Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገር​​​​​​​ከአዲሱ መንግሥት የሚጠበቁ ቀዳሚ ተግባራት በወፍ በረር!

​​​​​​​ከአዲሱ መንግሥት የሚጠበቁ ቀዳሚ ተግባራት በወፍ በረር!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

አሁን ስድስተኛው ዙር ብሔራዊ ምርጫ በአንፃራዊነት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተካሂዶ፣ ድኅረ ምርጫ ተግባራት የሚከናወኑበት ወቅት መሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ በብዙዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የተናጠል ውጤቶች የታወቀ ሲሆን፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተጠቃለሉ መረጃዎችን አጠናቅሮ አሸናፊዎችን እንደሚያስታውቅ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ማንም ያሸንፍ ማን ስለአገራችን ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ አካሄድ መነጋገር፣ እንዲሁም ዋስትና ላለውና አስተማማኝ ለሆነ የፖለቲካ መስተጋብር መዘጋጀትም የሚያስፈልገው፡፡

ኢትዮጵያ በታሪክ ረጅም ርቀት የተጓዘች አገር ብትሆንም፣ በዘመናዊ ፖለቲካ ዳራዋ ግን ከአንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረ ዕድሜ አልተጓዘችም፡፡ ከዚህ ውስጥ በተለይ ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ ተማረ የሚባለው ትውልድ የፊውዳሉን ሥርዓተ ማኅበር ለማፈራረስና በኋላም ወታደራዊ የነበረውን አምባገነን ወደ ሕዝባዊ መንግሥት ለመቀየር ከባድ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡

- Advertisement -

በወቅቱ ሺዎች ተሰውተዋል፣ የብዙዎች አካል ጎድሏል፣ የታሰረውን፣ የተሰደደውን፣ ጠፍቶ የቀረውን፣ ቤተሰቡ የተበተነውን፣ ወዘተ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ እንደ ዋዛ በእርስ በርስ ጦርነትና አለመግባባት የተጎተተው ዕድገትና የወደመው የአገር ሀብት እስካሁንም ጫናው እንዳለ ነው፡፡ በጣም አስቸጋሪ የነበረው ያ አስፈሪ ጊዜ ለመማሪያ አልበቃ ብሎን፣ አሁንም በሰሜን ኢትዮጵያ ደም አሳፋሳሽ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ግን እስከ መቼ?

ያ ሁሉ ውጣ ውረድ ታልፎ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ከእነ ችግሩም ቢሆን አዲስ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምዕራፍ ተከፍቶ ነበር፡፡ ያም ሆኖ የፖለቲካ ምኅዳሩ የተለየ አመለካከትና ብዝኃነት ማስተናገድ ተስኖት፣ የኢፍትሐዊነትና የዝርፊያ ችግር ገዝግዞት፣ ጠባብነትና አክራሪ ብሔርተኝነት በትኖት፣ የመልካም አስተዳደር መዳከም ተጭኖት ሌላ ለውጥ ለመጋበዝ ተገዷል፡፡ ለዚህም ነበር ከ2010 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር አዲስ የለውጥ ሙከራ ሊታይ የበቃው፡፡ ለውጡ የመጣው ከላይ በተነሱት ምክንያቶች  በውስጥም በውጭም ያለው ግፊት በማየሉ ነበር፡፡

ያም ሆኖ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ለውጥ ሲጀመር እንደሚያጋጥመው ያለ ቀውስ ተብሎ ብቻ የማይታለፍ ተደጋጋሚ ጥቃትና ግጭት፣ ውዝግብና አለመተማመን የፖለቲካውን አየር ሲያቆሽሸው ነበር የቆየው፡፡ የአገሪቱ በርካታ ዜጎች ለማመን በሚከብድ ሁኔታ መገደላቸውና መቁሰላቸው ብቻ ሳይሆን የደረሰው ከባድ መፈናቀል፣ የወደመው ሀብትና ንብረት እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ በየአካባቢው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በተፈጸሙ መፈናቀሎችና ዘር ተኮር ጥቃቶች ሕዝቡ እንዲነጣጠልና የአገር ገጽታ እንዲጠለሽ ከመደረጉ ባሻገር፣ አገር ከትናንቱ ተምራ ወደፊት ለመስፈንጠር እንዳትችል የሚያውኩ የፖለቲካ አሻጥሮች ገና ብዙ ሥራ የሚፈልጉ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

እናም በምንገኝበት ወሳኝ ወቅት ሕጋዊ ውክልና ያለው መንግሥት እንደ መመሥረቱ፣ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አንዳንድ የፖለቲካ ዕርምጃዎች መውሰድና የዴሞክራሲ ንፍቀ ክበቡን መፈተሸ አስፈላጊ ይሆናል እላለሁ፡፡ ለዚህም ለውይይት መነሻ የሚሆኑ አንዳንድ ነጥቦች በወፍ በረር አቀርባለሁ፡፡

ሕወሓት የፈጠረውን መፈላቀቅ መድፈን

ከሁሉ ቀድሞ መፍትሔ ማግኘት ያለበት በትግራይ ክልል በአሸባሪነት ከተፈረጀው ከሕወሓት መራሹ አማፂ ቡድን ጋር የተጀመረውን ጦርነት ማጠናቀቅ ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል ለዘመናት በጦርነትና በሰው ሠራሽ ችግሮች ሲጠበሱ የኖሩትን የትግራይ ወገኖችን ፈጥኖ ከችግር ለማውጣት መፍትሔ በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል በቅርብም ሆነ በሩቅ ያሉ የውጭ ኃይሎች የአገራችንን መንግሥት እጅ ለመጠምዘዝና ተፅዕኖ ለማሳደር የሚሹት በዚሁ ሕግ የማስከበር ጦርነት ምክንያት ፍላጎታቸውን እንዳይጭኑ መከላከል ስለሚያስችል ነው፡፡

እርግጥ ነው ሕወሓት እንደ ድርጅት ይዞት በቆየው ግትር አቋም ለውጥን ከመቀበል ይልቅ ወደ ጥፋት ነበር የነጎደው፡፡ በተለይ በፌዴራሉ መንግሥት ሕገወጥ የተባለውን የትግራይ ክልል “ምርጫ” በማካሄድ፣ ከገደብ ያለፈ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በማሠልጠንና በማስታጠቅ፣ ከመስከረም በኋላ ዕውቅና ያለው መንግሥት የለም” በሚል ፕሮፓጋንዳ በመጠመድ አገር ምድሩን አውኳል፡፡ ለዕርቅና ለሽምግልና ሲያስቸግርም ቆይቷል፡፡

በዚህ ብቻ ሳይሆን በየአካባቢው ዘር ተኮር ጥቃት እንዲባባስና የለውጥ ጅምሩ እንዲመክን ያልጫረው እሳት እንዳልነበር መንግሥት ሲከሰው ቆይቷል፡ ይህ ሁሉ ሳይበቃ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜን ዕዝ ላይ የወሰደው የክህደት ዕርምጃ ደግሞ በታሪክ ጭምር የሚያስወቅስ ድርጊት ነው፡፡ በእነዚህና በሌሎች በርካታ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አሻጥሮች የሚወቀሰው ሕወሓት መራሹ ቡድን፣ አሁንም ሕገወጥነቱ ተጋልጦ በጋራ ትግል ወደ ሕግ ካልቀረበ የሚያደርሰው ጥፋት ለአገር መዘዝ ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ለዚህም ነው ህልውናው መቋጫ ሊያገኝ ይገባዋል መባሉ፡፡

ግን እንዴት ይቋጭ ማለት አይቀርም፡፡ በቀዳሚነት በክልሉ አሉ የሚባሉ ሽፍቶችንና በሽብርተኝነት የተሰማሩ ኃይሎችን ትጥቃቸውን እንዲፈቱና ራሳቸውን ለሕግ ተገዥ እዲያደርጉ ጥሪ ማቅረብ ነው፡፡ ሲቀጥል ይህን ለሰላም የተዘረጋ እጅ ባለመቀበል ውጊያ ለመቀጠል የሚፈልግን ኃይል ጠንከር ባለ በትር በአጭር ጊዜ  ለመምታት መንቀሳቀስ የግድ ነው፡፡ ይህ ዕርምጃ በተቻለ መጠን ንፁኃንን በጠበቀና በፈጠነ ጊዜ እንዲጠናቀቅ መደረግም አለበት፡፡

ይህን ለማድረግ ደግሞ አሁን በተጀመረው መንገድ ድርጅቱን በትጥቅና ስንቅ ብቻ ሳይሆን፣ በፕሮፓጋንዳ የሚደግፉ አካላትን በማስቆምና የገንዘብ ምንጮቹን በማድረቅ ጭምር መጠናከር እንዳለበት የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ እርግጥ ይህ ድርጅቱ ቀድሞ ከዘረጋው መዋቅርና ከኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረፈው ሀብት ካካበተው የፕሮፓጋንዳ ጥንካሬ አንፃር ብቻ ሳይሆን፣ በውጭ ከበተናቸው ጀሌዎቹ አኳያ ትግሉ ቀላል አይሆንም፡፡ ምንም ቢባል ከሕዝብ የሚያል የለምና በተለይ ችግር ውስጥ የወደቀውን የትግራይ ሕዝብ ጭምር በንቃት በማታገል ድል መጨበጥ ግን የሚከብድ አይሆንም፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የትግራይ ሕዝብን ከረሃብና ከእርዛት ለመጠበቅም ሆነ ተጨማሪ ጉዳትና መከራ እንዳይደርስበት ለማድረግ፣ እንዲሁም እንደ ሌሎቹ ወገኖቹ ተረጋግቶ ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንዲመለስ አስፈላጊው ድጋፍና መተባበር መቀጠል አለበት፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያውያን ከመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ የሚኖረው የሞራልና የወገንነት አንድምታ በሚገባ መታየት አለበት፡፡ እዚሁ ላይ ሕዝብና የፖለቲካ ኃይሎችን የለየ የዕርቅና የአብሮነት ወይም የትግል ሥልት መከተል ለነገ የሚባል ሥራ አይደለም፡፡

ለውጡን ይበልጥ ማሳደግ

ኢሕአዴግን ከመንበረ ሥልጣኑ የገፈተረውን ለውጥ በመምራት አገር እያስተዳደረ ያለው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ መንግሥት፣ ከምርጫው በኋላ አገር የማስተዳር ዕድል ማግኘቱ ዕውን የሆነ ይመስላል፡፡ ይኼ አሸጋግራለሁ ብሎ ኃላፊነት ለተቀበለው ኃይል ተጨማሪና ቀጣይ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ሕዝቡም በንቃት ተሳትፎውንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነቱን እያሳደገ ከሄደ ወደ ሌላ ምዕራፍ የሚያሸጋግር  ውጤት ነው ሊባል ይችላል፡፡

ፈተናውም በዚያው ልክ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ በቀዳሚነት ለውጡ ይበልጥ ሥር የሚሰድበትና ሕዝብም በፍትሐዊነት የሚጠቀምበት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ፣ ብሔራዊ ምክክርና ዕርቅ፣ ወዘተ. ተግባራት መቅደም አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎችና የሕዝብ ወኪሎች በማሳተፍ መምከር፣ የሕግ የበላይነትን ያከበረ የፖለቲካ መስተጋብር መወጠንና የዴሞክራሲ ተቋማትን ይበልጥ ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ የለውጥ ኃይሉ ከዚህ ቀደም ነባሩን የፀረ ዴሞክራሲያዊና ነጣጣይ አካሄድ ለማስቀጠል የሚገፉ የአመራር፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ዘውጎችን በመቀየር ረገድ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ለመሻገር መሞከሩ ይታወቃል፡፡ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የተባለውን የወዳጅና የጠላት መፈረጃ አባትና ግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለም በመቀየር በአንድ በኩል የነፃ ገበያ ሥርዓት በነፃነትና በኃላፊነት ለማራመድ፣ በሌላ በኩል “መደመር“ በሚል አተያይ ሁሉም የራሱን በጎ እሴቶች አሰባስቦ ጠንካራ አገራዊ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለመፍጠር የሚያስችል ጉዞም ቢሆን ከእነ ችግሩ ተጀምሯል፡፡ ይህን ግን በሕግና በሥርዓት ብሎም በብሔራዊ መግባባት ማጠናከር የቀጣዩ ምዕራፍ ተግባር መሆን አለበት፡፡

በአገሪቱ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ምኅዳር በማጠናከርና አገረ መንግሥቱን በማረጋጋት ወደ ልማትና ዕድገት ተጠናክሮ የመግባት ጉዳይም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ለዚህም የተቋማትን ነፃነትና ገለልተኝነት፣ እንዲሁም ብቃት ማሳደግ ብቻ ሳይሆን በስብጥራቸው አገራዊ ገጽታ እንዲኖራቸው ማድረግ መተማመንን ይበልጥ እንደሚያሳድግ መዘንጋት አይገባም፡፡

እንደ መንግሥትም በብዙዎቹ ጉዳዮች ከሕዝብ ጋር መተማመን፣ ከሞላ ጎደል ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር መቀራረብና መደማመጥ ጠቃሚ ነው፡፡ እዚህ ላይ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡም የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር ግድ ይለዋል፡፡ ይህ የሚሆነውም  ገዥው ፓርቲ በመንግሥትነት ሚናው ተጠናክሮ መውጣት ሲችል ብቻ እንደ መሆኑ ምርጫው ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ማስታወስ ይገባል፡፡

በመንግሥት መዋቅር ደረጃ ብዙ ተነግሮላቸው፣ እስካሁን እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ባይሠሩም የሰላም፣ የዕርቅና የወሰን ኮሚሽኖች የያዙዋቸው ተግባራት የሚጠብቃቸው ሥራ ቀላል አይደለም፡፡ በተለይ እንደ ትግራይና አማራ፣ አፋርና አማራ፣ ሶማሌና አፋር፣ ደቡብና ኦሮሚያ፣ አዲስ አባባና ኦሮሚያ፣ ሐረሪና ኦሮሚያ፣ ወዘተ በእንጥልጥል ይዘዋቸው ያሉት የወሰንና የባለቤትነት ጥቄዎች ፈጣን መፍትሔ ማግኘት አለባቸው፡፡ እስከ ዞንና ወረዳ እየወረዱ የሚያጋጩ አጀንዳዎችን መድፈን የሚቻልበት አንዱ ጉዳይ ይኼው ነው፡፡

እዚህ ላይ እንደ መንግሥት ብቻ ሳይሆን እንደ ብልፅግና ፓርቲ ከምርጫ በኋላ ከሁሉ በፊት በየደረጃው በፓርቲው አባላትና አመራሩ መካከል ያለውን ልዩነት መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ የአመለካከት በተለይም የፕሮግራምና የሕገ ደንብ የግንዛቤ ውህደትና የተግባር አንድነት በጥብቅ መረጋጋጥም አለበት፡፡ የፓርቲው ሰዎች በውስጣቸው ሌቦችንና ጤነኞችን፣ ቆራጦችንና አስመሳዮቹን ማንጠር ይበጃቸዋል፡፡ ሕዝብን የሚያገለግሉና ጫንቃ ላይ ሆነው የሚቦጠብጡም ነጥረው መታወቅ ይኖርባቸዋል፡፡

ለፓርቲው ዓላማ ራሳቸውን መስዋዕት ለማድረግ ከልባቸው የሚሠሩትና ጊዜያዊ ጥቅም ፍለጋ ብቻ በፓርቲው ዙሪያ የተሰባሰቡ ልግመኞችን መለየትም እንዲሁ፡፡ አንድ ጊዜ ስለሕዝብ ጠንካራ አንድነት፣ ሌላ ጊዜ በብሔርተኝነት መናወዝ የሚያምራቸውን ውዥንብር ላይ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦችን ማራቅ ጠቃሚ ነው፡፡ በጥቂት ሰዎች የሚመራ ፓርቲ መገንባት ሳይሆን፣ ጠንካራ ውህደትና የኮር አመራር ክምችት ያለው እንዲሁም መታገያ መድረኩ የሰፋ ፓርቲ የመፍጠሩ ጉዳይም ቸል መባል የለበትም፡፡

ስለፓርቲያቸው ጥንካሬ ለሌላው ሕዝብ ለማስረዳት እንኳን ድፍረቱ የሌላቸው፣ የፓርቲያቸውን ድክመት በፓርቲው በራሱ ስብሰባ ላይም ለማንሳትና የማሻሻያ ሐሳብ ለማቅረብ ሀሞት የሌላቸው የራሳቸውን ጥቅም በማሳደድ ላይ የተወጠሩ ‹‹አባል/አመራር ተብዬዎች››ን ማጥናትና ማጥራት ለብልፅግና ብቻ ሳይሆን ለአገርም ይበጃል፡፡

በውጭ ግንኙነት ረገድ ኤርትራን ከመሰሉ ጎረቤት አገሮች ጋር ለመቀራረብ የሚያስችልና በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መጀመሩ የለውጡ ቱሩፋት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እንዲሁም ዜጋ ተኮር በሆነው የውጭ ግንኙነቱ አቅጣጫ መሠረት በብዙ ሺሕ የሚገመቱና በተለያዩ አገሮች ለዓመታት ታስረው የነበሩ ዜጎች ተፈተው ወደ አገራቸው  እንዲመለሱ መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ከጎረቤት አገሮች ጋር ወዳጅነትንና የጥቅም ተጋሪነትን በማለም ከግብፅና ከሱዳን ጋር የተጀመሩ ድርድሮችን በማጠናከር፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ወሳኝ ሚና አስጠብቆ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በትግራይ ግጭትና በሕገወጥ ተግባር ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙ ፖለቲከኞች ምክንያት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎችና አንዳንድ መንግሥታት የያዙትን የተንሻፈፈ አቋም ማስቀየርም ሌላው ተግባር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ ወይም ምልልስ ውስጥ መግባት ሳይሆን፣ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ የሚያከናውን የፖለቲካና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማደራጀትና ማብዛት ያስፈልጋል፡፡ አምባሳደርነትን ማረፊያና ጡረታ ማውጫ የማድረጉ አሳፋሪ አሠራር መታረም አለበት፡፡

ሌላውና ወሳኙ ተግባር መልካም አስተዳደር የሰፈነበትና ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ የመገንባቱ ሥራ ነው፡፡ ከቀድሞ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት እየተንከባለለ የመጣው በየደረጃው ያለ መንግሥታዊ መዋቅር አሁንም በየደረጃው ብዙ የማያስደስቱ አሠራሮች አሉበት፡፡ የሕዝቡ መንገላታትና ምሬት ጋብ ብሎ እንደሆን እንጂ ሥር ነቀል ለውጥ አልታየበትም፡፡ ለውጥ ተጀምሮ በተለይ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የመሬት፣ የገቢዎች፣ የቤትና መሰል ሀብቶች ቅርምትና ዝርፊያ ኢፍትሐዊነት ዜጎችን እጅግ በጣም እያበሳጨ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡     

ይህን ዓይን አውጣ ድርጊት ባለፉት ሦስት ዓመታት አንዳንድ ተችዎች ከሥርዓቱ ጋር ለማጣበቅ ተረኝነት፣ ባለጊዜ፣ አዳዲስ ነጣቂዎች፣ የኢሕአዴግ ግልባጮች… የሚሉ ስያሜዎች እየሰጡት ነበር፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለአገር ዕድገት ዋነኛ እንቅፋቶች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ በተለይ የብሔር ፖለቲካ በጋመበት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ብልሽቱ ከዴሞግራፊና ከዘር ቆጠራ ጋርም የሚያያዝ፣ ኢፍትሐዊነትን በማንገሥ ሕዝብን የሚያስቆጣ… በመሆኑ በጊዜ ካልታረመ አብሮ የማያኖር መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡

በእርግጥ በየትኛውም ዓለም ቢሆን መሬት ወሳኝ የዜግነት ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ባለቤትነት መንፈስን የያዘ ሀብት ነው፡፡ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማርሽ መቀየሪያ መሣሪያም ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፍትጊያ ውስጥም ቢሆን  መሬት ዋነኛው መዘውር ሆኖ ዘመናትን አስቆጥል፡፡ ነገር ግን በጠራ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌና መመርያ ወጥነት ባለው መንገድ ዜጎች የሚጠቀሙበት ካልሆነ፣ አሁንም መዋቅር ጨብጦ ገዥ መደብ መመሥረት የሚያምረው መብዛቱ አይቀርም፡፡

ከፊውዳሉ ሥርዓተ ማኅበር አንስቶ አሁን እስከምንገኝበት የታሪክ ምዕራፍ ሥልጣንን መንጠልጠያ በማድረግ የመሬት ዘረፋና ወረራ፣ ብሎም ሽሚያና ወከባ እየጎለበተ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ አሁን ያለው ሥርዓት ደግሞ ፖለቲካ ኢኮኖሚውን ይበልጥ ሊብራላይዝ” ማድረግ የሚፈልግ እንደ መሆኑ መጠን፣ ዜጎች በባለሀብቱ እንዳይራኮቱና ለከፋ የጭሰኝነት ችግር እንዳይጋለጡ መጠንቀቅ አለበት፡፡ እዚህ ላይ የሕዝቡ ተሳትፎም መነቃቃት አለበት፡፡

በመሠረቱ ይህን ሰፊና ብዝኃነት የሞላበት አገር ለረጅም ጊዜም ሆነ ለተገደቡ ዓመታት ለመምራት፣ በተለይም አሁን ባለው ሁኔታ ወሳኝ የሆኑ የሰላምና የደኅንነት ተግባራትን ማስቀደም እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ ወደ ማስፈታት፣ ብዙኃኑን ሕዝብ ወደ ሰላምና ልማት ፊቱን እንዲያዞር ለማድረግ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ሰፊና ትልቅ አደራ ውስጥ ደግሞ እንደ ቀደሙት ጊዜያት፣ በእከክልኝ ልከክልህ እየተሻሹና እየተወሻሹ መቀጠል አይቻልም፡፡ ሕዝብ ከትናንት በተሻለ በፍትሐዊነትና በእኩልነት እየተደመጠ ዘላቂ ጥቅሙ እንዲረጋገጥ መበርታት ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው nwodaj@yahoo,com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...