Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የሠራተኞችን መኖሪያ ቤት ችግር ማቃለል ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ 18,069 ሠራተኞችን የያዘው የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ፣ የሠራተኞችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል በጀመረው ሥራ ሠራተኞችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ትንሳዔ ይማም ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡

በፓርኩ የሚሠሩ ሠራተኞች ከተለያዩ ቦታ የሚመጡ በመሆኑ ሥራው በአንድ ፈረቃ ብቻ እንዲሠራ በመገደዱና የሠራተኛውን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል በማስፈለጉ፣ በፓርኩ ከባለሀብቶች ጋር በመተባበር የመኖሪያ ቤት ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡ በዚህም 4,000 ሠራተኞችን በሚያስተዳድረው ሸንትስ የቴክስታይልና ጋርመንት ኩባንያ የተገነባው ቤት ከ1,700 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች ማስረከቡን ተናግረዋል፡፡

አቶ አዳነ ሞላ ይባላሉ፡፡ አካል ጉዳተኛ ናቸው፡፡ በሸንትስ ጋርመንት መኖሪያ መንደሮች ውስጥ ከሚኖሩት አንዱ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ሰዓት በመሥራት የተሻለ ገቢ እያገኙ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ጠዋት 11፡00 ሰዓት ሜክሲኮ ቄራ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቴ መውጣት አለብኝ፡፡ ምክንያቱም 1፡15 ሰዓት ሲሆን በሥራ ቦታዬ መገኘት አለብኝ፤›› በማለት የገለጹት አቶ አዳነ፣ ሥራ ውለው 10፡30 ሰዓት ከሥራ ወጥተው እስከ ምሽቱ 2፡00 ሰዓት ተጉዘው ቤት የሚደርሱበት አጋጣሚ እንደነበርም አክለዋል፡፡  

ሼንትስ ከተቀጠሩ በኋላ ባሳዩት የሥራ አፈጻጸምና ብቃት ቤት ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ እንግልቱ ከመቀነሱም ባሻገር አምሽተው መሥራትና የምግብም ወጪ እዚሁ በመሸፈኑ የተሻለ ገቢ ሊያገኙ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ሸንትስ የመኖሪያ መንደር የተገነባው በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ መንደሩንም የገነባው ሼንትስ ጋርመንት የተባለ የደቡብ ኮሪያ ካምፓኒ ነው፡፡፡ አቶ አሰፋ ኢየሱስ ይትባረክ የሸንትስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ሸንትስ ወደፊት በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የሚቀጥራቸውን ጨምሮ ከ10,000 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የቤት ችግር ለማቃለል እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ 10 ባለ አራት ወለል ሕንፃዎችን የሚገነባ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አራት ብሎኮችን ሠርቶ በማጠናቀቅ ለ1,700 ሠራተኞች መስጠቱንና እየኖሩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ይህንን የሚያደርገው ከትርፍም በላይ ኢትዮጵያውያን ለኮሪያ ዘመቻ ያደረጉትን ውለታ ለመክፈል በማሰብ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ሸንትስ ጋርመንት ከ4,000 በላይ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ በዓመት ከ12 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያስገኝም አቶ ተስፋ ኢየሱስ ተናግረዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት 18,069  ሠራተኞች ያሉ ሲሆን፣ በተለይ ከሰበታና ከቢሾፍቱ የሚመጡት የኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ በመሆኑ በቡድን እየሆኑ ተከራይተው እንደሚኖሩ በመመልከታቸው፣ የደኅንነት ሥጋት በመኖሩና ሠራተኞቹ በፓርኩ ግቢ ውስጥ ቢኖሩ በፈረቃ 24 ሰዓት ለመሥራት እንደሚቻል በጥናት በመረጋገጡ የመኖሪያ ግንባታው እንዲተገበር ተደርጓል፡፡  

ፓርኩ ለቤት ግንባታ የሚሆን መሬት፣ ውኃና መብራት ማቅረቡንና ካምፓኒው ደግሞ የመኖሪያ ግንባታውን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ2006 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ በምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት በ121 ሔክታር ላይ ያረፉ 20 ሼዶችን ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ወጪ በመገንባት ሥራ መጀመሩ ይታወቃል፡፡

ዓመታዊ ገቢውም ከ44 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ በምዕራፍ ሁለት በግል ባለሀብቶች የሚለሙ ሼዶች ይገነባሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ጄጄ ጋርመንት ማስፋፊያ እየገነባ ነው፡፡ ሸንትስ የቴክስታይልና የጋርመንት ኩባንያ ሱሬዝ የተባለ የብቅል ፋብሪካ ግንባታ በአሥር ሔክታር መሬት ላይ እያካሄደ ነው፡፡ የኮቪድ-19 መመርመሪያ ኪት የሚያመርተው ቢጂአይም በዚሁ ምዕራፍ ሁለት ማስፋፊያ ውስጥ በመካተቱ፣ መስከረም 2014 ዓ.ም. ላይ ደግሞ ዲዛይን ጨርሰው ወደ ግንባታ የሚገቡ በመኖራቸው ፓርኩ በጠቅላላው ከ70,000 በላይ ሠራተኞችን እንደሚቀጥር ከድርጅቶቹ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በፓርኩ የሚሠሩ ሌሎች ድርጅቶችም ለሠራተኞቻቸው የመኖሪያ ቤት ይገነባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች