Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ኮቪድ ካሳረፈበት ኪሳራ ለመታደግ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በእጅጉ ከደቆሳቸው የቢዝነስ ዘርፎች ውስጥ ቱሪዝም በቀዳሚነት ሊቀመጥ ይችላል፡፡ የዓለም የቱሪዝም ኢንዱስትሪና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ቢዝነሶች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው እስትንፋሳቸው እስከመቋረጥ የደረሰበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከዓመት በላይ ቱሪዝም ጥቁር ጥላ አጥልቶበት መቆየቱም የዓለምን ኢኮኖሚ በእጅጉ ጎድቷል፡፡ ኢንዱስትሪው የያዛቸው ሠራተኞች ሥራ አልባ የሆኑበትን አሳዛኝ ሁኔታም ፈጥሯል፡፡ 

በዓለማችን የሚገኙ አገሮች አሁን በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከቱሪዝም የሚያገኙት ገቢ አሽቆልቁሎ ኢምንት ሆኗል፡፡ ወረርሽኙ በሰው ልጆች ጤናና ሕይወት ላይ ካደረሰው ጥፋት ባሻገር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውሶችን በማስከተል ያሳረፈውን ተፅዕኖ መልሶ ሕይወት ለመስጠት ብዙ ድካም ይጠይቃልም እየተባለ ነው፡፡

ሁሉም የዓለማችን አገሮች የጉዞ ዕገዳን ተግባራዊ በማድረግ ድንበሮቻቸውን በመዝጋት ‹‹ኧረ ኑና ጎብኙን›› የሚለውን የዘወትር ውትወታቸውን ትተው ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች እንዳይመጡ ጥሪ ማስተላለፋቸው ያገኙ የነበረውን ገቢ አሳጥቷቸዋል፡፡ አገሮች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ አቋርጠው መክረማቸው የዓለምን እንቅስቃሴ ከመግታቱ ባሻገር፣ የአየር ትራንስፖርት በረራን ቀንሷል፡፡ አንዳንድ አየር መንግዶችም ሥራቸውን እንዲያቋርጡ እስከማድረግ ደርሷል፡፡ ኪሳራ አስመዝግበው ያንሰራሩ አየር መንገዶችም አሉ፡፡

እንደ ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት ጥናት በኮቪድ-19 ምክንያት በአውሮፓ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ አገሮች 74 በመቶ ዝግ ሆነዋል፡፡  በአፍሪካ አኅጉር የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ አገሮች ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ 74 በመቶ፣ የአሜሪካ አገሮች 86 በመቶ፣ እሲያና ፓስፊክ አገሮች ደግሞ 66 በመቶ የቱሪዝም እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ቆይቷል፡፡

የቱሪዝም ኢንዱስትሪ መገታት የአየር ትራንስፖርትን ብቻ ሳይሆን ተያያዥ ቢዝነሶችንም ጎድቷል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ሆቴሎች፣ የባህል ምሽት ቤቶች፣ የአስጎብኚ ድርጅቶች፣ የመኪና አከራዮች፣ የዕደ ጥበብ አምራቾች፣ ምግብ ቤቶች፣ የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎችና ሌሎች በዚህ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ ተዋንያን ክፉኛ ተጎድተዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለድህነት እንደተጋለጡና ወረርሽኙ የዘላቂ ልማት ግቦች ከሆኑት አንዱ የድህነት ቅነሳ ላይ የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ እንዳደረገው መረጃው አሳይቷል፡፡ ኢትዮጵያም እንደቀሩት የዓለም አገሮች ኮቪድ-19 ካስከተለው ዘርፈ ብዙ ችግር አላመለጠችም፡፡

ኮቪድ-19 ያሳረፈው በትር ኢትዮጵያንም ነክቷል፡፡ በዓለማችን ወቅታዊ ፈተና ዙሪያ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በኮቪድ-19 ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የንግዱን ማኅበረሰብ በማወያየት ወረርሽኙ በንግድ ሥራቸው ላይ ስላስከተለው ጉዳት እንዲሁም የመፍትሔ ዕርምጃዎች ምን መሆን ይገባቸዋል? በሚል የማይስ (MICE: Meeting, Incentives, Convention and Exhibition) በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ወረርሽኙ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ አስከተለ የተባለው ችግር በሰፊው የተገለጸበት ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ኮቪድ-19 በኤግዚቢሽን፣ በስብሰባዎች ዝግጅትና መሰል ቢዝነሶች ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ጎድቷል፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያስጠናውና በምክክር መድረኩ ላይ የቀረበው ጥናትም ይህንኑ የሚያመላክት ነበር፡፡

 የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣ ቢዝነስ ሲሆን፣ አገሪቱ ከኒውዮርክና ጄኔቭ ቀጥላ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ሦስተኛዋ የዓለም አገር ናት፡፡ በተለይም መዲናይቱ አዲስ አበባ በየዓመቱ በርካታ ቀጣናዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎችን በማስተናገድ የስብሰባ ቱሪዝም እንዲያድግ ከፍተኛ ሚናን በመጫወት ላይ ትገኛለች ብሏል፡፡

በቅርብ የወጡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በኢትዮጵያ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ቁጥር ከ700 በላይ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ለገጽታ ግንባታ የሚያበረክቱት ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፣ ከዓመት በፊት የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ክፉኛ ከጎዳቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱና ዋናው ማይስ መሆኑንም ይጠቅሳል፡፡ በተለይም በኩነት ዝግጅት ላይ የተሰማሩ ኩባያዎች በአማካይ ከአምስት እስከ አሥር ሚሊዮን ብር ወይም በአማካይ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆን ገቢያቸውን ማጣታቸውን ምክር ቤቱ ባስጠናው ጥናት ላይ ተመልክቷል፡፡  

በኔትዎርኪንግና ኩነቶች ላይ ሥራቸውን ያደረጉ ኩባንያዎች ወረርሽኙ ከተከሰተ ወዲህ ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውንም አስመልክቶ፣ አብዛኛዎቹ ኩባንያዎች የቤት ኪራይ፣ የባንክ ብድር መክፈልና ደመወዝ መክፈል ባለመቻላቸው የተነሳ ሠራተኞቻቸውን ለመቀነስ ተገደዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ቀድሞ ወደ ነበሩበት ሁኔታ ለመመለስ በርካታ ወራትን ሊወስድባቸው እንደሚችልም በውይይት መድረኩ ላይ የቀረበው ጥናት ያሳያል፡፡

በወረርሽኙ ምክንያት እንደ አገር ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉና በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችም ሊደግፉ የሚችሉት ከ50 በላይ ትላልቅ ዝግጅቶችና ስብሰባዎች መሰረዛቸውንም ይኸው የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡ እነዚህን ስብሰባና የኢግዚቢሽን ቦታዎች በተቻለ ፍጥነት ወደ ቀድሞ ሥራቸው በመመለስ ማይስ  ኢንዱስትሪና ቢዝነስ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያንሰራራበት አጋጣሚ እንዲፈጠር የዘርፉ ተዋንያን ጠይቀዋል፡፡   

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ከጂአይዜድ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የተገኙ የኤግዚቢሽንና ኤቨንት አዘጋጅ ኩባንያዎች ኮቪድ-19 ስላሳደረባቸው ተፅዕኖ የተለያዩ መረጃዎችን በመጥቀስ የገለጹበት ነበር፡፡ እስካሁን የደረሰው ጉዳት እንዳይቀጥል ከዚህ በኋላ ምን መደረግ አለበት? የሚለው ላይም የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ በተለይ ከዚህ በኋላ በቱሪዝም ውስጥ ያለውን የእሴት ሰንሰለት የማስተሳሰር አስፈላጊነት፣ የኤቨንት ማኔጅመንትን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሰጥ ማድረግና በዘርፉ ብቃት ያላቸውን ባለሙዎች ማብዛት የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህም ሌላ የሙያ ክህሎት ዕውቀት ክፍተት መኖር ኢንዱስትሪው በሚፈለገው መጠን እንዳያድግ ምክንያት መሆኑንም በመግለጽ ጥራታቸውን የጠበቁ የመሰብሰቢያ ቦታዎችን የማመቻቸት አስፈላጊነት፣ በባንኮች በኩል የወለድ የዕፎይታ ጊዜ የመስጠት ዕድል  በኮቪድ ምክንያት የተሰረዙ ዝግጅቶች ወጪ የወጣባቸው በመሆናቸው ከመሰረዝ ይልቅ ለሌላ ጊዜ የማስተላለፍ አሠራር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ ላይ ከዚህ በኋላ የሚደረጉ ምክክሮች፣ ከባለድርሻዎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች የመንግሥት ኃላፊዎችን ማካተት ቢችል፣ ለስብሰባና ኤግዚቢሸን የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ መንግሥት ትብብር እንዲያደርግ፣ በሁነት ዝግጅት ዙሪያ የተሰማሩ ኩባንያዎች የአዕምሮ መብት ባለቤትነት እንዲረጋገጥ የማድረግ አስፈላጊነትና የመሳሰሉት ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

እንደ ጥናቱ ከሆነ ታይዋንና ሲንጋፖር የመሳሰሉ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ዕድገት ላይ የደረሱ የዓለማችን አገሮች የኮቪድ ወረርሽኝ ባመጣው ጉዳት ምክንያት ከቱሪዝም ያገኙት የነበረውን ገቢ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ አጥተዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ እነዚህ አገሮች በርካታ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ቀደም ብለው ወደ ነበሩበት ሁኔታ በመመለስ ላይ ናቸው፡፡

በእነዚህ አገሮች ከተወሰዱት ዕርምጃዎች መካከል የክትባት አቅርቦትና ሽፋን ማደግ መሆኑን በቀረበው ጥናት ተገልጻል፡፡ ሌላው እንደ ምክረ ሐሳብ የተነሳው ጉዳይ የኮቪድ ወረርሽኝ መቼ እንደሚያቃ በማይታወቅበት ሁኔታ እጅና እግርን አጣጥፎ መቀመጥ ዋጋን የሚያስከፍል መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም በቨርቹዋል የሚደረጉ ዝግጅቶችን፣ ስብሰባዎችንና ዓውደ ርዮችን ማድረግ ጠቃሚ እንደሚሆን እንዲሁም የኮቪድ-19 ፕሮቶኮልን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ለአብነትም ያህል ማኅበራዊ ርቀትን በጠበቀ መልኩ ኩነቶችን ማዘጋጀት ጠቃሚ እንደሆነ የዓለም አቀፍ ልምድን ዋቢ በማድረግ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

የቱሪዝም ወይም የማይስ ኢንዱስትሪን ዘላቂ ለማድረግ ከተፈለገ የቱሪዝም ገበያ ላይ በስፋት ሊያሠራ የሚችል አሠራርን መዘርጋት ጠቃሚ እንደሆነ በነበረው የምክክር ወቅት ተገልጿል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሳው ጉዳይ ደቡብ አፍሪካ በማይስ ኢንዱስትሪ ከዓለም ስመ ጥር ከሚባሉ መዳረሻዎች አንዷ መሆኗን በማስታወስ ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሰው የአገሪቱ ቱሪዝም መሠረቱ ሰፊ የሆነ፣ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎችና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን የሚዘወር መሆኑ ጭምር ነው ተብሏል፡፡

በመሆኑም የቱሪዝም መሠረተ ልማትን ማስፋፋትና በዘርፉ የሠለጠኑ ሰዎችን ማግኘት መቻል ዘርፉን ለማሳደግ የሚረዱ ቁልፍ ዕርምጃዎች ናቸው፡፡ በተለይም በመንግሥት በኩል በሆቴልና ቱሪዝም ዙሪያ ለሚሰማሩ ዜጎች የማበረታቻ ዕርምጃዎችን ማመቻቸትና መንግሥት በተቻለ መጠን በኩነት ዝግጅት ላይ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ሥራዎችን መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ተመጣጣኝ ብድር በማመቻቸት ከደረሰባቸው የኢኮኖሚ ኪሳራ እንዲያንሰራሩም ሆነ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ዘርፉን ተወዳዳሪ ሊያደርገው እንደሚችልም ተገልጿል፡፡

አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ በኢትዮጵያ እንዲኖር ማድረግ፣ የኢትነርኔት አገልግሎት መዘርጋትና የማይስ ስትራቴጂን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግም  ከቀረቡ ምክረ ሐሳቦች ይገኙበታል፡፡

ከዚህም ባለፈ የማይስ ኢንዱስትሪ እንዲያድግ ጥራቱን የጠበቀና ተጠያቂነት ያለውን አሠራር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመድረኩ ላይ የተሰነዘረ ሲሆን፣ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የንግድ ምክር ቤቱ ተመሳሳይ የውይይት መድረኮችን እንደሚፈጥርና በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ሰፋፊ ጥናቶችን እንደሚያደርግ ተነግሯል፡፡

ኮቪድ-19 በመከላከል እንዲሁም ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻ አገሮች በአሁኑ ወቅት የቱሪዝም ገቢያቸው መልሶ እንዲሠራ ለማድረግ የተጠቀሙትን ዘዴ በመቃኘትና  በመጠቀም ኢንዱስትሪው እንዲንሰራራ ማድረግ ተገቢ ነው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች