Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉዓባይ - የካይሮ የሴራ ፖለቲካ መልህቅ!

ዓባይ – የካይሮ የሴራ ፖለቲካ መልህቅ!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው                                                           

ዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግዙፍ አገራዊ ሕልምና ተስፋ ነው፡፡ የዛሬው ብቻ ሳይሆን፣ የመጪውም ትውልድ ራዕይ የተጋመደበት የትውልድ፣ የልማትና የዕድገት መተግበሪያነቱም ተደጋግሞ የተነገረ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 80 በመቶ ገደማ መድረሱ ብቻ ሳይሆን፣ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት ሊከናወን ቀናት መቅረታቸው የፕሮጀክቱ ፍጻሜን መቃረብ አመላካች ወቅት ነው፡፡ እንበርታ ፍጻሜውን አድርሰን ታሪካችንንም እንቀይር፡፡

የዚህን አገራዊ ታላቅ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋዩን ያስቀመጡትና የተጀመረው፣ ‹‹መሐንዲሶቹ እኛ፣ አናጢዎቹም እኛ፣ ግንበኞቹም እኛ ሁነን፣ በታላቅ አገራዊና ሕዝባዊ መነሳሳት ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ለመላቀቅ በራሳችን አቅም፣ ያለ አንዳች የውጭ ዕርዳታና ዕገዛ እንሠራዋለን፤›› በተባለው መሠረት ግዙፍ ግድብ ችቦ ሆኖ ሊበራ ተቃርቧል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ቀላል የማይባሉ አገራዊ ፈተናዎችና ጫናዎች እየተደቀኑ፣ በተለይ የካይሮ ፖለቲከኞች ያልተቋረጠ ሴራና መጋፋት እየቀጠለ መሆኑ በሚገባ የሚታወቅ ሀቅ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በእርግጥ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጅምሩ ጀምሮ ብዙ ያከራከረ፣ ብዙ የተባለለት፣ በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ትኩረትን የሳበና ያነታረከ ነበር፡፡  ቢሆንም ኢትዮጵያ በራሷና በልጆቿ አቅም የጀመረችውን የግድቡን ግንባታ፣ ቃሏን ጠብቃ ወደ ፍጻሜው ለማድረስ በትጋት እየሠራች መሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ በመንግሥታት መለዋወጥና የውስጥ መደነቃቀፎች ወቅት እንኳን ሥራው ሳይጓተት እንዲቀጥል መደረጉ ለትውልዱ ኩራት ነው፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታው አስፈላጊው ደረጃ ላይ ሲደርስም የውኃ መሙላትና ማከማቸቱ ተግባር በየደረጃው ይቀጥላል፡፡ የዓባይ ወንዝ የእኛው ቢሆንም፣ ድንበር ተሻጋሪና የዓለም አቀፍ ወሰኖችን የሚያቋርጥ በመሆኑ ኢትዮጵያ አቅም አግኝታ ግድቡን ከሠራች የውኃው ፍሰት ይቀንሳል በሚል፣ በተለይ ግብፅ በየዘመኑ  ያልጎነጎነችብን ሴራና ያልቆፈረችልን ጉድጓድ አለመኖሩን ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ መዳሰስ የተፈለገው፡፡ እናም እስከ መጨረሻዋ ሰከንድ የሚቆም ሴራም ሆነ ጫና ስለሌለ ምንጊዜም ነቅቶና ተዘጋጅቶ መገኘትንም ማስታወስ ይፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ በሰላም የምታምንና ሰላም አክባሪ አገር ነች፣ ነበረች፡፡ የዓባይ ውኃን  በጋራ እንድንጠቀምበት ተፈጥሮ የሰጠን፣ የተጋሪዎቹም የጋራ ሀብት ስለሆነ በጋራና በሰላም ልንጠቀምበት እንችላለን በሚል ዛሬም በእምነቷ ፀንታ ቀጥላለች፡፡ ይህ እውነትና እምነት የማይዋጥላቸው አካላት በተለይ ግብፃዊያን ፖለቲከኞች፣ እንደ ጥንቱ ሴራና ደባ ሁሉ ዛሬም ከጀርባ ሆነው ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎችን በሁሉም መስክ በመርዳትና በማገዝ የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ ከዲፕሎማሲ ጨዋታው ጀርባ ሌላ ሰፊ ቁማር እንደሚጫወቱ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በሚገባ ያውቁታል፡፡

ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ለመልማት ያላት ፍላጎትም ሆነ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን ሳትጎዳ ግድቡን ለኃይል ማመንጫ መጠቀም ማቀዷ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ተገቢና ትክክለኛ አቋም ነው፡፡ ግብፆች የእነሱ ባልሆነው የተፈጥሮ ሀብት ምንጩ ኢትዮጵያ መሆኗን እያወቁ፣ የዓባይ ውኃ ታሪካዊ ባለቤቶች ነን” ሲሉ እውነቱን የሚያውቀው የዓለም ሕዝብ እየሳቀባቸው መሆኑን ለመረዳት አልቻሉም፡፡ እርግጥ ዓለም ኢፍትሐዊ ገጽታም ስላላት የዓረብ ሊግን የመሳሰሉ ጥርስ የሌላቸው አንበሶች ሲደግፏቸው መታየቱ አልቀረም፡፡

ከዚህ ቀደም የካይሮ ሰዎች ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ለሚገነባ ማንኛውም ግድብ ዓለም አቀፍ ብድር እንዳታገኝ ታላላቆቹን መንግሥታትና የብድር ተቋሞቻቸውን ጭምር በመጠቀም ሲያስከለክሉ ኖረዋል፡፡ ዛሬ ጊዜው ባልተጠበቀ ሁኔታ በመለወጡና የውስጥ አቅማችን እየደረጀ በመምጣቱ፣ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ተጠቅማ ግድብ ለመሥራት የማንንም የውጭ ለጋሽም ሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅት ብድር ባትጠይቅም ማደናቀፉ ግን እንደ ቀጠለ ነው፡፡ የብድርና የዕርዳታው በር ሲዘጋ በውጭ ኃይሎች ጫናና አሸማጋይነት ስም የእጅ ጠምዛዛ ሙከራውም እንደ ቀጠለ ነው፡፡

በዚህ ረገድም ቢሆን ግን ያሰቡትን ድል ማግኘት እንዳልቻሉ የሰሞኑ መረጃዎቻቸው አረጋግጠዋል፡፡ ለአባባሉ አንዱ ማሳያ የግብፅ መንግሥት በኢትዮጵያና በዓባይ ጉዳይ ላይ አሉኝ የሚላቸው ዋነኛዋ የፖለቲካ ኤክስፐርትና አፈ ቀላጤ አማኒ አል ተዋል የሰሞኑ አስተያየት ነው ሴትየዋ ‹‹በአሜሪካና በአውሮፓ ላይ የጣልነው ተስፋ ይዞን ጠፋ…›› እያሉ ነው፡፡

እኚህ ሴት ሽንጣቸውን ገትረው በየዓለም አቀፍ ሚዲያው ሲሞግቱ እንደ ከረሙ ይታወቃል። የግብፁ አል አህራም፣ፖለቲካልናስትራቴጂካዊ ሴንተር የአፍሪካ ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት አማኒ፣ ሰሞኑን አል አህራም ባወጣው ሐተታ ላይ ተስፋ አስቆራጩን እውነት በግልጽ ከመናገር ያላገዳቸው መሬት ላይ ያለው እውነት ግድቡን የሚያስቆም እንዳልሆነ ጠንቅቀው በመገንዘባቸው ነው።

በተለይ የአሜሪካ መንግሥትን አስመልክተው ሲናገሩ፣ ‹‹ ባይደን ከህዳሴ ግድብ ጉዳይ ጋር ገና አልተዋወቁም፣ ቅድሚያ የሰጡት ጉዳይም አይደለም፡፡ የአሜሪካ መንግሥታት በተለይ ዴሞክራቶች በታሪክ የኢትዮጵያ ወዳጆች ናቸው። በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ማዕቀብ የጣሉት ደግሞ ነጥለው ትግራይ ውስጥ ባለው ነገር ነው፡፡ ይህ ነገ በሁለቱገሮች ግንኙነት መሀል ምን እንደሚያመጣምናየው ይሆናል። የባይደን ልዩ መልዕክተኛ በአካባቢው ምልልስ ቢያደርግም ውጤቱን ግን እስካሁን አላሳወቀንም…›› ነበር ያሉት፡፡

ተንታኟ ከአውሮፓም የሚጠብቁት ነገር ስላለመኖሩም፣ ‹‹ከአውሮፓ ብዙ አልጠብቅም። እንግሊዝን ጨምሮ አውሮፓውያን ግብፅ በታሪክ በናይል ወንዝ ላይ የበዛ ድርሻ አላት ብለው ያምናሉ። እንዲህ ዓይነት ስሜት ለምን እንዳደረባቸው አላውቅም…›› ብለዋል አማኒ። ይህ ለእነሱ ተስፋ መቁረጥና ኢፍትሐዊ ዕሳቢያቸውን ለማረም ዓይናቸውን የሚገልጥ ሁኔታ ለእኛ መነቃቃትና ሞራል የሚሰጥ ነው፡፡

በመሠረቱ ግብፅም ሆነች ሌሎቹ ባዕዳን፣ ‹‹ኢትዮጵያ ደሃ አገር ስለሆነች ግድብ ለመገንባት የሚያስችል አቅም የላትም›› በማለት መጀመርያ ላይ ተሳልቀው ነበር፡፡ እነሱ ጠግበው ሲያድሩ የዓባይ ውኃ ባለቤት የሆነችው አገራችን ለበርካታ ዓመታት በድርቅና በቸነፈር እየተመታች ዕርዳታ ጠያቂና ተመፅዋች ሁና የኖረችበትን አስከፊ የትናንት ታሪክ እያስታወሱ፣ በምን ተዓምር ነው በከፋ ድህነት ውስጥ የኖረችና የራሷን ሕዝብ መግባ ለማኖር እንኳን ያልቻለች ምድር ዓባይን ያህል ወንዝ የምትገድበው ብለው ነበር፡፡

ያም ሆኖ በአንዳንድ የግብፅ በሳል ምሁራንና ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ አንድ ቀን አቅም አግኝታ በዓባይ ውኃ ላይ ግድብ ትገነባለች የሚለው ሥጋት የተወገደ አልነበረም፡፡ ሥጋቱ ግን የተፈጥሮን ወራጅ ውኃ ገድበው በውኃ ያስጠሙናል ከሚል ሳይሆን፣ የውኃ ኃይል ሚዛኑን ይቀይሩታል፡፡ የልማትን ጥቅም ከቀመሱም ወደ የማያባራ የልማት ፍላጎት ይገባሉ ከሚል ጭንቀት የሚመነጭ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹በመጪዎቹ ዓመታት 100 ግድቦች እንሠራለን›› ሲሉ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር በደስታ የቦረቁት፡፡

የካይሮ ፖለቲከኞች ከጥንት ጀምሮ የነበራቸው ይህ ፍርኃት ነው በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ ዘመናት ታላላቅ ሴራዎችና በደሎች እንዲፈጽሙ ሲያነሳሷቸው የነበሩት የሚለው መላምት አሁንም ብዙ ተቀባይነት አለው፡፡ ቀዳሚው ጥፋት ኢትዮጵያን ለመውጋትና ለማዳከም ከሚደረጉት ጦርነቶች ጀርባ ሁሉ ጥንትም ዘንድሮም ግብፆች ነበሩ/አሉ የሚባለው እውነት ነው፡፡ ትርፉ ውርደትና ውድቀት እየሆነባቸው መጨረሻቸው ሁሉ ክሽፈት ሆኖ እንጂ የተቀየረ ስትራቴጂ ያላቸውም አይመስልም።

ሌላው ቀርቶ አሁንም ድረስ በጦርነትና በኃይል የሚያሰሉ፣ እናውድም፣ እንደምስስየሚሉ ኋለ ቀር ፖለቲከኞች ያላቸው መሆኑ ነው አሳዛኙ እውነት፡፡ ለአብነት ያህል በቅርብ ጊዜ ሃምዳን ሰባሂ የተባሉ ሳልቬሽን ፎሮንት የተሰኘው የግብፅ ዋነኛው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፣ በታላቁ ህዳሴ ግድባችን ላይ ያሠራጨው ጊዜ የለንም እናውድመው” መልዕክት  የሚዲያዎች አጀንዳ ሆኖ ነበር የሰነበተው።

ሰውዬው በድፍረት፣ ‹‹ጊዜ የለንም፣ የኢትዮጵያን ግድብ በማውደም ለሁለተኛ ጊዜ ውኃ እንዳትሞላ ማድረግ አለብን። ይህን ማድረግ ካልቻልን ግብፅ በታሪኳ ያላየችውን ታለቁን የሽንፈት ፅዋ ትጎነጫለች። ግብፅን የምንፈልጋት ከሆነ ራስን የመከላከል ዕርምጃ ኢትዮጵያ ላይ እንውሰድአሁኑኑ፡፡ ግድቡ ለሁለተኛ ጊዜ ውኃ ከተሞላ አለቀልን። ይህ ከሆነ ውኃ ብቻ ሳይሆን፣ የምናጣው ሉዓላዊነታችንን፣ ነፃነታችንንና ሕይወታችንን ጭምር ነው። ሁላችሁም ኃላፊነታችሁን ተወጡ፡፡ ግብፅን የመታደጊያ ጊዜ አሁን ነው…›› ሲሉ ተራ የሴራ ፖለቲካና የማስፈራሪያ ሸቀጣቸውን አራግፈዋል፡፡

እኚሁ ሰው ተመሳሳይ ይዘት ያለው መልዕክት ከወር በፊትም አስተላልፈው ነበር። አካሄዱ ግን የህዳሴ ግድብን በተቻለ መጠን የተለመደው የውስጥ ግለታቸው ማብረጃ ለማድረግ የሚነፋ የፕሮፓጋንዳ ጥሩንባ  ነው። ግብፆች ለዘመናት በዓባይ ውኃ ሲጠቀሙ፣ የተለያዩ ግድቦች ሲሠሩ፣ ልማቶችን ሲያካሂዱ፣ ሰው ሠራሽ ሐይቆችን ሲፈጥሩ፣ ታላላቅ የሙዝና ብርቱካን እርሻዎችን በማልማት ለዓለም አቀፍ ገበያ እያቀረቡ ብሔራዊ ገቢያቸውን ሲያሳድጉ፣ ወዘተ. ባለቤቷ ኢትዮጵያ በራሷ የዓባይ ውኃ ግድብ እንዳትገነባ ዓለም አቀፍ ጫና እስከ መፍጠር ሲራመዱ ዝም ስለተባሉ፣ ዛሬም እዚያው ኋላ ቀር ጊዜ ላይ የቆምን መስሏቸዋል፣ ወይም እንዲሆን ፈልገዋል፡፡

በየትኛውም ማስፈራሪያና ሴራ ግን የተጀመረው የብርሃን ጉዞ የሚደናቀፍ አይሆንም፡፡ በተለይ ደግም በምክንያታዊና ፍትኃዊ የውኃ አጠቃቀም መርህ የተቃኘ፣ በአብዛኛው የናይል ተፋሰስ አገሮች ስምምንት ላይ በተመሠረተ አቅጣጫ የተጀመረና የታችኛው ተፋሰስ አገሮችንም እንደማይበድል የተረጋገጠ ፕሮጀክት በምን አመንክዮ ሊቆም ይችላል፣ አይታሰብም፡፡

በእርግጥ ፈርኦናዊያኑ ማስፈራሪያ ብቻ ሳይሆን ጥንትም ጉራና ጉንደት ላይ ዘልቀው ጦርነት ቢከፍቱም፣ የኢትዮጵያ መሬት መቀበሪያቸው ሆኖ በውርደት መመለሳቸውን አይስቱትም፡፡ ነገም ቢሆን አንዳንድ የካይሮ ሴራ ተዋናዮች ከጀርባ ሆነው አገር ማድማታቸው ነው ላይቆም የሚችለውን ግን መዘንጋት አይገባም፡፡

ግብፆች እኮ ባለፉት አምስት አሠርት ዓመታት በኤርትራ በኩል በነበሩ ግጭቶች (እስካሁኑ የትግራይ ችግር) ከጀርባ ሆነው በተደጋጋሚ አዋግተውናል፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ላስታወሰውም ግብፅ እንዲሁ ከአራት አሠርት ዓመታት ወዲህ በእጅ አዙር ከሶማሊያ ጋር አዋግታናለች፡፡ በተለይ የሶማሊያ መሪ በነበሩት ዚያድ ባሬ ጊዜም ሆነ ከውድቀታቸውም በኋላ የነበሩትን የተለያዩ የጦር መሪዎች በመርዳትና በማስታጠቅ፣ ኢትዮጵያን እንዲወጉ ስታደርግ ለመቆየቷ ብዙ መረጃዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡

በዚህም ግንባር ቢሆን ግን አገራችን እስካልፈረሰች ዘግይተንም ቢሆን ሕልማችን ከመሳካት ስላልታገደ የተሸነፉበት መድረክ ነው (አሁን ገና በተሟላ መረጋጋት ላይ የማትገኘው ሱዳን የአገራችንን ድንበር ጥሳ በመግባት ለፈጸመችው ሉዓላዊነትን የመጋፋት ወንጀል ተባባሪዋ ግብፅ መሆኗን ማስተባበል አዳጋች ነው)፡፡

በውስጥ ፖለቲካችን ረገድም ቢሆን አገራችን በሃይማኖት፣ በብሔርና በፖለቲካ ልዩነት ስም እንድትተራመስ ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም፡፡ ግብፅ ከዓመታት በፊት አንስቶ በሰላማዊ መንገድ ሳይሆን፣ በጦርነት ጥቅማችንን እናስከብራለን ያሉ ኃይሎችን ማለትም ሻዕቢያ፣ ሕወሓት፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ወዘተ. በተለያዩ መንገዶች ስትረዳ መቆየቷ ይታወቃል፡፡ ይህ ዓይነቱ የጥፋት መንገድ አሁንም የቆመ ባይሆንም፣ መንግሥትና ሕዝብ ግን ተደጋግሞ የሚሸረበውን ሴራ እያከሸፉ፣ ታላቁን ፕሮጀክትና ሌሎች ፀረ ድህነት ትግሎችን ከማከናወን አልታገቱም፡፡

ይህ ሁሉ ደባ እየተፈጸመ ያለው ግን በተጨባጭ ኢትዮጵያ የግብፅ ሕዝብን የውኃ ፍላጎት የምትገድብ ሆና ሳይሆን፣ ለምን ቀና ማለት ትጀምር በሚል የጥቂቶች ሰይጣናዊ ፖለቲካ አካሄድ ነው፡፡ በተለይ ‹‹እኛ ብቻ እንኑር ሌላው ቢፈልግ ይጥፋ›› በሚለው ስግብግብና ሰብዓዊነት የጎደለው አቋም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፕሮጀክቱን ስትወጥንም ሆነ ዛሬ ‹‹የዓባይ ውኃ ለሁላችንም ይበቃል፣ ተደማምጠንና ተከባብረን ብንጠቀምበት ለሁላችንም ይበጃል›› ነው እያለች ያለው፡፡

ያንን የባርነት ዘመኗን የሞኝ ዘፈን ይዛ ስታላዝን የኖረችው ግብፅ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ሥር ያልወደቀች፣ በቅኝ ግዛት ዘመን ውልና ስምምነት የማትገዛና የማትቀበል አገር መሆኗን አምና መቀበል ተስኗት እንደምን ኖረች የሚለው ጥያቄ ብዙዎችን ያስገርማል፡፡ አሁንም ቢሆን ግድቡ በክረምት የሚሞላና የሚባክን ውኃን የሚያስቀር እንጂ፣ ካይሮን የማይጎዳ እንደሆነ፣ የዓባይ ውኃም 86 በመቶ ምንጩ ኢትዮጵያ መሆኑን ዓለም ያውቃል፡፡ መፍትሔውም በሴራና በተንኮል መጠቃቃት ሳይሆን በፍቅርና በመተሳሰብ መጠቀም ብቻ ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡

ግብፃዊያን የአገር መሪዎች ኢትዮጵያ የጀመረችው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በምንም መንገድ ሊቆምና ሊገታ እንደማይችል ያውቃሉ፡፡ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት እንደሚካሄድ፣ ቢካሄድም የጎላ ተፅዕኖ እንደማያሳድርባቸውም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው አማካይነት ጭምር በቅርቡ እስከ መናገር ደርሰዋል፡፡ የሕዝባቸውን የተሰቀለ ቀልብና የውስጥ ፖለቲካቸውን ሽኩቻ ግን ይፈሩታል፡፡

ግን በአክትቪስት ተብዬዎቻቸውና በአበዱ ፖለቲከኞቻቸው የሚዘንበው ፕሮፖጋንዳና ማሳሳት፣ እንዲሁም የሴራ ፖለቲካቸው አለመቆሙ ብዙ እያስተዛዘበ ይገኛል፡፡ ያም ቢሆን ኢትዮጵያዊያን ጠንክረን ከቀጠልን ታላቁ የህዳሴ ግዳባችን በዓለም ሰባተኛው፣ በአፍሪካ ደግሞ የመጀመርያው ትልቅና ግዙፉ ግድብ ሆኖ እንደሚዘገብ ከማድረግ የሚገታን ኃይል አይኖርም፡፡

የህዳሴው ግድብ ግንባታ በስኬት መገባደድ ለአገራችንና ለሕዝቧ ዳግም ውልደትና ታላቅ ትንሳዔ ነው፡፡ አሁንም ግን ኢትዮጵያውያን በሰላምና በመነጋገር ተቀራርቦ ልዩነቶችን ለመፍታት መትጋት አለብን፡፡ በሚነሱ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ፍላጎቶች አገራችንን ለውጭ ጠላት አሳልፎ የመስጠቱ አዙሪትም በጋራ ትግል ሊያበቃለት ይገባል፡፡ ከሁሉ በላይ ከማንም ጋር ቢሆን  በጋራ ተጠቃሚነት፣ በመልካም ጉርብትናና በወዳጅነት መርህ መጓዙ ነው ተመራጩ መንገድ፣ ከግብፅም ጋር ቢሆን፡፡

ማጠቃለያ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የአገራችን ብቻ ሳይሆን፣ የቀጣናው ሕዝቦች ተስፋ የሚሆንበት ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ ይህ ውጤት የተገኘው ደግሞ ባለፉት አሥር ዓመታት በሕዝባችን በተከፈለ ከፍተኛ መስዋዕትነት ነው፡፡ የሕዝብ መስዋዕትነቱና የመንግሥት ትግሉ ግን ነገም ሊቆም አይችልም፡፡ የግብፅ ፖለቲከኞች ወደ ቀልባቸው ተመልሰው በሰጥቶ መቀበልና በትብብር መንፈስ ከአገራችን ጎን እስካልቆሙ፣ ወይም ግድቡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ራሱን የሚጠብቅ ኑኩሌር” መሆን እስካልቻለ ድረስ፡፡ ባይ የካይሮ የሴራ ፖለቲካ መልህቅ መሆኑ ግን መቼም የሚቀር አይደለም!!                                                                                                                                       

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...