ከደረጃ በታች የሆነ ቡና ወደ ጎረቤት አገሮች እየተላከ ነው
ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውለውና በተለምዶ በተረፈ ምርት ደረጃ (Under Grade) የሚመደበውን ቡና በበቂ ሁኔታ ባለማግኘቱ፣ አባል ድርጅቶቹ መቸገራቸውን የኢትዮጵያ ቡና ቆይዎችና የተቆላ ቡና ላኪዎች ማኅበር አስታወቀ፡፡
በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም ለአገር ውስጥ ገበያ የሚውለውና ከደረጃ በታች የሚመደበው የቡና ምርት፣ በጎረቤት አገሮች ተቀባይነት አግኝቶ ለገበያ መቅረቡ ለእጥረቱ እንደ አንድ ምክንያት ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮያ ቡና ቆይዎችና የተቆላ ቡና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ምኒልክ ሀብቱ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ኤክስፖርት ከሚደረገው የቡና ምርት በደረጃ ዝቅ ብሎ የሚገኘውንና በተለምዶ በተረፈ ምርት ደረጃ የሚቀርበውን ቡና ከግብይት ማዕከሉ በበቂ ሁኔታ እየተገኘ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት በማኅበሩ የታቀፉ ከ70 በላይ ቡና ቆይ ድርጅቶች ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃቸውን አስረድተዋል፡፡
በቡና ግብይት አዋጅ መሠረት ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ቡና የሚቆሉ ድርጅቶች ቡና ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ብቻ እንዲገዙ እንደሚጠበቅባቸው ያስታወቁት አቶ ምኒልክ፣ ሆኖም በዓመት እስከ 80 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ሊቀርብ ከሚገባው የቡና አቅርቦት ፍላጎት የአገር ውስጥ ቆይዎች ከምርት ገበያው በማግኘት ላይ ያሉት ግማሽ ያህሉን ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የምርት እጥረት ብቻም ሳይሆን በተገኘው የቡና ምርት ዋጋ ላይም ከፍተኛ ጭማሪ እንዳለ ያስታወቁት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፣ ለአብነት ከሦስት ዓመት በፊት በፈረሱላ 950 ብር ገደማ ይሸጥ የነበረው ደረጃ ‹‹ለ›› ቡና በሰኔ ወር ሦስት ሺሕ ብር ገደማ እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያም ሆነ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ማኅበሩ በተደጋጋሚ እንዳሳወቀ ያስረዱት አቶ ምኒልክ፣ ጉዳዩ በጊዜ ዕልባት የማይሰጠው ከሆነ ብዙኃኑን የዘርፉ አካላት ከሥራ ከማግለሉ በተጨማሪ፣ በሌላ በኩል በሕገወጥ መንገድ የሚደረግ የቡና ንግድ እንቅስቃሴ እንዲስፋፋ በር እንደሚከፍት ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ኡመር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቡና ግብይት ሒደት በተለይም ወደ ውጭ የሚላከው ምርት ከፍተኛ እመርታ በማሳየቱ ገቢ አየተገኘ ነው፡፡ ኤክስፖርት ከሚደረገው ቡና ተርፎ ለአገር ውስጥ የቡና ቆይዎች ፍጆታ የሚውለው ቡና እጥረት መከሰቱን ለባለሥልጣኑ ከቀረቡ ጥያቄዎች እንደተረዱ አስታውቀዋል፡፡
ጥያቄውን መሠረት በማድረግ በአቅርቦቱ ሒደት ላይ ጉልህ ሚና ካላቸው የቡና ነጋዴዎች፣ ላኪዎችና የክልል የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች ኃላፊዎች ጋር በተያዘው ሳምንት አጋማሽ በጉዳዩ ላይ ባለሥልጣኑ ውይይት እንዳደረገ ገልጸዋል፡፡
ከቡና ላኪዎቹ ጋር በተደረገው ውይይት ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ቡና ግብይት ሒደት ከደረጃ በታች የሆነውን ላኪዎቹ በተቻለ መጠን ወደ ምርት ገበያ የሚያቀርቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ የአገር ውስጥ ቡና ቆይዎችም ምርቱን በማዕከሉ በበቂ ሁኔታ የሚያገኙበት ሁኔታ ለማመቻቸት ገንቢ ውይይት እንደተደረገም አስታውቀዋል፡፡
ለምርቱ እጥረት እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች አንዱ የሆነው በተለምዶ ተረፈ ምርት የሚባለውና ከደረጃ አምስት በታች የሆነው ቡና፣ ከዚህ በፊት ለአገር ውስጥ ግብይት ሲቀርብ እንደቆየና ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ሱዳን ባሉ አገሮች ተፈላጊነቱ ስለጨመረ፣ ይህም የውጭ ምንዛሪ ለአገር ከማስገኘት አንፃር የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ስለሚጫወት ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ሳቢያ መሆኑን አቶ ሻፊ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጥ ቡና የሚጠቀሙ ተቋማት ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር የራሳቸውን ሚና ስለሚጫወቱ ግብይቱን የሚመለከት መመርያ ከማዘጋጀት አንስቶ፣ ሊቀረፉ የሚገባቸውን ችግሮች ለመፍታት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ለውጭ ገበያ የሚውለው የቡና ምርት ጥራት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻሎች ስላሉ በተለምዶ ተረፈ ምርት የሚባለው የቡና ምርት በበቂ ሁኔታ እንደማይገኝ፣ ይህም ቡናን ወደ ውጭ በመላኩ ሒደት ጥሩ አስተዋጽኦ ቢያደርግም ተረፈ ምርቱን በሚፈልጉት አካላት ላይ እጥረት እንደፈጠረ ለመረዳት ይቻላል ብለዋል አቶ ሻፊ፡፡
በክልሎች ደረጃ ጉዳዩም ይፋ የተደረገ በመሆኑ ከቡና ላኪዎችና ነጋዴዎች ባሻገር የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች እንዲሁም ለአገር ውስጥ ቆይዎች የሚሆን ቡና እንዴት ማቅረብ እንደሚችሉ፣ ገንቢ ውይይት መደረጉን አክለዋል፡፡