ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት 3፡00 ሰዓት አካባቢ በመኖሪያ ቤታቸው ከጓደኛቸው ሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራ ጋር የተገደሉት ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ገዳይ መሆኑ የተረጋገጠበት ጠባቂያቸው አሥር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፣ በሞት እንዲቀጣ ቢጠየቅም ፍርድ ቤት በዕድሜ ልክ እሥራት እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጠ፡፡
ውሳኔውን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ወንጀሎች ችሎት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሆን፣ ቅጣቱን ዕድሜ ልክ እስራት እንዲሆን ውሳኔ የሰጠው፣ ከሳሽ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሹ በሞት እንዲቀጣ ያቀረባቸው አራት የቅጣት ማክበጃ ሐሳቦች ውድቅ በማድረግ ነው፡፡
ተከሳሹ ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው፣ በወቅቱ የአማራ ክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ከነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጋር በመገናኘትና ተልዕኮ በመቀበል መሆኑን፣ ዓቃቤ ሕግ በስፋት ዘርዝሮ ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡ በዕለቱ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ የክልሉ ዓቃቤ ሕግ ቢሮ ኃላፊ አቶ ምግባሩ ከበደና የፕሬዚዳንቱ አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴም በባህር ዳር ከተማ መገደላቸው ይታወሳል፡፡
ግድያውን አቀነባብረዋል የተባሉት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመታኮስ በባህር ዳር ዙሪያ ዘንዘልማ በሚባል ሥፍራ መገደላቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡