Saturday, April 20, 2024

​​​​​​​ከተኩስ ማቆም ውሳኔው ጀርባ የታቀደው ፖለቲካዊ መፍትሔ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የመንግሥት ሚዲያዎች ሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ ይዘውት የወጡት ዘገባ በብዙዎች ላይ የተደበላለቀ ስሜት ሲፈጥር፣ገሚሶች ላይ ደግሞ ደስታን እንዲሁም እውነተኛ የሰላም መፍትሔ ዕውን መሆንን እንዲናፍቁ አድርጓል። 

ሰኞ አመሻሽ ላይ የተሰማው ይህ ዜና በትግራይ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በትግራይ ክልል ላለፉት ስምንት ወራት ገደማ የዘለቀው ውጊያ እንዲቆም የተኩስ አቁም ስምምነት የማድረግን አማራጭ ለፌዴራል መንግሥት ያቀረበ ነበር። 

ይህ መረጃ ይፋ በተደረገበት ወቅት ከትግራይ ክልል ይወጡ የነበሩ ያልተረጋገጡ መረጃዎች፣ ሕወሓት የሚመራው ኃይል ወደ መቀሌ ከተማ እየተቃረበ መሆኑን የሚገልጹ ነበሩ።

የነገሮች በአንድ ቀን ውስጥ መለዋወጥ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተደባለቀ ስሜት ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል።

የመጀመርያው የተኩስ አቁም ስምምነት አማራጭ ለፌዴራል መንግሥት ለውሳኔ መቅረቡ በተሰማ በአንድ ሰዓት ውስጥ፣ የፌዴራል መንግሥት ባወጣው መግለጫ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያቀረበውን ጥያቄ በአዎንታ ተቀብሎ የተናጠል የተኩስ ማቆም ማድረጉን ይፋ አድርጓል። 

 

በዚህ ሰዓት ደግሞ ከወደ ትግራይ ይወጡ የነበሩት መረጃዎች የሕወሓት ኃይል ወደ መቀሌ ከተማ መግባቱን የሚገልጹ ነበሩ።

የፌዴራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ ማቆም ማወጁና የተኩስ ማቆሙ ውሳኔም፣ ከዚያው ዕለትና ሰዓት አንስቶ ተፈጻሚ እንደሚሆን አስታውቋል።

የፌዴራል መንግሥት ላሳለፈው ውሳኔ እንደ መነሻ የተጠቀመበት ምክረ ሐሳብ የመጣው ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ያላቀረበው ምክረ ሐሳብ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ተቀምጠዋል።

በመሠረታዊነትም የክረምት ወቅት እየገባ ከመሆኑ አንፃር፣ በትግራይ ክልል በዚህ ክረምት ዘር መዝራትና ወደ ቀጣይ የመሰብሰብ ሥራ መግባት ካልተቻለ በማኅበረሰቡ ላይ የሚፈጠረውን አደጋ የተመለከተ ነው።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም በላይ (/) እንደገለጹትየክልሉ አርሶ አደር በዚህ ክረምት ወደ እርሻ ካልገባ የዘር ወቅት ስለሚያልፍ በቀጣይ ገበሬው ለዓመታት ተረጂ ሆኖ የመኖር አደጋ ይገጥመዋል።

የፌዴራል መንግሥት ባለፉት ስምንት ወራት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ፣ ለክልሉ የመንግሥት አግልግሎት ለማስቀጠልና ጉዳት ለደረሰባቸው መሠረተ ልማቶች ጥገናና ግንባታ 100 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ገልጸዋል።

ለዚህም ሲባል ክልሎች ከበጀታቸው ቀንሰው የትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋም ድጋፍ ማድረጋቸውን የጠቀሱት አብርሃም (/)፣ ይህም በአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ በተለይም በሌሎች ክልሎች ላይ የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይ ደግሞ ሰብዓዊ ዕርዳታው ወደሚፈለገው ቦታ ለማድረስ፣እርሻ ሥራ እንዳያመልጥ ለማድረግ፣ የተፈናቀለውንም ተረጋግቶ ወደ የቤቱ እንዲመለስ ተጨማሪ የፖለቲካ አማራጭ በማስፈለጉ በተደጋጋሚ ከመንግሥት ጋር ንግግር መደረጉን ገልጸዋል።

‹‹የተኩስ አቁም ስምምነቱ ገበሬው ተረጋግቶ እንዲያርስ፣ ለችግረኞች የሰብዓዊ ድጋፍና የዕርዳታ ቁሳቁስ ለማድረስ፣ የተፈናቃዮችን ቤት ጠግኖ ወደ ቦታቸው ለመመለስ ነው፤›› ብለዋል።

የጊዜያዊ አስተዳሩን ጥያቄ በአዎንታ መቀበሉን በመግለጽ የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉን ይፋ ያደረገው የፌዴራል መንግሥት ደግሞ፣ ከላይ ከተጠቀሱት መነሻ ምክንያቶች በተጨማሪ ሌሎች ዝርዝር ሁኔታዎችንም እንደተመለከተ ካወጣው መግለጫ መመልከት ይቻላል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩ ከተጠቀሱት ዝርዝር ምክንያቶች ባሻገር የክልሉን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ወዳጆች ሲቀርቡ የነበሩ የመፍትሔ ሐሳቦችን የፌደራል መንግሥት ሲያጤናቸው መቆየቱንልጿል። 

‹‹ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተከታታይ ያቀረበውን ጥያቄ መንግሥት ከተለያየ አቅጣጫ ተመልክቶታል፡፡ በአንድ በኩል አካባቢውን ከሚመራ አካል የቀረበ በመሆኑ፣ በሌላ በኩል ጥያቄው ከመቅረቡ በፊት በተለያየ ጊዜ ከክልሉ ተወላጆች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት የተደረገበት መሆኑን ከግምት ውስጥ አስገብተናል፤›› በማለት የፌዴራል መንግሥት አስታውቋል።

በተጨማሪም፣ ‹‹በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከመቼውም በላይ ለአገራችን ሰላም የሰጡት ልዩ ትኩረት ከግምት ውስጥ ገብቷል፡፡ ይህንንም ሰላም የኢትዮጵያ አንዱ አካል የሆነውን የትግራይ ሕዝብ ተቋዳሽ ሊሆን ይገባል ተብሎ ስለሚታመን፣ የትግራይ ሕዝብም ሰላምና ለውጥ ፈላጊ መሆኑ በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ የቆየ መሆኑን ስለሚታወቅየአገሪቱን ሉዓላዊነት ከውጭ ኃይሎች ከተሰነዘሩ ትንኮሳዎች ለመከላከልና ሁለተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ ለመሙላት ትኩረት መስጠት የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ በመሆኑ›› የተናጠል የተኩስ ማቆም ውስኔውን ለማሳለፍ ምክንያት እንደሆነ፣ የፌዴራል መንግሥት ባወጣው መገለጫ ዘርዝሯል።

ነገር ግን መሠረታዊ ምክንያቱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያነሳቸው በክልሉ ሕዝብ ላይ እየደረሱ ያሉ መከራዎች መሆኑን ይገልጻል።

‹‹መላው ሕዝብም እንደሚረዳው፣ የተበተነው የሕወሐት ኃይል በመሸገባቸው አካባቢዎች ገበሬው ተረጋግቶ ወደ እርሻ ሥራ መግባት አልቻለም፡፡ ባለፈው ዓመት የአንበጣ መንጋ በስፋት ያጠቃው ክልል በመሆኑ፣ የግብርና ሰብል ምርት በበቂ ሁኔታ አላገኘም፡፡ ከአንበጣ የተረፈውን መሰብሰብ እንዳይችል የመሰብሰቢያ ጊዜው አለፈ፡፡ አከባቢው የግጭት ቀጣና ሆነ። በዚህ ሁኔታ ይኼንን ክረምት ያለ እርሻ ሥራ የሚያሳልፍ ከሆነ፣ ለገበሬው በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆንበታል፤›› ብሏል።

በማከለም፣ ‹‹የሕወሓት የጥፋት ኃይል በሚነዛው የሽብር መረጃ›› የተነሳ ሕዝቡ የጦርነት ጋሻ ሆኖ እየተማገደ እንደሆነና ከዚሁ ጋር ተያይዞም፣ ‹‹ሲዋጋ ሚሊሻ፣ ሲጠቃ ሲቪል›› የሚሆን ኃይል እየተፈጠረና በዚህም ምክንያት ቤታቸው የፈረሰባቸው፣ እርሻቸው የተስተጓጎለባቸው፣ አካባቢያቸውን ለቅቀው የተፈናቀሉ ሁሉ የተረጋጋ ኑሮ ለመኖር አለመቻላቸውን ይጠቁማል፡፡

በዚህም መሠረት ገበሬው ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዲያከናውን፣ የዕርዳታ ሥራው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ ሆኖ እንዲሠራጭ ሲባል ይህ የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ ያለ ቅድመ ሁኔታ በሰብዓዊነት ላይ የተመሠረተ በተናጠል የሚተገበር የተኩስ አቁም ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉን የፌዴራል መንግሥት አስታውቋል፡፡

በመሆኑም ሁሉም የፌዴራልና የክልል ሲቪልና ወታደራዊ ተቋማት፣ ከመንግሥት በሚሰጣቸው ዝርዝር አፈጻጸም መሠረት ይኼን የተኩስ አቁም እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ መታዘዛቸውን አስታውቋል።

የተኩስ አቁሙ ውጤታማነትና ሥጋቶች 

የተናጠል የተኩስ አቁም ከመታወጁ ሰዓታት አስቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት ተቆጣጥሮት ከነበረው የመቀሌ ከተማ ለቆ መውጣቱን የተለያዩ የውጭ ሚዲያዎች የዘገቡ ሲሆን፣ ይኼንን ተከትሎም የሕወሓት ኃይል ወደ ከተማው መግባቱን ጨምረው ዘግበዋል።

የሕወሓት ኃይል ወደ መቀሌ መግባቱን የሚገልጹ የውጭ ሚዲያ ዘገባዎች በወጡበት ሰኞ አመሻሽ ላይ፣ የመቀሌ ነዋሪዎች በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ደስታቸውን ሲገልጹ የሚያሳዩቪዲዮ ምሥሎችም በማኅበራዊ ድረ ገጾች ሲዘዋወሩ ተስተውሏል።

ይህንን ተከትሎም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተብሎ በፌዴራል መንግሥት የተቋቋመው አካል የማስተዳደር ሚናና የሕወሓት ኃይል ወደ መቀሌ መግባት መካከል የሚፈጠረው መጣረስ፣ የተኩስ አቁሙ ውሳኔው ተግባራዊነት ወይም ዘላቂነት ላይ ሥጋታቸውን የሚገልጹ አሉ።

የፌዴራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ ማቆም ማወጁን ይፋ ባደረገበት መግለጫው ላይ የተቀመጡ ሁለት መልዕክቶችም፣ የተኩስ ማቆም ውሳኔው ተግባራዊነትና ዘላቂነት ላይ ጥያቄ የሚያጭሩ ሆነው ይታያሉ።

አንደኛው መልዕክት፣ ‹‹… ይኼን መልካም ዕድል (የተኩስ ይቁም ውሳኔውን) ለክፉ የሚጠቀሙ ወገኖች ካጋጠሙ ግን የፌዴራል መንግሥት አስፈላጊውን ሕግ የማስከበር ተግባር እንደ አግባቡ የሚያከናውን ይሆናል፤›› የሚል ነው።

በዚሁ መግለጫ ላይ የሰፈረውና የተኩስ ማቆም ውሳኔው አፈጻጸም ላይ ጥያቄ የሚያጭረው ሌላው መልዕክት፣ የተኩስ ማቆም ውሳኔው የእርሻ ወቅት እስከሚያልፍ ድረስ ብቻ የሚቆይ ሆኖ መታወጁ ሌላው ነጥብ ነው።

‹‹ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ (በተናጠል ተኩስ ለማቆም መታወጁ) ዋነኞቹን የጥፋት መሪዎች ለሕግ የማቅረብ ሥራና የተጀመረው የምርመራ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፤›› ተብሎ በፌደራል መንግሥት የሰፈረው መልዕክት፣ የውሳኔውን አፈጻጸም ሊያወሳስበው ይችላል የሚል ሥጋት ፈጥሯል።

ከተኩስ ማቆም ውሳኔ ጀርባ የታሰበው ፖለቲካዊ መፍትሔ

የተናጠል የተኩስ ማቆም ውሳኔውን አስመልክቶ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሰጡት መግለጫዎች ውስጥ የተሰነቀረ አንድ መልዕክት ይስተዋላል።  ይኸውም ፖለቲካዊ የመፍትሔ አማራጭን የተመለከተ ነው።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም (ዶ/ር) ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ የክልሉ አርሶ አደር ተረጋግቶ እንዲያርስ፣ ለችግረኞች የሰብዓዊ ድጋፍና የዕርዳታ ቁሳቁስ ለማድረስ፣ የተፈናቃዮችን ቤት ጠግኖ ወደ ቦታቸው ለመመለስ ሲባል የፖለቲካ አማራጭ አስፈላጊ መሆኑን መንግሥት ከመረዳቱ በተጨማሪ፣ ቀጣይ የፖለቲካ አማራጭ አስፈላጊነት ላይም በማመን መሆኑን ገልጸዋል።

‹‹ለትግራይ ሕዝብ ፖለቲካዊ መፍትሔ መፈለግ ያለበት መንግሥት እንጂ፣ ለሕዝቡ ግድ የሌለው የሕውሓት ጥፋት ኃይል ሊሆን አይችልም፤›› ያሉት አብርሃም (ዶ/ር)፣ በመሆኑም መንግሥት ይበልጥ ሆደ ሰፊ ሆኖ ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን መስጠት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

በማከልም፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት በረሃ ካለው ኃይል መካከል የሰላም መንገድ የሚፈልግ በመኖሩ፣ ለዚህ ኃይል ዕድል መስጠት አስፈላጊ ነው፤›› ብለዋል።

የፌዴራል መንግሥት ባወጣው መግለጫም ይኼው ሐሳብ የተገለጸ ሲሆንበዚሁ መግለጫም፣ ‹‹በአንድ በኩል በክልሉ ያሉትን ችግሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በረሃ ከተበተነው የሕወሓት ኃይል ውስጥ ሁኔታዎች ቢመቻቹለት ወደ ሰላም ሊመጣ የሚችል ኃይል ይኖራል ተብሎ ስለታመነ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ጥያቄ መንግሥት በአዎንታዊነት ተቀብሎታል፤›› ብሏል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -