Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉበትግራይ የተካሄደው ፖለቲካዊ ውሳኔና የመቀሌ መለቀቅ አንድምታ!

በትግራይ የተካሄደው ፖለቲካዊ ውሳኔና የመቀሌ መለቀቅ አንድምታ!

ቀን:

በያሲን ባህሩ

ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ በአዳዲስ የፖለቲካ ሁነቶች የተሞላ ነው፡፡ ቀዳሚዎቹ ምርጫና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ንትርኮች ይምሰሉ እንጂ፣ የትግራይና የሕወሓት ጉዳይም እንደ አዲስ አገርሽቶ በመንተክተክ ላይ ነው፡፡ በተለይ መከላከያና መንግሥት ትኩረታቸውን ወደ አገር አቀፉ የምርጫ ሰላማዊነትና ደኅንነት ላይ አተኩረው የኃይል መሳሳት ሲፈጠር፣ ጁንታው በትግራይ ክልል ሕዝቡንም እያነሳሳ በሠራዊቱ ላይ ጥቃት ማድረሱ ተሰምቷል (በሕወሓት አፈላጤዎች መረጃ መሠረት ከሰኔ 11 እስከ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለ ጊዜ ከ30 ሺሕ በላይ የሚሆን ሠራዊት ከጥቅም ውጪ ማድረጉን ተናግሯል)፡፡ መከላከያም ጠንካራ የመልሶ ማጥቃት በመጀመሩ ጦርነቱ እንደ አዲስ አገርሽቶ ብዙ ጉዳት አድርሷል፡፡

ይህ ፈታኝ ሁኔታ ደግሞ በአንድ በኩል በወንድማማቾች መካካል ቢሆንም ብዙዎችን ለዕልቂት ዳርጓል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ መድረሱ ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በአገር ላይ ከፍተኛ ጫና ለማድረስ አሰፍስፎ የቆመበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በተለይ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያና አንዳንድ ኃያላን አገሮች በተዛባው ትርክትም ሆነ፣ ሕወሓት በሚጠቀመው የፕሮፓጋንዳ ውዥንብር እየተነዱ በመንግሥት ላይ ቀላል የማይባል ጫና አሳድረዋል፡፡

- Advertisement -

ይህ በእንዲህ እያለ ግን ባልተጠበቀና ብዙዎችን ባስደነገጠ ሁኔታ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር ባቀረበው የተናጠል የተኩስ አቁም ጥሪ መሠረት፣ የፌዴራሉ መንግሥት ፈጣን ምላሽ ሰጥቶ ሠራዊቱን ከመቀሌ አውጥቷል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ አሸባሪና ጁንታ ለተባለው ኃይልና ደጋፊዎች ከፍተኛ ደስታን የፈጠረ የድል ወሬ የፈጠረላቸው ሲሆን፣ በብዙኃኑ ሕዝብ ውስጥ ደግሞ ግራ መጋባትና ተሸንፈን ይሆን የሚል ሥጋትን ያጫረ ነበር፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ መንግሥት ፈጣንና በቂ መረጃ ባለመስጠቱ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን እንደገለጹት ግን ከትግራይ ዋና ዋና ከተሞች በተለይም ከመቀሌ ጦሩን ያወጡበት ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስትራቴጂካዊ ምክንያት ለብዙዎች አሳማኝ ነው፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእልህ ጦሩን መማገድ እንደማይፈልጉና ከዚህ ቀደም በነበሩ አገዛዞች የተሠራውን ስህተት መድገም እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል፡፡ ከኢኮኖሚያዊ፣ዲፕሎማሲያዊናፖለቲካዊ ምክንያት ባሻገር የሠራዊቱን የጦር ሜዳ ሰሞናዊ ቆይታ ሲያብራሩ የነበረው ሁኔታ ግን ሳዑዲና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በየመን ከነበራቸው ዘመቻ ጋር አመሳስለውታል፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ ባለፉት ሳምንታት በሕዝብ ደረጃ የደረሰበትን ክህደት በገለጹበት ወቅት፣ የታያባቸው የመከፋት ስሜት ብቻ ሳይሆን፣ ብዙዎቹ ታዳሚዎችም  ሲናደዱ ተስተውለዋል፡፡ ለአብነት ሲያነሱም፣ ‹‹አንድ ቦታ ላይ ሕዝቡ መከላከያ ገብቶ ይጠብቀን ብሎ ጥሪ አቅርቦ መከላከያ በቦታው ከገባ በኋላ፣ ሁኔታውን ለማስተካከል የተወሰኑ ወታደሮችን በቦታው አስቀምጦ ወደ ሌላፍራ ለዘመቻ ሄደ፡፡ ነገር ግን ማታ ላይ በቦታው የቀረውን ወታደር ይጠብቀን ብሎ የጠራው ሕዝብ መሣሪያም ገጀራም ይዞ ወጥቶ ጨፍጭፎታል፤›› ብለው ሲናገሩ ክፉኛ ያልተከዘ አልነበረም፡፡ ይኼ ድርጊት ዕውን አብሮ የሚያኖር ነው ያልንም ብዙ ነበርን፡፡

በመሠረቱ የትግራይ ቀውስ መነሻ የክልሉ አስተዳዳር (ሕወሓት) እና የፌዴራሉ መንግሥት አለመግባባት የወለደው ነበር፡፡ በተለይ በትግራይ የነበረው አስተዳዳር ራሱን በመንግሥትነት ቁመና በማደራጀትና ትጥቅ በማሰባሰብ ወይም በተለያዩ የፕሮፓጋንዳ ሥልቶች የፌዴራሉን መንግሥትና ተቋማቱን ከማጠልሸት ባሻገር ምርጫ አካሂዳለሁ ብሎ ወደ መንቦጫረቅ መግባቱ፣ ብሎም የፌዴራል መንግሥቱ የሥልጣን ጊዜ አልቋል ማለቱ ያስከተለው ዳፋ ነበር፡፡ ለሽምግልናም ሆነ ለመካሪ አልመች ያለውም ይኼው ኃይል እንደነበር የታወቀ ነው፡፡

ይህ አልበቃ ብሎት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከመከላከያራዊታችን ላይ ጥቁር ጠባሳ የጣለ ጥቃት በመላው ትግራይ እንዲደርስ ያስደረገውም ከዚያ በኋላ ነበር፡፡ የሕወሓት ኋላቀር ፖለቲከኞችና በጦሩ ውስጥ አቆጥቁጦ የነበረው ጁንታ፣ በሰሜን ላይ አድብቶ ጥቃት የፈጸመበት ሁኔታ አሳዛኝም የሚያስቆጭም ነበር፡፡

ፅንፈኞችራዊቱ ለትግራይ ሕዝብ ያለውን አጋርነትና አስተዋፅኦ ክደው፣ በተለያዩ ምክንያቶችና ሴራ ከትጥቁ እንዲርቅ አድርገው፣ አንዳንዱ ‹‹አገር ሰላም›› ብሎ በተኛበት የፈጸሙት ክህደት በየትም ዓለም ያልተለመደና ወገን ከሚባል ኃይል የማይጠበቅ ወንጀል እንደነበር ተደጋግሞ ተብሏል፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚደረግ የመንግሥት ለውጥም አገር እንደሚበትን ያላሰላ ውዳቂ ምኞት ነበር፡፡

ድርጊቱ ግን መላውን ሠራዊታችንን እጅግ ያስቆጣ፣ የአገሪቱንዝቦች ክፉኛ ያሳዘነ ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥት ሕግን ለማስከበር ለሚወስደው ማንኛውምርምጃጋዊነትን ያለበሰ ነበር፡፡ በዚህም ምንም እንኳን ቀላል የማይባል መሣሪያ ተዘርፎ ቁጥሩ ትንሽ ያልሆነ ጁንታ ከአዛዥነትና ከተዋጊነት ቢከዳም፣ ሠራዊቱ በሚያስደንቅ ፍጥነትና ጀግንነት የጠላትን አከርካሪ በመስበር፣ የተዘረፈውን ለማስመለስና የትግራይ ሕዝብን ነፃ ለማውጣት ያገደው ኃይል አልነበረም፡፡

በአስደንጋጭ ሽንፈት የተንኮታኮተው የጁንታው ርዝራዥም ወደ ሽምቅ ውጊያ ገብቶ አገር ለማድማትም ሆነ አልሞትኩም አለሁ ለማለት አልቦዘነም፡፡ ያንኑ መከረኛ የትግራይ ሕዝብ እያስገደደ ልጆቹን ወደ ጦርነት ማስገባቱና ስንቅ አቀባይ ማድረጉ (ሕዛባዊ ጦርነት እናደርገዋለን ሲሉ እንደነበር ልብ ይሏል!!) ሳያንስ፣ ንፁኃንን ምሽግ አድርጎ ‹‹የጎሬላ›› ውጊያ በመቀጠሉ፣ በርካታ ንፁኃን ለከፋ ጉዳትና ሰብዓዊ ቀውስ ተጋልጠዋል፡፡ ይህም በሐሰተኛ የትግራይ አክቲቪስቶችና የዳያስፖራ አባላት ይበልጥ እየተጋነነ በመራገቡ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ወቀሳ አስከትሏል፡፡

ሰሞኑን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ደጋግመው እንዳረጋገጡት፣ ትናንትም ሆነ ዛሬ የትግራይ ሕዝብ እንዲለማና ሰላሙ እንዲጠበቅ እንጂ እንዲጎዳና ዳግም ወደ ችግር እንዲገባ የሚፈልግ መንግሥት የለም፡፡ ሌላው ሕዝብም ቢሆን ለተጋሩ በጎ ከመመኘት ያለፈ ነገር አይኖረውም፡፡ ‹‹መጥፎ ካለ ጥሩ አይጠጣም›› ነውናብሪተኛው ድርጅት ግን ሕግ ተላልፎ ሕዝብ ለመማገድ በመድፈሩ ይኼ ሁሉ አገራዊ ቀውስ ተከስቷል፣ ገጽታችን ጨልሟል፡፡ የምዕራባዊያንን ጣልቃ የመግባት ፍላጎትንም አንሯል፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ወገኑ ጋር የሚኖርበት ሁኔታም ገና መልስ ያገኘ ጉዳይ አይደለም፡፡

እናም ኃላፊነት እንደሚሰማው መንግሥት ብቻ ሳይሆን እንደ አሁኑ ትውልድ ሥልጡን አተያይ፣ ‹‹በእልህ ምላጭ ያስውጣል››ሳቤ የቀውስን ጊዜ ማራዘም አይገባም፡፡ ላድርግ ቢባልም ተደራራቢ ኪሳራ የሚያስከትልና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያስወግዝ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የትግራይን ሕዝብ ክፉኛ የሚጎዳ ስለሆነ በመንግሥት በኩል ብቻ በተወሰደ የተናጠል ተኩስ አቁም መደረጉና ወደ ፖለቲካዊ የሕግ ማስከበር ዕርምጃ መገባቱ የተሸለ ነውሊጠላም አይገባም የሚለው ሚዛን የሚደፋ ጭብጥ ሆኗል፡፡

በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፣ ‹‹ጁንታው በቀዳሚው ውጊያ ተሸንፎና ተጠራርጎ ወደ ጫካ ከገባ በኋላ የሽምቅ ወጊያ የጀመረ ቢሆንም፣ የመከላከያ ሠራዊታችን እየተጠቃ ያለው ግን በሕዝብ ነው፡፡ ራሳችን በምንቀልበው ሕዝብ የምንጠቃ ከሆነ፣ በእልህ አንዴ ገብተንበታል በሚል በዚያ መቆየት ፋይዳ የለውም!›› ማለታቸው፣ በሠራዊቱ ላይ በታጣቂዎችም ሆነ ራሱ ሊወረን መጣ ብሎ በተዛባ ሥሌት ባኮረፈው ሕዝብ መጠቃቱ ወታደራዊ ሥጋት የሚፈጥርና አደጋ በመሆኑ፣ ውሳኔው ፖለቲካዊ ብቻ ነው ሊባል አይችልም፡፡ በዚህ ላይ ደጀን ወደሚለው ሕዝብ መጠጋቱ በወታደራዊ ቋንቋም የማፈግፈግ ሥልት ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

እዚህ ላይ የማይካደው ጭብጥ ግን ይህ የአገርና ሕዝብ ብሔራዊ ሠራዊት ሴት ወንድ፣ ቄስ ሼሕ፣ ልጅ አዋቂ ሳይባል በእጅና በመሣሪያ ብቻ ሳይሆን በምግብ ጭምር ጥቃት እንደሚደርስበት ሲሰማውና የባዕድነት መንፈስ ሲወረው ወደ ጭካኔ ዕርምጃ የሚገባ እንደነበር ነው፡፡ ምልክቶች ታይተው እንደነበር ማረጋገጫውም የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አንድ ቤተሰብ በትግራይ ክልል እዳጋ ሐሙስ አካባቢ ለግዳጅ ይዞት የሄደውን አሽከርካሪ ያቃጠሉበት ከመንደር የወጡ ወጣቶች ሲሆኑ፣ ይህንን ነውርና ወንጀል ለመከላከል የሠራዊት አባላት ተኩሰው እስከ መግደል መድረሳቸውን ያስታውሳል፡፡

 ይህንን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ጦሩ በሕዝብ ነው እየተገደለ ያለውና ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ጦሩ እንዲቆይ ካደረገን ጦሩ ወዳልተፈለገ ዕርምጃ ሊገባ ይችላል!›› በማለት ሥጋታቸውን ያስቀመጡት፡፡ በተለይ በመቀሌና ዙሪያዋ ተቀምጦ የነበረው ከ20 ሺሕ በላይ ጦር በዚህ አስከፊ ምልክት ውስጥ በአካባቢው እንዲሰነብት ማድረግ ከታሪክ አለመማርና ዓለምን ሊያሳዝን የሚችል ጥፋት ሊከሰት እንደሚችል ነው የሠጉት፡፡

‹‹መጀመሪያ የገጠመን የተደራጀ፣ የታጠቀና ዩኒፎርም የለበሰይል ነበር፡፡ እሱን በሁለትስት ሳምንታት ውስጥ አስወግደናል፡፡ ከዚያም የተወሰነ የጎሬላ ውጊያ ነበር፡፡ አሁን ግን በየመንደሩ ስንሄድ የሚገጥመን ጦር የለም፡፡ የምናገኘው ሕዝብ ነው፡፡ በቃ ሰላም ነው ብለን ስናልፍ ግን ከጀርባችን ሕዝብ ነው ባልነው አካል እንጠቃለን!›› የሚለው የመሪው ንግግር ያሳዘነው ብዙዎችን ነው፡፡ ዕውን እንደሚባለው የትግራይ ሕዝብና ሕወሓት አንድ ሆነው ነው? ወይስ ሕዝቡን ከጥፋተኛው ቡድን የሚነጥል የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ባለመሠራቱ ነው የሚለው እንቆቅልሽ በጥብቅ መመርመር ያለበት የቤት ሥራ ሆኗል፡፡

በእርግጥ ጦርነት ጎጂና አጥፊ ነው፡፡ ባለፉት ስምንት ወራት በትግራይ ውጊያ ብዙዎች ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ አካላዊናነ ልቦናዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከዚያም ከዚህም በቢሊዮን ብሮች የሚገመት የአገር ሀብትና ንብረት ወድሟል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ገና ባላለቀው የመልሶ ማልማትና የሰብዓዊ ዕርዳታ የመንግሥትን ሃያ በመቶ ያህሉን የዓመት በጀት (100 ቢሊዮን ብር ገዳማ) በልቷል፡፡ ይህ ሁሉ ችግር የተጠነሰሰው በጁንታው መሆኑ ባይካድም፣ የተጎዳችው ግን አገራችንንናዝቧን መጠራጠር አይቻልም፡፡

ይህን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹በዚህ ጦርነት ወደ 100 ቢሊዮን ብር ገደማ አውጥተናል፡፡ ይህም ለትግራይ ከምንመድበውመታዊ በጀት 13 እጥፍ በላይ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ግን እያወጣን ለመቀጠል ፍላጎት የለንም!›› ማለታቸውን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ይኼ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በበርካታ ቢሊዮን የሚገመት የአገር ሀብት ወደ ጦርነት መማገዱም አልቀረም፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን አሁንም ያ ክልል በምንና እንዴት ሊተዳዳር ይችላል የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ነው፡፡ ምርጫውን ሕዝቡ ወስኗልና ይሞክረው ከተባለ ግን ሰብዓዊ ቀውሱ ይባባሳል እንጂ ሊረግብ አይችልም (መከላከያ መቀሌን በለቀቀ ዕለት 38 ዜጎች በእርስ በርስ ግጭት ሞቱ መባሉን ያስታውሷል!!)፡፡

በአስከፊው የእርስ በርስ ጦርነት እንደ መንግሥት ሁሉ፣ ሕወሓት እንደ ድርጅት የደረሰበት ጉዳትም የገዘፈ ነው፡፡ ‹‹በፊት ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ›› እንደሚባለው ቢሆንም፣ በርካታ የጁንታው አዛዦችና የፖለቲካ መሪዎች (እነ ሥዩም መስፍን፣ ዓባይ ፀሐዬ፣ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ ደብረ ፅዮን የመሳሰሉ) ሙት፣ ቁስለኛ፣ እስረኛ (እነ አቦይ ስብሃትን ልብ ይሏል) ሆነዋል፡፡ አሁን በከበሮ ሞራል ለመገንባት ቢሞከርም፣ ቀላል ግምት የማይሰጠው ወጣትና ተዋጊያቸው፣ በተቆጣ ብሔራዊ ጦር ተለብልቧል፡፡ ነገ በታሪክም እነሱ በለኮሱት ጦርነት ለተሰው (መርዶ ሲነገር ብዙ ጎጆ ፅልመት መልበሱ አይቀሬ ነውና) የመከላከያ ሠራዊት አባላትም ተወቃሽና ተከሳሽ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡

 እንደ መንግሥት ሰዎች መግለጫ እስካሁን ውድ ዋጋ ቢከፈልም፣ መንግሥት ያስቀመጠውን ግብ ያልመታ ዘመቻ እንዳልተካሄደ ይነገራል፡፡ በተለይ የሕወሓትን ሕገወጥ እንቅስቃሴና አገር የማዳከም ሴራ ክፉኛ መምታት ተችሏል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ የጁንታው ሕገወጥ አካሄድ ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለጎረቤቶቻችንና ለቀጣናውም ሥጋት የሚጥል ነበር ነው ያሉት፡፡ አሁን ያ ሥጋት እንዳይኖር መደረጉን በመጠቆም፡፡

 ይህንኑ ሐሳብ የሚጋራ አስተያየታቸውን የሰጡት ዶ/ር ዓብይም፣ ‹‹በትግራይ ባካሄድነው ዘመቻ ተይዘውብን የነበሩትን መሣሪያዎች በሙሉ አስመልሰናል፡፡ ማስተካከል የምንፈልገውንም አስተካክለናል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን እንደ ቅኝ ገዥ ያውም ያለ ሕዝብ ፍላጎት ክልሉን ይዘን የመቀመጥ ዕቅድ የለንም፤›› ሲሉ ነው ያስረዱት፡፡

በዚያ ላይ አሁን ላይ መቀሌ ከዘመቻው በፊት የነበራትን የስበት ማዕከልነት አጥታለች፡፡ ስለዚህ ከመቀሌ መውጣት ከሌሎች ቦታዎች ከመውጣት የተለየ ፋይዳ የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከዘመቻው በፊት ጁንታው የነበረው ወታደራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ አቅም አሁን የለም፡፡ ከጦርነቱ በፊት በትግራይ ክልልና በሌሎች ክልሎች መካከል የነበረው ልዩነት ሰፊ ነበር፡፡ አሁን ግን እኩል ሆኗል ወይም ከዚያ በታች ወርዷል፤›› ማለታቸው የሥጋቱን መውረድ በሚገባ የሚሳይ ነው፡፡

በዚህ ላይ የትግራይ ሕዝብ ያየዘውን አቋም ለመመርመር የሚረዳው የፅሞና ጊዜ እንዲኖረውና ነገሮችን በትክክል እንዲያገናዝብድል መስጠት ማስፈለጉን፣ እንደ አገርም አሁን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳያችን ትግራይ ሳትሆንየህዳሴው ግድብ በመሆኑ ጦሩ ትኩረቱን ወደ ምዕራብ እንዲያደርግ ይረዳዋል ሲሉም ነው ያስረዱት፡፡

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የጁንታውላማ ማሸነፍ፣ ሥልጣን መያዝ፣ ወዘተ አይደለም፡፡ እኔ አመድ ስለሆንኩ አብራችሁኝ አመድ ሁኑ ነው፡፡ እኛ በተቀደደልን ቦይ አንፈስም፡፡ ነገሮችን ቆም ብሎ አይቶ የራስን አካሄድ መምረጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ ቆም ብለን አይተን ነው የወሰነው!›› ማለታቸውን እንደ ትክክለኛ ዕርምጃ የወሰዱት አሉ፡፡ በተለይ የደርግ መንግሥት ከዚህ ቀደም ለ17 ዓመታት ያህል በመንቻካ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተማግዶ በአገር ላይ ደረሰውን ጉዳት በማስታወስ፡፡

 በአንዳንድ ወገኖቸች ዘንድ የሠራዊቱን ከመቀሌና አካባቢው መውጣት ለአማራ ክልልና ሕዝብ ጉዳት ነው፡፡ ትግራይና አማራን በወልቃይትና ራያ ጉዳይ ስምምነትም ሆነ መቋጫ ባላስቀመጡበት ጊዜ ጁንታው አቅም አሰባስቦ ጦር ከመስበቅ አይመለስም ብለዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ የአማራ ከልል መንግሥትም ሆነ አብን የተሰኘው የክልሉ ተፎካካሪ ኃይል ጠንካራ ምላሽ ያለው መግለጫ ያወጡ ሲሆን፣ በርካታ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎችም የአማራ ሕዝብ በየትኛውም አጋጣሚ ሳይዘናጋ በተጠንቀቅ ሴራውን እንዲመክት አሳስበዋል፡፡

የዶ/ር ዓብይ ማብራሪያም ከእነዚሁ እውነታዎች የተለየ አይደለም፡፡ ‹‹አማራ ክልል ከሁለት ዓመት በፊት ያለበትጋት የለበትም፡፡ ተክዷል የሚሉ ኃይሎች ሕዝቡን እየናቁ ነው፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አይደለም ዛሬ 30 ዓመታት ዱላ እየወረደበት እንኳን ከፍ ሲል ኢትዮጵያዊ ነው ዝቅ ሲል የበጌ ምድር ሰው ነው፤›› ብለዋል፡፡ በእርግጥ በራያም ሆነ በወልቃይት ጉዳይ ላይ ያሉት ነገር አልነበረም፡፡ የሕወሓት አማፂ ቡድን ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ግን መቀሌ በመግባት የሚቆም ትግል እንደሌለ ከመናገር አልፎ፣ ወደ አማራም ሆነ ወደ ጎረቤት አገር እንደ አስፈላጊነቱ ልንንቀሳቀስ እንችላለን ማለቱ የነገሩን አልቦ መቋጫ ያሻል፡፡

ከእነዚህ እውነታዎች ጀርባ ግን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫናም ለፌዴራሉ መንግሥት ወሳኔ ዋነኛው መንስዔ እንደሚሆን መካድ አይቻልም፡፡ በተለይ አሜሪካ በአገሪቱ መሪዎች ላይ የጉዞ ዕገዳ መጣላቸው ብቻ ሳይሆን ሌሎች ማዕቀቦችን ለማፀደቅ ደፋ ቀና ማለታቸው የመንግሥትን ሥጋት እንዳበረታው ይነገራል፡፡ ለዚህም ነው ዶ/ር ዓብይ፣ ‹‹አንዳንድ ነገሮችን መግዛት ፈልገን በገዛ ገንዘባችን እንዳንገዛ በአሜሪካና በጀርመን ያለን አካውንት ተዘግቶብናል፤›› እስከ ማለት የደረሱት፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ ከፍተኛ የብሔራዊ ሥጋትን የሚያመጣና ተጋላጭነትን የሚያባብስ በመሆኑ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡

በአጠቃላይ ጦርነቱ መቆሙና ሌላ አማራጭ መፈለጉ በጎ ተግባር ሆኖ፣ ነገ ሒሳብ ለማወራረድ በሚል ሌላ ቀውስና የእርስ በርስ ጦርነት የማያስነሳ መሆኑ ግን መረጋጋጥ አለበት፡፡ ከሕወሓትም ሆነጁንታው ባህሪ አንፃር አዘናግቶ ሌላ ጉዳትና መዳፈር አለማድረሱም፣ በሌላ በሦስተኛ ወገን ጭምር ተይዞ መተማማኛ ቢበጅለት ይጠቅማል፡፡ ከሁሉ በላይ በየጢሻው የወደቁ ጀግኖች ተገቢውን ክብር እንዲያገኙና መላውራዊታችንም ሞራሉ እንዲጠበቀ መደረግ አለበት፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን አሁንም የትግራይ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ በፅሞናና በሰከነ መንገድ መቋጫ የሚያገኝበትን መንገድ መፈለግ ይገባል፣ ያስፈልጋልም፡፡ ሕወሓት ግን ያበደና ያበቃለት ድርጅት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...