Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትወገብን የማጥበቅ ግዴታ!

ወገብን የማጥበቅ ግዴታ!

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ስለዓለማችንና ስለቀጠናችን ልብ ሊባሉ የሚገባቸው ሽርክት ነጥቦች

1. ዓለማችን ቢያንስ ሦስት ልዕለ ኃያላያዊ ሠፈር እያበጀች ብትሆንም፣ የጆ ባይደን አሜሪካ ጀርመን – አውሮፓንና እነ ጃፓን ያሉበትን ደቡብ ምሥራቃዊ ሠፈር በዱሮው የሽርክና ቀፎ ውስጥ ይዛ ከቻይናና ከሩሲያ ጋር መጋጠሚያ ለማድረግ እየሞከረች ነው፡፡ የሰኔ መጀመርያ ቀናት 2013 ዓ.ም. የቡድን ሰባት አገሮች (ከእስያ አንድ ጃፓን፣ ከሰሜን አሜሪካ (አሜሪካና ካናዳ)፣ ቀሪዎቹ ‹‹አውራዎች›› ካሮጌው አውሮፓ የሆኑበት) ስብሰባና ከዚያ የተከተለው የኔቶ ምክክር በአንድ ላይ ቻይናና ሩሲያን በጠርናፊ አገዛዝነት፣ በፀጥታ ሥጋትነትና ፍላጎታቸውን በጉልቤነት የሚፈጽሙ፣ በተለይ ቻይናን በወታደራዊ ግስጋሴና በሥልታዊ የኢኮኖሚ አዳርሴነት ሥሏቸዋል፡፡ አሜሪካ ልትመራ የምትሞክረው የኢኮኖሚ ጦርነት የእኛ ቢጤ ደካማ አገሮችን ከቻይና ሥልታዊ ‹‹ምጥመጣ›› የማዳን ትግል እንዲመስል ተደርጎም አጊጧል፡፡ የቻይናን ሩጫ ከኢኮኖሚ አዳርሴነት እስከ መሣሪያ እሽቅድምድም ለመቀናቀንም ታስቧል፡፡ ቻይናም በውጭ ጉዳዩዋ በኩል፣ ‹‹አሜሪካ ታማለችና ቡድን ሰባቶች የልብ ትርታዋን ቢለኩላት ይሻላል፤›› እስከ ማለት ድረስ ኃይለ ቃሏን አንራለች፡፡ እናም የቀዝቃዛ ጦርነት ዱብ ዱቡ የተጀመረ ይመስላል፡፡ አሜሪካ፣ ጀርመን – አውሮፓንና ጃፓን – እስያ ፓስፊክን በዱሮ የጎራ ዘይቤ አስተባብራ፣ ቻይናና ሩሲያን ለመተናነቅ የያዘችው ውጥን፣ ከቀፎ አልፎ ሥጋ ማበጀቱና እየጎለበተ የመሄዱ ነገር ግን አጠያያቂ ነው፡፡ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ እንበል፡፡

- Advertisement -

የዓለማችን የኢኮኖሚ ግንኙነቶች ከቀላል የሁለት ጎራ ሠልፍ በላቀ ደረጃ እየተወሳሰቡ መጥተዋል፡፡ የቻይና ግዙፍ ኢኮኖሚ፣ ግዙፍ የንዋይ ካፒታልና ግዙፍ ነጋዴነት ከደሃ አገሮች እስከ አሜሪካ ድረስ የረዘመ ነው፡፡ ደሃ አገሮች አሁን ባሉበት ሁኔታ፣ በልማት “አጋርነት” ቻይናን ዘወር በይ ለማለት የሚያስደፍራቸው ወይም ለማስናቅ የሚፎካከር (በትንሹም በትልቁም ጀርባ የማይሰጥና ልቅጣ የማይል) አጋዥ የላቸውም ማለት ይቻላል፡፡ ጠንከር ያለ ኢኮኖሚ ያላቸው የእስያ ኢንዶ-ፓስፊክ አገሮች አውስትራሊያን ጨምሮ ከቻይና ጋር የደራ የኢኮኖሚና የንግድ ትስስር አላቸው፡፡ አውሮፓ የገበያ ትስስሯ ከቻይናም አልፎ ከሩሲያ ጋር የተጠላለፈ ነው፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ፣ የአሁኑ ዓለማዊ ሥርዓት ካፒታሊዝምን እጠብቃለሁ/እገረስሳለሁ የሚሉ የማይቻቻሉ የዓላማና የርዕዮተ ዓለም ቡልኮዎች የሉትም፡፡ የግል ይዞታ ድንበር ተሻጋሪ ግዙፍ ኩባንያዎችና ከበርቴያዊ ትርፍ አካባችነት ከሞላ ጎደል የሁሉም ኃያላን አገሮች እውነታና ሩጫ ነው፡፡ ቻይና ውስጥ ያለው የኮሙዩኒስት ፓርቲ ሠራተኛውን ሕዝብ፣ ገበሬውንና የግል ቱጃሩን ሁሉ ያካተተና በካፒታሊስት አትራፊነትና በነፃ ገበያ ውድድር መሐንዲስነት ምዕራባውያኑን አላስይዝ ያለ ነው፡፡ በሩሲያ ያለው አምባገነንነት የብዙ ፓርቲ ዴሞክራሲ ክራባት ያለው ነው፡፡ እነዚህን ከመሳሰሉ ገጽታዎች አኳያ የአሁኑ ዓለማዊ ሥርዓት የትናንትናው የ‹‹ሶሻሊስት››/ካፒታሊስት ጎራዎች ዲቃላ ነው ሊባል ይችላል፡፡

የቀድሞው የሁለት ጎራ ርዕዮተ-ዓለማዊ ክንብንብ ተገፎ ወድቋል፡፡ በሌላ አባባል፣ እምብርታዊው ጉዳይ (የኢኮኖሚ ጥቅም ሸሚያ)፣ እርቃኑን ወጥቶ የሁሉንም አገሮች እሽቅድምድ የሚገዛ ሆኗል፡፡ ከደኅንነት ጥበቃ ባሻገር በዓለማችን የምናያቸውም የአገሮች ስብሰቦች ገበያ ጥበቃንና ንግድን የማሳካት ትርታ ያላቸው ናቸው፡፡ በሁለት ልዕለ ኃያላዊ ፍጥጫና የኃይል ሚዛን ትግል ውስጥ አገሮችን ሁሉ የሚለካ (የሚያቀርብና የሚያርቅ፣ አንዱ ጀርባ የሰጠው በሌላው ታቃፊ እየሆነ፣ ደሃ አገሮች በጭፍራነት የሚዘረዘሩበት፣ ከዚያም አልፎ አገሮች ለአውራ ኃያላኑ የእጅ አዙር መጎሻሸሚያ ሜዳ የሆኑበት) ሁለት ዋልታ ገብ እውነታ የለም፡፡ የተባበረችው አሜሪካ አካል እስከ መባል ትታማ የነበረችው እንግሊዝ የትራምፕ አሜሪካ የቻይናውን ‹ህዋዌ› ብልጥ የስልክ መገናኛ “መሰለያ ነው” በሚል ሽፋን ከአሜሪካ ገበያ ያስወጣ በነበርበት ጊዜ በ‹ህዋዌ› አማካይነት ‹ጂ አምስት› የሚባለውን የመረጃ መገናኛ ቴክኖሎጂ ትውልድ ለማዘርጋት የደፈረችው የአዋጭነት ጥቅሟን አይታ ነበር፡፡ አሜሪካም ሆነች አውሮፓ በደሃ አገሮች አካባቢ ቻይና ያላትን ተሰፋፊነት ለመፎካከር የሚችሉት፣ የበለጠ የልማት ጥቅም ይዘው ከመጡና  አመሳቃይ የሆነ አሮጌ አርጩሜያቸውን በሌላ ሥልት ከቀየሩ ነው፡፡ ይህ ፉክክር ደግሞ ተፋጠው የሚናጩ ግዙፍ ጎራዎች መፍጠርን የማይሻ፣ እያንዳንዱ ባለፀጋ አገርና የባለፀጋ አገሮች ቡድን ብልጠቱን የሚያሳይበት ሩጫ ነው፡፡

በሌላ በኩል ዓለም አቀፋዊ የንዋይና የኢኮኖሚ ቀውስ ከኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መንስኤዎች ባሻገር፣ በአየር ንብረት መዛባትና ዓለም አቋራጭ በሆኑ ተዛማች በሽታዎች አስተዋፅኦ ምክንያት፣ የመከሰቻ ምልልሱ ከመፍጠኑ በላይ የቆይታ ጊዜው እየተራዘመ መሄድ አምጥቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2008 የተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ አገገመ ሲባል እየታደሰ ዛሬ ድረስ ዘልቋል ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ዓይነቱ የኢኮኖሚ ቀውስ ጊዜ (በተለይ በአፍላው ሰዓት) የትኛውም አኅጉር ለሌሎቹ አስፈላጊነቱ ጎልቶ ይወጣል፣ ያኔ የአፍሪካም የገበያ መድኅንነት ልብ ይባላል፡፡ ቻይናማ ከገበያነት በላይ ለንዋይም ትፈለጋለች፡፡ በንዋይ ረገድ አሜሪካ ከቻይና ብድር ጋር እንደመጣበቋም፣ የአሜሪካ የቀረርቶ ዕድሜ እስካሁን እንደታየው የክፋ ቀን ትግግዝን ሰብሮ አልሄደም፡፡

የኢኮኖሚ ቀውስና የምድር ሚዛን ቀውስ መባበስ ደግሞ የርዕዮተ ዓለም ጎራ ለሌላት የዛሬዋ ዓለም ራስ ምታቷ ሆኗል፡፡ የበረዶ መቅለጥ፣ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት፣ ድርቅና የደን ቃጠሎ፣ የዝናብ ወቅት መዛባት፣ በውኃ የተሸፈነ ምድር መስፋት ጉዳቱ እየከፋ ከሳይንቲስቶች እስከ ፖለቲከኞች፣ ከመንግሥታት እስከ ተራ ነዋሪ ድረስ የሚያሳስብ ሆኗል፡፡ ፖለቲካዊ ቀውስንና የአረንጓዴ ለውጥ እንቅስቃሴን እያስፋፋና ዓለም አቀፋዊ ንቅናቄ እያደረገውም ነው፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ደም ግባት ውስጥ ደግሞ፣ የዓለም ሀብት በጥቂት ግለሰቦችና ኩባንያዎች እጅ ውስጥ የመሰባሰቡና የብዙዎች መራቆት ግንዛቤ አለ፡፡ እነዚህ እውነታዎች የዓለም ሕዝብ የኃያላን ትንቅንቅ መደበኛ ሠልፈኛ እንዳይሆን የሚቀናቀኑ ጎራ ዘለል እውነታዎች ናቸው፡፡

2. በዚህ ግንዛቤ ማዕቀፍ ውስጥ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናችንን ጥቅምና አዋጪ አካሄድ ስናስብ የሚከተሉን ጥቅል ነጥቦች ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

ዓለማችን አጭር ጊዜ ከቆየው የአሜሪካ ብቸኛ ልዕለ ኃያላዊ ጌትነት መውጣቷ፣ የሁለት ጎራ ሠልፍ ውስጥ ለመቀርቀር የዛሬው ዓለም አለመመቸቱ (ከሁለት የዘለሉ ልዕለ ኃያላዊ ዝንባሌዎች መኖራቸው) ለአፍሪካም ለቀጣችንም እንዳቅሚቲ ለመንከላወስ ሻል ይላል፡፡ የየትኛውም ልዕለ ኃያል/ጎራ ታማኝ ሎሌ ሆኖ ሌላው ጠላቴ የሚል ጋሻ ጃግሬነት ውስጥ አለመግባት፣ ኩርፊያና መነቃቀፍ ኖረም አልኖረ ከሁሉም አገሮች፣ ከሁሉም ኃያላንና ልዕለ ኃያላን ጋር በጋራ ጥቅም ወዳጅ መሆንን የማይቆለፍ አቋም አድርጎ መያዝ፣ ለአፍሪካም ለቀጣናችንም የሚበጅ ነው፡፡

በጫና፣ በማዕቀብና በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ላለመጎዳት ዓለም አቀፋዊና አፍሪካዊ ተቀባይነት ባለው በምርጫ መንግሥት በሚለዋወጥበት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መተዳደር፣ በሁለገብ ልማት አማካይነት የሕዝብ ኑሮና የሰብዓዊ መብቶች እንክባካቤ ዕድገት ውስጥ መሆን፣ አሸባሪነትን ተጋግዞ መታገልና ማምከን፣ ከየትኛውም ጎረቤት ጋር የሚፈጠር አለመግባባትን በውይይትና በድርድር ለመፍታት የሚቻለውን ያህል መጣጣር፣ በአገርነትም ሆነ በቀጣና ደረጃ የፖለቲካ መረጋጋት ውስጥ ረዥም ጊዜ ለመቆየት ሁነኛ ዋስትናችን ነው፡፡

  • ይህ አጠቃላይ መቃን (ማዕቀፍ) እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በመቃኑ ውስጥ የሚደርሱ ቀውሶችንና ድንቅፍቅፎችን ከመቃኑ መሰበር ጋር ያምታቱና የተቻኮሉ ድምዳሜዎች/ውሳኔዎች ከሚያደርሱት ጉዳት መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ሕግ የሁሉም አዛዥ የመሆኑ ነገርና የሰብዓዊ መብቶች እንክብካቤ ዴሞክራሲ በተቋቋመበት ሁሉ በደንብ የሚሳካ አድርገው ብዙ የዋሆች ይገምታሉ፡፡ በተለማማጇ አፍሪካና በኢትዮጵያ ደረጃ ይቅርና ለመብቶች መቆርቆር ‹‹ከእኛ በላይ ለአሳር›› በሚሉት አሜሪካና አውሮፓ ውስጥ እንኳ ብዙ ገመና አለ፡፡ ስደተኞች የዜግነት መታወቂያ አግኝተው እንኳ፣ ሥርዓታዊ አያያዙ ሥውር በሆነ ሥልት ‹‹የአህያ›› ከሚባሉ ጉልበት ነክ ሥራዎች ብዙ እንዳይርቁ የሚያደርግ ነው፡፡ ሩሲያንና ቻይናን “በጉልበት የሚያስቡ” የሚሏቸው አውሮፓና አሜሪካ የራሳቸው በየአገሩ ጦር (በአየርና በየብስ) እያሰማሩ ጣልቃ በመግባት ብዙ የሰው ልጅ ጉስቁልና ማምረታቸው አይታሰባቸውም፡፡ በምዕራብ በተለይም በአሜሪካ ያለው የዘረኝት ባርነት (በጥቁሩም በነጩም ላይ)፣ የላሸቀ ወሲብ ባርነት፣ የአደንዛዥ ዕፅ ባርነት፣ ውስጣዊ ጉስቁልና ከማድረስም አልፈው በሆሊውድ ፊልምና በመዝናኛ ሚዲያ አማካይነት ዓለምን እያጠቁ ይገኛሉ፡፡ በእስር ቤት አያያዝ አሰቃይነት አሜሪካ በቤቷም በደጅም ንፁህ አይደለችም፡፡ የጓንታናሞ እስር ቤት፣ የአፍጋኒስታንና የኢራቅ ልምድና በሌሎች አገሮች ውስጥ የፈጠረቻቸው የድብቅ እስር ቤቶች ታሪክ ለዚህ ምስክርነት ከበቂ በላይ ናቸው፡፡

በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ውስጥ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ግድፈቶች በዴሞክራሲ ልምድና ባህል ማነስ፣ በልማት ማነስ፣ በዘዴዎች/በቴክኖሎጂዎች እጥረትና በኢዴሞክራሲያዊ ግርሻዎች ምክንያት ገና ለረዥም ጊዜ ሄድ መለስ ማለታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ በደሎች በተከሰቱና በተጋለጡ ቁጥር ‹‹ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት የሚባለው ውሸት ነው!›› የሚል ክልፍልፍ ድምዳሜ ላይ መንጠላጠል ቁልቁል ከመሳብ በቀር ወደ መሻሻል አይወስድም፡፡ እንከኖችን የዴሞክራሲ ባህል ግንባታና የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ዕድገት ውስጥ ከመሆን አለመሆናችን ጋር ማገናዘብ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የከረረ ጫጫታ መምጣት ያለበት የዴሞክራሲ መቃን በተሰበረ ጊዜ ነው፡፡ የእኛ ልሂቃን በዚህ ረገድ እስካሁን ካለፉባቸው የነቀፋና የኩነና ልምዶች ብዙ መማር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ሰነድ ያዘላቸው አንቀጻዊ ፍሬ ነገሮች አንዳቸው ከሌላቸው ጋር ተገናዝበው እንደ መድረሻ ኮከብ የምንመራባቸው እንጂ፣ ማለፍና መውደቃችንን የምናሳርምባቸው ቀይ እስክሪብቶዎች አለመሆናቸው ሊጤን ይገባዋል፡፡

  • የኢትዮጵያ የመንግሥት መሪዎች፣ ምሁራንና ልሂቃን በምንተነፍሰውና በምናደርገው ነገር ረገድ፣ ከሌሎች የአፍሪካ ልጆች ይበልጥ ታሪክና የአቀማመጣችን እውነታ ኃላፊነት አሸክሞናል፡፡ ሀ) በአፍሪካ የነፃነት ትግልና በአፍሪካ አንድነት/ኅብረት ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ በጎ አሻራ አላት፡፡ በዚሁ ቅርስ ምክንያት የአፍሪካ አንድነት/ኅብረት መቀመጫ ሆነን (ከአኅጉራዊ ማኅበሩ መወለድ ጀምሮ) ቆይተናል፡፡ ለ) በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ኢትዮጵያ ያላት አቀማመጥ ፈርጥ መሰል ነው፡፡ በጎረቤቶቻችን ውስጥ የሚሆነው ነገር እኛን ይዳብሳል፣ የእኛም ሥራ ጎረቤቶቻንን ይዳብሳል፡፡ ከዚያም በላይ የድንበር ጣጣዎችን ከጨረስን ከግለሰብና ከፓርቲ የመንግሥት መሪነት ጋር የማይዋዥቅ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ነባራዊ ዕድል አለን፡፡ በተሻጋሪ ወንዞች፣ በመንገዶች፣ በወደቦች፣ በኤሌክትሪክ ኃይልና በአየር መንገድ ግንኙነቶች፣ ድንበር ተሻጋሪ ተባዮችን/በሽታዎችን፣ ወንጀልንና አሸባሪነትን፣ በአጠቃላይ የጋራ ፀጥታና ሰላምን ተጋግዞ በመቆጣጠር መስኮች እየተያያዝን ነው፡፡ ነፃ ግብይይት ውስጥም እየገባን ነው፡፡ ኢኮኖሚ ጠቀስ ጫና/ማዕቀብ ከታላላቅ ጉልበተኞች በኩል ቢመጣብን፣ አካባቢያዊ ተራክቧችን ላለመውደቅ የምንውተረተርበት አንዱ ተስፋችን ነው፡፡ ግብይይቶችን፣ ብድሮችንና የብድር ክፍያዎችን ዓይነት በዓይነት (ሸቀጥ በሸቀጥ) በማስኬድ ለዶላር ባርነት እንደማናድር ለዓለም ማሳየት እንችላለን፡፡ ደቡብ ሱዳን ውስጥ አዋጭነቱ ተገምግሞ በተጋገዘ አቅም የነዳጅ ማጣሪያ ቢኖር የእኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ከነዳጅ ጋር በቀጥታ (በዶላር ችግር ጊዜ) መገበያየት ይችላል፡፡ ከድንበርተኛ ጎረቤቶቻችን ጋር ያለንን ዝምድና ይቀጥል ይሆን የሚል ሥጋት የሚጎበኘው ኢኮኖሚያዊ ዝምድናችን በአግባቡ ስላልተገመደና ውሎ ያደረ የድንበር ክፍተት ከአጋጣሚ ጥቀመኝነት ጋር ስለተገናኘ ነው፡፡

የሆነ ሆኖ ግን በአፍሪካችን ድህነት እስካልተሸነፈ ድረስ፣ በጌታ አገሮች ጉርሻ ሸብረክ የሚል አለመታጣቱንና ግለሰብ የአገር መሪዎች/ቡድኖች ሊሙለጨለጩና ሊወራጩ እንደሚችሉ ግን መዘንጋት የለበትም፡፡ ለዚህ የቅርብ ምሳሌ እንፈልግ ብንልም አናጣም፡፡ በተረፈ እንደ ቆቅ ነቅቶ መጠበቅ ከሚያሻውና የግብፅን ሕዝብ ህሊና ‹ናይል የእኔ ብቻ› በሚል አተያይ አስሮ ካኖረው ከግብፅ ገረ መንግሥት በስተቀር፣ ቀሪው የድንበርተኛ ጉርብትናችን አረረም መረረ በቀላሉ የማይቆረጥ የጋራ ዝምድና ሊለማበት የሚችል ነው፡፡ ከኤርትራ ጋር ያለን ዝምድና ደግሞ ከዚህም የሚያልፍ ነው፡፡ በክፉም በደጉም እንደማንላቀቅ የአንዳችን ሕመም ሌላችንንም እንደሚያመን 2013 ዓ.ም. ብቻውን ብዙ አስተምሯል፡፡ የአንድ ረዥም ማኅበራዊ የጋራ ታሪክ ውጤት እንደ መሆናችንም መንትያነት አያንሰንም፡፡ እናም በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ኢትዮጵያ ለህልውናዋ የሚበጃት በሕገ መንግሥታዊ (ዴሞክራሲያዊ) ትድድር፣ በልማት ግስጋሴ፣ በኅብረተሰብ ኑሮ ፍትሐዊነት መስፋት፣ በሰብዓዊ መብቶች እንክብካቤ ዕድገት ውስጥ እየተጓዙ ምሳሌ መሆንና ያለ ጫና መተጋገዝ ነው፡፡

እነዚህ ግንዛቤዎች ከተዋሀዱን ከአንዳንድ አወቅን ባዮች የምንሰማው ‹‹እኛም እጅ የምንጠመዝዝበት ቀን ይመጣል! የቀጣናችን ኃያል አገር የምንሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም…›› ባይነት ምን ያህል አሮጌ/የጉልቤዎች ናፍቆት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ለኢትዮጵያ ‹‹እጅ ጠምዛዥነትም›› የአካባቢ ጉልቤነትም ጥቅሟ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ጥቅም ፈርጣዊ አቀማመጧን በጋራ ልማትና በሰላም ትግግዝ፣ በመከባበር መሙላት ነው፡፡ ለምሳሌ በአረንጓዴ ልማቷ ውስጥ የዛፍ ተከላን ከጎረቤቶቿ ጋር ለማያያዝ እያደረገችው ያለው ጥረት የምሥራቅ አፍሪካ አረንጓዴያዊ ጉዞ ፈርጥ የመሆን አንድ መገለጫ ነው፡፡ 

አገራዊ ዕውንን በትክክል የተረዳ ዓላሚነትና አካሄድ

በአሁኑ ጊዜ በከተማም በገጠርም ያሉ ብዙ ወላጆች የልጆች አሳዳጊነታቸው መጠለያና ቀለብ ችሎ ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ደረጃ እንደ ወረደ፣ ልጆችን የመቅረፅ ሚናቸውን ‹‹ዘመናዊ›› በሚባል ግን ላሻቃ በሆነ የምዕራብ ባህል ወረራ እንደተሰረቁ ልብ አይሉም፡፡ ይህን በ‹ዝመና› የሚያጭበረብር ሌባ በመመከት ረገድ ትምህርት ቤቶችና መንግሥት የረባ ዕገዛ እየሰጧቸው አይደሉም (የችግሩ ጥልቀት ራሳቸውንም በአግባቡ ያባነናቸው አይመስልም)፡፡ ፊልሞችና የመገናኛ ብዙኃን መዝናኛዎች በአመዛኙ የዝመና ተብዬው ሌባ መሣሪያዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ አገር ውስጥ የተመረቱ ፊልሞችና የዘፈን ቪዲዮዎች ሳይቀሩ ከሞላ ጎደል የምዕራብ ኮፒነትን (‹ሬፕሊካ›ነትን) ለምደው ሲያለምዱ እናገኛቸዋለን፡፡ እናም እውነታውን ያልተረዱ ወላጆች ስለልጃቸው አጓጉል ብልሽት ወሬ ሽው ቢላቸው ‹‹የእኔ ልጅ አይነካካውም!…›› እስከ ማለት ይደርሳሉ፡፡ አንዳዶች የሰሙትን እውነት ከመቀበል ፋንታ ህሊናን በመጨፈን ከእውነታ ራሳቸውን ይደብቃሉ፡፡ ጉዳቸውን በዓይናቸው ባዩ ጊዜ ደግሞ መሬት ተሰንጥቃ ብትውጣቸው ይመኛሉ፡፡ ከማባረር እስከ ‹‹ካልገደልኩ!›› ባይነት የማይበጅ ዕርምጃ የሚወስዱም ጥቂት አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዓ ምድር በመረዳት ረገድም፣ ከዘመን ወደ ኋላ በመቅረትም ይሁን በልሂቃዊ ስንፍና የዕውናዊ ግንዛቤ ችግርተኛነት ውስጥ መውደቅ በኢትዮጵያ ውስጥ ትናንትናም ታይቷል፣ ዛሬም አለ፡፡ አንዳንዶች እውነታ መቀየሩን ማጤንም ተስኗቸው ትናንትና ላይ ተገትረው ‹‹ለራስ ምታት ቅቤ እሰሩበት፣ ለቡዳ ክታብ አንግቱበት›› የሚል ዓይነት መፍትሔ ይዘው ይንቀዋለላሉ፡፡ ግንዛቤያቸውን በትኩስ ዕውናዊ ይዘት ለማበልፀግ ስንፍናና ግብዝነት ያወካቸው ደግሞ፣ ከእውነታ የተዋወቀ የመለኝነት ድህነታቸውን በምኞታዊነትና በጀብደኝነት አጣጥተው አየር ላይ ይሰፋሉ፡፡ አየር ላይ እየተራመዱ አሸናፊነታቸው ይታያቸዋል፡፡ ቁንጣሪ ሆነውና የረባ ነገር ሳይዙ ለአገር እንተርፋለን ይላሉ፡፡ ቃዥተው ከግንብ ሲላተሙ እንኳ፣ በግንቡ ስለመመታታቸው እንጂ ቅዠታቸው እንዳስመታቸው አይናገሩም፡፡

በምርጫ 97 ጊዜ እውነታዊ የፖለቲካ መለኝነት ኖሮ ቢሆን ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሁሉን ተቆጣጣሪ ስለነበር በ1997 ዓ.ም. እንደማይሸነፍ ተማምኖ ‹‹እንከን የለሽ ምርጫ አደርጋለሁ›› ባይነቱን እያሳሳቁ (ወደ ከፋ የጉልበት ሥራ እንዳይገባ በአንዴ ሙሉ አሸናፊነት ለማግኘት ሳይስገበገቡ) በሕወሓት/ኢሕአዴግ አጠቃላይ አሸናፊነት ውስጥ ጥቂት ድል ይዞ አብሮ በመሥራት የምርጫ ቦርድን፣ የፍርድ ቤቶችንና የብዙኃን ማኅበራትን አሻንጉሊትነት፣ ወዘተ የሚቀንሱ ማሻሻያዎች እንዲያድጉ አስተዋጽኦ ማድረግ፣ ያገኟቸውን ምጥን ድሎች ይዘውም ሕወሓት/ኢሕአዴግን ማሳሳቃቸውን ቀጥለውበት፣ የገዥው የአፈና ጥንቃቄዎች የተንገላጀጁበትና ማን አሸንፎኝ ባይ መተማመኑ የተቀናጣበት (ማሻሻያዎችም የተበራከቱበት) ሁኔታ ለምቶ፣ አዝጋሚ የለውጥ ጥርቅሞች በአፈና መቀልበስ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ሲደረስ፣ ዴሞክራሲን ሙሉ አሸናፊ ማድረግ ዋና የአካሄድ ጥበብ ተደርጎ በተያዘ ነበር፡፡ እንዲህ ያለ ጥበበኝነት ታጥቶ የ1997 ዓ.ም. ጭላንጭል ድርግም ተደርጎ ጠፋ፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ አምባገነንነቱንና የምርጫውን ይስሙላነት ከበፊቱ አብሶት አረፈው፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ውጊያ ጊዜ ከተቃዋሚዎች ጋር የፈጠረው መለሳለስ እንኳ አላራራው ብሎ ‹‹በድል›› ሰዓት (2002) በተካሄደ ምርጫ ጊዜም በዚያው በተለመደ ስስቱና የአገዛዝ ዘይቤው ቀጠለበት፡፡

ከ2007 ዓ.ም. በኋላ እያደገ በመጣ ትግል የፊጥኝ ተይዞ ባለበት ሁኔታ ውስጥ የተደረገው የጠቅላይ ሚኒስትር ቅየራ፣ ደም ግባቱ የሕወሓት ኢሕአዴግን ገዥነት ከማዳን የተለየ (አስፈሪውንና ዋናውን የሕወሓት ጌትነት እያሳሳቁ) ወደ ለውጥ የመጓዝ ትልምን በብብቱ የያዘ ነበር፡፡ የአያያዝ ጥበበኝነትንና የሕዝብን የድጋፍ ጎርፍ ካላገኘ በቀላሉ ሊቀነጠስ የሚችል ሰላላ የለውጥ ዕድል ብቅ ያለበት፡፡ የለውጡ ቡድን በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር በዓለ-ሲመት አንስቶ ያካሄዳቸው ቆራጥና ብልህ ንግግሮችና ዕርምጃዎች፣ በሕወሓታዊ መንጋጋ ውስጥ የነበረውን የለውጥ ዕድል ወደ ሕዝብ ላንቃ ያስገባ ነበር፣ በአጥለቅላቂ የሕዝብ ድጋፍ አሳፍሮ፡፡ ነገር ግን አጥለቅላቂው ድጋፍ እንዳይከፋፈልና እንዳይፈዝ የማያቋርጥና የሚያድግ እንክብካቤና ዕገዛ ይሻ ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ ብልህ ሚና፣ የሕወሓት ኢሕአዴግ ተቃዋሚ ነን ከሚሉት ቡድኖች በእጅጉ ይጠበቅ ነበር፡፡ ቡድኖቹ ግን ከጥፋት በመማር ልምምድ ያልለፉበትን ልባምነት ከየት ያምጡት? ምርጫ 97 የአምባገነንነት መጠናከሪያ ሆኖ ከከሸፈ በኋላ የተደረጉ ግምገማዎችን መነሻ አድርገው የያኔ የተቃውሞ ተሳታፊዎች በጊዜው ያሳዩት ኩነና፣ ፉከራና ሽለላ አላዋቂነት እንደ ነበር የተነተነ ሂስ አላደረጉም፡፡ ከዚያ ይልቅ እስከ ዛሬ ድረስ ምርጫ 97 ሲነሳ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ኮሮጆ ገልባጭነትንና ጨካኝ ጥይትን ከማውራት በቀር፣ የራሳቸውን ወፍራም ጅልነት ለራሳቸውም ለሌላውም መማርያ እንዲሆን ሲዘከዝኩት አላየንም፡፡ እንደተቆነኑና ጣታቸውን ሕወሓት/ኢሕአዴግ ላይ እንደጠቆሙ የመጋቢት 2010 ዓ.ም. የለውጥ ኩራዝ በራባቸው፡፡ ከሚኮንኑት ሕወሓት/ኢሕአዴግ ውስጥ የወጡ ለውጠኞችን አጅቦ መቆምና እነሱን እያሞገሱ ለሕዝብ ማዕበላዊ ድጋፋቸው አዳማቂ መሆን በተቃዋሚነት ለኖሩት ፖለቲከኞች የማይመጥን ነው፡፡ እነሱ ‹‹የሕዝብ መሪ›› እንጂ ከገዥ ቡድን ጋር ሲነጉዱ ኖረው ገልበጥ ላሉ ግለሰቦች እሽክም ባዮች (አጨብጫቢ) አይደሉም፡፡ አለመቸኮል ቢበዛ ቀዝቃዛና ጥያቄ ምልክት የበዛበት ድጋፍ ነገር ቆንጠር አድርጎ መለገስና ከርቀት መተቸት፣ ለእነሱ ክብረኛ ሚና ይህ ነው፡፡ በ1997 ጊዜ ሕወሓት/ኢሕአዴግን ‹‹ጨለማ›› ራሳቸውን ‹‹ብርሃን›› እያሉ መሸለል! የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት መስዋዕትነትን በዘረኛ መማገጃነት መተርጎም! በድኅረ ሚያዝያ 2010 ጊዜ ደግሞ ቆሞ ማየትና ማሽሟጠጥ! ይህ ፍዘት ከ1997 ልምድ ‹‹ትምህርት ከመውሰድ›› የመጣ ይሆን!?

እና ሕወሓት/ኢሕአዴግ ዓምደ መንግሥቱን ለራሱ ታማኝ አድርጎ ከመቅረፁ እውነታ አንፃር፣ ፖለቲከኞችና ሕዝብ በተሳሉበት አገራዊ የድጋፍ ተገን፣ የለውጡን ኩራዝ ከተተናኳይ ወጀብ ጠብቆ የማንደርደር (ክፍተት የመንፈግ) ቁልፍ ተግባር፣ የኢሕአዴግ ተቃዋሚ ነን ሲሉ በነበሩ ፓርቲዎች በአግባቡ ልብ ሳይባልና ሳይለማ ቀረ፡፡ ዳር ቆሞ ተመልካችነትና ጠባቂነት እየጨመረ ሄደ፡፡ ሕወሓታዊ የለውጥ ተቀናቃኝ ሻጥሮችና የእነ ኦነግ ሥውር ሥራ ለመሹለክለክ ክፍተት አገኙ፡፡ ‹‹ዴሞክራሲ›› እንሻለን የሚሉ ፓርቲዎች በሌላ ጅልነት (በታዛቢነትና ሕዝብን በማያነቃንቅ ፍዝ ደጋፊነት) ባይገነዙና የለውጥ ጉዞው ክፍተት ባይፈጠርበት ኖሮ፣ የለውጡ ተቀናቃኞች ጋሻ ጃግሬዎችን አደራጅተው የማፈናቀልና የማጋጨት ሴራቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ሰፊ ፋታ ባላገኙ ነበር፡፡ የኦነግ ተነጣይ ክንፎች ዓይናችን ሥር መሣሪያ እያሹለከለኩ ከምዕራብ ዳርቻ እስከ መሀል ሸዋና ወሎ ድረስ የታጠቁ ቡድኖችን ባላሰማሩ፣ ያ ሁሉ የሕዝብ መፈናቀልና ደም መፍሰስ ባልተከሰተ፡፡ በቆንጨራ፣ በድንጋይና በእሳት የሰው ነፍስ የሚበላ ጭካኔና ጥላቻ ወጣቶቻችን ላይ መጋለብ ባልቻለ፣ ሰሜን ዕዝን ወግቶ አገር እስከ መበተን ያቀደ ሴራ ፋፍቶና አብጦ እዚህ ሁሉ ቀውስ ውስጥ ለመዘፈቅ ባልዳረገን ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር መንግሥት ከሱዳን ድንበር አካባቢ ሠራዊቱን ባላነሳ፣ ሱዳንም አጋጣሚ ተመቸኝ ብላ ድንበር በመግፋት ባልቆሸሸች፣ በአውሮፓ አሜሪካ አካባቢ የተንጋጋብን ውንጅላ ሁሉ ባልመጣ ነበር፡፡ ግጭትና ማፈናቀሉ፣ እስከ አረመኔያዊ ዕብደትነት አድጎ ከሥፍራ ሥፍራ እስከ ትግራይ ድረስ የወለደው ብዙ ሕይወትና ንብረት ያወደመ ጥፋት ሁሉ፣ የፖለቲካችንና የፖለቲከኞቻችን ግተ-ደረቅነትና ስንፍና ያስከፈለን ኪሳራ ነው (እዚህ ላይ በ‹-ሸኔ› እና በሕወሓት በኩል የታየው ሰቅጣጭ የጭካኔ ባህርይ የፖለቲካችን ከልምድ ያለ መማር — እጅግ አስጠሊታው — የዝቅጠት ፈርጅ መሆኑ አይረሳ)፡፡ አውሬያዊ ጥቃት/ጥፋት ወደ ዕብደት ተቀይሮ በየደጃቸው እየመጣና ሕዝብ ሲያስጨንቅ እያዩ እንኳ ብዙዎቹ “ሰላማዊ” ፓርቲዎች ገዥውን ፓርቲና መንግሥትን ባለ ጥፋት ከማድረግ ወጥተው፣ የራሳቸውን ተጠያቂነት ማየት አልቻሉም ነበር፡፡ የደረሱበትን ያህል እንኳ የነቃ አስተዋጽኦ (ሕዝብን አያይዞ ሰላም አማሾችን በመነጠል ጥረት እንኳ) ለለውጡ ዕገዛ አላደረጉም — የሰው፣ የንብረትና የለውጥ ግስጋሴ ኪሳራችንን ያከፋ ጉልህ ጥፋት፡፡

በእኛው ጥፋት የተበራከተ ብዙ መስዋዕትነት በተከፈለበት ሁኔታ ውስጥ ብቅ ያለው የ2013 የምርጫ እውነታ፣ ትክክለኛ ግንዛቤ ይዞ ትክክለኛ ውሳኔ ከማድረግ አኳያ ከ1997 ጋር ሲተያይ ብዙም አስቸጋሪ አልነበረም፡፡ የ1997 ምርጫ ይጠይቅ የነበረው ተግባር አምባገነን ገዥን አንገላጆ ጥገናዊ ማሻሻያዎችን ከመዳፉ እየፈለቀቁ የማጠራቀምን ከባድ ተግባር ነበር፡፡ በ2013 ምርጫ ጊዜ አገራዊ አንድነትንና ለውጡን የማትረፍ ነገር የኢትዮጵያ ኅብረተሰብን ከመተላለቅ የማዳን ጉዳይ ነበር፣ የማያመራምር፣ የአገር ምጥ የሆነ ተግባር፡፡ ይህንን የሞትና የሽረት ተግባር የመወጣት ተልዕኮም በዋናነት ከብልፅግና ፓርቲ መንግሥታዊ አመራር ጋር የተጣበቀ መሆኑ ግጥጥ ያለ ሀቅ ነበር (ተጋድሎው ይካሄድ የነበረው በብልፅግና መንግሥት እየተመራ ነበርና)፡፡ በውጭም በውስጥም ያሉ ብዙ የአገር ልጆች መንግሥትን በአገር ወዳድነት ያግዙ የነበረውም ለዚህ ነበር፡፡ የ2013 ምርጫን “ከንቱ! ከምርጫ በፊት ድርድርና የሽግግር መንግሥት! ቅድሚያ የሕገ መንግሥት መሻሻል!” ያሉ አቋሞች የጥቂቶች (የኢትዮጵያን እውነታ ለመቀበልና ከገንታራ አቋማቸው ለመላቀቅ ዕንቢኝ ያሉ) ፖለቲከኞች አቋሞች መሆናቸው፣ ብዙ ፓርቲዎች በምርጫው ተስፋ አድርገው መሳተፋቸውና ከሁሉም በላይ አያሌ ሕዝብ አገራዊ አንድነቱንና ለውጡን ከማስቀጠል አኳያ ምርጫው ይበጀኛል ብሎ ለእንግልት ሳይበገር ድምፁን መስጠቱ፣ የነበረው እውነታ ‹‹መጀመርያ መቀመጫዬን›› የሚያስብል ለልብታ ከባድ እንዳልነበር የሚጠቁም ነው፡፡

እናም የጥፋት ፀፀት የተሰማውና የኢትዮጵያና የለውጡ ኩራዝ መትረፍ ከብልፅግና ፓርቲ በሥልጣን መቀጠል ጋር በብዙ ነገሩ የተያየዘ የመሆኑን እውነታ ወዶም ሆነ እያቃረው መቀበል የቻለ ፓርቲ፣ በዚህ በሰኔው 2013 ምርጫ ለአባላቱና ለደጋፊቹ ብልፅግናን ምረጡ እስከ ማለት ድረስ ቢሄድ ኖሮ እንኳ አስተዋይነት እንጂ አጨብጫቢነት አይሆንበትም ነበር፡፡ ይህንን ማድረግ ይበዛብኛል ያለ ፓርቲ ቢያንስ የብልፅግና ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ የመሆን ጥረት ፈተና እንዳይወድቅ፣ በመሸነፍ ሥጋት ወደ ኢዴሞክራሲያዊነት እንዳይንከባለል፣ ይህም በሚፈጥረው አሉታዊ ስሜት የኢትዮጵያና የለውጡ ዕጣ ባልተጠበቁና በማያስተማምኑ ፓርቲዎች አሸናፊነት ምክንያት ድንግዝግዝ ውስጥ እንዳይገባ፣ የፉክክር ፈተናውን ላቅልል ቢል አስተዋይነት ይሆን ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን ልባምነት ፊት ለፊት አውጥቶ ያሳየ ነበር ማለት ባይቻልም፣ ለውጡ እንደይመክን ስሱ በመሆን ረገድ ከነባሮቹ ተቃዋሚ “ፓርቲዎች” ይልቅ ከስደት ትግል መልስ የተቋቋመው ኢዜማ በብዙ ነገር (በፖለቲካ ብስለት፣ በአርቆ አስተዋይነት፣ በድርጅት አቅምና በሕዝብ ተቀባይነት) የትና የት ያጣጥፋቸዋል፡፡ ለወደፊቱም ብልፅግና ፓርቲን የመፎካከር ተስፋ የሚታየው በእዚሁ ፓርቲ ላይ ነው፣ እስካሁን እንዳስተዋልነው፡፡

ድርብርብ ፈተናችን ምትሐተኝነትን አይሻ ይሆን?

ምርጫው ከሞላ ጎደል ተጠናቀቀ፡፡ ከዚህስ በኋላ? ፖለቲከኞቻችን ካለፈው ተምረው ለኢትዮጵያ አንድነትና መታደስ አንድ ላይ ይተምሙ ይሆን? ቀሪ ፈተናዎቻችንን የማለፉ ተግባር በኅብረት መትመምን አሁንም እየተማፀነ ነው፡፡ በውስጥና በውጭ የሞቀው አገር ወዳድ አርበኝነትም ፖለቲከኞቻችንን ኧረ አትፍዘዙ እያለ ነው፡፡ በህዳሴ ግድብ ሙሌት ላይ ያተኮረው የሱዳንና የግብፅ ጫና ዓረብ ሊግን “እስከ ማስተባበር” ሄዷል፡፡ በተግባርም በሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ ወገኖቻችን (መኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ጭምር) መቀጣጫ ስለመደረጋቸው ለመስማት ብዙ ጊዜ አልፈጀም፡፡ ወዲህም ወዲያ ቢባል የውኃ ሙሌቱ ተፈጥሯዊ መርሐ ግብር ያለው ነው፡፡ በሌላ በኩል በትግራይና በኦሮሚያ ያለው የሕወሓት-ሸኔ ሽፍትነት፣ ለሕዝብ ጥያቄና ጉስቁልና አሳቢ ነኝ ከሚል ቆዳ የተሠራ ልብስ ሳይደርብ ራቁቱን መቅረት አለበት፡፡ እንደ እነ አፍጋኒስታን ከታሊባን ጋር ተደራድራችሁ እንደምትሆኑ ሁኑ ከሚል “የአሳቢዎቻችን” ምክር የተሻለ አዛላቂ መፍትሔን የማሳካታችን ነገርም፣ ወደ ሰላም የመግባት ጥሪ ጆሮ ሊያገኝ በሚችልበት ደረጃ ቡድኖቹ ሲፈርጡ፣ ራቁታቸውን ሲቀሩ ወይም የለውጣችን አመርቂነት ሲያሳጣቸው ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ውጤቶችን ፈጥኖ ማግኘት ደግሞ ምትሐታዊ ጥበብ ይሻ ይመስለኛል፡፡ የምትሐት ጥበበኞች ትርዒታቸው የሚሰምርላቸው ትርዒታቸው ሰምና ወርቅ ስላለው ነው፡፡ ወርቃዊ ትርዒታቸውን ልብ እንዳንል በሽፋናዊ ፈጣን እንቅስቃሴ ትኩረታችንን ያቄሉታል፣ ወይም የሚሠሩትን ነገር በተለያየ ሳይንሳዊ ቴክኒክ ሰውረው ለዓይን የማይታመን ያደርጉታል፡፡ በእኛ አገር ከጥንት ጀምሮ ምትሐት የሚችሉ፣ አንዱን ነገር በሌላው ውስጥ የሚሰወሩ፣ ገና ነው ሲባል የሚያቀላጥፉ፣ እዚህ ናቸው ሲባል ከማዶ የሚታዩ ነበሩ ይባላል፣ ዛሬም አሉ ይባላል፡፡ የዚህ ዓይነት ጥበበኞች በመንግሥት ቤት ውስጥ አይኖሩ ይሆን? 

ምትሐት ሠራም አልሠራ ግን አንድ ላይ መትመም ሰምሮልንና ከሞላ ጎደል የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ ተጎናፅፈን የአሁኑን እጅግ እጅግ ውድ ክረምት በአግባቡ ለመጠቀም፣ በየትኛውም ሥፍራ ያለ ተፈናቃይነትንና ዕርዳታ ጠባቂነትን ወደ አምራችነት አሰማርቶ የአገሪቱን ጥቅል ምርት ማስመንደግ፣ የረሃብ ሥጋትን በየትኛውም አካባቢ ማስቀረት፣ እናም የመንግሥትን የዕርዳታ ጫና ማቅለልና የኑሮ ውድነቱን ማርገብ የሁላችንም የርብርብ ትኩረት መደረጉ፣ ከሕዝብ የአንጀት ጉዳይ ጋር መገናኘት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በህዳሴ ግድብ የዘንድሮ ውኃ ሙሌት ላይ ያሉ ጫጫታዎችንና እክል ፈጠራዎችን በማኮምሸሽ ረገድ፣ የፖለቲከኞቻችን አንድ ላይ መትመም የሚኖረው አንድምታዊ ጉልበት የትየለሌ ነው፡፡

ይደሩ ይዘግዩ ከማይባሉት ከእነዚህ ተግባሮች አኳያ፣ የድኅረ ምርጫ ነገረ ሥራችን ብዙ ዋጋ ካስከፈለ ልምዳችን ትምህርት መውሰድ አለመውሰዳችን የሚታይበት ሌላ የፈተና ወቅት ነው፡፡ ነገሮችን አግንነን ምርጫውን ሰድቦ ለሳዳቢ ከመስጠትም በላይ፣ ሌላ ኪሳራ የሚያስከፍል ግርግር ወደ ማነሳሳት እንሄዳለን? ወይስ በውጤታማነት ጥቅል ባህርዩና በወደፊት ትምህርት ሰጪነቱ ምርጫውን አቅፈን፣ ፈጥኖ ከመታረም ያመለጡና ውጤት ላይ ጫና ያላቸው ብልሽቶች ቢኖሩ በተገቢው ሥርዓት በኩል አቤት በማለት፣ ለአቤቱታና ለክስ ፈጣን መፍትሔ በመስጠትና የተሰጠ ውሳኔን/ብያኔን በመቀበል፣ ሥርዓት አክብሮ አብሮ መሥራትን እንደምንችልበት እናስመሰክራለን? ከማስመስከርና ክፏችንን የሚጓጉ ኃይሎችን ወሽመጥ ከመበጠስ በላይ፣ ወደ የሚብስብን አጣዳፊ የርብርብ ተግባራችንስ ቀልባችንን እናዞራለን? ለውጣችንና አገራችን ከተጠሟቸው አንገብጋቢ ነገሮች አንዱ እንዲህ ያለውን የፖለቲከኞች ጉብዝና ነው፡፡

የምርጫውን ዝባዝንኬ በቶሎ ካቀላጠፍን ወዲያ፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ አንድነት ውስጥ የምናስብ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይሎችና ምሁራን የጋራ መግባባት ሰምሮልን ኅብረተሰባችንን በአገር ሰላም ግንባታ፣ በልማትና የሕዝብ ኑሮን በማቅለል ተጋድሎ ላይ ማነቃነቅ ከቻልን ድላችን ብዙ ነው፡፡

የጎረቤቶቻችንን ሕዝቦች ማክበርና ዓባይ ያስተሳሰረን ሕዝቦች ላላቸው ፍትሐዊ  የውኃ ጥቅም ታማኝ መሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የመላ ኅብረተሰባችን አቋም እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የማንም ጉያ ውስጥ ሳትገባ በጋራ ጥቅም ከማንኛውም አገር ጋር ተወዳጅቶ የመኖር መርህ ያላትና በምሥራቅ አፍሪካ ጉርብትና ውስጥ አብጤ (ቡልዶዘር) የመሆን ፍላጎት የሌላት፣ ህልሟኗ ጥረቷ በእኩልነትና በመተጋገዝ አብሮ መልማት ላይ ያነጣጠረ፣ የጋራ ሰላምንና ወዳጅነትን ለመንከባብ የትኛውንም አለመግባባትና የግጭት ክስተት በውይይት/በድርድር መፍታትን ከምንም ነገር በላይ የምታበልጥ ስለመሆኗም ፅኑ እምነቴ ነው፡፡ የህዳሴ ግድብ ስኬትም ዓላማ ከጅምሩ ማንንም መጉዳት አይደለምና የግድቡ መጠናቀቅና ወደ ታለመለት ሥራ መግባት፣ ለሱዳንና ለግብፅ ሕዝቦችም “ኢትዮጵያ ዓባይን ገድባ በነፍስህ መጥታብሃለች!” ከሚል የማስፈራሪያ እስራት ነፃ መውጪያቸው እንደሚሆንም ይታመናል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አቋም ሁሉን በአቀፈ የኢትዮጵያ ጉባዔ መንፀባረቁ ዋጋው ከፕሮፓጋንዳ በላይ ነው፡፡

ጠመንጃ አምላኪነት ጋር የቆረቡና ሕዝብን ሰላም መንሳትንና ግድያን “ፖለቲካ” ያደረጉ የጥፋት ኃይሎች እንደምን ከሕዝብ ጋር ሊፋጠጡ ይችላሉ እያልኩ ሳሰላስል፣ ከሰኔ 21 ቀን 2013 ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብና ለክረምቱ ሳስቶ የተናጠል የተኩስ ማቆም ማድረጉን የዕለቱ ዕለት ማታ መስማቴ በድፍኑ መልካም ይመስለኛል፡፡ ማን ያውቃል? ውሳኔው ያልጠበቅነውን ምትሐታዊ ውጤት ወደፊት ይፈለቅቅልንም ይሆናል፡፡ ከዚህም ባሻገር ወደፊት የሕዝብ ለሕዝብ መግባባትን፣ ስምምነትንና መተማመንን መሠረት ያደረጉ (መሬት ለመመንተፍም ሆነ የራስ በራስ አስተዳደርን ለመደፍጠጥ በማይመች አደራጃጀት) በልማት አቅም የተመጣጠኑ “ክልሎች” የመፍጠር ዕድል ኖሮ፣ በዚያ አማካይነት ትግራይም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች የተሻለ የመልማት አቅም የማግኘታቸው በር ክፍት እንደሚሆንም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የትግራዊም ሆነ የሌላ አካባቢ የኢትዮጵያ ዜጋ ህልውናው በየአካባቢው ያልታጠረ መሆኑን፣ አገሩ ሰፊዋ ኢትዮጵያ መሆኗን በሁላችንም ልብ ውስጥ የሚሞላ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አየር ንብረት የማልማት ሥራ በአዲሱ መንግሥት ትኩረት እንደሚያገኝም እተማመናለሁ፡፡

የፓርቲዎች ፕሮግራሞች ወይም በምርጫ ጊዜ የሚያሰናዷቸው ዕቅዶች ማንም “የብቻዬ ናቸውና እንዳይቀዳብኝ/ካልተመረጥኩ ለመጪው ምርጫ አስቀምጣቸዋለሁ” ተብሎ የሚሰስትባቸው አይደሉም፡፡ እነሱን ይዤ ብቅ ጥልቅ እያደረግሁ እኖራለሁ ማለትም ከጊዜ ወደ ኋላ መቅረት ነው፡፡ በአንድ የምርጫ ዘመን ውስጥ ብዙ ነገሮች ይቀያየራሉ፡፡ የሰሰትንለት መርሐ ግብር ሊያረጅ ይችላል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህያውነት የሚኖራቸው ሁኔታዎች ባልተቀየሩብኝ ወይም ዕቅዴ በሌላው ተፈጻሚ ሳይሆን በቆየልኝ በሚል ፀሎት ሳይሆን፣ ሥልጣን ቢይዙም ባይዙም ለሕዝብ ይበጃል ብለው ያቀዱት ነገር በወቅቱ ተፈጻሚነት እንዲያገኝ በመታገልና የተለወጡ እውነታዎች ይዘዋቸው የሚመጡ ተግባሮችን እያነበቡ ትኩስ መርሐ ግብሮችን በመቀመር ነው፡፡ በእኛ አገር ፖለቲካ ውስጥ ሕዝብና ኑሮን የሚመለከቱ የፓርቲ ዕቅዶች ተልዕኮ ከፓርቲ ይልቅ ሕዝብን መጥቀም መሆኑን የመቀበልና ለዚያ የማደር ችግር አለ፡፡ “እከሌ ፓርቲ እኔ ያነሳሁትን ጥያቄ ኮርጆ ወሰደ” ተብሎ ነቀፋና ንቀት ሲረጭ እንደታዘብን ሁሉ፣ ምርጫ ዘመቻ እስኪ ደርስ መርሐ ግብርን በሚስጥር መያዝን አስተውለናል፡፡ የቀዳም ቢጠየቅ እንኳ ከመሸምጠጥ አይመለስ ይሆናል፡፡ ከእከሌ ፓርቲ ወስደኩ ማለት ስለሚያስንቅ፡፡ ይህንን ዓይነት ዝተት አስተሳሰብ ማፈራረስና በየምርጫ ዘመኑ አሸናፊ የሆነ ፓርቲ በተፎካካሪዎቹ ፓርቲዎች በኩል የፈለቁ ዕቅዶችን ፋይዳ ገምግሞ የሥራ ዕቅዱን ማበልፀጉ የሚያስከብርና አስፈላጊ ነው፡፡ የአሁኑ የፓርቲዎች መተባበር ለዚህ ዓይነቱ ለውጥ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ፓርቲዎች በጋራ መግባባት ጉባዔም በኩልም ሆነ በጋራ ምክር ቤታቸው በኩል፣ ይብሳሉ የሚሏቸው ጉዳዮች ተሰሚነት እንዲያገኙ መጣጣር ይጠበቅቸዋል፡፡ ለምሳሌ ኢዜማ ያነሳቸው የሕዝብ ቁጥር ምጣኔ አሳሳቢነት ጉዳይና የሕዝብ ቆጠራ ትክክለኛነት በፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች የመበረዙ ችግር፣ እንደ ዋዛ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ድጎማና የውክልና ወንበር እያታሰበ የሚካሄድ የሕዝብ ቆጠራን አጠያያቂነት ሳይነኩ ሙስናን ማሸነፍ እንዴት ይቻላል?

1999 ዓ.ም. በጻፍኩት ‹‹የሰሚ ያለህ›› በተሰኘ መጽሐፌ ውስጥ በጉራጌ ማኅረሰቦች አካባቢ ዝነኛ የሆነውን “ዕድሜ ልክ ሽምብራ ከመቆርጠም ለተወሰኑ ዓመታት መቆርጠም” የሚል አባባል ለጊዜው ችግር ይበጅ ብዬ ሰንዝሬ ነበር፡፡ ከዚያ ጊዜ ይበልጥ የዛሬው እውነታችን አፍ አውጥቶ ይህንን አባባል አንገብጋቢ አድርጎታል፡፡ የአባባሉ ይዘት ብክነትንና ዘርፎ ማዘረፍን የሚቃረን ነው፡፡ ዕርዳታና ድጋፍ የመሸምቀቅ አርጩሜ ቆጥቁጦን ከሆነ መፍትሔው ኮስማና አቅማችንን መቀየር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከባካና አኗኗር መውጣት ትንሹ ማኮብኮቢያ ነው፡፡ በዚህ ጥቅል አርበኝነት ውስጥ ብዙ ነገሮች ይመጣሉ፡፡ በመንግሥት ቤትና በግል በኩል ያለ ተምነሽናሽነትንና አድፋፊ የሀብት አጠቃቀምን መቀነስ፣ የቅንጦት ዕቃዎችን ከማስገባትና ነዳጅ የሚፈጁ ተሽከርካሪዎችን ከመጠቀም መቆጠብ፣ ግብርን ባለመሸፈጥና በተቋማት ውስጥ የሚካሄድ ምዝበራን፣ እንዲሁም የኮንትሮባንድ ቅብብልን በመታገል አገርን ማገዝ፣ አገራዊ የውጭ ምንዛሪ ጥሪትን ለማሳደግ ሁሉም በአቅሙ መረባረብ፣ ፈጣን ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች ውስጥ ባለሀብቶች ከመጋፋት ይልቅ፣ ገቢ ዕቃዎችን ወደ የሚተኩና ወጪ ንግድን ወደ የሚያሳድጉ የማምረት መስኮች ማለፍና ባለሀብቶች ወደዚህ እንዲሳቡ የመንግሥት ማገዝ ሁሉ የተጋድሎ ፈርጆች ናቸው፡፡ ስለብክነት ሳወራ ‹ንቅናቄ› ቀመስ ተግባሮችን በሚያስተዋውቁ ሽብርቆችና በ2013 የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ያስተዋልኳቸው አንዳንድ ኩንስንስ እንቅስቃሴዎች ትዝ ትዝ እያሉኝ ነው፡፡ ብዙ ሰው የመረጣቸው ፓርቲዎች ጌጣ ጌጥና የማስታወቂያ ጋጋታ አስመርጦናል ብለው ያስባሉ ብዬም አላምንም፡፡ የክረምት በጎ አድራጎት መርሐ ግብር ተጀምሮ የደካማ አዛውንቶችን ከሞት የማይሻል ኑሮ የማቅናት እንቅስቃሴን ባየሁ ጊዜ፣ በተቀናጣ ሽብርቅ ላይ የሚውልና የናረ ቅንጡነት ላይ በየምሽቱ የሚፈስ ገንዘብ አቅጣጫውን ወደዚህ ዓይነትና ራስ አገዝ ጥቃቅን ሥራዎችን ወደሚያበዛ በጎ ሥራ ቢያዞር ስንት ወገን ተመስገን ባለ ብዬ አሰብኩ፡፡ ቁጥብ አኗኗር በራሱ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ያለውም ጥቅም የዋዛ አይደለም፡፡ የመንግሥት ሰዎችና የግል ደልቃቆች በዚህ የቋፍ አቅማችን ጊዜ ለሌላው አርዓያ እንሆናለን ብለው አምነው ይህንን የአኗኗር ለውጥ በአደባባይ ቢያንፀባርቁትና በተግባር ቢሞካክሩት ምሳሌነታቸው ብዙ ተከታይ እንደሚያፈራ አልጠራጠርም፡፡

ቀበቶና መቀነት ባጠበቀ ቆራጥነት አኮብኩበን የልማት ግስጋሴን፣ ሰላምንና የዴሞክራሲ ነፃነትን የሚያንቦገቡግ ጉዞ ውስጥ ከተመምን፣ አያያዛችን ገና በጅምሩ ደረጃ ላይ ትልቁን የምትሐት ሥራ፣ ማለትም ሕዝብን የማባላትና በየጥጋጥጉ ልተኩስ ባይነትን የመበታተክ ሥራ እንደሚያካሂድልን ሙሉ እምነቴ ነው፡፡ እንዲህ ያለው በጎ ስኬት ኢትዮጵያ ላይ እንደሚፈካም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡                                                                                                

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...