Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ 34 አትሌቶች ተለዩ

በቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ 34 አትሌቶች ተለዩ

ቀን:

የሳምንታት ዕድሜ የቀረው የ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ተሳታፊ አገሮች ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ይገኛሉ፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ተራዝሞ የነበረው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ አትሌቶች በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ ረድቷችዋል፡፡ በቂ የዝግጅት ጊዜ ከማግኘት ባሻገር በተለያዩ ዓለም አቀፍ ማጣሪያ ውድድሮች ላይ መሳተፍ የሚችሉበትን አጋጣሚም ነበራቸው፡፡

በተለይ በኦሊምፒክ ቅድመ ማጣሪያ ውድድር ወቅት በርካታ አትሌቶች በተለያዩ መድረኮች ላይ ሰዓታቸውን ከማሻሻል ባለፈ፣ አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችለዋል፡፡  ለስምንት ወራት የዘለቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን ዝግጅትም፣ ወደ ጃፓን ለማቅናት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡

ሐሙስ ሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቶኪዮ 2020 (2021) ዝግጅትን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ  አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዜዳንት  ደራርቱ ቱሉ  እንዲሁም የሥራ አስፈጻሚ አባላት በተገኙበት ስለወቅታዊ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት እንዲሁም ወደ ቶኪዮ የሚያመሩ የመጨረሻ አትሌቶችን ስም ዝርዝር ይፋ አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ከወንዶች 800 ሜትርና ከዕርምጃ በስተቀር በሌሎቹ ርቀቶች ላይ ስትወከል  በሁለቱም  ፆታ ተወክላለች፡፡ እንደ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማብራርያ ከሆነ ምንም እንኳ 38 አትሌቶችና ለማስመረጥ በዕቅድ ቢያዝም፣ አንዳንድ ርቀቶች ላይ አትሌቶች ሰዓት ማሟላት ባለመቻላቸው ምክንያት የታቀደው ቁጥር አለመሳካቱን አስረድቷል፡፡

ከኅዳር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ  ዝግጅት ሲያደርጉ የሰነበቱትና ማጣሪያውን ያለፉ 34 አትሌቶች ወደ ቶኪዮ የሚያመሩ ይሆናል፡፡ በሁሉም ርቀት ላይ ሦስት አትሌቶች የተመረጡ ሲሆን፣ አንዳንድ ተጨማሪ አትሌቶች በተጠባባቂነት ተይዘዋል፡፡

በወንዶች 10 ሺሕ ሜትር ላይ በዋነኛነት አገሩን የሚወክለው ሰሎሞን ባረጋ፣ 5000 ሜትር ላይ ተጠባባቂ ሆኖ ሲያዝ በተመሳሳይ ርቀት ላይ የሚወዳደረው ጌትነት ዋለ፣ 3000 ሜትር ላይ ተጠባበቂ ሆኖ ያመራል፡፡

በሴቶች የ5000 ሜትር ተወዳዳሪዋ ጉዳፍ ፀጋይ፣ በ10,000 ሜትር ርቀት ላይ በተጠባባቂነት ተይዛለች፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ብሔራዊ ቡድኑ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፣ ለዝግጅቱም ይረዳ ዘንድ ክልሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም  ከተለያዩ ተቋማት  የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

ኦሊምፒክ ኮሚቴው የመጨረሻዎቹን አትሌቶች ስም ዝርዝር ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ለዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ የሚልክ ሲሆን፣ የመጨረሻዎቹንም ተጓዥ  አትሌቶች ስም ዝርዝር ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ ሆኖ እንደሚወስን አስታውቋል፡፡

አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለቶኪዮ ኦሊምፒክ አትሌቶችን በብቃት የሚያዘጋጁ 17 አሠልጣኞች ከኅዳር 2 ጀምሮ ሥልጠና ሲሰጡ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ በመጨረሻም በሄንግሎ ማጣሪያ ሁለትና ከሁለት በላይ አትሌቶችን ያስመረጡ አሥራ አንድ አሠልጣኞች አትሌቶቻቸውን ይዘው በቶኪዮ እንደሚሳተፉ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አብራርቷል፡፡

የመጨረሻ ስም ዝርዝር በተላለፈ በኋላ ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ክፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችና የስፖርቱ ቤተሰብ በተገኘበት አሸኛኘት እንደሚደረግላቸው ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ ባሻገር በብስክሌት፣ በወርልድ ቴኳንዶ እንዲሁም በዋና ትወከላለች፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት አስፋውና የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ወንድሙ ኃይሌ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ እያደረጉት ያለውን ዝግጅት በመግለጫው አብራርተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ሁለት የዋና ስፖርተኞች አክሪዴሽን አግኝተው ወደ ሥፍራው ለማቅናት ዝግጅት መጨረሳቸውን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታወቋል፡፡

በዘንድሮ ቶኪዮ ኦሊምፒክ ከፍተኛ የሆነ ፉክክር እንደሚኖር ከወዲሁ ከፍተኛ ግምት አግኝቷል፡፡ የሁሉም ተሳታፊ አገር አትሌቶች ለአንድ ዓመት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተከትሎ ጨዋታውን አጓጊ አድርጎታል፡፡

በተለይ በዘንድሮ የቅድመ ማጣሪያ ውድድሮች እንዲሁም የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮናዎች ላይ የተመዘገቡት አዳዲስ ክብረወሰኖች፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ አዲስ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ ሰሎሞን ባረጋ፣ ጌትነት ዋለ፣ ጉዳፍ ፀጋይ፣ ለተሰንበት ግደይ እንዲሁም ለምለም ኃይሉን የመሳሰሉ አትሌቶች ከፍተኛ ግምት አግኝተዋል፡፡ በተለይ ቀድሞ በኬንያና በኢትዮጵያ አትሌቶች መካከል ብቻ የነበረው ፉክክር፣ በዘንድሮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ዑጋንዳና ሌሎች አገሮችም እንደሚጋሩት ይጠበቃል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...