በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ውስጥ ሲሠሩ ቆይተው፣ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን የያዘ ‹‹የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኅብረት›› የተባለና በአሁኑ ጊዜ ከ12 በላይ ድርጅቶች የተካተቱበት ድርጅት ዋና ዳይሬክተርና የሕግ ባለሙያ ሆነው እየሠሩ የሚገኙት አቶ መስዑድ ገበየሁ፣ የቆይታ ዓምድ እንግዳ ናቸው፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን ስድስተኛው አገራዊ ምርጫን በሚመለከት ዜጎችን በማስተማርና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎችን ስለመከናወናቸው አጠቃላይ የምርጫ ሒደቱንና ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት ከታምሩ ጽጌ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡- ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከተወሰኑ አካባቢዎች በስተቀር ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡ በአጠቃላይ የምርጫ ሒደቱ (የድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ) ላይ ያለዎትን አስተያየት ቢገልጹልን?
አቶ መስዑድ፡- ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሁላችንም እንደምናስታውሰው መደረግ የነበረበት ባለፈው ዓመት 2012 ዓ.ም. ነበር፡፡ ነገር ግን የምርጫው ጊዜ እየተቃረበ ባለበት ወቅት፣ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነው ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) በኢትዮጵያም በመከሰቱ ሊራዘም ችሏል፡፡ በተለይ የፖለቲካ ሪፎርም በመምጣቱና የፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋት፣ የመገናኛ ብዙኃን በነፃነት እንዲሠሩ መፈቀዱ፣ የሲቪክ ማኅበራት ሕግ መለወጡና ሌሎችም መሻሻሎች እየታዩ ስለነበር፣ ሕዝብ የተነቃቃበትና የምርጫውን ጊዜ በጉጉት ሲጠብቅ በተፈጠረው ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሟል፡፡ ምርጫው መራዘሙ ደግሞ ብዙ ውጥረቶችና ችግሮች እንዲያጋጥሙ ምክንያት ሆኗል፡፡ ያ ሁሉ አልፎ ምርጫው ባሳለፍነው ሳምንት መጀመርያ ላይ ተደርጎ አልፏል፡፡ የተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ ካልተደረገባቸው በተለይ ሶማሌና ሐረሪ ክልሎች፣ እንዲሁም የተወሰኑ የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች በስተቀር በመልካም ሁኔታ የመጀመርያው ደረጃ ተጠናቋል፡፡ እንደ አጠቃላይ ምርጫውን በሚመለከት እንደ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት መራጮችን ስለምርጫና ጥቅሙ በማስተማር፣ በምርጫው ወቅት ደግሞ ክትትል በማድረግ፣ ሰብዓዊ መብቶችን ከማስጠበቅ አንፃር የምርጫ ሒደቱ አካታች ስለመሆኑ ማለትም (ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ተፈናቃዮችን) ያካተተ ስለመሆኑ፣ ፓርቲዎች በፕሮግራማቸው ላይ ስለማካተታቸው፣ በምርጫ ክርክሮች ስለመሳተፋቸውና እነዚህን ወገኖች በሚመለከት ይቀርቡ የነበሩ ክርክሮች ምን ያህል አካታች እንደነበሩ በትኩረት ስንከታተል ቆይተናል፡፡
የምርጫ አንዱ መመዘኛ አካታችነትና አሳታፊነት ነው፡፡ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑትን የመደራጀት መብት በማክበር ምርጫው ምን ያህል አሳታፊ እንደነበርም ተመልክተናል፡፡ በዚህም ከመቶ በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ስለነበር፣ ምንም እንኳን መብዛታቸው የሚመከር ባይሆንም፣ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ባሉባት ኢትዮጵያ አብዛኛው በፖለቲካው የመወከል ዕድል አግኝቷል ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው በለውጡ ከታዩ መልካም ነገሮች መገናኛ ብዙኃን ያለ ገደብ በነፃነት እንዲሠሩ መደረጉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከመደበው የሰዓት ድልድል ሌላ፣ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶችም በሴቶች፣ በአካል ጉዳተኞችና በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብት ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት አስችሏቸዋል፡፡ ይኼንን ካለፉት አምስት ምርጫዎች አንፃር ስንመለከተው እጅግ በጣም የተሻለ ነበር፡፡ ይህም ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ማኅበራቱ በማስተማር፣ ምርጫውን በመታዘብና በቀጣይ በድኅረ ምርጫውም ሒደቶችን ለመከታተል ሰፊ ሥራ ሠርተዋል፣ እየሠሩም ናቸው፡፡ ያሉት ውስንነቶች እንዳሉ ሆነው በለውጡ የተገኙ ዕድሎች ሊበረታቱ የሚገባቸው ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በሪፎርሙ ከተከናወኑ ሥራዎች አንዱ የሲቪል ማኅበረሰብና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅን መቀየር ነው፡፡ በአዋጁ መቀየር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በብዛት መደራጀትና መንቀሳቀስ ከመቻላቸው፣ በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ ማኅበረሰቡን ከማስተማርና ግንዛቤ እንዲኖረው ከማድረግ አንፃር የሚፈለግባቸውን ያህል ሠርተዋል ማለት ይቻላል?
አቶ መስዑድ፡- የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በምርጫው ዙሪያ ያደረጉት እንቅስቃሴ በቂ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ለማወቅ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የማኅበራቱ አስተዋጽኦ ምን ያህል እንደነበር ለማወቅ ይረዳል፡፡ ለቀጣይም የማኅበራቱ እንቅስቃሴ የሚቀጥል በመሆኑ ያላቸውን ጥንካሬና ድክመትም መታወቅ አለበት፡፡ ሕጉ ሲሻሻል መንግሥት በዴሞክራሲ፣ በሰብዓዊ መብትና በሰላም ጉዳይ ላይ መሻሻሎች እንዲመጡ ቃል መግባቱ ይታወሳል፡፡ ብዙዎቹም ድርጅቶች በእነዚህ መብቶች ላይ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ልምድና አቅም እንዳላቸውና እንደሌላቸው መታወቅ አለበት፡፡ ሌላው ሲቪል ማኅበራቱ በመላው የአገሪቱ ክፍሎች እንደ ልባቸው ተዘዋውረው እንዳይሠሩ ያደረጓቸው በርካታ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ እነዚህና የመሳሰሉትን ሁሉ ለማወቅ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ምርጫ ሒደት በመሆኑ ከዚህ በፊት ከነበረውና አሁን ካለው አንፃር ሲነፃፀር ማኅበራቱ ብዙ ነገር ሠርተዋል፡፡ መመሥገን ያለባቸው አሉ፡፡ በአገሪቱ የዴሞክራሲ መሠረት ለመጣል የሚያስችል ጥሩ ጅማሮ በመሆኑ ማኅበራቱ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሰው መሥራት ባይችሉም እንኳን፣ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ትምህርት ሰጪ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት አድርገዋል፣ እያደረጉም ነው፡፡ በሌላ በኩል በተገኘው አጋጣሚ ሕዝቡ በምርጫ እንዲሳተፍ በቅድሚያ ምን ማድረግ እንደሚገባው ሁሉ ለማስተማር ሞክረዋል፡፡ በአጠቃላይ ስለምርጫ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት አድርገዋል፡፡ የምርጫ ሒደት ጤናማ ካልሆነ ውጤቱም ጤናማ ስለማይሆን፣ ኅብረተሰቡ በዚህ ዙሪያ ምን ማድረግ እንዳለበት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት አድርገዋል፡፡ ምንም እንኳን ጥናት ቢያስፈልገውም እንደ አጠቃላይ ስናየው ግን ከነበረውና ከመጣንበት ሁኔታ አንፃር ሲታይ፣ ጥሩ ሥራ የተሠራበትና ሊበረታታ የሚገባው እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ግን በቂ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ እስከ ምሽት 3፡00 ሰዓት ድረስ በመሠለፍ ድምፅ ሰጥቷል፡፡ ይኼ የሆነው የሲቪል ማኅበራት በፈጠሩት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና መነቃቃት ነው ብለው ያስባሉ?
አቶ መስዑድ፡- እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነገር ብዙ ባለድርሻ አካላት መኖራቸውን ነው፡፡ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኃንና የሲቪል ማኅበራት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በመሆኑም ለሕዝቡ መነቃቃትና ለታየው እንቅስቃሴ በርካቶች አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም፣ የሲቪል ማኅበራትም የራሳቸው ድርሻ አላቸው ማለት ይቻላል፡፡ የጎላ ባይሆንም ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡ ሁላችንም መረዳት ያለብን ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም የነቃ ሕዝብ ነው፡፡ ሁኔታዎችን የሚገመግመውና የሚያሳልፈው በዝምታ ነው፡፡ ታጋሽና ቻይ ሕዝብ በመሆኑ አያውቅም ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ የሲቪል ማኅበራት ግንዛቤ በመፍጠር ላይ ያንን ያህል የጎላ ሥራ ሠርተዋል ማለት ባይቻልም፣ ሕዝቡ ባለው የፖለቲካ ዕውቀትና ግንዛቤ ላይ የቻሉትን ያህል አስተዋጽኦ አድርገዋል ማለት ይቻላል፡፡ ሌሎቹ ባለድርሻ አካላት ያደረጉት አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ለመምረጡ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ብዙዎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተደራጁት ዘርን መሠረት አድርገው ቢሆንም፣ በተመሳሳይ ብሔር ውስጥ የተለያየ ስያሜ ይዘው በመደራጀት ሕዝቡን ግራ ከማጋባት ባለፈ፣ በምርጫ ወቅት ድምፁ እንዲበታተን በማድረጋቸው በምርጫ ውድድር አሸናፊ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
አቶ መስዑድ፡- ይኼ እውነተኛና ትክክለኛ አስተያየት ነው፡፡ ሰዎች ብዙ ዓይነት ማንነት አላቸው፡፡ እነዚህን ማንነቶችን ባከበረ ሁኔታ አንድ ሆኖ መደራጀትና ትኩረት በሚደረግባቸው ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ሲገባ፣ የተበታተነ አደረጃጀትን በመከተል ዋጋ እየከፈሉ ነው፡፡ የብሔር ፖለቲካ በየትኛውም አገር ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ኢትዮጵያም ውስጥ እየሆነ ያለው ይኼው ነው፡፡ ሕዝብ የሚፈልገውንና የሚያስፈልገውን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብን ለማገልገል መነሳት ወይም መደራጀት በሚያስፈልገው ነገር ላይ እንጂ፣ በዘርና በማንነቱ ላይ ብቻ ማተኮር ተገቢ አይደለም፡፡ ያ ካልሆነ የሕዝብ ድምፅ እየተበታተነ የሚፈልገውን እንዳያገኝ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም የምርጫ ሥርዓታችን ጭምር መፈተሽ አለበት፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው የምርጫ ሥርዓት የተሻለ ድምፅ ያገኘ ፓርቲ መንግሥት የሚመሠርትበት ሥርዓት ነው፡፡ ይኼ ማለት ከአሸናፊ ፓርቲ በታች ድምፅ ያገኘ ፓርቲ ድምፅ የሰጠውን የማኅበረሰብ ክፍል መወከል ቢኖርበትም ሥርዓቱ አይፈቅድም፡፡ ይኼ ደግሞ መንግሥት ከመሠረተው ፓርቲ ጋር ያለው ግንኙነት መልካም አይሆንም፡፡ ለሕዝብ መሆን፣ ለአገር ዕድገት፣ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው ሰላም ለማምጣት እንቅፋት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ይህንን ለማስተካከል በየምርጫ ሥርዓቱ መስተካከል አለበት፡፡ ድምፅ የሰጠ ማኅበረሰብ በሰጠው ድምፅ መሠረት መወከል መቻል አለበት፡፡ እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት በድኅረ ምርጫ ከምንሠራቸው ሥራዎች አንዱ በምርጫ ሥርዓት ዙሪያ ይሆናል፡፡ ዜጎች በመረጡት ሰው መወከል አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች አደረጃጀትና የፖለቲካ ፕሮግራማቸው ተፈትሾ ቁጥራቸውን ከማብዛት ይልቅ፣ ሰብሰብ ብለው የፖለቲካ ሥራቸውን እንዲያራምዱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የሠለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ በሲቪል ማኅበራት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በሕዝቡ ተሳትፎ መስተካከል ያለበት ነው፡፡ ይህ ከሆነ የተበታተኑ ድምፆችን ወደ አንድ በማምጣት የሚፈለገው ደረጃ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ አሁን አጀማመሩ ጥሩ ባይመስልም በሒደት እየተስተካከለ እንደሚዲሄድና የተሻለ ነገር እንደሚገኝ ተስፋ ያለው ነገር ይታያል፡፡
ሪፖርተር፡- ጽንፍ በያዘ የፖለቲካ አደረጃጀት በአንድነቷና በባህሏ የምትታወቀውን ኢትዮጵያ የመበታተንና ሕዝቦቿንም አደጋ ውስጥ የመጣል ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በቅድሚያ የሚያስፈልጋት ምርጫ ሳይሆን አገራዊ ስምምነት ነው፡፡ ከምርጫ በኋላም ቢሆን መንግሥት የሚመሠርት ፓርቲ ሌሎቹን ፓርቲዎች በመያዝ ጥምር መንግሥት መመሥረትና አገራዊ ስምምነት መፍጠር ይኖርበታል የሚሉ ምሁራን አሉ፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
አቶ መስዑድ፡- ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር ነው፡፡ ገበያ ላይ ቀርበው ሕዝቡ የሚፈልገውን በካርዱ የሚገዛበት ሒደት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የፖለቲካ ሥልጣን የሚያዘው በምርጫ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡ እኛም እንደ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ወይም ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት የምንመክረው ሥልጣን መያዝ ያለበት በምርጫ እንዲሆን ነው፡፡ በምርጫ ሒደት አብላጫ ድምፅ አግኝቶ መንግሥት የሚመሠርት ፓርቲ አገር ይመራል፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት የሚፈቅደውም አብላጫ ድምፅ ያገኘ መንግሥት እንዲመሠርት በመሆኑ፣ አሸናፊ የሆነ ፓርቲ ጥምር መንግሥት እንዲመሠርት አይገደድም፡፡ ምርጫ የዴሞክራሲ መገለጫ በመሆኑ፣ አሸናፊው ፓርቲ ሁሉንም አካታች በሆነ ሁኔታ የተጀመሩ የዕርቀ ሰላም እንቅስቃሴዎች፣ የድንበርና የማንነት ኮሚሽንና ሌሎችንም ተቋማት በማጠናከር ችግሮችን በጋራ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ምርጫው ቅቡልነት ያለው መንግሥት እንዲመሠረት ስለሚያደርግ ጠንካራና በራሱ እየወሰነ የሚሄድ መንግሥት ያደርገዋል፡፡ ይህ ማለት አሸናፊነትን ብቻ ለማንፀባረቅ ሳይሆን፣ በምርጫ ውድድር የተሸነፉ የፖለቲካ ፓርቲ ተወዳዳሪዎችንም (የፓርቲ መሪዎችን) በተለያየ ሁኔታ በማካተት ያላቸውን ዕውቀት በመጠቀም የሕዝብ አገልጋይ እንዲሆኑ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ማለትም በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊና በሌሎች ዘርፎች በማካተት ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ የተሻለ ተወዳዳሪ እንድትሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የሌሎች አገሮችን ጫና ብቃት ባላቸው ኢትዮጵያውያን መመከት ስለሚያስፈልግ፣ የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን ትተን ሕዝብንና አገር የሚጠቅም ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አሸናፊውም ቢሆን ተሸናፊዎቹም የየራሳቸው ችሎታና ብቃት ስለሚኖራቸው ተቀራርቦ መሥራቱ ለሕዝብና ለአገር ይጠቅማል እንጂ ጉዳት የለውም፡፡
በመሆኑም ጥምር መንግሥት መሥርቶ አገራዊ ስምምነት መፍጠር አስፈላጊ ቢሆንም፣ ይህ ግን የአሸናፊውን ፓርቲ ይሁንታ የሚፈልግ እንጂ እንደ ግዳጅ ሊወሰድ ስለማይቻል፣ አሸናፊው ፓርቲ ግን ከዚያ ባልተናነሰ ሁኔታ በመሥራት የሚያስፈልጉትን የሰላምና የአንድነት ሥራዎችን ማከናወን ይችላል፡፡ ትልቁ ነገር ሥርዓት ነው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ የፍትሕ ሥርዓት፣ የመልካም አስተዳደር ሥርዓትና ሌሎች ሥርዓቶችን በተገቢው ሁኔታ በመዘርጋት የተፈለገውን ውጤት ማግኘት ይቻላል፡፡ ተቋማት በፖለቲካ ቅኝት ወይም ተቀባይነት ሳይሆን፣ መመራት ያለባቸው በዕውቀት ከሆነ የሚፈልገውን ነገር ማግኘት ይቻላል፡፡ ከማንኛውም ነገር በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የምሁራን ድርድር ነው፡፡ ምሁራን መስማማት አለባቸው፡፡ ታሪክ በአግባቡ መጻፍ አለበት፡፡ የማይሆኑ አሳሳች ትርክቶች መቆም አለባቸው፡፡ ሌላው በዲፕሎማሲ ላይ መሠራት አለበት፡፡ የአገር ሉዓላዊነት መከበር አለበት፡፡ ይህንን ለዓለም ሕዝብና መንግሥታት መንገር የሚችሉ ኤክስፐርቶች ያስፈልጉናል፡፡ የውጭ ፖሊሲያችን ሪፎርም መደረግ አለበት፡፡ አገሮች ከአገሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በደንብ የሚያውቅና የሚረዳ ባለሙያ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምደባ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እስከ ድጋፍ ቅስቀሳ ድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን ሲያስተናግድ ቆይቶ፣ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምፅ በመስጠት ተጠናቋል፡፡ ከነበረው ውጣ ውረድና ውጥረት አንፃር የድምፅ አሰጣጥ ሐዲቱ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ እርስዎ ሒደቱን እንዴት ይገመግሙታል?
አቶ መስዑድ፡- እውነት ነው፡፡ በዚህ ምርጫ ብዙ ሰው ሥጋት ነበረበት፡፡ ኢንተርኔት እንዲዘጋና ማኅበራዊ ሚዲያዎች እንዲዘጉ የሚጠይቁ ነበሩ፡፡ ያ የሆነው ደግሞ እንዲፈሩ ያደረጓቸው ብዙ ምክንያቶች ስለነበሩ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም፣ የተፈራው ምርጫ ያለ ምንም ችግር ተካሂዷል፡፡ በዚህ መንግሥት መመሥገን አለበት፡፡ ምክንያቱም ኃላፊነቱን በአግባቡ ተወጥቷል፡፡ የነበረው ፍርኃት አልፎ በውድድሩ የተሸነፉ አንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች መሸነፋቸውን በማብሰር፣ ለቀጣይ ውድድር ራሳቸውን አስተካክለውና ተዘጋጅተው እንደሚቀርቡ እየገለጹ መሆኑ እጅግ በጣም ትልቅና መለመድ ያለበት ነው፡፡ ይህ የሠለጠነ አካሄድ ነው፡፡ ያሸነፈን ‹‹እንኳን ደስ አለህ›› ብሎ መሸነፍን መቀበል፣ ካሸነፈው የበለጠ ትልቅ አሸናፊነት ነው፡፡ ያሸነፈ ፓርቲ በማሸነፉ የሚደሰትበት የመጨረሻ ግብ ሳይሆን፣ ትልቅ ኃላፊነት የሚወስድበትና ግዴታ የሚገባበትም ነው፡፡ ኃላፊነትን መሸከምና የገባውን ቃል የሚፈጽምበት የቃል ኪዳን መፈጸሚያ መንገድ ነው፡፡ የአሸናፊነትና የተሸናፊነት መሆን የለበትም፡፡
ሪፖርተር፡- በምርጫ ውድድሩ የተሸነፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በማኅበራዊ ድረ ገጽ መሸነፋቸውን በመግለጽ ለአሸናፊው ፓርቲ አባላት፣ ‹እንኳን ደስ አላችሁ› እያሉ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ሊበረታታ የሚገባውና አገሪቱንም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ምሥረታ መሠረት የሚጥል ስለመሆኑ አስተያየታቸውንም የሚሰጡ አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
አቶ መስዑድ፡- ይኼ የፖለቲካ ውድድር ነው፡፡ ሐሳብን ለሕዝብ መስጠት ነው፡፡ ሕዝብ የወደደውን ያደርጋል፡፡ ሕዝብ እኔን ካልመረጠኝ፣ ተፎካካሪዬ የተሻለ ሐሳብ አለው ማለት ነው፡፡ ‹‹እኔ ለምን አልተመረጥኩም›› ሳይሆን፣ ‹‹የእኔ ሐሳብ ተቀባይነት ያጣው ለምንድነው?›› የሚለውን ቆም ብሎ ማየትና መገምገም ያስፈልጋል፡፡ በተወዳደሩባቸው አካባቢዎች በመሄድ ‹‹ምን ማድረግ ነበረብን? የእኛ ችግር ምን ነበር?›› ብሎ በመጠየቅ፣ ለቀጣይ በደንብ ተዘጋጅቶ መቅረብ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ተወዳድሮ መሸነፍ ድምፅ አላገኙም ማለት አይደለም፡፡ በዚህም የብሽሽቅ ፖለቲካ ውስጥ መግባትም የለብንም፡፡የመረጠውን ሕዝብ ማክበር አለብን፡፡ የተሻለ ሐሳብ ያላቸው ተፎካካሪዎች ‹‹ተሸንፈናል›› ብሎ መቀመጥ ሳይሆን፣ አሸናፊውን በመቅረብ የሙያ ዕገዛ ለማድረግ መጠየቅና ባላቸው ዕውቀት ልክ መረዳዳት ያስፈልጋል፡፡ አሸናፊ ፓርቲም በሩን ብቻ ሳይሆን ልቡንም ከፍቶ መቀበልም ለአገርና ለሕዝብ ዕድገት በመተባበር መሥራት ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- በምርጫ የሚያሸንፈው ተፎካካሪ ፓርቲ መንግሥት መሥርቶ አገር ከመምራት ባለፈ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?
አቶ መስዑድ፡- ሌሎቹም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫው አሸንፈው መንግሥት በመመሥረት ለመረጣቸው ሕዝብ ቃል የገቡትን ለመፈጸምና አገር ለመምራት ነው፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የራሳቸው ሙያና ቤተሰብ ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን አብላጫ ድምፅ ባለማግኘታቸው አሸናፊ መሆን አልቻሉም፡፡ አሸናፊ የሚሆነውም ፓርቲ አመራሮች ይዘው የቀረቡት ሐሳብ አሸናፊ ሆኖ አገር መምራት የሚያስችላቸውን ዕድል ቢጎናፀፉም፣ ከተፎካካሪያቸው የበለጡት ባገኙት አብጫ ድምፅ እንጂ፣ ሁሉም ሕዝብ ስለመረጣቸው አይደለም፡፡ 46 ተፎካካሪ ፓርቲዎች የየራሳቸው ጠንካራ የሆነ ደጋፊና መራጭ ሕዝብ አላቸው፡፡ ይህ የሚያሳየው ሁሉም ፓርቲዎች የራሳቸው የሆነና ይብዛም ይነስም በመረጣቸው ሰው ልክ ተቀባይነትን ያገኘ ሐሳብ ይዘው ቀርበዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን መራጭ ሕዝቦች ማክበር ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የተሸነፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ መሪዎች ለአሸናፊው ዕውቅና መስጠትና ‹እንኳን ደስ አለህ› ማለት አለባቸው፡፡ አሸናፊውም ከብሽሽቅ ፖለቲካ ወጥቶ ለተሸናፊዎቹ ዕውቅና መስጠት፣ ‹እናንተ ተሸነፋችሁ ማለት የመረጣችሁ ሕዝብ የለም ማለት አይደለም፡፡ ሐሳባችሁን የተቀበለና የመረጣችሁ ሕዝብ ስላለ ተቀራርበን በመደጋገፍ አብረን እንሠራለን›› ብሎ ለመረጣቸው ሕዝብና ለፖለቲከኞችም ክብር መስጠት ያስፈልጋል፡፡
የሁለቱም ማለትም የአሸናፊውም ሆነ የተሸናፊው የፖለቲካ አመራሮች ዓላማና ግብ የመረጣቸውን ሕዝብ ከማገልገል ባለፈ ኢትዮጵያን ማልማት፣ ማሳደግና ሉዓላዊነቷን ጠብቆ ማኖር ስለሆነ አንዱ ለሌላው ክብርና ዕውቅና መስጠት የኢትዮጵያን አንድነት ጠብቆ ማስቀጠል ነው፡፡ በጋራ ተባብሮ አገርን ማስቀጠልና ሕዝብን ማገልገል በሁሉም ነገር አሸናፊነት ነው፡፡ ይህ ሥራ የፓርቲ አመራሮች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላትም ጭምር ነው፡፡ እንደ መንግሥትም ሆነ እንደ ሕዝብ ተቀራርቦ መሥራትና አገርን ማልማት ተቀዳሚው ተግባር በመሆኑ፣ ከሁሉም በላይ በፍቅር አንድ ሆኖ መሥራት ወሳኝ ነው፡፡ ሁሉም በአገር ልማትና ዕድገት የየራሱን ሚና እንዲጫወት ብዙ መሥራት ያለበት አሸናፊና መንግሥት የመሠረተው የፖለቲካ ፓርቲ በመሆኑ፣ ከወዲሁ አስቦና ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መግባት ይኖርበታል፡፡ በዚህ ምርጫ የተሸነፉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ለምን እንደተሸነፉ ራሳቸውን በመገምገም፣ ስህተታቸውን በማረምና በማሻሻል ለቀጣይ ምርጫ ብቁ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቅረብ እየተዘጋጁ፣ እንዲሁም ከመንግሥት ጋር በመሥራት የተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ አምስት ዓመታት ለአሸናፊው ኃላፊነትን መሸከምና በብቃት ለመወጣት አካታች የሆነ ሥራ ጠንክሮ መሥራት ሲሆን፣ ለተሸናፊዎች ደግሞ ስህተትን በማረምና ብቁ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ ብዙ የቤት ሥራዎችን የመጨረሻ ጊዜ ነው፡፡ ይህንን በድል ለመወጣት ሁሉም ተባብሮና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ውጤታማ ለመሆን መጣር እንጂ፣ የትም ለማያደርስና ውጤቱም ከንቱ ለሆነ የብሽሽቅ ፖለቲካ ጊዜ መስጠት ተገቢ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በአመራርነትና በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ብቃት ያላቸው ምሁራን፣ በሳል የፖለቲካ ዕውቀት ያላቸው፣ በሰብዕናቸውም የተመሠገኑና የተከበሩ ተወዳዳሪዎቸ ያለ ምንም ጥርጣሬ ‹‹አሸናፊዎች ናቸው›› ተብሎ ቅድመ ግምት የተሰጣቸው ቢሆንም፣ ውድድሩን ሳያሸንፉ ይቀራሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ‹‹የኢትዮጵያን ሕዝብ ማወቅ አይቻልም፣ ቅኔ የሆነ ሕዝብ ነው›› የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በአባባሉ እርስዎ ይስማማሉ?
አቶ መስዑድ፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ አዋቂ ሕዝብ ነው፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ሚዲያዎች በደንብ አላስተማሩም፣ ግንዛቤ አላስጨበጡምና ሌሎች ነገሮችም ሲባሉ እንሰማለን፡፡ ነገር ግን በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ድምፁን ለመስጠት የወጣውን ሕዝብ ዓይተናል፡፡ ፍፁም በሆነ ትዕግሥት እስከ ምሽቱ 3፡00 ሰዓትና አድሮም ድምፁን ሰጥቷል፡፡ ይህ የሆነው እንደተባለው ቅስቀሳ ተደርጎለት ወይም በተሰጠው ትምህርት ሳይሆን፣ ሕዝቡ አዋቂና በራሱ መንገድ የገባው መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ብዙ ችግሮችና በደሎችን ዝም ብሎ ቢያሳልፍም ለዘላቂ ሕይወቱ፣ ለአገሩ አንድነትና ዕድገት ማን እንደሚሻለው ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው፡፡ በመሆኑም የሚጠቅመውን መርጧል፣ ይመርጣልም፡፡ ነገር ግን ካላቸው ዕውቀት፣ የሥራ ልምድ፣ የፖለቲካ ዕውቀትና ሰብዕና አንፃር ቢመረጡ ጥሩ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የፖለቲካ አመራሮች አልተመረጡም ወይም አይመረጡም፡፡ ይህ አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫም ነው፡፡ ሕዝብ ‹‹ይሆነኛል፣ ያስተዳድረኛል፣ የአገርን የሕዝብ ሰላም ሉዓላዊነት ያስጠብቃል›› ብሎ ያመነበትን ይመርጣል፡፡ ሕዝብ አይሳሳትም፡፡ ምንም እንኳን ሳይመረጡ ለቀሩ የፖለቲካ አመራሮች ክብርና ድጋፍ ያለው ቢሆንም፣ ለውድድር ከቀረቡት ውስጥ ለይቶ ከመረጠ የሚሆነውን ያውቃል ማለት ነው፡፡ ሕዝቡ የመረጠው ፓርቲ ግን ለእነዚህ የፖለቲካ አመራሮች ቦታ በመስጠት በአንድም ይሁን በሌላም ሕዝብ እንዲያገለግሉ ማድረግ አለበት እንጂ፣ ሕዝብ እንደተሳሳተ ማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡ ሕዝብ በራሱ የሚያውቅ በመሆኑ ግምቶችን ባለመፈጸሙ ‹‹ቅኔ የሆነ ሕዝብ ነው›› በማለት እንደማይታወቅ አድርጎ የተሳሳተ ትርጉም መስጠት ሳይሆን፣ የሚመራውንና የሚሠራለትን መርምሮ የሚረዳ ‹‹ቅኔ ፈቺ ሕዝብ ነው›› ሊባል ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ ተቋቁሞ፣ በሰው ኃይልም ይሁን በተቋም ደረጃ በተሻለ አደረጃጀት ላይ ያለ ተቋም ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአጭር ጊዜ ውስጥ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማድረግ ሰፊና ትልቅ አቅም የሚጠይቀውን ሥራ በመወጣት፣ እንዲሁም ምንም እንኳን የተለያዩ አሉታዎች ቢኖሩም ገለልተኛነቱን በማስጠበቅ፣ የተጣለበትን ኃላፊነት እንደተወጣና በመወጣት ላይ ያለ ተቋም መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በምርጫው ዕለት በታዩ የተለያዩ ጉድለቶች ደግሞ እየተወቀሰ ነው፡፡ ይህንን ተቋም እርስዎ እንዴት ይገመግሙታል?
አቶ መስዑድ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ሪፎርም ከፈጠራቸው ተቋማት መካከል አንዱና ቀዳሚውም ተቋም ነው ማለት እችላለሁ፡፡ እንደ ተቋም ሁሉም ሕዝብ የሚስማማበትና በግልጽም እየታየ ያለ አሠራርን እየተገበረ ያለ ተቋም በመሆኑ፣ ገለልተኛ ሆኖ እየሠራ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ ምንም እንኳን በአገሪቱ ቀዳሚ አምስት ምርጫዎች የተደረጉ ቢሆንም፣ ተቋማዊ ትውስታ አስቀምጦ ያለፈ ተቋም የለም፡፡ ተቋሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ዓመታት የሚጠይቅን ሥራ አጠናቆ ምርጫው እንዲፈጸም ማድረጉ ብቻ ሊያስመሠግነው ይገባል፡፡ በሥራ ላይ ብዙ ችግሮች ይከሰታሉ፡፡ ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ እንኳን እንደዚህ ያለ ግዙፍ ሥራ ተሠርቶ ቀርቶ በትንሽ ሥራ ግዙፍ ስህተቶች ያጋጥማሉ፡፡ ከወረቀት ኅትመት፣ ከአስፈጻሚዎች ሥልጠናና ተያያዥነት ካላቸው ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮች እንዳሉ ዕሙን ቢሆንም፣ እንደ አጠቃላይ ሲታይ ግን የሚያስመሠግንና የሚታይ ሥራ ሠርቷል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ትልቅም ስኬት ነው፡፡ አንዳንድ ስህተቶችም ከሰዎች ባህሪይ የተነሳ የተከሰቱ መሆናቸውን የእኛ ድርጅቶች ያረጋገጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ‹‹እንከን የለሽ›› ምርጫዎችን ለማድረግ ገና በዙ ዘመናት ቢቀሩንም፣ እንደ ጅምር ግን መሠረት የጣለ አሠራርን ዘርግቶ አልፏል ማለት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በሶማሌና በሐረሪ ክልሎች ሙሉ በሙሉ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ደግሞ አንዳንድ አካባቢዎች የድምፅ መስጫ ቀን ሆኖ ተወስኗል፡፡ ነገር ግን ለክልሎቹ ምክር ቤቶች ካልሆነ በስተቀር በፌዴራል ደረጃ የሚያመጡት ለውጥ እንደሌለና ዋናው የምርጫ ሒደት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. መጠናቀቁን የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
አቶ መስዑድ፡- ምርጫው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በአንድ ቀን መደረግ ነበረበት፡፡ ይህም አሠራር በሕግ ጭምር የተደገፈ ነው፡፡ ነገር ግን ምርጫው እንዳይደረግ የሚያደርጉና ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ሲያጋጥሙ፣ ምርጫው በሌላ ጊዜ እንዲደረግ የሚፈቅድም አሠራር እንደሚኖር በሕግ ጭምር ተቀምጧል፡፡ ምንም እንኳን አሁን በአገራችን ምርጫ ካልተደረጉባቸው አካባቢዎች ተመርጠው ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚገቡ ወይም በፌዴራል የሚወከሉት ተመራጮች ከቁጥር አንፃር ምንም ለውጥ ሊያመጡ አይችሉ ይሆናል፡፡ ዋናውና ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ምርጫ የሕዝቦችን ድምፅ ማስከበሪያ መሣሪያ መሆኑን ነው፡፡ የመራጮች ድምፅ መከበር አለበት፡፡ በመሆኑም ‹‹ለውጥ አያመጣም›› የሚለው ሳይሆን ሕዝብ መምረጡና የሚወክለው ተመራጭ መኖሩ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ አስተሳሰብ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በትግራይ ክልል በተፈጠረው ጦርነትና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ጋር በተያያዘ፣ በተለይ አሜሪካና ሌሎች የአውሮፓ አገሮቸ ሉዓላዊነትን በሚጋፋ ሁኔታ ተፅዕኖ ለማሳደር እየሞከሩ ነው፡፡ ምርጫውንም፣ ‹‹የይስሙላ ምርጫ›› በማለት በየሚዲያዎቻቸው ሳይቀር የማጣጣልና ዕውቅና የመንሳት እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ እርስዎ እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረት ኃላፊነትዎ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
አቶ መስዑድ፡- አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ከፍተኛ ጦርነት እየተካሄደበት ባለው የትግራይ ክልልና በአገሪቱ በበርካታ ቦታዎች በሚከሰቱ ግጭቶች በርካታ ዜጎች ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉና ሕይወታቸውንም እያጡ ነው፡፡ በእርግጥ የመፈናቀሉ ጉዳይ ረዘም ያለ ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡ ችግሮቹ ፖለቲካዊ መሠረት ያላቸውና ዘርን መሠረት ያደረጉ ቢሆኑም፣ መፈታት ያለባቸው በአገሪቱ መንግሥትና ሕዝቦች መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን ይህንን የአገር ውስጥ ጉዳይ ወንዝ ተሻጋሪ በማድረግ አሜሪካና የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ጣልቃ የመግባት ሙከራ የማድረግና ጫና የመፍጠር አዝማሚያ ላይ ናቸው፡፡ በተጨማሪም እነሱ ያሉት ካልሆነ በስተቀር አገሪቱ እንደምትበታተንና የእርስ በርስ ግጭት እንደሚነሳ በሚዲያዎቻቸው ጭምር በመታገዝ ብዙ ነገሮችን በማድረግ ላይ ነበሩ፡፡ በተለይ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫን በማጣጣል በምርጫው ዕለት ወይም በማግሥቱ አገሪቱ መፍቻ ወደ ሌለው ቀውስ ውስጥ እንደምትገባ የራሳቸውን ትንበያና ቅስቀሳ ሲያደርጉም ተስተውለዋል፡፡ ነገር ግን እነሱ ያልታዘቡት ምርጫ ፈፅሞ ምርጫ እንደማይሆን ሲደሰኩሩ ቢቆዩም፣ እውነታው ግን ሌላ ሆኖ አልፏል፡፡ ስለዚህ መንግሥት በዲፕሎማሲው ላይ ጠንክሮ በመሥራት እውነታውን ማስረዳትና ያለውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተሻለ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ያሉትን ችግሮችም በአፋጣኝ መፍታትና አገራዊ አንድነት ላይ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ አገር ውስጥ ያለውን ሁኔታ በብቃት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስረዳት፣ ለኢትዮጵያ የዓይባን ግድብ መሙላት ምን ማለት እንደሆነ በብቃት የሚያስረዳ ብቃት ያለው ባለሙያ ማሰማራትና ከባለ ድርሻ አገሮች ጋርም ስምምነት ላይ ለመድረስ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡