Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​​​​​​​ኢትዮጵያ ለድፍድፍ የምግብ ዘይት ግዥ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ያህል ያስፈልጋታል ተባለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ለድፍድፍ የምግብ ዘት ግዥ ብቻ ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋትና የአገሪቱን የምግብ ዘይት ፍላጎት ለመሙላት  ከፍተኛ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተመለከተ፡፡

በወቅታዊ የምግብ ዘይትና ግብዓት ችግሮች ዙሪያ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገ ምክክር ላይ እንደተገለጸው፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የምግብ ዘይት ፍላጎት የአገሪቱ የዘይት ፋብሪካዎች ከሚያመርቱት ምርት በእጅጉ የበለጠ ሆኖ መገኘትም በቀጣይ የዘይት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል ተነግሯል፡፡

የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎችን የግብዓት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ በሚል ርዕስ በተዘጋጀው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንዳመለከቱት፣ በ2014 በጀት ዓመት የአገሪቱ የምግብ ዘይት ፍላጎት 906 ሚሊዮን ሌትር ሲሆን፣ ይህም 993 ሚሊዮን ዶላር ይጠይቃል፡፡

ለ2014 ዓ.ም. የምግብ ዘይት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ መነሻ በማድረግ በተሠላ ስሌት ለ2014 ዓ.ም. እና ለ2015 ዓ.ም. አገሪቱ ለድፍድፍ የምግብ ዘይት ግዥ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያስወጣት ከሚኒስትሩ ንግግር ለመረዳት ተችሏል፡፡ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ለድፍድፍ የምግብ ዘይት እንደሚወጣ ታሳቢ የተደረገው የውጭ ምንዛሪ ከዚህ ቀደም ከውጭ የተጣራ የምግብ ዘይት ለማስገባት ከሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ በላይ የሚጠይቅ ነው፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በቅንጅት በሠራው ሥራ አሥራ አራት የነበሩትን ማጣሪያ ያላቸው የዘይት ማምረቻዎች ወደ 30 ማሳደግ የተቻለና አጠቃላይ የማምረት አቅማቸው ከ89 ሚሊዮን ሌትር ወደ 1.25 ቢሊዮን ሌትር እንዲያድግ ቢደረግም፣ እነዚህ የዘይት ማምረቻዎች ግን ከአቅም በታች የሚያመርቱ በመሆኑ ፍላጎቱን ሊያሟሉ አልቻሉም፡፡

በዕለቱ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ፣ አሁን ላይ 95 በመቶ የሚሆነው የምግብ ዘይት ከውጭ የሚገባ በመሆኑ አሁንም ድፍድፍ ዘይትን መሠረት አድርገው እያመረቱ ያሉ የዘይት ማምረቻዎች በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ እስካልተጠቀሙ ድረስ ለምግብ ዘይት የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ሆኖ እንደሚቀጥል አሳይቷል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብ ዘይት ፋብሪካዎች ማስፋፋት፣ በቁጥርም ከዕጥፍ በላይ ማሳደግና የምግብ ዘይት ምርትን ከውጭ ማስመጣት ማስቀረት ባለመቻሉ ክፍተቱን ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን አሥር ዓመታትን እንደሚጠይቅ በዕለቱ ከተደረጉ ገለጻዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡  

በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ በሥራ ላይ ባሉ የዘይት ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች የአገሪቱን ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ ለማሟላት የማምረት አቅም የተፈጠረ መሆኑን አቶ መላኩ ቢገልጹም፣ በቅባት እህል አቅርቦት ችግር ምክንያት ድፍድፍ ዘይት ከውጭ በማስገባት አጣርቶ ማቅረብ የግድ ሆኗል፡፡

በቀጣይ ዓመታት በግብርናና በአምራች ኢንዱስትሪው መካከል ጠንካራ የግብዓት ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ ለምግብ ዘይት በግብዓትነት የሚውሉ የቅባት እህሎችን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገባውን የድፍድፍ ዘይት ለማስቀረት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊው የግብርና ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን በመሥራትና ከግብርና ጋር ጠንካራ ትስስር በመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራ ይሆናል ያሉት አቶ መላኩ፣ ይህንን በአገር ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እየተጫወቱ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመቀናጀት ይሠራል ብለዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በዘርፉ ሌሎች ሥራዎች መሠራታቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ከእነዚህም መካከል ከዘይት ተረፈ ምርት ፋቲ አሲድ 46,580 ቶንና ስቴሪን (የአትክልት ቅቤ) 32,606 ቶን በማምረት ለሳሙናና ለአትክልት ቅቤ ግብዓት ከውጭ ለማስገባት በዓመት ወጪ ይደረግ የነበረውን 75.23 ሚሊዮን ዶላር ሙሉ በሙሉ ማስቀረት መቻሉን አሳውቀዋል፡፡

ዘርፉ የድፍድፍ ዘይትን በአገር ውስጥ በማጣራት ሒደት ለ4,000 ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡ አሁናዊ የአገራችን የማምረት አቅም 1.25 ቢሊዮን ሌትር መድረሱና ለዚህም ውጤት መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተቀናጅቶ ከሠራ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 ሚኒስትሩ ከምግብ ዘይት ጋር ተያይዞ የተሠራውን ሥራ እንዲህ ባለ መልኩ ይግለጹት እንጂ፣ በተጨባጭ በገበያ ውስጥ የሚታየው ግን የምግብ ዘይት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ነው፡፡    

በኢትዮጵያ ወደ ላይ የወጣው የዋጋ ንረት አሁንም ከመጨመር በቀር መረጋጋት የማይታይበት ሲሆን፣ ለዚህም አንዱ በምግብ ዘይት ላይ እየታየ ያለው ያልተቋረጠ የዋጋ ንረት ነው፡፡

የምግብ ዘይት ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ዕድገት ከሌሎች አንፃር ሲታይ የተለየ የሚያደርገው ባለፉት ጥቂት ተከታታይ ወራት ግዙፍ የሚባሉ የዘይት ማምረቻዎች ወደ ሥራ በገቡበት ማግሥት መሆኑ ነው፡፡ ገበያውን ያረጋጋሉ የተባሉት ፋብሪካዎች ይህንን ማድረግ ካለመቻላቸውም በላይ፣ በዓመቱ አጋማሽ ላይ ቢበዛ ከ350 ብር ያልበለጠ ዋጋ የነበረው አምስት ሌትር የምግብ ዘይት ዋጋ አሁን ላይ ከ560 ብር እስከ 600 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

ከትናንት በስቲያ የምግብ ዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት በተደረገው ውይይት ላይ እንደተመለከትነው ደግሞ፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉ የምግብ ዘይት ማምቻዎች የማምረት አቅም አገሪቱ በዓመት ያስፈልጋታል ተብሎ ከሚታመነው የዘይት ፍጆታ በላይ ነው፡፡ ነገር ግን የማምረት አቅም አላቸው ቢባልም በአቅማቸው ልክ እያመረቱ አይደለም፡፡

መንግሥት እነዚህንና ሌሎች ተዛማጅ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍና በመንግሥት በኩል የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፉን ለማሳግድ በተለይ አቅሙና ፍላጎቱ ያላቸው የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን በማስተባበር፣ መሬትና ብድር አቅርቦት በማመቻቸት በኢትዮጵያውያን እጅግ ዘመናዊና ግዙፍ የሆኑ የምግብ ዘይት ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ማቋቋም መቻሉም አንድ ማሳያ እንደሆነ አቶ መላኩ ይግለጹ እንጂ፣ በተጠቃሚዎች ዘንድ የእነዚህ ማምረቻዎች መቋቋም ገበያው ላይ ለውጥ አላመጣም፣ እንዲያውም ብሷል ብለው እንዲሞግቱ እያደረገ ነው፡፡  

አሁን ያሉትን የዘይት ማምረቻዎች አቅም በተመለከተ ከተሰጠው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ እነዚህ የዘይት ማምረቻዎች ከአቅም በታች ለማምረት የተገደዱበት ዋነኛ ምክንያት የግብዓት ዕጥረት ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በኢትዮጵያ ከሚመረተው አጠቃላይ የሰብል ምርት ውስጥ ለዘይት ምርት የሚሆኑ የቅባት እህሎች ድርሻ ስድስት በመቶ ብቻ መሆንና ከዚህም ውስጥ አብዛኛው ወደ ውጭ የሚላክ መሆኑ፣ የዘይት ማምረቻዎቹ ግብዓት እጥረት እንዲገጥማቸው እንዳደረገ በዕለቱ የቀረበ አንድ ጥናት አመላክቷል፡፡

እንደ ጥናቱ ከሆነ፣ ከሚመረተው አጠቃላይ የቅባት እህል ውስጥ ለዘይት ምርት ግብዓት የሚውለው 2.7 በመቶው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን የቅባት እህል ምርት በማሳደግ ማምረቻዎቹን በአቅማቸው እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ አሁን ያለውን የምግብ ዘይት ፍላጎት ለመሙላት ግን በመንግሥት ደረጃ በቀጣይ ዓመታት መሠራት አለበት ተብሎ ዕቅድ መወጣቱ ተገልጿል፡፡

በዕቅዱ መሠረት ከሦስት እስከ አምስት ዓመት በምግብ ዘይት ኢትዮጵያ ራሷን እንድትችል መታቀዱ አንዱ ነው፡፡ ከ5-10 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ ከውጭ የሚገባውን ዘይት እዚሁ ለማምረት ዕቅድ ተይዟል፡፡

በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የግብርና ሚኒስቴርም ባለድርሻ ሆኖ የቀረበ ሲሆን፣ በምግብ ዘይት አገሪቱ ራሷን እንድትችል በጋራ ለመሥራት ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ላይ ደርሷል ተብሏል፡፡

በጋራ በሚሠራው ሥራ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ይረዳል ተብሎ እንደ መፍትሔ ሐሳብ ከቀረቡት የቅባት እህሎችን ምርታማነት መጨመር የሚለው አንዱ ነው፡፡ በመስኖ ጭምር እንዲመረት ማድረግ የግድ ነው ተብሏል፡፡ እንደ ስንዴ ሁሉ የቅባት እህል በመስኖ እንዲመረትና የዘይት አምራቾች በቅባት እህል ማምረት ላይ እንዲሠሩ ማድረግ የሚሉትም ተጠቅሰዋል፡፡ የፖለቲካ ውሳኔዎችም ገበያ ማረጋጋት ይችላሉ የሚል እምነት ተንፀባርቋል፡፡

በቀረቡ ጥናቶች መሠረት አሁን ላሉ የዘይት ፋብሪካዎች ከስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የቅባት እህል ያስፈልጋቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ማጣሪያ ያላቸውን 30 የዘይት ማምረቻን ጨምሮ 232 የምግብ ዘይት ኢንዱስትሪዎች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 26 የሚሆኑት መካከለኛና ከፍተኛ የሚባሉ ናቸው፡፡ 206ቱ ደግሞ አነስተኛ የሚባሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተለይ 206ቱ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ የግብዓት ችግር ያለባቸው ሲሆን፣ ይህንን ችግራቸውን ለማቃለል በክላስተር ደረጃ እንዲደራጁ ይደረጋል ተብሏል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች