Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርስለተዛባው ዘገባ ይቅርታ እንጠይቃለን

ስለተዛባው ዘገባ ይቅርታ እንጠይቃለን

ቀን:

ለዚህ እርምት ጥያቄ ምክንያት የሆነው ጉዳይ ሪፖርተር ጋዜጣ አማርኛ ዕትም ጥቅምት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. አንድ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛን በተመለከተ ያወጣውን ዘገባ ነው፡፡ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ዳኛ አየለ ዱቦ ስሜን በተመለከተ ያቀረበው የዲስፒሊን ውሳኔ ሐሳብ ጋዜጣው በተዛባና የዳኛውን ስም በማጥፋት ዘግቧል፡፡

ይህም የዘገባው ምንጭ ያልተጠቀሰ መሆኑ ነው፡፡ በዘገባው እንደተመለከተው የዜናው ምንጭ ከየት እንደሆነ አልተጠቀሰም፡፡ አንድ ጊዜ ሲዘገብ ምንጭ መጠቀስ እንዳለበት አያከራክርም፡፡ ግዴታም ነው፡፡ የዘገባው ምንጭ መጠቀስ ዜናው የተገኘው ተዓማኒ ከሆነ ምንጭ እንደሆነ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ ምንጭ  አለመጠቀሱ ዜናው ተዓማኒነት ካለው ምንጭ ተገኝቷል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ስለሆነም የገባው ምንጭ በአግባቡ እንዲጠቀስ እላለሁ፡፡

በዘገባው የቀረበው የገንዘብ መጠን ዳኛው የያዘውን መዝገብ በፍፁም የማያሳይና እጅግ ከእውነት የራቀ አንባቢው ማኅበረሰብ የተዛባ አስተያየት እንዲኖረው የሚያደርግና የዳኛውን ስም የሚያጠፋ ነው፡፡ በመሠረቱ አንድ ዘገባ ሲቀርብ ሕዝብ እውነታውን እንዲረዳ ታስቦ ነው፡፡ የቀረበው ዘገባ ላይ ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ደረቅ ቼክ ለተለያዩ ሰዎች ፈርመው ሰጥተዋል ተብሎ ተደጋግሞ በቁጥር ሳይሆን፣ በአኃዝ ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዘገባው የተጠቀሰው መዝገብ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው፡፡ በአራዳ ምድብ ችሎት የነበረው መዝገብገ ላይ ተከሳሾች ፈርመው ሰጥተዋል፣ የተባለው ቼኮች በድምሩ 5,442,000.00 (አምስት ሚሊዮን አራት መቶ አርባ ሁለት ሺሕ)  ነው፡፡ ይህ ደግሞ በፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የውሳኔ ሐሳብ ላይ በሰንጠረዥ ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል ከአራዳ ምድብ ችሎት ከነበረው መዝገብ ውጪ ዳኛው ቃሊቲ ምድብ ችሎት አስቀድሞ ሲመለከታቸው የነበሩት ሁለት መዝገቦች በዘገባው ተጠቅሰው ብቻ ነው የታለፉት፡፡ የቃሊቲ ምድብ ችሎት መዝገቦች ላይ የተጠቀሱት ቼኮች የያዙት የገንዘብ መጠን ደግሞ 3,968,000.00 (ሦስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ስልሳ ስምንት ሺሕ ብር) ነው፡፡ አጠቃላይ ቢደመር እንኳ 9,410,000.00 (ዘጠኝ ሚሊዮን አራት መቶ አሥር ሺሕ) ነው፡፡ በመሆኑም በዘገባው የተገለጸው መዝገብ የአራዳ ምድብ ብቻ ሆኖ እያለ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ደረቅ ቼክ የተሰጠበት ነው በማለት ተደጋግሞ በአኃዝ (በቁጥር ቢሆን የታይፒንግ ስህተት ነው ሊባል ይችላል) ለሕዝብ መገለጹ፣ ለሕዝብ የተሳሳተ መረጃ ከመስጠትም አልፎ ሕዝብ በዳኛው ላይ አሉታዊ አመለካከት እንዲይዝ የሚያደርግና የዳኛውን ስም ያጠፋ ነው፡፡ የዘገባው ምንጭ ከማንና ከየት እንደሆነ አለመገለጹ ይህ ዘገባ ሲቀርብ ከትክክለኛ ምንጭ እንዳልሆነ ያሳያል፡፡

በቃሊቲ ምድብ ችሎት መዝገቡ እንዲጣመር ጥያቄ ቀርቦ ፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስተያየት ሳያቀርብ መዝገቡ እንደተጣመረ በዘገባው በተዛባ መልኩ ቀርቧል፡፡ የቀረበው ዘገባ የሚያመለክተው የመዝገብ ይጣመር ጥያቄ አራዳ ምድብ ችሎት ቀርቦ ውድቅ መደረጉን ነው፡፡ በሌላ በኩል የአራዳ ምድብ ችሎት መዝገብ ቃሊቲ ምድብ ችሎት የቀረበው ዳኛው መዝገቡን ለመመርመር በሰጠው ትዕዛዝ እንደሆነ መዘገቡ ሲታይ በተከሳሽ በኩል የመዝገብ ይጣመር ጥያቁ ሳይቀርብ ፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጥያቄውን በማስመልከት መልስ ሳይሰጥ እንደሆነ ነው፡፡

ይህ አዘጋገብ ዳኛው መዝገቡን ያለ ጥያቄ በሥልጣኑ በትዕዛዝ እንዳስመጣ ያመለክታል፡፡ ነገር ግን የውሳኔ ሐሳቡ ላይ በዚህ መልኩ አልተቀመጠም፡፡ የዲስፒሊን ክስ አቅራቢ ፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም ባቀረበው አቤቱታ ላይ መዝገቡ የአንደኛ ተከሳሽ አማኑኤል አዲሱ ጠበቃ ባቀረበው የመዝገብ ይጣመርልኝ አቤቱታ ላይ እኛ መልስ ሳንሰጥ ተጣምሮብናል ያለ ሲሆን፣ ዳኛውም በሰጠው መልስ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በሐምሌ 2009 ዓ.ም. በተጻፈ መልስ መዝገቡ ቢጣመር ተቃውሞ የለንም ማለቱን መግለጹ በውሳኔ ሀተታ ላይ የቀረበውን ዘገባው አላካተተውም፡፡ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ (በጉባዔው ውሳኔ ሐሳብ ገጽ ስምንትና ዘጠኝ ላይ ጥፋተኛ የተባልኩበት ከአንድ እስከ ስድስት በተጠቀሱት ውሳኔዎች ውስጥ) ያልተገለጸ ነገር ዘግቦታል፡፡ ይህ የሚያሳየው ዘገባው ወደ አንድ ጎን ያጋደለና ትክክለኛውን መረጃ የያዘ አለመሆኑን ነው፡፡

የተከሳሾች ዋስትና የተፈቀደው ቀደም ሲል ዋስትናቸው ያስከለከለው ድንጋጌ በብይን ተቀይሮ እንደሆነ ሳይሆን፣ የተከለከለውን ዋስትና በድጋሚ እንደፈቀደ ተዘግቧል፡፡ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ የሚያመለክተው ተከሳሾች ዋስትና ተከልክለው በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ትዕዛዝ ተሰጥቶ፣ በተከሳሾች ላይ የቀረበባቸውን አንቀጽ በመቀየር በቸልተኝነት እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ዋስትና ጥያቄያቸውን አዲስ ነገር ተገኝቷል ብሎ ተቀብሎ በዋስ ለቋቸዋል የሚል ሆኖ እያለ በመዝገቡ ላይ በቸልተኝነት እንዲከላከሉ ብይን ሳይሰጥ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ የተከለከለውን ዋስትና ጥያቄ የክልከላ ትዕዛዝ/ብይን/ውሳኔ በመሻር እንደ ገና ተቀብሏል ተብሎ መዘገቡ የውሳኔ ሐሳቡን በተዛባ መልኩ ኅብረተሰቡ እንዲረዳው የሚያደርግና ያልሆነን ነገር እንደሆነ በመቁጠር መዘገብ ስም ማጥፋት ነው፡፡

የክስ ይዛወርልኝ ጥያቄ የሚቀርበው የክስ ጭብጥ ከመሰጠቱ በፊት ለበላይ ፍርድ ቤት የሆነና የበላይ ፍርድ ቤትም ጥያቄው ተገቢ ነው ብሎ ሳያረጋግጥ መደረጉ ሥነ ሥርዓት ሕጉን የተከተለ አይደለም ተብሎ መዘገቡ ጉዳዩን በአግባቡ ያለመረዳት ጭምር ነው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ጉዳዩ መዝገብ ይጣመር ጥያቄ ሆኖ ሳለ ክስ ይዛውር ጥያቄ እንደሆነ መዘገቡ ስህተት ነው፡፡ የመዝገብ ይጣመር ጥያቄ የሚቀርበው መዝገቡን ለሚያየው ችሎት እንጂ እንደ ክስ ይዛወር ጥያቄ ለበላይ ፍርድ ቤት አይደለም፡፡

የመዝገብ ጥጣመር ጥያቄ በቀረበ ጊዜ የጥያቄውን አግባብነት መርምሮ የመቀበል ወይም ያለመቀበል ሥልጣን የችሎቱ ነው፡፡ በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ (የወ/መ/ሥ/ሥ ሕግ አንቀጽ 116 (2) እና 117 (1) በተሳሳተ ሁኔታ ተተርጉሟል የሚል እንጂ ጥያቄውን ችሎት የመቀበል ሥልጣን የለውም አልተባለም፡፡ በተሳሳተ ሁኔታ ተተርጉሟል የተባለውም ስህተቱ ምን እንደሆነ በዝርዝር አላመለከተም፡፡ የቀረበው ዘገባ ግን በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የቀረበው የዲሲፒሊን ክስ በመገልበጥ ተመልክቷል፡፡ የተገለበጠውም ቢሆን በአግባቡ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በውሳኔው ሐሳብ ላይ ያልተመለከተ በመሆኑ ዘገባው በትክክል የቀረበ አይደለም፡፡

የዲሲፒሊን ውሳኔው ከጥቅምት 3 እስከ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰጠና ከሥራና ደመወዝ ዕገዳ የተጣለው ከጥቅምት 5/2011 ጀምሮ ሆኖ እያለ ጥቅም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሆኖ እያለ ጥቅምት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ታግዷል መባሉ ስህተት ነው፡፡

የቀረበው ዘገባ በእኔ በኩል ያለውን ስለመዝገቡ ሁኔታ ተጠይቆ ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ልዩ ስብሰባ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ አስተያየት አሰባስቦ ጉዳዩ በአግባቡ ታይቶና የእኔ ሐሳብም ተካትቶ እንዲቀርብ ለምሳሌ ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ የመራበትን በተከታይ ዘገባ አላቀረበም፡፡

በአጠቃላይ ዜናው የተገኘበት ምንጭ ያልተጠቀሰ በመሆኑ ዜናው የተገኘው ተዓማኒ ከሆነ ምንጭ ነው ሊባል የሚችል ባለመሆኑ፣ ዜናው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጥፋተኛ ነው በማለት ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ (በጉባዔው ውሳኔ ሐሳብ ገጽ ስምንትና ዘጠኝ ላይ ጥፋተኛ የተባልኩበት ከአንድ እስከ ስድስት በተጠቀሱት) ሳይሆን በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የቀረበውን የዲሲፒሊን ክስ ዝርዝር የያዘና ሚዛናዊ የጎደለው በመሆኑ፣ ዜናው በመዝገቡ ውስጥም ሆነ በውሳኔ ሐሳቡ ላይ የሌለ እጅግ የተጋነነና የተዛባ ፍሬ ነገር ዘገባ ለሕዝብ የቀረበ በመሆኑ የእኔን ስም ያጠፋና ሕዝቡ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ አመኔታ እንዲያጣ ያደረገ ዘገባ በመሆኑ፣ የተፈጠሩት ስህተቶች ታርመውና ተስተካክለው እንዲሁም ሚዛናዊነት ጠብቀው እንዲታረም አመለክታለሁ፡፡

ከዝግጅት ክፍሉ

      በወቅቱ በዘገባው ለተፈጠረው አኃዛዊ የገለጻ ስህተት ወዲያውኑ ዕርማት የተሰጠ ቢሆንም፣ የተከበሩ ዳኛ አቶ አየለ ዱቦ ስሜ እርማቱ ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ ክስ በመመሥረታቸው፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሰኔ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. አከራክሮ መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ ጉዳዩ እስከ ሰበር ችሎት ድረስ ክርክር የተደረገበት ቢሆንም፣ ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔውን በማፅናቱ፣ ከላይ እንደተገለጸውና ራሳቸው ዳኛ እየለ ያቀረቡልንን የዕርማት ነጥቦች እንዳሉ በማተም አርመናል፡፡ ለተፈጠረው የዘገባ ስህተት ዳኛ አየለ ዱቦ ስሜንና አንባቢዎቻችንን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...