ባለፈው ዓመት ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ከተገደለው ድምፃዊው ሃጫሉ ሁንዴሳ ጋር በተያያዘ የታሠሩትና ክስ የተመሠረተባቸው እነ ጃዋር መሐመድ፣ ፍርድ ቤት የሚሰጣቸው ውሳኔዎችና ትዕዛዛት እየተከበሩ አለመሆናቸውን በመግለጽ ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ አስታወቁ፡፡
አቶ ጃዋር ሲራጅ መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሀምዛ አዳነና አቶ ደጀኔ ጣፋ እንደማይቀርቡ ያሳወቁት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ወንጀሎች ችሎት በፊርማቸው አረጋግጠው በላኩት ደብዳቤ ነው፡፡
ተከሳሾቹ በደብዳቤያቸው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ እንዳይፎካከሩ መንግሥት የሃጫሉን ግድያ ምክንያት በማድረግ እንዳሰራቸው ጠቁመው፣ ለፍትሕ ተቋም ክብር በመስጠት የቀረበባቸውን ክስ ሕጋዊ በሆነ መንገድ በትዕግሥትና ዓርአያነት ባለው መልኩ፣ ሕግ አክባሪ ዜጎች መሆናቸውን ለማስመስከር መሞከራቸውን ገልጸዋል፡፡ በወቅቱም ፍርድ ቤቱን ጨምሮ ለሁሉም የሕግ አስከባሪ አካላት ተገቢውን ክብር መስጠታቸውንና ይህንንም ያደረጉት ፍርድ ቤቱ የሚሰጠውን ውሳኔ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ተግባራዊ ያደርጋል በሚል እምነት እንደነበር አክለዋል፡፡
ተከሳሾቹ ከሒደቱ የተረዱት ግን ፍርድ ቤት የሚሰጠው ውሳኔና ትዕዛዝ በሕገወጥ መንገድ እየተጣሰ፣ በነፃ የተሰናበቱ ተከሳሾችና ተጠርጣሪዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እየተጠለፉ ወደ ማይታወቅ ቦታ እየተወሰዱ መሆኑን፣ የኦነግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጃል አብዲ ረጋሳን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ በመሆኑም የፍትሕ አካላትን ውድ ጊዜ ከማባከን ውጪ ፍትሕን ለማስፈን አንዳችም ፋይዳ አለው ብለው ስለማያምኑ፣ ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ በፈቃደኝነት ወደ ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ አሳውቀዋል፡፡ አስፈጻሚው አካል ለሕግ የበላይነት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር በማሳየት፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እምነት ኖሯቸው ወደ ችሎቱ በቅርቡ እንደሚመለሱ ተስፋ እንደሚያደርጉም አክለዋል፡፡
ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤቱ የላኩት ደብዳቤ ከተነበበ በኋላ ዓቃቤ ሕግ ተቃውሟል፡፡ ተገደው እንዲቀርቡ፣ የማይቀርቡ ከሆነ ግን በሌሉበት እንዲታይ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
የተከሳሾቹ ጠበቆች ባቀረቡት መከራከርያ ሐሳብ እንዳስረዱት፣ ደንበኞቻቸው ፍርድ ቤቱን ያከብራሉ፡፡ እነሱም የተነበበውን ደብዳቤ መፃፋቸውን እንደማያውቁና ምናልባት በነፃ የተለቀቁ ተከሳሾችና ተጠርጣሪዎች እንደገና እየታፈሱ መታሰራቸውን ሲሰሙ የሥነ ልቦና ጫና ሊሆን ስለሚችል፣ አግባባተውና አናግረዋቸው እንዲቀርቡ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ተገደው ወይም በሌሉበት የሚለው የዓቃቤ ሕግ ጥያቄ ተገቢ አለመሆኑን አክለዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ፣ ‹‹የተያዘው ሽምግልና ሳይሆን የወንጀል ክስ ነው፡፡ እናግባባለን የሚለው ተቀባይነት የለውም፤›› ካለ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት በድጋሚ ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ክርክር በዝምታ በማለፍ፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በዝግና ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው መሰማት አለመሰማታቸውን በሚመለከት ለማከራከር ለሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡