በቀደም ዕለት ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ሲሆን ሠፈሬ ውስጥ የሚገኘው ምርጫ ጣቢያ ደረስኩ፡፡ በእኔ ቤት ከማንም ቀድሜ መገኘቴ ነበር፡፡ ግን አልነበረም፡፡ ከእኔ በፊት በግምት ከ300 በላይ ሰዎች በሁለት ረድፍ ተሠልፈው ወረፋ ይዘዋል፡፡ ለምርጫ ጣቢያው ጥበቃ የተመደቡ ፖሊሶች ፈትሸውኝ ሠልፉን ከተቀላቀልኩ በኋላ፣ ከፊቴ ከተሠለፉ ሰዎች የማውቃቸው ካሉ ብዬ እየተንጠራራሁ ሳይ ብዙዎቹን አየሁዋቸው፡፡ የዕድሜ እኩዮቼ ሳይሆኑ በአካባቢያችን የተከበሩ አዛውንት እናቶችና አባቶች ናቸው፡፡ በጣም ተንጠራርቼ ሳይ እማሆይ ማንም ሳይቀድማቸው ከፊት ገጭ ብለዋል፡፡
እሳቸው ሁሌም ቢሆን ቤተ ክርስቲያን ለማስቀደስ ማንም የማይቀድማቸው ጠንካራ የ80 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡ ከእማሆይ ቀጥሎ ጡረተኛው ሃምሳ አለቃ አሉ፡፡ ሃምሳ አለቃ መቼ እንደሚተኙ ግራ ይገባኛል፡፡ ሁሌም ንቁ ናቸው፡፡ መደዳውን አባቴና እናቴ ከእኩያ ጎረቤቶቻቸው ጋር አሉ፡፡ የሚገርም ነገር ከእኔ የዕድሜ እኩዮች የሚታዩት ሦስት ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ተኝተዋል ማለት ነው፡፡
የምርጫ አስፈጻሚዎችና የፓርቲ ታዛቢዎች እየተንጠባጠቡ ስለመጡ ድምፅ መስጠት የተጀመረው አንድ ሰዓት ሊሆን ሲል ነው፡፡ የእኔ ቢጤው ችኩል ጎረምሳ ሲያጉረመርም አዛውንቶቹ እርስ በርሳቸው እየተጨዋወቱ በትዕግሥት ተራቸውን እየተጠባበቁ ነው፡፡ የድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ ጎታታ ስለነበር ሠልፉ ንቅንቅ ሳይል ፀሐይ ወጥታ አናታችንን መውቀር ጀምራለች፡፡ ቀደም ያሉት ዳስ ቢጤ ዘንድ ደርሰው የዕድር ወንበር ላይ ወገባቸውን አሳርፈው ከንዳዱ ተከልለዋል፡፡
ሰዓቱ እየገፋ ሲሄድ ጎታታው ሠልፍም በመጠኑ ቀስቀስ እያለ ነበር፡፡ ከረፈደ ቁርሳቸውን በልተው የመጡ የእኔ እኩዮች ሰላሳ ደቂቃ ያህል ከመቆማቸው ሲያጉረመርሙ ይሰማሉ፡፡ ተጨማሪ ሰላሳ ደቂቃ ሲጨመርማ ጥለው የሄዱም ነበሩ፡፡ አዛውንቶቹ ግን በትዕግሥት ወረፋቸውን ይዘው መርጠው ሲሄዱ ድምፃቸውም አልተሰማም፡፡ እኔ ሁሌም ግርም የሚለኝ ከወጣቶች ይልቅ የአዛውንቶች ፅናት ነው፡፡ ያሰቡትን ካላሰኩ በስተቀር ንቅንቅ የሚባል ነገር የለም፡፡ ቀበሌ፣ ዕድር፣ ሆስፒታል፣ ወይም ሌላ ሥፍራ ቢሄዱ መሰልቸት ዓይታይባቸውም፡፡ እኔ ደግሞ በዚህ ባርያቸው እቀናባቸዋለሁ፡፡
እማሆይና ሃምሳ አለቃ ድምፅ ሰጥተው ተከታትለው ብቅ አሉ፡፡ ከኋላ በኩል የመሰላቸትና የማጉረምረም ድምፅ የሰሙት ሃምሳ አለቃ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣ ‹‹የምን ማጉረምረም ነው… ዛሬ እኮ ሥራ የለም ስለተባለ በትዕግሥት ጠብቃችሁ ድምፃችሁን ስጡ እንጂ… ፓርቲዎቹ ስንትና ስንት ድካም አሳልፈው አይደለም እንዴ ምረጡን ብለው የሚፎካከሩት… እኔ ተናግሬያለሁ ለማይረባ ከንቱ ነገር ከምታባክኑት ጊዜ ላይ አገራዊ ግዳጃችሁን ተወጡ…›› ብለው በቁጣ ሲናገሩ ዝምታ ሰፈነ፡፡
እማሆይ ሳቅ እያሉ፣ ‹‹ሃምሳ አለቃ የምርጫ ቅስቀሳ ነው ተብለው እንዳይታሰሩ እንሂድበት…›› ሲሏቸው ፀሐይ ያንገበገው ምድረ ጎረምሳ አካባቢውን በሳቅ አደበላለቀው፡፡ እማሆይና ሃምሳ አለቃ ተያይዘው ሲሄዱ ጎልማሶቹና አዛውንቶቹ የወጣቶቹን ችኩልነት ሲተቹ፣ ወጣቶቹ ደግሞ በራሳቸው ላይ በተሰነዘረው ቁጣና ተግሳፅ ሲሳቁ እኔም ወጉ ደርሶኝ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፄን ሰጥቼ ወደ ቤቴ ሲረፋፍድ ተመለስኩ፡፡ ቴሌቪዥን ከፍቼ የተለያዩ ቻይናሎችን ስቀያይር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አዛውንቶቹን የቀደማቸው የለም፡፡ ይገርማል፡፡
ቤት ሆኜ በስልክ ከወዳጆቼ ጋር ስለምርጫው ስንነጋገር በዚህ ምርጫ የአዛውንቶች ተሳትፎ ርዕሳችን ነበር፡፡ አንደኛው እነሱ አካባቢ ገና ከምርጫው በፊት በነበሩት ቀናት ውይይቱ፣ ምርጫው በሰላም ተጠናቆ አገር እንዲረጋጋና የወትሮው ሕይወት እንዲቀጥል አካባቢን በሚገባ መቃኘት ላይ እንደነበር ሲነግረኝ ገረመኝ፡፡ ‹‹ለዚህም ሲባል ጎህ ሳይቀድ ወደ ምርጫ ጣቢያ ሄዶ ድምፅ መስጠት፣ ከዚያም ሌባ ወይም ተንኮለኛ ችግር እንዳይፈጥር ሠፈርን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ሲነጋገሩ ስሰማ አስተዋይነታቸው የሚደንቅ ነበር…›› እያለ ነገረኝ፡፡
እርግጥ ነው እኛም አካባቢ በምርጫ ቅስቀሳው ሰሞን ፖስተሮች እንዳይቀደዱና ምርጫውን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ችግሮች እንዳይከሰቱ ወጣቶችን ሲያሳስቡ የነበሩት አዛውንቶቻችን ነበሩ፡፡ በምርጫው ዕለትም ከፊት ረድፍ ተሠልፈው የሚፈልጉትን የመረጡት እነሱ ናቸው፡፡ ለአገራቸው የሚያስቡና የሚጨነቁ ብቻ ሳይሆኑ በፀሎት ጭምር የሚተጉት እነሱ ለመሆናቸው እኔም አረጋግጣለሁ፡፡ እናቴም ሆነች አባቴ በዘወትር ፀሎታቸው አገራቸው አትረሳም፡፡ እማሆይም ሆኑ ሃምሳ አለቃ ለአገራቸው እንደሚፀልዩ ሠፈሩ ጭምር ያውቃል፡፡
በምርጫው ማግሥት ወደ ሥራ ለመሄድ መኪናዬን ከጊቢ ሳወጣ ከሃምሳ አለቃ ጋር ተገናኘን፡፡ ይህንን አጋጣሚ አላባክንም ብዬ ከመኪና ወርጄ ሰላምታ አቀረብኩላቸው፡፡ ለሰላምታዬ የሞቀ ምላሽ ከሰጡኝ በኋላ አልፈውኝ ሊሄዱ ሲሉ፣ ‹‹ሃምሳ አለቃ ትናንት ምርጫ ጣቢያ ሲቆጡ እኮ ደንግጬ ነበር…›› ብዬ የወሬ አጀንዳ ከፈትኩላቸው፡፡ ለግማሽ ደቂቃ ያህል ትኩር ብለው በቦዙ ዓይኖቻቸው ሲያዩኝ ቆይተው ሳቅ አሉ፡፡ መጀመሪያ አስተያየታቸው አስደንግጦኝ ነበር፡፡
‹‹ምን ነበር ያስደነገጠህ?›› አሉኝ ኮስተር ብለው፡፡ ‹‹ያው እማሆይ እንዳሉት የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ…›› ከማለቴ፣ ‹‹ኧረ ተወኝ እባክህ… በመብታችሁ አታላግጡ ማለትና እከሌን ምረጡ ማለት ምን አገናኘው ብለህ ነው… እማሆይ ያው ሲቀልዱ ነው… እናንተ ግን የምር አታደርጉትም እንጂ ካደረጋችሁት ታስቁኛላችሁ… ወጣቱ ምናለበት ሐሞተ ኮስታራ ቢሆንና የሚበጀውን ቢያውቅ የሚለው ነው የሚያሳስበኝ እንጂ የቃላት ስንጠቃ ፖለቲካ አይደለም… ለማንኛውም መልካሙን ሁሉ እመኝልሃለሁ…›› ብለውኝ ተሰነባበትን፡፡ ማታ አባቴን ከሃምሳ አለቃ ጋር ስለነበረኝ ቆይታ ስነግረው፣ ‹‹እሱ እኮ ቅኔ ማለት ነው… ሰምና ወርቁን መለየት የአንተ ፋንታ ነው…›› ሲለኝ፣ ‹‹ይህ ሕዝብ ቅኔ ነው›› የሚባለው አባባል ትርጉሙ አልገባ ብሎኝ ይኸው አለሁ፡፡ እውነትም ቅኔ፡፡
(ዘውድነህ ይልማ፣ ከቀበና)