‹‹ጂርቱ፣ ጂርቱ፣
ቦሌ ጂራ ጄዳ›› ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ከሦስት ዓመት በፊት በሚሌኒየም አዳራሽ በነበረው ዝግጅት ላይ ወደ መድረክ ከወጣ በኋላ አድናቂዎችን የጠራበት ቃል ነበር፡፡ ከዛች ቅፅበት በኋላ ‹‹ጅርቱ›› የምትለዋ ቃል በበርካቶች ልብ ውስጥ ቀርታለች፡፡ ሕፃን አዋቂው ሳይቀር ‹‹ጅርቱ›› ሲል ይደመጣል፡፡
ሃጫሉ በመድረኩ ላይ እንደወጣ በአዳራሹ ለነበሩት አድናቂዎቹ ‹‹አላችሁ›› ሲል ይጠይቃል፡፡ ታዳሚውም ጂራ ወይም አለን ሲል ይመልስለት ነበር፡፡ ሃጫሉ ገና በለጋ ዕድሜ በአምቦ የተለያዩ የመዝናኛ ሥፍራዎች ላይ ነበር ማዜም የጀመረው፡፡
ሃጫሉ በመዝናኛ ሥፍራዎችና በመሸታ ቦታዎች ላይ የሚያሳልፈው ጊዜ በቤት ውስጥ ባይወደድለትም፣ እሱ ግን ለሙዚቃው ከነበረው ፍቅር የተነሳ ማዘወተሩን ቀጠለበት፡፡ ይኼ የሙዚቃ ፍቅር አድጎ ከ17 ዓመት የወጣትነት ዕድሜው ጀምሮ ሙዚቃን መጻፍ እንደጀመር ይነገርለታል፡፡
በተለይ በፖለቲካ ምክንያት በልጅነቱ እስር ቤት መግባቱ ግጥሞቹን ለመጻፍ ትልቅ ዕድል ከፍቶለት ነበር፡፡ የመጀመርያ አልበሙንም ‹‹ሰኚ ሞቲ›› በ2001 ዓ.ም. ነበር ለሕዝብ ጆሮ ያደረሰው፡፡ በጊዜው ተደማጭነትን ያተረፈው የመጀመርያው አልበም ሰኚ ሞቲ በመላ ኦሮሚያ ሲደመጥ ነበር፡፡ ሃጫሉ በሙዚቃ ውስጥ ፖለቲካዊ የሆነ ጭብጦችና መልዕክቶችን በውስጡ ያዘሉ በመሆኑ የኦሮሞ ወጣቶችን በማነቃቃት፣ የማኅበረሰቡን ስሜት፣ ባህል፣ ትውፊት፣ አንድነትና ችግር አጉልቶ የማሳየት አቅም ነበረው፡፡
በተለይ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ በነበረው ሕዝባዊ አመፅ ተከትሎ የሃጫሉ ሙዚቃ ወጣቱን ከማነቃቃት አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ሃጫሉ ‹‹ዋኤ ኬኛ›› ወይም የእኛ ጉዳይ የተሰኘው አልበሙ፣ እ.ኤ.አ. 2013 ለአገር ውስጥ ለገበያ ማቅረብ ባለመቻሉ ወደ አሜሪካ አምርቶ በአማዞን ለመሸጥ ተገዷል፡፡ ሁለተኛው አልበሙ ለአገር ውስጥ ገበያ አለመዋሉን ተከትሎ፣ አገር ውስጥ የድምፃዊው ወዳጆች ከረጅም ጊዜ ቆይታ ነበር ማዳመጥ የቻሉት፡፡ ዋኤ ኬኛ ከሌሎቹ ሥራዎች በእጅጉ የተወደደና በርካታ ጉዳዮችን በውስጡ የያዘ ነበር፡፡
በዋኤ ኬኛ አልበም ውስጥ “Waa’ee Keenya yoo Itti Dhisan Silaa Nama hin Dhiisu” ይላል፡፡ – የእኛን ጉዳይ ቢተዉትም እሱ እንደሆነ አይተወንም እንደማለት ነው፡፡ ለዚህም ሃጫሉ ቢተዉትም የማይተወውን የዚህን አገር ጉዳይ ለአንድ ፈጣሪ መተው ይሻላል በሚል መልዕክት በጊዜው የነበረው የሕዝቡ መገፋትና በእስር ቤት መንገላታትን በሙዚቃው ውስጥ ይገልጻል፡፡
ሃጫሉ ‹‹ማለን ጅራ›› ወይም ምኑን ኖርኩት የሚለው ቪዲዮ ክሊፕ ሌላኛው በበርካቶች የተወደደና በውስጡ ፖለቲካዊ ይዘት የነበረው ሙዚቃ ነበር፡፡ በዚህ ክሊፕ የዓመቱ ምርጥ ክሊፕ ሽልማቱንም ተጎናፅፎበታል፡፡ በአገሪቷ የመጣውን ለውጥ ተከትሎም በ2012 ዓ.ም. ‹‹ጂራ›› ወይም አለን ነጠላ ሙዚቃ ሌላኛው በበርካቶች ዘንድ የተወደደ ነበር፡፡
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ገላን አካባቢ በጥይት ተመቶ ሕይወቱ ያለፈው ሃጫሉ፣ የሙት ዓመት መታሰቢያ ቀኑና የሦስተኛ የሙዚቃ አልበም ምርቃት ተከናውኗል፡፡ ሃጫሉ ሕይወቱ ከማለፉ በፊት የሠራውን ሦስተኛ አልበም ሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ቤተሰቡ እንዲሁም አድናቂዎቹ በተገኙበት በስካይላይት ሆቴል ተመርቋል፡፡
‹‹ማል መሊሳ›› – ምንድነው መፍትሔው የተሰኘው አልበሙ 14 ሙዚቃዎችን በውስጡ የያዘ ሲሆን፣ በመጀመርያው ዙር 300 ሺሕ ቅጂ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በአጠቃላይ እስከ 500 ሺሕ የሲዲ ቅጂ ለገበያ ለማቅረብ እንደታቀድ በሥነ ሥርዓቱ ተገልጿል፡፡ የሲዲ ሽያጩ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ከማክሰኞ ሰኔ 22 ቀን ጀምሮ መሠራጨት ጀምሯል፡፡
አልበሙን በሲዲ ለማያገኙ ወዳጆቹ፣ በኦንላይን ሽያጭ ስፖቲፍ (Spotify) ዓይቲዩንስ (iTunes) እንዲሁም በአማዞን ማግኘት እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም ባሻገር በስሙ አዲስ ዩቲዩብ፣ ፌስቡክ ቻናልና የተለያዩ ድረ ገጾች በአስተባባሪዎቹ በኩል ተከፍተዋል፡፡ ከቀናት በፊት የተከፈተው የዩቲዩብ ቻናል ከ45 ሺሕ በላይ ሰብስክሪብሽን እንዲሁም ከ90 ሺሕ በላይ የፌስቡክ ተከታዮችን ማፍራት ችሏል፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለቤተሰቦቹ ከአገር ውስጥና ከውጭ ከ141 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡ በአዲስ አባባ ከተማ በስሙ የተሰየመ ሐውልት ግንባታው ተጠናቆ ይፋ ሆኗል፡፡
የ34 ዓመት ወጣትና የሦስት ልጆች አባት የነበረው ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል በአገሪቱ ከፍተኛ መደናገጥና አመፅን አስከትሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡