Saturday, July 13, 2024

ግብፅና ሱዳን ዳግም ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ለመሄድ ምን ገፋቸው?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውዝግብን በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ለመፍታት እንዳልተቻለ በመግለጽበአራትዮሽ አደራዳሪነት ድርድሩ እንዲካሄድ የጠየቁት ግብፅናና ሱዳንአሁን ይህንን ጥያቄያቸውን አንስተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታ ምክር ቤት እንዲይዘው ሰሞኑን በይፋ ጠይቀዋል።

በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ሲካሄድ የቆየው ድርድር መፍትሔ ሊያስገኝላቸው እንዳልቻለ የገለጹት ግብፅና ሱዳን ከሦስት ወራት በፊት ባቀረቡት ሌላ የድርድር አማራጭ፣ ከአፍሪካ ኅብረት በተጨማሪ ሦስት ዓለም አቀፍ አካላት ተጨምረው በጋራ ድርድሩን እንዲመሩ ሲጠይቁ እንደነበር ይታወቃል። ከአፍሪካ ኅብረት በተጨማሪ በአደራዳሪነት እንዲካተቱ የተጠየቁት አካላትም የአሜሪካ መንግሥት፣ የአውሮፓ ኅብረትና ተመድ ነበሩ።

በዚህ ጉዳይ ላይ ቀድሞውንም ፅኑ አቋም የነበራት ኢትዮጵያ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ብቻ መካሄድ እንዳለበትሌሎች አካላት ደግሞ ዕገዛ ሊያደርጉ እንደሚችሉ በመግለጽ ጥያቄውን ውድቅ አድርጋለች።

ይህንን ተከትሎም የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ቲሽስኬዲ (Felix Tshisekedi) ባለፈው ግንቦት ወር በግብፅ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ በመገኘት ድርድሩ የሚካሄድበትን አዲስ አማራጭ አቅርበዋል። 

ፕሬዚዳንት ፊሊክስ የሦስቱ አገሮች መሪዎችን በተናጠል በአካል በማግኘት የተሻለ መፍትሔ ያመጣል ያሉትን የድርድር አማራጭ እንዳቀረቡ፣ የኢትዮጵያ ተደራደሪ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ጌዲዮን አስፋው (ኢንጂነር) ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለሪፖርተር ገልጸዋል። 

አዲስ የቀረበው የድርድር አማራጭም ሦስቱ አገሮች የግድቡ የመጀመርያ ዙር የውኃ ሙሌት ላይ ብቻ የታኮረ ድርድር በማድረግ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ፣ ቀሪውን የልዩነት ነጥብ በቀጣይ ምዕራፍ ድርድር መፍትሔ እንዲፈልጉለት የሚጠይቅ እንደሆነም ጌድዮን (ኢንጂነር) ገልጸዋል።

ይህ የድርድር አማራጭ ከዓመት በፊት በኢትዮጵያ የቀረበ እንደሆነና ሁለቱ አገሮች በዚህ አማራጭ የሚስማሙ ከሆነ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ እንደሆነ የሚያምኑ ቢሆንምሁለቱ አገሮች ግን የቀረበውን አማራጭ እንደሚያጤኑት ከመግለጽ ውጪ ስምምነታቸውን እንዳላሳወቁ አስረድተዋል።

ከዚያ ይልቅ የአገር ውስጥ ሚዲያዎቻቸውን በመጠቀም የቀረበውን የድርድር አማራጭ ለማምታታት እንደሞከሩ ጌዲዮን (ኢንጂነር) ተናግረዋል።

‹‹እኔ እስከተረዳሁት ድረስ በፕሬዚዳንት ፊሊክስ የቀረበው የድርድር አማራጭ ሦስቱ አገሮች በቅድሚያ በግድቡ የመጀመርያ ዙር የውኃ ሙሌት ላይ ስምምነት እንዲደርሱ የሚል ነው። ግብፅና ሱዳን ግን ይህንን በማምታታት በመጪው ሐምሌ ወር በሚካሄደው የውኃ ሙሌት ላይ በቅድሚያ ስምምነት እንዲደረስ የሚል አማራጭ እንደቀረበ አድርገው እያወሩ ነው፤›› ብለዋል። 

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመርያ ዙር የውኃ ሙሌት ማለት ከመሬት እስከ ግድቡ ቁመት 625 ሜትር (ከባህር ወለል በላይ 625 ሜትር) የሚከናወነውን የውኃ ሙሌት የሚያካትት እንደሆነ የገለጹት ኢንጂነሩ፣ ይህንንም ሁለቱም አገሮች የሚያውቁትና የሙሌት ሒደቱንም በተመለከተ በሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ቡድን ስምምነት የተደረሰበት መሆኑን ያስረዳሉ።  ዘንድሮ በሐምሌ ወር የሚካሄደው የውኃ ሙሌት የመጀመርያው ምዕራፍ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መሆኑንም አስረድተዋል። 

ግብፅና ሱዳን በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የቀረበውን የድርድር አማራጭ እንደሚቀበሉም ሆነእንደማይቀበሉ እስካሁን በይፋ ያሉት ነገር የለም።

ሐሙስ ሰኔ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ፊሊክስ ድርድሩን ለማስቀጠል ከሦስቱ አገሮች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ ለውይይት የቀረበው አጀንዳም የውኃ ሙሌቱን በተመለከተ የመረጃ ልውውጥ አካሄድና ከዚሁ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። ይሁን እንጂ ለሐሙስ ተይዞ በነበረው አጀንዳ ላይ ታቅዶ የነበረው የበይነ መረብ ውይይት ማካሄድ ሳይቻል ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ተወስኗል።

በኢትዮጵያ በኩል በዚህ ውይይት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) ሲሆኑጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሳወቁት የግድቡ የውኃ ሙሌት የመረጃ ልውውጥን አስመልክቶ የኅብረቱ ሊቀመንበር በሚያቀርቡት ሰነድ ላይ ለመወያየት አጀንዳ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ውይይቱን ማካሄድ እንዳልተቻለና ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መደረጉን ገልጸዋል። 

ፕሬዚዳንት ፊሊክስም ለአፍሪካ ኅብረት ቢሮ ሙሉ ሪፖርት በተገቢው ጊዜ እንደሚያቀርቡ፣ የህዳሴ ግድቡን ጉዳይ አሁንም በአፍሪካ ኅብረት እጅ እንደሚቆይ ማሳወቃቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት በጠራው የሐሙሱ ውይይት ላይ የተፈጠረው ምን እንደሆነ በይፋ ባይነገርምለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሪፖርተር ምንጮች ወይይቱ መካሄድ ያልቻለው ግብፅና ሱዳን የተጀመረውን የአፍሪካ ሚናን ትተው ጉዳዩን ወደ ተመድ የፀጥታ ምክር ቤት መውሰዳቸውን በማሳወቃቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህ ውይይት ላይ የሦስቱ አገሮች መሪዎች መገኘት የነበረባቸው ቢሆንም፣ በግብፅ በኩል የተገኙት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት እንዳልሆኑና በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ እንደተወከለች አስረድተዋል። በሱዳን በኩልም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ሳይገኙ ቀርተዋል።

ግብፅና ሱዳን ከሁለት ሳምንት አስቀድሞ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ የህዳሴ ግድቡን ውዝግብ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ለመፍታት የተደረገው ጥረት በኢትዮጵያ እምቢተኝነት ሊፈታ አለመቻሉን በመግለጽ፣ የፀጥታው ምክር ቤት ጣልቃ ገብቶ ጉዳዩን እንዲይዘው ጠይቀዋል።

ሁለቱ አገሮች መንግሥቶቻቸውን ወክለው በተናጠል በጻፉት ደብዳቤ ጉዳዩ መፍትሔ ሳያገኝ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ምዕራፍ የውኃ ሙሌት ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገች እንደሆነ በመጥቀስስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ ሙሌቱን በመጪው ሐምሌ ብታካሂድ ከፍተኛ ጉዳት በሕዝባቸው ላይ እንደሚደርስ አስታውቀዋል።

በመሆኑም ጉዳዩ ሰላማዊ መፍትሔ የማያገኝ ከሆነ ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢም ሆነ ለመላ አኅጉሩ ጠንቅ የሚፈጥር አለመረጋጋት ሊፈጥር እንደሚችል በመጠቆም፣ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።

በመሆኑም ሁለቱ አገሮች ቀደም ሲል አለመግባባቱን በድርድር ለመፍታት እንደሚቻል በማመን አሜሪካን ያካተተ ተጨማሪ አደራዳሪ እንዲገባ ያቀረቡትን አማራጭ እርግፍ አድርገው፣ የፀጥታው ምክር ቤትን ጣልቃ ገብነት ጠይቀዋል። 

ግብፅና ሱዳን ዳግም ወደ ተመድ ለመሄድ ምን ገፋቸው?

የህዳሴ ግድቡ ውዝግብ በፀጥታው ምክር ቤት ጣልቃ ገብነት ለመፍታት ይቻላል ብለው ያመኑት ግብፅና ሱዳን፣ በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. አቤቱታቸውን አቅርበው የነበረ ሲሆንበወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰጠው ምላሽ የፀጥታው ምክር ቤት የህዳሴ ግድቡን ጉዳይ ሊመለከት እንደማይገባ በመግለጽ ተቃውሞ ነበር። 

በወቅቱ ኢትዮጵያ ካቀረበቻችው መከራከሪያዎች አንዱ የህዳሴ ግድብ አንድ የልማት ፕሮጀክት እንደሆነና የፀጥታው ምክር ቤት አንድን የልማት ፕሮጀክት ከሰላምና ደኅንነት ጋር አገናኝቶ መመልከት ከጀመረ፣ ወደማይወጣውና ማለቂያ ወደ ሌለው ውዝግብ ውስጥ የሚከተው እንደሆነና ይህም ለዓለም ሰላም የበለጠ ጠንቅ እንደሚሆን የሚገልጽ ነበር። 

ሌላኛው መከራከሪያ ነጥብ ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው መርሁ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውዝግብን ለመፍታት ጉዳዩን እንደያዘው የሚገልጽ፣ የተመድ ቻርተር ደግሞ ለአኅጉራዊ ችግር መፍቻ አማራጮች ቅድሚያ የሚሰጥ እንደሆነ የሚጠቅስ ነበር።

ይህ ጉዳይ አሁንም በአፍሪካ ኅብረት እጅ ሥር ሆኖ ሳለ፣ እንዲሁም ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ከሦስት ወራት በፊት ውዝግቡ በድርድር እንደሚፈታ በማመን ከአፍሪካ ኅብረት በተጨማሪ አሜሪካ፣አውሮፓ ኅብረትና ተመድ በአደራዳሪነት ተካተው የድርድር አመራሩ እንዲጎለብት ጠይቀው ሳለ፣ ላይ ሁሉንም አማራጭ ትተው ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ለመሄድ ምን ገፋቸው? የዚህ ጥያቄ አንደኛው ምላሽ የሚገኘው የአሜሪካ መንግሥት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ውዝግብን በተመለከተ እያንፀባረቀ ባለው አቋም ነው።

ወትሮውንም ቢሆን ቴክኒካዊ ጉዳዩ ሳይሆን የህዳሴ ግድቡ ለኢትዮጵያ የሚፈጥረው ፖለቲካዊ አቅምና አጠቃላይ ፖለቲካዊ አንድምታው ያሳሰባት ግብፅ ለጉዳዩ መፍትሔ እንድትሻላት የተጠጋቻት አሜሪካ ድጋፍ አድርጋ የነበረ ቢሆንም፣ አዲሱ የአሜሪካ መንግሥት (የጆ ባይደን አስተዳደር) ግን በህድሴ ግድቡ ላይ የነበረውን ለግብፅ ያደላ አቋም በመቀየር፣ ለዘብተኛና ሦስቱም አገሮች የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ መፍትሔ አስፈላጊነትን መሠረት ያደረገ አቋም ማራመድ መጀመሩ ግብፅን አስከፍቷል።

የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ያቀረቡት የሁለት ምዕራፍ የድርድር አማራጭ፣ ከአሜሪካ መንግሥት ምክረ ሐሳብ የተቀዳ መሆኑ ደግሞ የግብፅን መንግሥት የበለጠ አበሳጭቷል።

ከአራት ሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የተወያየው የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ፣ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በኢትዮጵያ፣ግብፅናሱዳን መካከል ሊፈታ ያልቻለውን ውዝግብ አስመልክቶ ተወያይቶ ነበር። 

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ሰክሬታሪ ሮበርት ጎደክስን በእማኝነት በመጥራት የመከረው የአገሪቱ ሴኔት፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውዝግብን በሰላም ለመፍታት የአሜሪካ መንግሥት ሚና ምን እንደሆነና ጉዳዩ በሰላም ካልተፈታ በአፍሪካ ቀንድ ብሎም በአሜሪካ ጥቅም ላይ የሚኖረውን አሉታዊ አንድምታ ቃኝቷል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሆነ ፕሬዚዳንት ባይደን በህዳሴ ግድብ ምክንያት ወደ ግጭት እንዳይገባ በጥንቃቄ እየተመለከቱት እንደሆነ የገለጹት ሮበርት ጎደክስይህ አለመግባባት ወደ ግጭት የሚያመራ ከሆነ ጠንቁ ለአካባቢው ብቻ እንደማይሆን ገልጸዋል።

‹‹የዚህ አካባቢ አለመረጋጋት በቀይ ባህር፣ በሜዲትራኒያንና በኢንዶ ፓስፊክ ቀጣና ጭምር ተፅዕኖ ይኖረዋል። በዚህም ምክንያት አሜሪካ ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ሰጥታለች፤›› ብለዋል። 

በመሆኑም አሜሪካ የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ በአፍሪካ ኅብረት ጉዳይ በሚመራ ድርድር እንደሚፈታ በማመን፣ በዚህም መሠረት ውዝግቡ መፍትሔ እንዲያገኝ  ጄፍሪ ፊልትማንን ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ መመደቧን አስረድተዋል።

የድርድሩ አካሄድን በማስመልከት በሰጡት አስተያየትም፣ ‹‹የአሜሪካ መንግሥት አቋም ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ሥር ሆኖ እንዲካሄድ ነው። የድርድሩ አካሄድም በሁለት ተከፍሎ ቢከናወን የተሻለ መፍትሔ ሊገኝበት ይችላል በሚል አቋም፣ ሁለት የድርድር መንገዶችን ጠቁመናል፤›› ያሉት ሮበርት ጎደክስ፣ ‹‹የመጀመርያው ምዕራፍ ድርድር ግብፅንና ሱዳንን በእጅጉ ያሠጋውና በመጪው ሐምሌ ወር ይካሄዳል ተብሎ የሚገመተው የግድቡ የውኃ ሙሌት ላይ ትኩረት በማድረግ ስምምነት እንዲደረስበት ነው፤›› ብለዋል።

ሁለተኛው ምዕራፍ ድርድር ደግሞ የረዥም ጊዜ የውኃ አጠቃቀምና የግድቡ አስተዳር ላይ አተኩሮና ጊዜ ተወስዶ ዘላቂ የመፍትሔ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል፣ የአሜሪካ መንግሥት በማመን ይህንኑ አማራጭ እንዲከተሉ ምክረ ሐሳብ አሜሪካ ማቅረቧን ገልጸዋል።

የሦስቱ አገሮች ውዝግብን በተመለከተ ሲያስረዱም፣ ‹‹በግድቡ ላይ የሚነሱት የውዝግብ ነጥቦች ሳይንሳዊ መፍትሔ አላቸው፡፡ አገሮቹን እያወዛገበ ያለው ቴክኒካዊ ጉዳይ ሳይሆን ፖለቲካዊ ፍላጎት ነው። ይህንን የፖለቲካ ፍላጎቶቻቸውን አመቻምቸው መፍትሔ ላይ ለመድረስም ፈቃደኛ አይደሉም። ለዚህም ነው ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት ሥር መካሄድ ያለበትና በአፍሪካ ኅብረት ሥር መካሄድ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ እንኳን መግባባት ያልቻሉት፤›› ብለዋል። 

በአሜሪካ በኩል የተያዘው አቋም ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት እንዲመራ መሆኑን የጠቆሙት ሮበርት ጎደክስየአሜሪካ መንግሥት በቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነና የድርድሩ ሒደትን ለሚመራው ለአፍሪካ ኅብረትም ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

በዚህ የአሜሪካ አቋም የተከፋቸው ግብፅ አሜሪካንና የአውሮፓ ኅብረትን፣ እንዲሁም ተመድን በአደራዳሪነት ለማሳተፍ ያቀረበችውን ጥያቄ በመተውና የአፍሪካ ኅብረትን ሚና በመግፋት ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ማምራትን ምርጫዋ አድርጋለች።

ለዚህም ይረዳት ዘንድ የአሜሪካን ነርቭ የሚነካውን የፍልስጤም ጉዳይ በመምዘዝ የዓረብ ሊግን ማሳተፍ የጀመረች ሲሆንየዓረብ ሊግም የፍልስጤምንና የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጉዳይ አጣምሮ እንዲመክርና የአቋም መግለጫ እንዲያወጣ ግፊት አድርጋለች። 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -