የሚከናወነው በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፡፡
ማኅበሩ በየጊዜው ለሚያከናውነው ሥራ ተፈጻሚነት ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከምንጊዜም በላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ማኅበሩ መገንዘቡን አመልክተው፣ ማኅበሩ በቦርድ የሚተዳደርበትን አቅጣጫ ተቀይሶ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡