Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እኛው ነን!

እንዴት ሰነበታችሁ? ምርጫውና ውጤቱ እንዴት እያደረጋችሁ ነው? “ማሸነፍና መሸነፍ” የሚባሉ ቃላት ብቻ ደምቀው በሚሰሙበት ስሜታችን ውስጥ፣ “እኛ” የሚለው ዋና ጉዳይ ለምን ይሆን የሚዘነጋው? እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት አሸናፊውም ተሸናፊውም ወገኖቼ በመሆናቸው ብቻ እፅናናለሁ። ችግር ካለም ሕግ ይፍታው እላለሁ፡፡ ታዲያ እኔ ቀብራራው አንበርብር ይህችን ብትነትብም ውበቷ አላልቅ ያለች ካፖርት እየደረብኩ፣ እንደ አዛውንት እያደረገኝ ምክር ለማካፈል ብቅ ስል አይግረማችሁ፡፡ የእኔ ዋና ጉዳይ ከአገሬ ሰላም ውሎ ማደር ጋር ነው፡፡ ሰላም እንዲኖር ደግሞ ለፍትሕ ዕድል መስጠት ተገቢ እንደሆነ የደላላ ጭንቅላቴ ይነግረኛል፡፡ የተበደለ የሚካሰው በሕግ ወይም በሽምግልና እንጂ በጉልበት እንዳልሆነ ከድሮ ጀምሮ የማውቀው እውነት ነው፡፡ ጉልበት የሚመርጡ ለጊዜው እንጂ የትም አይደርሱም፡፡ “ሰይፍ የሚወዱ በሰይፍ ይወድቃሉ” እንዲሉ፡፡ ለማንኛውም ነገም ሌላ ቀን ስለሆነ ለነገ መዘጋጀት ይገባል ባይ ነኝ፡፡ እኔ ነኝ ያልኩት!

‹‹የዚህች ዓለም ነገር እንደ ማካሮኒና ፓስታ ነው…›› ይላል አደባባይ ላይ የቆመው ወፈፌ። ‹‹አንዳንድ ሰው እኔ ፓስታ አይስማማኝም ባይሆን ማካሮኒ ምንም አይለኝም ይላል፣ ዱቄቱ ግን አንድ ነው…›› ሲል፣ ከትርፍ ሰዓቱ ላይ ሌላ ትርፍ ሰዓት ሰርቆ መንገደኛው እያዳመጠ ይስቃል። ወፈፌውም፣ ‹‹የዚህ ዓለም ነገርም እንዲሁ ነው…›› እያለ ሐሳቡን ይደጋግማል። የእሱን ጩኸት ባልሰማ ብዬ መንገዴን ቀጠልኩ። እንዴት ነው ሰው ልክ ልኩን ሲነግሩት መስማት የጀመረው እባካችሁ? እውነት ሥልጣኔ ገባን ማለት ነው? ጊዜ በተትረፈረፈበት አገር ውስጥ እንኳን የወፈፌ ንግግር አይደለም፣ ሌላውን ደንዝዘን በማየታችን ለትዝብት ተዳርገን የለም ወይ? በአንድ ወቅት ቻይና ነው አሉ የታዘበን፡፡ ቻይናመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ላቡን ጠብ አድርጎ ሲለፋ የእኛ ሰው አካፋ ተደግፎ ያየው ነበር ተባለ፡፡ ቻይናውያን የባቡሩንና የመኪናውን መንገድ አጠናቀው ሌላ ቴክኖሎጂ ሲጀምሩ እንዴት ሆነን ይሆን የምንጠብቃቸው? አለበለዚያ፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች አሁንም አሉ እንዴ?›› እያሉ እንዳይጮሁ በበኩሌ እሠጋለሁ፡፡ አሁንም ባለፈ ጉዳይ ላይ ስንነታረክ የዛሬው ብቻ ሳይሆን የነገውም እንዳያመልጠን እፈራለሁ፡፡ ምን ልበል ታዲያ!

ይገርማችኋል የኪሴ ነገር ሲራቆት ምንም እንኳን ሆዴ ቢጮህብኝ የማንጠግቦሽን ፊት ማየት ክብድ ይለኛል።  እንዲያው ብቻ በደህና ቀን ንፉግ አትሁኑ እንጂ እጅ ያጠረ ቀን ብድር መላሽ አታጡም፡፡ ‹‹ስጥ ይሰጥሃል…›› አይደል የሚለው መጽሐፉስ? ታዲያ የተረፈኝ ቀን የተቋደሱኝን ፍለጋ በየምግብ ቤቱና በየግሮሰሪው ስንከራተት እውላለሁ። ኑሮ ‹‹በእከክልኝ ልከክልህ›› ሕግ ካልተመራ ዘንድሮ የሚቻል አይደለም። አግኝተው ያጠገቡኝ ዕለት ማንጠግቦሽን እህል ዘግቶኛል ብዬ ተጠቅልዬ ለጥ እላለሁ። ካልተገኘ ባዶ ሆዴን ገብቼ በአሞኛል ሰበብ እንቅልፌን እየበላሁ አድራለሁ። ግን ብቻዋን አቅርባ ስትበላ ሳይ ታሳዝነኛለች። መቼስ ምን ይደረግ ሲታጣ የቤቱን ለቤት ሰው፣ የውጪውን ደግሞ ለውጭ ሰው መተው ተገቢ ይመስለኛል። ‹‹የቄሳርን ለቄሳር›› አይደል የሚባለው? አንዳንዶች ለፈጣሪ የሚሰጡትን አሥራት ከግብር ዕዳ ላይ ያወራርዳሉ የሚባለው እውነት ነው እንዴ? ይኼ ‹‹የምቀኛ›› ወሬ ነው ከተባለ ‹‹ምን ይደረግ ምቀኝነት ባህላችን ነው…›› ማለት ይበቃናል፡፡ ምቀኛ የሚያደርገን እኮ ዕጦት ነው፡፡ የዕጦት ምንጩ ደግሞ አለመሥራት ነው፡፡ የማንሠራው ደግሞ በሚረባውና በማይረባው ስለምንባላ ነው፡፡ አይደል እንዴ!

ሽቅብ እየተጓዝኩ ሳለሁ የሴቶች ልብስ መሸጫ ቡቲክ ደረስኩ። ገንዘብ ቢኖረኝ ብዬ ተመኘሁ። አዎ ቢኖረኝ ምናለ ከተሰቀለው አንዱን ሹራብ ለማንጠግቦሽ ብገዛላት። እንዲህ ስመኝ ሳለሁ ሦስት ወጣት ሴቶች መጥተው ካጠገቤ ቆሙ። በሚያዩት ልብስ የተገረሙ ይመለሳሉ፡፡ ‹‹ምንድነው ይኼ ሱሪ?›› ብላ ጠየቀች አንደኛዋ ቆንጆ። ወጣቱ ነጋዴ፣ ‹‹ቬል ነው ፋሽን ስለሆነ ነው ያመጣነው…›› አላት። ‹‹እንዴስኪኒፋሽን ነው ብላችሁን ገዝተን ገዝተን ምንም ሳንለብሰው ደግሞ አሁን ቬል ፋሽን ሆነ ትላላችሁ?›› አለችው ሌላዋ ተናዳ። የፋሽን ነገር እንዲህ የሕይወታቸው አካል የሆኑ ሴቶችን ማየት ከጀመርን ቆየን። የመብትና የእኩልነት ነገር ደግሞ እንቅልፍ ነስቷቸው የሚብከነከኑትን ማየት መጀመራችንም እንዲሁ። ‹‹ምን እናድርግ ብለሽ ነው? ፋሽን ሆኗልና አምጡልን የምትሉት እናንተው ናችሁ…›› አላት። ‹‹አንዴ አጥብቡት አንዴ አስፉት ትላላችሁ። ዕድሜ ለቻይና በል ዋጋውን ተናገር እስኪ?›› አለችው። የእኔ መቆም እንኳን ለእነሱ ለእኔም አልታወቀኝም። ‹‹አምስት ሺሕ ብር…›› አለ፡፡ ‹‹መጨረሻው?›› ስትለው፣ ‹‹መጨረሻው ነው! ፊክስድ!›› አላት፡፡ በላስቲክ የታሰረውን ጥቅል መዥረጥ አድርጋ አውጥታ ስታስታቅፈው አንጀቴ ከታሰሩት ብሮች ጋር አብሮ ተገለባበጠ። እንዴት ነው ጃል? አንድ አገር ውስጥ ነው ያለነው? ወይስ የመደብ ልዩነቱ እየሰፋ ነው? አይ ጊዜ እግዜር ይይልህ፡፡ ሊገባኝ ስላልቻለ ወዳጆቼን ፍለጋ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ ወዳጆቼን ስነግራቸው ጊዜ ሳይሆን የተወረረ መሬት ነው ችግሩ ሲሉኝ፣ ካርድ አውጥቶ በድምፁ መቅጣት ሲኖርበት አፉን ባዶ ሜዳ ላይ የሚያሾል መንጋ ደሜን ያፈላዋል፡፡ አናዳጅ ሁሉ!

ዙሪያዬን ገልመጥ ገልመጥ ባደርግ ዓይኖቼ የተሰቀሉትን ልብሶች እያስቃኙኝ፣ ጆሮዎቼ ደግሞ በየሱቁ የተከፈተውን የሬዲዮ ድምፅ ያስደምጠኛል፡፡ አሁንም ደንዝዤ የልብስ ገበያ ውስጥ እንደቆምኩ ገባኝ፡፡ ሳልጠግብ ብለብስ ምን ይሠራልኛል? ፈጥኜ ወደ ግሮሰሪና መብል ሠፈር መሄድ እንዳለብኝ ገባኝ። ምግብ ሲባል በሰኔ ፆም ከምንም ነገር በላይ አዋዜው ቀድሞ አፍንጫዬን የሚያውደው አምሮቱ ነው? ወይስ ምትሃት አለው? እግሮቼን ወደ እዚያው ላቀና ስል ተመሥገን ፈጣሪ አልኩ። እግር በነዳጅ ቢሠራ ምን ይውጠኝ ነበር? ተመሥገን! ያለ ቅጥ ከፍ ባለው ድምፃቸው ከተከፈቱት ሬዲዮኖች አንዱ ከምርጫው ውጤት በላይ ሒደቱ ስኬታማ ሆኖ ማለፉ ደስ የሚያሰኝ ነው የሚለውን ሐተታ ሰማሁ። ውጤት ችግር እንዳለበት በማስረጃ ተደግፎ ሲቀርብ ይጣራ ማለት የግድ መሆኑን፣ አላስፈላጊ ድርጊት የፈጸሙ ደግሞ በሕግ እንዲጠየቁ ቢደረግና የሕዝብ ድምፅ ቢከበር የሚለው ዋነኛ ማጠንጠኛ ሆኖ ሲነገር ነበር፡፡ በእርግጥ እኔ ደላላ እንጂ የፖለቲካ ሳይንቲስት ወይም የሕግ ባለሙያ አይደለሁም፡፡ ወዳጄ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር የሕዝብ ድምፅ መስረቅ ይቅር የማይባል ኃጢያት ነው፡፡ ነገር ግን ማስረጃ የማይቀርብበት አቤቱታ ደግሞ በሕግ ፊት ተቀባይነት የለውም…›› የሚለው አባባሉ አይረሳኝም፡፡ ‹‹ሰረቀ የተባለን ሲቻል እጅ ከፍንጅ ካልሆነ ነቃሽ ምስክር ይዞ ፍትሕ አደባባይ መገተር እንጂ፣ እንደ ዶናልድ ትራምፕ ባዶ ሜዳ ላይ ማጓራት መሳቂያ ያደርጋል…›› ያለኝም አይዘነጋኝም፡፡ እንዴት ይረሳል!

ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ሰሞኑን አብረን ድድ ማስጣት ጀምረናል። እሱ እረፍት ወስዶ ሥራ ስለሌለው፣ እኔም ምን ጮሌ ደላላ ብሆን በምርጫው ሰሞን ሥራ በመቀዛቀዙ ቦዝነናል። እናማ ምን ነገረኝ መሰላችሁ? ‹‹የምንወደውንና የምንጠላውን የማናውቅ ሆነን እስከ መቼ ነው የምንኖረው?›› አለኝ፡፡ እንጃዬን በትካሻዬ ሰብቄ መለስኩለት። እውነት ነው። አንዳንዴ ስለምንጮህለት፣ ስለምንጮህበት፣ ስለምንወደው፣ ስለምንጠላው፣ ስለምንፈርድለት፣ ስለምንፈርድበት ነገር እኮ ግራ ተጋብተን  ነው የምንታይው። ቆይ ግራ ተጋቡ ተብሎ  ነው የተፈረደብን? ወይስ ግራ መጋባት የሥልጣኔና የዕውቀት መገለጫ ነው የተባልነው? መልሱ ራሱ ግራ የገባው መሆን አለበት፡፡  ምንድነው ደንቀፍቀፍ የሚያደርገኝ? ነገር እየበላሁ ከቤቴ ስወጣ ሁለት የተለያዩ የግራ እግር ጫማዎች ማድረጌ የገባኝ እኩለ ቀን ካለፈ በኋላ ነው፡፡ ለካ እንደኔ እየሆኑ ነው ግራ የሚያጋባ ነገር እየተናገሩ አገሩን ግራ የሚያጋቡት ማለት ስጀምር እንቅፋቱ እያደናቀፈ ከሐሳቤ አለያየኝ፡፡ የሰሞኑ ወጀብ ነው መሰለኝ!

በምርጫው ማግሥት እኔ በምሄድበት አቅጣጫ ተቃራኒ ብዙ ሰዎች እየሮጡ ሲመጡ ተመለከትኩ፡፡ አሯሯጣቸውና አመጣጣቸው ወደ እኔ ይመስላል፡፡ ግን አጠገቤ ደርሰው ካለፉኝ በኋላ ድንጋጤው ሳይለቀኝ ምንድነው ብዬ ጠየቅኩ። ‹‹ሁሉም ፓርቲዎች ተመጣጣኝ ውጤት በማግኘታቸው በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥምር መንግሥት ሊመሠረት ነው ብሉ ምኞቱን አውርቶ ነው…›› አለኝ አንዱ፡፡ ‹‹የአገር ነገር ብዙ ያስወራል…›› አሉ አዛውንቱ ባሻዬ። ታዲያ ሩጫው ያልተጣራ ወሬ ለማውራት ይሆን? ‹‹ወይ ጉድ የዘንድሮ ወሬ ኦሊምፒክ ላይ ቢወዳደር በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎች አጥልቀን ነበር…›› ብላቸው፣ ፈገግ እያሉ፣ ‹‹ወሬማ እንዲህ ላለው ቁምነገር መቼ አብቅቶ? ወሬ ለኦሊምፒክ አይደለም ለመንደር ውድድርም ብቃት የለውም…›› አሉኝ፡፡ ከምኞት ወሬ ጆሮአችሁን ይጠብቀው እንጂ ሌላማ ምን እላችኋለሁ? አንዱ በቀደም ዕለት፣ ‹‹አንበርብር የሚወራውን እውነት ነው እንዴ?›› ሲለኝ፣ ‹‹ምኑ?›› ማለት፡፡ ‹‹ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ተወዳድረህ መሸነፍህ…›› እያለ በትካዜ ሲያየኝ በቆመበት ጥዬው ሄድኩ፡፡ ምን ላድርገው ታዲያ ይህንን ጅል!

እንዲህ ጉደኛና አስገራሚ ክስተቶችን እያስተናገድኩ ሳለሁ አንድ የውጭ ዜጋ ቤት ፈልጎ ሲያጠያይቅ አገኘሁት። ወዲያው በቀልጣፋው ምላሴ እንግሊዝኛውን ከምልክት ቋንቋ ጋር ደበላልቄ ከያዙት ደላሎች ነጥቄ ወሰድኩት። ከየት እንደመጣ ለመጠየቅ የፈጀብኝ ጊዜ እሱ ከአገሩ የመጣበትን ጊዜ ይስተካከላል ብል ማጋነን አይሆንብኝም። አይ እንግሊዝኛ? አሁን ማን ይሙት እኔ ደላላው አንበርብር በእንግሊዝኛ መታማት ነበረብኝ? ግን ቋንቋ እንጂ ሌላ አይደለም። እንዲያው እንግሊዝኛን እንዲህ አካበድነው እንጂ ተሟሙቼም ቢሆን መግባባቴ አይቀርም፡፡ እንዳልኳችሁ ሞቼ… ሞቼ… ከየት መጣህ ስለው ከቱርክ አለኝ። ልቤ ብርግግ አለ። ይህ ሰው አገሩ ከአውሮፓ ዋንጫ ተሸንፋ ስትሸኝ በንዴት ወዲህ መጥቶ ይሆን ብዬ ነዋ። ‹‹ለማንኛውም ከአማርኛ በተጨማሪ በርካታ አገር በቀል ልሳኖችን ባውቅ የሚጠቅመው እኔን እንጂ፣ አንድ ወፈፌ አለው እንደተባለው ሕዝብን የመነጣጠያ ወይም አገር የመከፋፈያ አይደለም፡፡ ለማንኛውም ከቻላችሁ ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ ፈረንሣይኛ፣ ሩሲያንኛ፣ ስፓኒሽ፣ ዓረብኛ፣ ቻይኒኛ (ማንዳሪን) ወዘተ ልመዱ፡፡ ዓለም አቀፋዊ ትሆናላችሁ፣ አትሞኙ…›› እያለ የሚመክረን ምሁሩ ወዳጄ ነው፡፡ ልክ ነው አይደል!

ትንሽ ተሯሩጬ ለቱርኩ ኮንዶሚኒየም ቤት አገኘሁለትና ተከራይ ብለው እንቢ አለኝ። ‹‹ካገኘህ የምድር ቤት እንጂ ፎቅ ላይ ወጥቼማ መሬት ቢንቀጠቀጥ ምኔ ሊተርፍ ነው?›› አይለኝ መሰላችሁ? ግርም ብሎኝ በአርባ ምናምን ሺሕ ብር ቪላ ቤት አከራየሁት እላችኋለሁ። የቤቱ ጌታ ቱርኩን ይዤላቸው ስሄድ በደስታ ፍንድቅ እያሉ፣ ‹‹ሐበሻ ይዘህ የመጣህ መስሎኝ ተናድጄ ነበር…›› ሲሉኝ በሆዴ፣ ‹‹ዘረኛ ኪራይ ሰብሳቢ…›› አልላቸው መሰላችሁ? እንዲህ ዓይነቶቹ ደግሞ መብዛታቸው፡፡ ‹‹አገሬን… አገሬን…›› እያሉ በየአደባባዩ ይዘምራሉ፣ በየጓዳቸው አገር ያጠፋሉ፡፡ ከንክኖኝ ስለነበር፣ ‹‹ሐበሻ ወገንዎን ለምን ጠሉ?›› ስላቸው፣ ‹‹ተወኝ ወንድሜ! የሚረባ ነገር በማይበላበትና ከሰው በታች በሚኖርበት አገር ውስጥ ፋይዳ ቢስ ፖለቲካ ላይ ውሎ ማደር የሚወድ የእኛ ሰው ብቻ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ለወሬ ጊዜ የለኝም፡፡ ከብጥብጥ ውጪ መፍትሔ የማያመነጭ የሐበሻ ፖለቲካ በአፍንጫዬ ይውጣ…›› ብለው በዓይናቸው ሲገረምሙኝ ደነገጥኩ፡፡ ወይ ምሬት!

በሉ እስኪ እንሰነባበት። መቼም ዘንድሮ ለመኖር ሲባል ጥረት መኖር አለበት። ኑሮ እንዲህ ትከሻችንን አጉብጦትም ቢሆን ለመኖር ስንል መታገል ይገባናል። ሌላው ቀርቶ ዱቄቱ አንድ ሆኖ ሳለ ከፓስታና ከማካሮኒ እናማርጣለን እንዳለው ወፈፌ፣ የማይለያይ ነገርን ለማለያየት እንታገላለን፡፡ ያውም የማይቻለውን፡፡ መራጩም እኛ፣ ተመራጩም እኛ። አሸናፊውም እኛ፣ ተሸናፊውም እኛ፡፡ ያለንም እኛ፣ የምንኖርም እኛ፡፡ እኛው ነን ያለነው! መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት