Thursday, June 13, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የአንድ ዕለት ከፊል ጋዜጣዊ መረጃ ትረካ

በሽብሩ ተድላ

ይህ ጽሑፍ ሐምሌ 16 ቀን 1954 ዓ.ም. በዕለተ ሰኞ (Monday 23 July 1962)፣ “በኢትዮጵያ ሄራልድ ” (Ethiopian Herald) የትምህርት ቤቶች መልቀቂያ ፈተና፣ በተለምዶ “የአሥራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና” የሚባለው (Results of the Ethiopian School Leaving Certificate Examination)  በሚል ርዕስ ባሰፈረው ገለጣ ላይ የተመሠረተ ትንተና  ነው፡፡

ዘመን (ወቅት) የሕይወት ተሳትፎ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ለምሳሌ ጣሊያን ኢትዮጵያን ባትወር  ኖሮ፣ ስመጥር አርበኞች አይኖሩንም ነበር፡፡ ይህን ከገለጥኩ በኋላ  ከላይ በተጠቀሰው ጋዜጣ ላይ  በሰፈረው የፈተና ውጤት  መረጃ ላይ መሥርቼ፣ ከታሪክ አጋጣሚ ጋር አዛምጄ፣ ትረካ አቀርባለሁ፡፡ በዋናነት ደረጃ በጋዜጣው ስማቸው የሰፈረውን ግለሰቦች የፖለቲካ ተሳትፎ ሁኔታ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ ሆኖም በተጓዳኝ በዚያን ዘመን ይሰጥ የነበረውን ፈተና ዓላማ በጨረፍታ እነካካለሁ፡፡

ዳሰሳው ከእኔ የግለሰቦች እውቅና ጋር የተቆራኜ ነው፡፡ ስለሆነም የእይታው አድማስ በጣም ጠባብ ነው፡፡ ሆኖም ከሚከተለው ትንተና ስንመለከት፣ በአንድ ዕለት፣ ከፊል  ጋዜጣዊ መረጃ ጠባብ መድረክ፣ መጠነኛ ጉዳይ ማስተናገድ አንደሚቻል አመላካች ነው፡፡ በፈተና ውጤት ዝርዝር ውስጥ፣ እኔ ከማወሳቸው በተጨማሪ፣ የፖለቲካ ተሳትፎ፣ ሙያዊ ጉሉህ አስተዋፅዖዎች የነበሯቸው ግለሰቦች እንደነበሩ እገምታለሁ፡፡

በዚያ ጋዜጣ ስሞቻቸው የሰፈሩ ሦስት መቶ አሥራ ሁለት ተፈታኞች ነበሩ (መዝገቡ ሦስት መቶ አሥራ አራት ቢሆንም፣ ሁለት ስሞች ተደጋመው ተመዝግበዋል፡፡ ያንን እሳቤ ውስጥ አስገብቸ ነው ሦስት መቶ አሥራ ሁለት ብየ የወሰድኩት)፡፡ እኔ ትረካዬን የመሠረትኩት ከነሱ በሃያ ዘጠኝ ተፈታኞች ብቻ ላይ ነው፡፡ ጋዜጣው ላይ ስማቸው ስለሰፈረው ሌሎች ተፈታኞች መረጃ ቢገኝ፣ ትረካውን ከተለያዩ እቅጣጫዎች መዳሰስ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ያንን ለማድረግ ፈቃዳኛ ለሆኑ አንባብያን፣ የጋዜጣውን ኮፒ “በኢሜል” ልልክላቸው እችላለሁ፡፡

በዚያን ዓመት የአሥራ ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ አንድ ሺ አምስት መቶ ገደማ ተሳታፊዎች እንደነበሩ ግርድፍ መረጃ አለ፡፡ ከነኝህ ተፈታኞች በተለያዩ ደረጃዎች ፈታናውን ለማለፍ የቻሉ በጋዜጣው ተመዝግበዋል፡፡ እንዲሁም ተጨማሪ ትምህርት ወስደው፣ ከዚያም ተፈትነው፣ በፈተናው ውጤት ላይ ተመሥርቶ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሊገቡ የሚችሉ ተፈታኞች ስም ዝርዝር በዕለቱ ጋዜጣ ተመዝግቧል፡፡ 

በመጀመሪያ ደረጃ፣ “ረድፍ አንድ” ብዬ በሰየምኩት፣ ፈተናውን በአመርቂ ውጤት ያለፉ ተመዝግበዋል፡፡ እነሱም ፈተናውን ያለፉ በተለያዩ ደረጃዎች ነበር፡፡ ሁለት ተፈታኞች ፈተናውን በ”በጣም ከፍተኛ ማዕረግ”  (Very Great Distinction) አልፈዋል፣ የውጭ ተወላጅ ይመስላሉ፣ እነሱም  “ባኩል ራቲላል” ( Bakul Ratilal) እና “ሊዮን ጃቴ” (Leon Jatte)  ናቸው፡፡

 “በከፍተኛ ማዕረግ” (Great Distinction) ሦስት ተፈታኞች አልፈዋል፡፡ ከነሱም ውስጥ አንዷ የውጭ ተወላጅ ስም ያላት ልጃገረድ ናት (Anahid Nalbandian)፣ የሙዚቃ መምህሩ የናልባንዲያን ወንድም ልጅ መሆኗን ሰምቻለሁ፡፡   አምስት “በማዕረግ” (Distinction) ያለፉ፣ ሁሉም ያገር ቤት ስሞች ያሏቸው፤ እና ካለ ማዕረግ ያለፉ  (Passed)  ደግሞ ስድሳ ስድስት ተፈታኞች ነበሩ፡፡ ከነሱም ውስጥ የውጭ ተወላጅ ስሞች ያሏቸው ሁለት አሉ፣ “ቫሩጅ ማቩሊያን” (Varouj Mavoulian) እና “አዝኒቭ አቫኪያን” (Azniv Avakian)፡፡ በረድፍ አንድ ውስጥ (የፈተናቸው ውጤት አመርቂ የነበረ) የተዘረዘሩት ሰባ ስድስት ተፈታኞች ብቻ ነበሩ፡፡

ከዚያም በሁለተኛ ደረጃ፣ “ረድፍ ሁለት” ብዬ በሰየምኩት፣ “በድጎማ ያለፉ”  (Passed with compensation)፣ ማለት የሚፈለገውን መስፈርት ሙሉ በሙሉ ያላሟሉ፣ ሆኖም ያለምንም ተጨማሪ ፈተና ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብተው ሊማሩ የሚችሉ፣ ሠላሳ አምስት ተፈታኞች ስም ዝርዝር ይታያል፡፡ ከነሱም ውስጥ ሦስት የውጭ ተወላጅ ስሞች ያሏቸው አሉ፣ እነሱም “ኦኒግ ቦጎሲያን” (Onnig Boghossian)፣ “ሞሃመድ እስ ባሆብሺ” (Mohammed  S Bahobeshi) እና “ዮሃንስ ኤሬአና” (Yohannes Ereanna)፡፡

በሦስተኛ ደረጃ፣ “ረድፍ ሦስት” ብዬ የሰየምኩት፣ ሁለት መቶ ሦስት ፈተናው በበቂ ሁኔታ ያላለፉ፣ ሆኖም በክረምት በሚዘጋጅ የትምህርት ፕሮግራም ተሳትፈው፣ በነሐሴ መጨረሻ ፈተና ወስደው ያለፉት ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለመግባት እንደሚችሉ ተገልጧል፡፡   ከዚህም ዝርዝር ውስጥ የውጭ ተወላጅ ስሞች ያሏቸው ሦስት ግለሰቦች አሉ፣ “ሃሳን ኤለሚ” (Hassan Elmi)፣ “ማዩ ቶማስ” (Mayou Thomas) እና “ሙስታፋ ሞሃመድ ኢማም” (Mustafa Mohammed Immam)፡፡ ሦስተኛው የውጭ ተወላጅ ስም የመሰለኝ  ያልተለመደ ሦስት ቃላት ስላካተተ ነው፡፡

በአመርቂ ደረጃ ፈተናውን ካለፉት (በማዕረግ ያለፉትንም ያካትታል)፣ ምድብ አንድ፣ ሰባ ስድስት ግለሰቦች ውስጥ፣ በዛ ያሉ ግለሰቦች በተለያዩ ድርጅቶች ጠለላ፣ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ፣ የፖለቲካ  ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ከነሱም ውስጥ በቂ መረጃ ያገኘሁላቸውን ወይም በቅርብ የማውቃቸውን ብቻ አወሳለሁ፡፡ እነሱም አንድርያስ እሸቴ፣ ታረቀኝ ገብረየሱስ፣ ኃይሉ አየለ፣ ተመስገን ኃይሌ፣ ዓለም ሰገድ ሃብቱ፣ ሔኖክ ክፍሌ፣ ጠዓመ በየነ፣ ዓባይ አብርሃ፣ ታደለ መንገሻ፣ ዮሴፍ ገብረ እግዚአብሔር፣ አየለ መሸሻ፣ አዲስ ተድላ፣ ሰሎሞን በየነ እና አስፋው አየልኝ ናቸው፡፡ በተጨማሪ በጨረፍታ የዘመኑ ፖለቲካ የነካካቸውን ሦስት ወይዛዝርት አወሳለሁ፡፡ እነሱም ገነት ፍሥሐ፣ ሃና ጉተማ፣ እና ሰብለወርቅ ፍሥሐ ናቸው፡፡

ከምድብ ሁለት በድጎማ ካለፉት (Passed with compensation)  መኻል ተስፋ ደስታ እና ሸዋንዳኝ በለጠ ይገኙቸዋል (ሁለት ግለሰቦች)፡፡ በሦስተኛ ደረጃ፣ “ረድፍ ሦስት” ብዬ የሰየምኩት፣ በክረምት በሚዘጋጅ የትምህርት ፕሮግራም ተሳትፈው፣ በነሐሴ መጨረሻ ፈተና ወስደው ያለፉትና ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከገቡት፣ ጉልህ  የፖለቲካ  ተሳትፎ፣ ወይም ጉልህ ሙያዊ  አውቅና የነበራቸውን እማወሳቸው ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ ገብሩ መርሻ፣ ታዬ አበጋዝ፣ ከበደ ውብሸት፣ መስፍን አበበ፣ መዝገበ በየነ፣ አልማዝ ወንድሙ፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ፣ ጌታቸው ጳውሎስ፣ እና መዓዛ ቅጣው ናቸው (አሥር ግለሰቦች)፡፡

ዝርዝር ገለጣ አነሆ፡፡

በከፍተኛ ማዕረግ ያለፉት ሁለት የአገር ቤት ስያሜ ካሏቸው አንዱ አንድርያስ እሸቴ፣ በሰሜን አሜሪካ ከታወቁ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቆ፣ አዚያው በአሜሪካ በተለያዩ ስመጥር ዩኒቨርሲቲዎች ለዘመናት አስተማሪ ነበር፡፡ አንድርያስ እሸቴ በሰሜን አሜሪካ ተማሪዎች ማኅበር ከፍተኛ ተሳትፎ ነበረው፣ ከፍተኛ ተደማጭነትም አትርፎ ነበር፡፡ ከአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ጋር  በጣምራ ለመሥራት ከሚሞክሩት አንዱ ተራማጅ ተማሪ ነበር፡፡ በነሐሴ 1960 ዓ.ም. በሃምቡርግ (ጀርመን አገር) በተካሄደ ስብሰባ ላይ ከሰሜን አሜሪካ ተማሪዎች ማኅበር ተሳታፊዎች የነበሩት እሱ፣ ዓለምሰገድ ሃብቱ፣ ደሳለኝ ራህመቶ፣ ኃይሌ መንቆሪዮስ፣ ታምራት ከበደ እና ሔኖክ ክፍሌ ነበሩ፡፡ ከነሱም ውስጥ ሦስቱ (ዓለምሰገድ ሃብቱ፣ ሄኖክ ክፍሌ፣አንድርያስ እሸቴ) የዚያን ዓመት ተፈታኞች ነበሩ፡፡

አንድርያስ እሸቴ፣ በዘመነ “ኢሕአዴግ” ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪነት፣ ብሎም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግሏል፡፡ ዩኒቨርሲቲውን ሲለቅ  በሚኒስትር ማዕረግ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ (መለስ ዜናዊ) አማካሪ ሆኖ ነበር፡፡ አንድርያስ እሸቴ በፖለቲካዊ አስተሳሰቡ፣ የሚያደንቁት ግለሰቦች እንዳሉ መጠን በተቃራኒ  ሁኔታ የሚፈርጁት፣ የሚወቅሱት አሉ፡፡

ሁለተኛው ታረቀኝ ገብረየሱስ፣ ከቀኃሥ ዩኒቨርሲቲ እንደተመረቀ፣ በሰኮላርሽፕ ድጋፍ ስታንፈርድ ዩኒቨርሲቲ ተምሮ ፒኤችዲ ካገኘ በኋላ፣ ኬንያ በሚገኝ አንድ የምርምር ተቋም ውስጥ በምርምር ላይ ተሠማርቶ ነበር፡፡ ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስ ፋካልቲ በኬሚስትሪ እስተማሪነት ለዘመናት አገልግሏል፡፡ ታረቀኝ ገብረየሱስ፣ በደርግ ዘመን መባቻ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ማኅበር ለሁለት ሲከፈል፣ ያፈንጋጩ (የተራማጁ) “ፎረም” በመባል የሚታወቀው ስብስብ አባል ነበር፣ እኔም የዚያ ስብስብ አባል ነበርኩ፡፡

ዋናው የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማኅበር ከሁለት መቶ በላይ አባላት ሲኖሩት፣ የ”ፎረም”  አባል የነበሩ አሥራ ስምንት መምህራን ብቻ ነበሩ፡፡ ብዙዎች የፎረም አባሎች ከፍተኛ የፖለቲካ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ በዚያም መንስዔ በደርግ ዘመን፣ በመንግሥት ተቃራኒ ወገን የተገደለ፣ በመንግሥት የተገደሉ፣ የታሰሩ፣ የተሾሙ፣ መንግሥትን የወጉ፣ የተሰደዱ ይገኙባቸዋል፡፡ የዚያን ዘመን የፖለቲካ ግንዛቤን ይረዳ ዘንድ፣ ፎረሙ “ተራማጅ መዘገበ ቃላት” በሚል ርዕስ አንድ መዝገበ ቃላት አሳትሞ ነበር፡፡

በማዕረግ ካለፉት አምስት ግለሰቦች፣ አንዱ ኃይሉ አየለ ለዘመናት “ኤንጂኔሪንግ ፋካልቲ” በአስተማሪነት እንዲሁም በተለያዩ ኃላፊነቶች፣  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል የአካዳሚ ፕሬዚዳንት ሆኖም አገልግሏል፡፡ ኃይሉ አየለ “ዩዝዋ” (University Students Uninion of Addis Ababa-USUAA) ሲመሰረት የመጀመሪያ ፀሐፊ ሆኖ ማኅበሩን መርቷል፡፡ ከዚየም እሱ ከሌሎች የተማሪዎች ማኅበር መሪዎች ከነበሩ ጋር ታስሮ ነበር (ሌሎቹ መስፍን ካሱ፣ ዓባይ አብርሃ- “ኒዩስ” National Union of Ethiopian Students-NUEUS -ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚደንቶች፣ እና  የተማሪዎች መጽሔት የ”ስትራግል” ኤዲተር  ተመስገን ኃይሌ ነበሩ)፡፡ በድምሩ አራት ተማሪዎች ታስረው ነበር፣  ከነሱም ውስጥ ሦስቱ (ማለት ተመስገን ኃይሌ፣ ዓባይ አብርሃ እና ኃይሉ አየለ) የዚያን ዓመት  ፈተና ተፈታኞች ነበሩ፡፡

የጂኦሎጂ ምሩቅ የነበረው ተመስገን ኃይሌ፣ በኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት፣ ከኤርትራ ሽምቅ ተዋጊዎች ግንኙነት አለህ (አባል ነህ) ተብሎ ተይዞ በመርምራ ላይ እንዳለ፣ የመኖሪያ ቤቱን ለማስፈተሸ መስቀል አደባባይ አካባቢ ወደ ሚገኝ አፓርትማ (አንበሳ ሕንፃ) ተወስዶ ነበር፡፡ ቤቱ በመፈተሽ ላይ እንዳለ፣ ከፖሊሶች አምልጦ (በቅርብ የማውቀው እዚያው የነበረ የሕዝብ ደኅንነት አባል እንደነገረኝ)፣ ከፎቅ ዘሎ ራሱን አጠፋ፡፡ በተራማጅ ተማሪዎች አካባቢ “የክሮኮዳይል” ህቡዕ ድርጅት መሥራች ነበር ተብሎ ይታማል፣ መሥራቹ ገብሩ ገብረወልድ ነበረ የሚሉም አልጠፉም፡ ተወያይተው በጋራ “ክሮኮዳይልን”  መሥርተውት ይሆናል)፡

ዓለምሰገድ ሃብቱ በሰሜን አሜሪካ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሚና የነበረው ነበር፡፡ የፖለቲካን ንቃት ለማዳበር ዓላማ የነበራቸው ብዙ ጽሑፎችን በማበርከት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በ1960 ዓ.ም. ሃምቡርግ በተካሄደው ስብስባ፣ የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን ማኅበር ወክሎ ተሳታፊ ነበር፡፡ እንዲሁም፣ በአሜሪካ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች በሰኔ 30 ቀን 1961 ዓ.ም. በዋሽንግተን የሚገኘውን የኢትዮጵያን ኤምባሲ ሲወሩ፣ ቀዳሚ ተሳታፊ ነበር፡፡ በዚያ መንስዔ ለሳምንታት በዋሽንግተን ወህኔ ቤት ታግቶ ነበር፣ እኔም እዚያው ነበርኩ፡፡ ዓለምሰገድ ሃብቱ በኒው ዮርክ ከተማ በሚገኝ የኒው ዮርክ ሲቲ ዩኒቨርሲቲ (City University of New York) በአስተማሪነት ለዘመናት ተሳትፏል፡፡

ሔኖክ ክፍሌ ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በሰሜን አሜሪካ የነበሩ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ነበረው፡፡ በ1962 ዓ.ም. በገነፈለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ንቅናቄ፣ የገንዘብ ድጋፍ ታበረክታለችሁ፣ እጃቸሁ አለበት ተብለው፣ ተፈርዶባቸው ወደ ወህኒ ቤት ከወረዱት ተራማጅ ግለሰቦች አንዱ ነበር (ሌሎቹ ወርቁ ፈረደ እና ታምራት ከበደ ነበሩ)፡፡ ምንም አንኳን እያንዳንቸው የሰባት ዓመት እስራት ቢበየንባቸውም፣ በምሕረት ከወራት በኋላ ከወህኒ ቤት ለመውጣት ችለዋል፡፡  ሔኖክ ክፍሌ በመጀመሪያ ጭላሎ ልማት ድርጅት ውስጥ (አርሲ)፣ ከዚያም ለዘመናት በአንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ሠርቷል፡፡

ጠዓመ በየነ የሕግ ባለሙያ ሲሆን፣ በኃይለ ሥላሴ መንግሥት መቋጫ አካባቢ፣ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን በአባልነት ተሳታፊ ነበር፡፡ ከዚያም ወደ ኤርትራ ሄዶ በሙያው (ሕግ) የኤርትራን መንግሥት በተለያዩ ደረጃዎች አገልግሏል፡፡

ዓባይ አብርሃ በቀኃሥ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበረው ተማሪ ነበር፡፡ የዩዝዋ (USUAA) ምክትል ፕሬዚዳንት ነበር፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በዚያ ምክንያት ከሌሎች ጓዶቹ ጋር ታስሮ ነበር፡፡  በ1950ዎች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ወክሎ (ከፍሥሐ ባይህ ጋር ይመስለኛል) በዓለም አቀፍ የተማሪዎች ስብሰባ ለመሳተፍ፣  ወደ ሞንጎሊያ  ዑላን  ባቶር ከተማ (Ulan Bator) ሄዶ ነበር፡፡

እኔ በዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ ሽሬ እንዳሥላሴ በነበርኩበት ዘመን፣ እሱም አዚያው አካባቢ የልማት ሠራተኛ ስለነበረ ብዙ ጊዜ እንገናኝ ነበር፡፡ ከዚያም በኢሕአፓ አባልነቱ የደርግን መንግሥት ተቃውሞ፣ በጎንደር ክፍለ ሃገር በሽምቅ ውጊያ በመሳተፍ ላይ እንዳለ ተሰዋ፡፡ ሞቱን ለበላይ አካል ለማብሰር፣ በክፍለ ሀገሩ የደርግ አባል ሹም በገብረሕይወት ትዕዛዝ፣ አንገቱ ተሰይፎ ለእይታ ወደ ጎንደር ከተማ ተወስዶ እንደነበረ ሰምቻለሁ፡፡

ታደለ መንገሻ  የጤና መኰንን ሲሆን፣ በዘመነ ደርግ “የወዝ ሊግ” አባል ሆኖ የፖለቲካ ተሳታፊ ነበር፡፡ በደርግ መንግሥት በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ሠርቷል፣ ለምሳሌ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በምክትል ሚኒስትርነት፣ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒሰቴር በሚኒስትርነት አገልግሏል፡፡

ዮሴፍ ገብረእግዚአብሔር (የስብሐት ገብረእግዚአብሔር እና የተወልደ ገብረእግዚአብሔር ታናሽ ወንድም) የሕግ ምሩቅ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፋካልቲ አባል ሆኖ ዩኒቨርሲቲውን በተለያዩ ላፊነት ደረጃዎች  አገልግሏል፡፡ ከዚያም በዘመነ ደርግ የሪፐብሊኩ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሆኖ በኃላፊነት ተሳትፏል፡፡

አየለ መሸሻ በባህር ዳር ከተማ የነበረውን የመምህራን ማሠልጠኛ ተቋም (ፔዳጎጂ) በኃላፊነት  መርቷል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተዘዋወረ በኋላ፣ ለዘመናት የሬጅስትራሩን ክፍል በኃላፊነት ይመራ ነበር (የሬጅስትራሩ ቢሮ ትልቅ ኃላፊነት ያለው የዩኒቨርሲቲው አካል ነው፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ ማስገባት የሚያበቃውን የበር ቁልፍ ሆነ፣ የዩኒቨርሲቲውን ትምህርት አጠናቀው ምሩቅ ሆነው የሚወጡበትን በር ቁልፍ -ሁለቱም ቁልፎች- ሬጅስትራሩ መዳፍ ውስጥ ነው የሚገኙት)፡፡

አየለ መሸሻ በደርግ ዘመን መባቻ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ማኅበር ለሁለት ሲከፈል፣ ያፈንጋጩ (የተራማጁ) “ፎረም” በመባል የሚታወቀው ስብስብ አባል ነበር፡፡ በተጨማሪም  ለዓመታት የከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን ስኮላርሽፕ ኮሚቴ ሊቀመንበር ነበር፣ በአስተማሪነትም አዲስ አበባ  ዩኒቨርሲቲን  አገልግሏል፡፡

በአመርቂ ደረጃ ፈተናው ካለፉት ስብስብ ውስጥ በደርግ ዘመነ መንግሥት ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው፣ አዲስ ተድላ የዚያን ዘመን ፈተና ያለፈ ነበር፡፡ አዲስ ተድላ የአየር ኃይል  ሱፐር ሶኒክ ጀት አብራሪ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ከኤንጅኔሪንግ ፋካልቲ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በሜካኒካል ምሕድስና ምሩቅ ነው፡፡ አዲስ ተድላ የደርግ (የሠራተኛው ፓርቲ) የፖሊት ቢሮ፣ እንዲሁም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበር፡፡

አዲስ ተድላ በልዩ ልዩ ኮሚቴዎች ሰብሳቢነት፣ በምርት ዘመቻ ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ሊቀመንበርነት (ዋናው ሊቀመንበር ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ነበሩ) ተሳታፊ ነበር፡፡ ከግንቦት 1981 ዓ.ም. የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ፣ በሌተና ጀኔራል ማዕረግ የመከላከያ ሠራዊት የበላይ ሹም ነበር፡፡ የደርግ መንግሥት ከወደቀ  በኋላ፣ በጣሊያን ኤምባሲ ግቢ ውስጥ የአገር ቤት ስደተኛ ሆኖ፣ ለሠላሳ ዓመት ገደማ አሳልፎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ነፃ አየር በመተንፈስ ላይ ይገኛል፡፡

በዚያው ዘመን በዚሁ ምድብ ፈተናውን ያለፉ ሁለት ከፍተኛ የአየር ኃይል መኮንኖች አሉ፡፡ አንዱ ሰለሞን በየነ በብርጋዲየር ጀኔራል ማዕረግ የኢትዮጵያ አየር ኃይልን አገልግሏል፡፡ ሰለሞን በየነ  በግንቦት የመንግሥት ፍንቀላ ሙከራ ጊዜ አስመራ ነበር የሚገኝ፡፡ በአስመራ የነበሩ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ሁሉ ሲገደሉ፣ በስልት ከመገደል ያመለጠ ገለሰብ ነው (እሱ እንደሚለው “በስድስተኛው ሴንሱ” ተጠቅሞ ነበር ከመገደል የተረፈ)፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰለሞን በየነ በሽማግሌ ደረጃ፣ በእርቅ መድረክ ተሳታፊ ሆኗል (ከሰለሞን በየነ ጋር ኮተቤ ለሦስት ዓመታት አንድ አዳሪ ትምህርት ቤት ነበርን)፡፡

አስፋው አየልኝ (ኮሎኔል) የአየር ኃይል በራሪ መኰንን ሲሆን፣ በደርግ ዘመን በኬንያ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክሎ፣ በሚሊታሪ አታሼነት አገልግሏል፡፡ ከዚያም በዓለም አቀፍ ድርጅት ተቀጣሪ ሆኖ ተሰማርቶ ነበር፡፡

በአመርቂ ሁኔታ ፈተናውን ካለፉት ውስጥ “በንከኪ” (በባለቤቶቻቸው ምክንያት) የፖለቲካ ተሳትፎ የነበራቸው ሦስት ወይዛዝርት አሉ፣ እነሱም ገነት ፍሥሐ (የባለቤቴ ታላቅ እህት፤ የኢዲዩ መሥራች አባል የነበረው የደረጀ ደሬሳ ባለቤት)፤ ሃና ጉተማ  (የወዳጄ የያህይራድ ቅጣው ባለቤት/ ያየህይራድ ሰፋ ያለ የፖለቲካ ተሳትፎ ነበረው) እና ሰብለወርቅ ፍሥሐ (የእኔ ባለቤት) ናቸው፡፡ ለትንተናው መሠረት ለሆነው ዕለታዊ ጋዜጣ በእጄ መግባት ምክንያት የሆኑት ባለቤቴ እና ታላቅ እህቷ ናቸው፡፡

 ከዚያም በሁለተኛ ደረጃ፣ “ረድፍ ሁለት” ብዬ በሰየምኩት፣ በድጎማ ያለፉ  (Passed with compensation) ሠላሳ አምስት ግለሰቦች ስም ዝርዝር አለ፡፡ በድጎማ ካለፉት መኻል ተስፋ ደስታ (ብርጋዲየር ጀኔራል) በደርግ ዘመን በአየር ኃይል ከፍተኛ መኰንን የነበረ፣ በ1981 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት መንስዔ ታስሮ አንድ ዓመት ከቆየ በኋላ፣ በሞት የተቀጣ ከፍተኛ መኰንን ነበር፡፡ 

በዚሁ በድጋፍ መልክ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለመግባት የቻለው ሸዋንዳኝ በለጠ፣ በደርግ ዘመን ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን የነበረው ግለሰብ ሲሆን፣ “የኢሠፓኮ” እና “የኢሠፓ ፖለቲካ ቢሮ ተለዋጭ አባል ነበር፡፡ ሽዋንዳኝ በለጠ የጎንደር ጤና መኰንን ምሩቅ ሲሆን፣ በትምህርቱ ንቁ ተሳትፎ እንደነበረው እና ጥሩ ውጤት ያመጣ እንደነበረም ይወሳል፡፡ ሸዋንዳኝ በለጠ በኢሕአዴግ መንግሥት ለዘመናት እስር ቤት እንዲቆይ ተደርጓል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ፣ “ረድፍ ሦስት” ብዬ የሰየምኩት፣ ሁለት መቶ ሦስት ፈተናውን በበቂ ሁኔታ ያላለፉ፣ ሆኖም በክረምት በሚዘጋጅ የትምህርት ፕሮግራም ተሳትፈው፣ በነሐሴ መጨረሻ ፈተና ወስደው፣ ያለፉትና ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከገቡት፣ ጉልህ የፖለቲካም ተሳትፎ፣ ወይም ጉልህ ሙያዊ አስተዋፅዖ የነበራቸውን አወሳለሁ፡፡

በዚህ ምድብ ከሚገኙ ከሁሉም ዝነኛው ብርሃነ መስቀል ረዳ ነው፡፡ ስለ ብርሃነ መስቀል ረዳ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በቂ መረጃ እንዳላቸው እገምታለሁ፡፡ በቀኃሥ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አንቅስቃሴ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበረው፣ የተማሪዎችን ፖለቲካዊ  እንቅስቃሴ የመራ፣ የብዙዎቹን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የቃኜ፣ የነቃ፣ ወጣት ነበር፡፡  ከጓዶቹ ጋር ሆኖ አይሮፕላን ጠልፈው ከወጡ በኋላ፣ በሽምቅ ውጊያ ሠልጥነው ተመልሰው በአሲምባ ተራራዎች ከሸመቁት አንዱ የኢሕኣፓ መሪ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ በህቡዕ ሲንቀሳቀስ ሰነባብቶ፣ በሰሜን ሸዋ አዲስ ግንባር ክፍቶ ሲታገል፣ ተይዞ የተገደለ ወጣት ነበር፡፡

ገብሩ መርሻ በቀኃሥ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነቁ ተሳትፎ ነበረው፡፡ ጥላሁን ግዛው በተገደለ ማግስት በነበረው ከፍተኛ የተማሪዎች ተቃውሞ፣ ፖሊስ በጣም አደገኛ ብሎ ከመዘገባቸው ሃያ ሰባት ተማሪዎች አንዱ ገብሩ መርሻ ነበር፡፡ በዚያም መንሥዔ ለእስራት ተዳርጓል፡፡ ሌሎች ስማቸው ከታወቁት መኻል፣ ዋለልኝ መኰንን፣ ተካልኝ ወልደ አማኑኤል እና ይርጋ ተሰማ ይገኙባቸዋል፡፡

ገብሩ መርሻ በደርግ ዘመን መባቻ የመንግሥት ሹም የነበረ፣ ከዚያም በኢሕአፓ አባልነት አሲምባ የገባ፣ ደርግን የወጋ ታጋይ ነበር፡፡ ኢሕአፓ ከትግል ረድፍ ስትወጣ፣ ወደ እውሮፓ ተሰዶ ኖሮ፣ የደርግ መንግሥት ሲወደቅ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት አገልግሏል፡፡

መስፍን አበበ በኢሕአዴግ መንግሥት ሚኒስትር የነበረ፣ ለዘመናት “ሃሮማያ” (አለማያ) በመምህርነት፣ በተመራማሪነት ያገለገለ ግለስብ ነው፡፡ በሙያውም፤ ማለት በአፈር ጥናት/ ተመራማሪነት አንቱ የተባለ ግለሰብ ነው፡፡

ታዬ አበጋዝ የዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረ በደርግ ዘመን መባቻ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ማኅበር ለሁለት ሲከፈል፣ ያፈንጋጩ (የተራማጁ) “ፎረም” በመባል የሚታወቀው ስብስብ አባል ነበር፡፡  ታዬ አበጋዝ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ውሎ የተገደለ ግለሰብ ሲሆን፣  እሥራቱ ብሎም የሞት ቅጣቱ፣ በወዝ ሊግ (እሱ የወዝ ሊግ አባል አንደነበረ ይወራል) እና በሰደድ መኻል ተክስቶ የነበረው ውዝግብ መንስዔ እንደነበረ እጠረጥራለሁ፡፡

ፀጋዬ ደመወዝ የኤንጂኔሪንግ ፋካልቲ ምሩቅ ሲሆን፣ አውራ ጎዳና መሥርያ ቤትን በመሐንዲስነት ለዘመናት አገልግሏል፡፡ ከዚያም የኢሕአፓ አባል ሆኖ በተአምር ከመገደል ተርፎ ተሰደደ፡፡ በስደት ዘመን የሕወሓት ደጋፊ ሆኖ ነበር፡፡ በ1980 ዓ.ም. በሳባቲካል ዚምባብዌ ዩኒቨርሲቲ ሳስተምር በነበረኩበት ዘመን፣ እሱ የከተማው (የሃራሬ) ምክትል ዋና መሐንዲስ ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡ ዚምባብዌ በነበርኩበት ዘመን ከዚያም በኋላ ብዙ ጊዜ እንገናኝ ነበር፡፡ የደርግ መንግሥት ከፈረሰ በኋላ፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የሱር ኮንስትራክሽን ማኔጀር  ሆኖ ሠርቷል፡፡

ከበደ ውብሸት በሰሜን አሜሪካ የተማሪዎች ንቅናቄ ተሳትፎ የነበረው፣ በኤምባሲ ወረራ ጊዜም (ሰኔ ሠላሳ 1961 ዓ.ም.) ከወራሪዎች አንዱ ሆኖ የታሰረ ግለሰብ ነበር፡፡ ከበደ ውብሸት ከሰሜን አሜሪካ አንድ ከማላስታውሰው ዩኒቨርሲቲ በመሐንዲስነት ተመርቆ፣ አገር ቤት ተመልሶ የደርግ መንግሥት እንደፈረሰ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ያገለግል ነበር፡፡

በዚሁ ረድፍ ውስጥ የነበሩ ጌታቸው ጳውሎስ እና አልማዝ ወንድሙ ጉልህ ባይሆንም ፖለቲካዊ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ አልማዝ ወንድሙ ከተራማጅ ሴት ተማሪዎች አንዷ ነበረች፡፡  በደርግ መንግሥት መባቻ፣ በደርግ አንድ ድርጅታዊ መዋቅር ተሳታፊ ነበረች፣ ሆኖም ከደርግ ጋር ብዙም አልዘለቀችም፡፡

ጌታቸው ጳውሎስ አውሮፓ የሚገኙ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር አባል ሆኖ፣ ቪየና ኦስትርያ በነሐሴ 1957 ዓ.ም. በተደረገው የተማሪዎች ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ነበር፣ እኔም እዚያው ነበርኩ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ በጭላሎ ልማት ድርጅት፣ እንዲሁም በግብርና ሚኒስቴር (ኤፒድ) ለብዙ ዘመን ሠርቷል፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ፣ አንድ የግል ጋዜጣ ‹‹ዕይታ›› የምትባል ማዘጋጀት ጀምሮ ነበር፣ ግን ያ ተግባር በተለያዩ ምክንያቶች ብዙ አልዘለቀም፡፡ ጌታቸው ጳውሎስ ደራሲ ነው፣ ብዙ መጻሕፍትን አሳትሟል፡፡

ጌታቸው ወልደሥላሴ ከታወቀው “የጆርጅያ ቴክ” ምሩቅ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “በኮምፒዩተር” ክፍል ኃላፊነት ለዘመናት አገልግሏል፡፡ መዓዛ ቅጠው በብሔራዊ ሎተሪ የበላይ ኃላፊነት ላይ ሆና መንግሥትን ለዘመናት አገልግላለች፡፡

ስለሆነም የዚያን ዓመት አሥራ ሁለተኛ ፈተና መልቀቂያ ተፈታኞች፣ በተማሪዎች እንቅስቃሴም ሆነ፣ በደርግ ዘመን፣ ወይም ከዚያ በኋላ በነበረ ፖለቲካዊ መድረክ ጉልህ ተሳትፎ ወይም ትልቅ ኃላፊነት የነበራቸው ግለሰቦች ነበሩ፡፡

ከዚህ ቀጥዬ ከላይ በመግቢያው እንደገለጥኩት፣ በዚያን ዘመን ይሰጥ የነበረውን ፈተና ዓላማ ለመተቸት እፈልጋለሁ፡፡ የፈተናውን ውጤት በግርድፉ ስንመለከት፣ እና ተፈታኞቹ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ የነበረውን ሁኔታ ስንዳስስ፣ የዘመኑን የአሥራ ሁለተኛ  ክፍል መልቀቂያ  ፈተናን፣ የትምህርት የመከታተል ብቃት መለኪያነት፣ ጥርጣሬ ላይ ይጥለዋል፡፡   ፈተናው ወደፊት ትምህርት የመከታተልን አቅም፣ ብቃት፣ መለኪያነቱ አስተማማኝ  ነው ወይ?  ያስብላል፡፡ ምክንያቱም በምድብ ሦስት ከታቀፉት ተፈታኞች፣ አስቸጋሪ ናቸው ተብለው በሚታሰቡ የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ክፍሎች (ለምሳሌ ኤንጅኔሪንግ ፋካልቲ) ገበተው ለመመረቅ በቅተዋል፡፡ በዚህ ምድብ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ፣ በምድብ አንድ እና ሁለት ከተጠቀሱት ተመሳሳይ ውጤት ያመጡ ብዙ ነበሩ፡፡ ከተመረቁ በኋላ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ተመድበው አገርን አገልግለዋል፡፡ ለምሳሌ መዝገበ በየነ ከኤነጂኔሪነግ  ፋካልቲ  ተመርቆ የትራንስፖርት ዘርፍ በኃላፊነት  ሠርቷል፡፡

በተጨማሪም የፈተናው ውጤት ከእንግሊዝኛ በቋንቋ ክህሎት ተመሥርቶ ያጋደለ ይሆን? የሚሉ መሰል ጥያቄዎችን ልናወሳ ይጋብዘናል፡፡ በበጣም ከፍተኛ ማዕረግ ያለፉት ሁለቱም  ተፈታኞች፣ በከፍተኛ ማዕረጉ ካለፉት ሦስት ተፈታኞች አንድ፣ በአመርቂ ሁኔታ ካለፉት ስድሳ ስድሰት ተፈታኞች ሁለቱ የውጭ ተወላጅ ስሞች ያሏቸው ናቸው፡፡ በጥቅሉ ከሰባ ስድሰት ፈተናውን በአመርቂ ሁኔታ ካለፉት (በማዕረግም ሆነ ካለማዕረግ) ስድስቱ የውጭ ተወላጅ ስሞች ያሏቸው ናቸው፡፡

ይህን ጥያቄ ላነሳ የተገደድኩ የውጭ ተወላጅ ስሞች ያሏቸው በአማካይ የተሻለ የእንግሊዝኛ ክህሎት ይኖራቸው ይሆን በሚል እሳቤ ላይ ተመርኩዤ ነው (የውጭ ዜጋ  ግለሰቦች ልጆች፣ በአንፃራዊነት ክፍያው ከፍ ያለ ከነበረው ሳንፎርድ ትምህርት ቤት ነበር የሚማሩ)፡፡

ለምሳሌ ከናዝሬት ትምህርት ቤት ከአሥራ ሁለት ተፈታኞች፣ አንድ በከፍተኛ ማዕረግ ያለፈች (Anahid Nalbandian)፣ ሦስት በአመርቂ ሁኔታ ያለፉ (Pass) እና ሁለት በድጎማ ያለፉ (Pass with Compensation) ይገኙባቸዋል፡፡ ስለሆነም በውጤት ላይ ተመሥርቶ፣ ከአሥራ ሁለት ተፈታኞች ስድስቱ ያለምንም ተጨማሪ ሁኔታ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብተው ለመማር ይችላሉ፣ ያም አምሳ በመቶ (50%)  ነው፡፡  በአገር  ደረጃ ሲታይ ከሺ አምስት መቶ ገደማ ተፈታኞች፣  ያለምንም  ተጨማሪ ሁኔታ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ለመማር የሚችሉ  ሰባ ስድሰት ብቻ ነበሩ፣ ያም አምስት በመቶ (5%) ገደማ ነው፡፡ 

የናዝሬት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ፣ ከሌሎች  በተለይ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ነበር፡፡ በዚያን ዘመን ፈተናው በማጥቆር ሳይሆን በጽሑፍ ነበር የሚስተናገድ፣ ያም ከፍተኛ የእንግሊዝኛ እውቀት  ይጠይቃል፡፡  ሆኖም የትምህር አሰጣጡም ከሌሎች የተሻለ እንደነበረ ይገመታል፡፡

ለዘመኑ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ዋና ግብዓት የነበረው የዓለም አቀፍ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እንደነበረ ይገመታል፡፡ በዚያን ዘመን የአሜሪካ በቪየትናም ጉዳይ ጣልቃ ገብነት እና ብሎም የግፍ ጭፍጨፋ፣ ዓለም አቀፍ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንቅናቄ ተጧጡፎ ነበር፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ የዕለት ተዕለት ተግባር ሆኖ ነበር፣ በተለይ በሰሜን አሜሪካና በፈረንሳይ፡፡ የ”ሮዴዚያ” (ያሁኗ ዚምባብዌ)፣ የደቡብ አፍሪካ፣ ለአገር ቤት የተማሪዎች እንቅስቃሴ እርሾ ሆኖ ነበር፡፡ በዚያን ዘመን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግራ ዘመም የፖለቲካ ይዘት፣ በአገራችን ፖለቲካ እይታ ላይ ትልቅ አሻራ አሳርፎ አልፏል፡፡

በአገር ላይ ጥሎት ካለፈው የለውጥ እንቅስቃሴ ተፅዕኖ ገና ለመገላገል አልቻልንም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተስፋ ጭላንጭሎች ቢታዩም (ንጉሣዊው ሥርዓት ሲገረሰስ፣ የደርግ መንግሥት ሲፈርስ፣ የሕወሓት ስውራዊ አገዛዝ ሲከላ)፣ ደመናው አሁንም እንዳንዣበበ ይገኛል፡፡  ደመናው ወደ ዝናብነት ተቀይሮ፣ ዘንቦ፣ አባርቶ፣ ውኃው ለልማት ግብዓትነት ይውላል የሚል ምኞት አለኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው  ሽብሩ  ተድላ  (ፒኤችዲየአዲስ  አበባ  ዩኒቨርሲቲ  የባዮሎጂና  የፓራሲቶሎጂ  ልሂቅ  (ኢመረተስ)  ፕሮፌሰር  ሲሆኑ፣  በርካታ  የጥናትና  ምርምር  ሥራዎቻቸውን  አሳትመዋል፡፡  ካሳተሟቸው መጻሕፍት መካከል  ማኅበራዊና  ሰብዓዊ  (ሶሺያል  ኤንድ  ሂዩማኒስትጉዳዮችን  በጥልቀት  ያቀረቡበት ከጉሬዛም  ማርያም  እስከ  አዲስ  አበባ  የሕይወት  ጉዞ  እና  ትዝታዬ  የተሰኘው  ይገኝበታል፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles