Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናመንግሥታዊ ተቋማት ለኦዲት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ፓርላማው ዕርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ

መንግሥታዊ ተቋማት ለኦዲት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ፓርላማው ዕርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ

ቀን:

ማዕከላዊ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የተበደረው 192.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል

ከወትሮ ባልተለመደ ሁኔታ የተወሰኑ የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች የተለያዩ ሰበቦችን በመፈጠር ኦዲት ላለመደረግ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ሊቆም እንደሚገባ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አሳሰበ፡፡ ፓርላማውም ዕርምጃ እንዲወስድ ጠየቀ፡፡

‹‹የተወሰኑ የክልል መንግሥታት ተቋማት ኦዲት ልታደርጉን አትችሉምና ከክልሎች ካልተፈቀደላችሁ አንተባበርም የሚሉ ማነቆዎች እየተስተዋሉ መምጣታቸው፣ በፍፁም ተቀባይነት የሌላቸውና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፋጣኝ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፤›› ሲሉ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ጠይቀዋል፡፡

- Advertisement -

ይህ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ እየታየ ያለ ችግር በፍጥነት ካልታረመ ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ፓርላማው ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታት አመራሮች ጋር በመነጋገር ለችግሩ አፋጣኝ ዕልባት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው 16ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት አፈጻጸምን በተመለከተ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ያቀረበውን ሪፖርት አዳምጧል፡፡

ወ/ሮ መሠረት ሁለት ሰዓታትን ያህል በፈጀው የ61 ገጽ የተቋማት ኦዲት ግኝት ሪፖርት፣ በበርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከሕግና ከአሠራር ውጪ የተከናወኑ ተቋማዊ ግድፈቶች መገኘታቸውን አመልክተዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ከጠቀሷቸው ግድፈቶችና በወቅቱ ያልተወራረዱ ወይም ከማን እንደሚሰበሰቡ ካልታወቁ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ከተገኘባቸው የመንግሥት ተቋማት መካከል፣ የብሔራዊ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን 1.9 ቢሊዮን ብር፣ ጤና ሚኒስቴር 1.5 ቢሊዮን ብር፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር 614.7 ሚሊዮን ብር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር 402.8 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 385 ሚሊዮን ብር ተገኝቶባቸዋል፡፡

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 336.6 ሚሊዮን ብር፣ የአገር አቀፍ የትምህርትና ምዘና ፈተናዎች ኤጀንሲ 296.7 ሚሊዮን ብር፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር 174 ሚሊዮን ብር፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት 126.6 ሚሊዮን ብር ከማን እንደሚሰበስብ በውል በማይታወቅ ሁኔታ በውዝፍ ተሰብሳቢ መባሉን ለፓርላማው የቀረበው ሪፖርት ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል በገቢዎች ሚኒስቴርና በጉምሩክ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤቶችና በሥራቸው ባሉ 12 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች፣ እንዲሁም በሌሎች 31 መሥሪያ ቤቶችና በአንድ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መሰብሰብ የነበረበት ነገር ግን ያልተሰበሰበ 390 ሚሊዮን ብር መገኘቱም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

በተመሳሳይ በገቢዎች ሚኒስቴር ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች በወጣው ሕግና ደንብ መሠረት፣ የመንግሥትን ገቢ በአግባቡ መሰብሰባቸውን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት፣ በሚኒስቴሩ ባሉ ስድስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና በጉምሩክ ኮሚሽን ሥር ባሉ ሌሎች ስድስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በታክስ ኦዲት ወይም በድኅረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት ውሳኔ መሠረት ያልተሰበሰበ 7.7 ቢሊዮን ብር መገኘቱ ተመልክቷል፡፡

እንዲሁም በ30 የመንግሥት ተቋማት የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ 450 ሚሊዮን ብር በወጭ ተመዝግቦ እንደተገኘም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ በተመሳሳይ ደንብና መመርያን ባለመከተል 96.8 ሚሊዮን ብር ተከፍሎ መገኘቱም ተገልጿል፡፡

የተሽከርካሪ አጠቃቀምን በተመለከተ 96 ተሽከርካሪዎቹ ሊብሬ የሌላቸው፣ 16 የሰሌዳ ቁጥር የሌላቸው፣ 93 የተሽከርካሪ ፋይል የሌላቸው፣ አምስት ሊብሬው ብቻ ኖሮ ተሽከርካሪው በአካል የሌለና ታርጋቸው ኢትዮጵያዊ ያልሆነ 95 ተሽከርካሪዎቹ መገኘታቸውን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

መንግሥት ከውጭ አገር በብድር ያገኘውን ገንዘብ በመልሶ ማበደር ስምምነት መሠረት ለልማት ድርጅቶች ያበደረውን ገንዘብ በገቡበት ውል መሠረት ወቅቱን ጠብቀው ተመላሽ ባለማድረጋቸው፣ ከተለያዩ ሰባት ድርጅቶች ከ2001 እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ 14 ቢሊዮን ብር በወቅቱ አለመሰብሰቡን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡

የዋና ኦዲተር የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት እንደሚያመላክተው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከመንግሥት ባለቤትነት ውጪ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶችን ፈቃድ አወጣጥና ዕድሳትን በተመለከተ በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀ መመርያ የለም፡፡ እንዲሁም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተዘጋጀ የፈቃድ አሰጣጥና ዕድሳት ስታንዳርድ አለመኖር፣ እንዲሁም የርቀት ትምህርትን ሊመራና ሊያስተዳድር የሚችል ምንም ዓይነት ሕግና መመርያ ወይም በባለቤትነት የሚመራው የተደራጀ ክፍል አለመኖሩ ተመልክቷል፡፡

በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመንግሥት ቋት በሚመደብ በጀት የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች በወቅቱ ታትመው መደርደሪያ ላይ ከመቀመጥ ባለፈ፣ ለሚመለከታቸው ኢንዱስትሪና ማኅበረሰብ እንዲደርሱና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ዩኒቨርሲቲው የራሱን ጥረት አለማድረጉን፣ የተሠሩት የጥናት ውጤቶችም ስላበረከቱት አገራዊ አስተዋጽኦ ግምገማ አለመድረጉን በምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ተገልጿል፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ለሥራ ዕድል ፈጠራ ድጋፍ የሚውል በ2012 በጀት ዓመትና በ2013 ዓ.ም. ስድስት ወራት ከተሰበሰበው 602 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ምን ያህሉ ክልሎችን ለመደገፍ እንደዋለ፣ እንዴት ለክልሎች እንደሚከፋፈል መሥፈርቱን ለማወቅ በተደረገ ቅኝት፣ ገንዘቡ ለታለመለት ዓላማ የዋለ መሆኑን ክትትል ስለመደረጉ የሚገልጽ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቢጠየቅም ማቅረብ አለመቻሉ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግሥት ብድርን በተመለከተ የብድር ፖሊሲ ሊያወጣና ተግባራዊ ሊያደርግ የሚገባ ቢሆንም፣ አሁንም ሁሉንም የአገር ውስጥና የውጭ አገር የውሰት ብድር የሚመራበት ብድር ፖሊሲ ስለመኖሩ ተጠይቆ ማቅረብ አለመቻሉን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ማዕከላዊ መንግሥት በቀጥታ ከብሔራዊ ባንክ የሚወስደውን የብድር መጠንና ጊዜ ገደብ በሕግ መወሰን የነበረበት ቢሆንም፣ ገንዘብ ሚኒስቴር በየዓመቱ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚወስደውን የብድር ጊዜና የብድሩን መጠን የሚገድብ ሕግ ስለመኖሩ ከኦዲት ማስረጃ ተጠይቆ ማቅረብ አለመቻሉ ተገልጿል፡፡

የሚገደብ ሕግ ባለመኖሩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያለ ገደብ በቀጥታ የወሰዳቸው ብድሮች ተከማችተው በ2002 ዓ.ም. 45.87 ቢሊዮን ብር የነበረው፣ በ2012 ዓ.ም. ያልተከፈለው ዋናው ውዝፍ ዕዳ 192.2 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል፡፡

ከውጭ አገር የተበደሩትን ዕዳ በውል ስምምነት መሠረት መክፈል ካልቻሉና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኢትዮ ቴሌኮም 213.9 ሚሊዮን ዶላር ዋና ገንዘብና 36 ሚሊዮን ዶላር ወለድ፣ ስኳር ኮርፖሬሸን 25.8 ሚሊዮን ዶላር፣ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል 96.9 ሚሊዮን ዶላር በዕዳ እንደተዘፈቁ የኦዲተሩ ሪፖርት ያሳያል፡፡

በብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ሪቴንሺን አካውንት መመርያ መሠረት የድርጅቶች የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ቀርቦ በንግድ ባንኮች በኩል ክፍያ ከመፈጸሙ በፊት፣ የቀረበው የውጭ ምንዛሪ ጥያቄው በቀጥታ ከተሰማሩበት ዘርፍ ጋር ተቀራራቢ መሆኑን ሳያረጋግጡ ከመመርያ ውጪ 15 ባንኮች ክፍያ መፈጸማቸውን ሪፖርቱ ያብራራል፡፡

የፌዴራል ኦዲተር ዋና መሥሪያ ቤት ያቀረበውን የኦዲት ሪፖርት በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ታደሰ መሰሉ የተባሉ የምክር ቤት አባል፣ አጠቃላይ የተቋማት ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርት ሲቀርብ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት የበላይ ኃላፊዎች መገኘት ሲገባቸው አለመገኘታቸው ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ይህ የሕዝብና የአገር ሀብት እየባከነና በተደጋጋሚ ተነግሯቸው አለመገኘታቸው፣ በምክር ቤቱ በደንብ መታየትና ውይይት ሊደረግበት ይገባዋል ብለዋል፡፡

አቶ ታደሰ አክለው፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚኒስትሮቻቸውን ይዘው ስለጉዳዩ መልስ ሊሰጡን ይገባል፤›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹እኔ በቆየሁናቸው 16 ዓመታት ስሰማቸው የነበሩ የኦዲት ሪፖርት ውጤቶች በጣም አሳሳቢ ናቸው፡፡ በመሆኑም ይህንን ጉዳይ መፍታት የማይቻል ምክር ቤት ዋጋ የለውም፤›› ብለዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አገራዊ ለውጡ ከመጣ ወዲህ የኦዲት ሪፖርቱ ምን ይመስላል ተብለው ከምክር ቤቱ አባላት ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹ግምገማችንን በዚያ በኩል አላየነውም፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን የኦዲት ሪፖርቱን ያላሻሻሉ መሥሪያ ቤቶች ችግሩ ሊቀጥል የቻለው ቆንጠጥ ስላልተደረጉ በመሆኑ፣ ሰው ባጠፋው ልክ ሊቀጣና ሊስተካከል ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን ለ12 ዓመታት በዋና ኦዲተርነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ በመጋቢት 2013 ዓ.ም. በጡረታ መሰናበታቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...