በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ እመርታ እያሳዩ ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱት የግል ባንኮች አንዱ የሆነው የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ በ2013 የሒሳብ ዓመት በተለያዩ የሥራ አፈጻጸሞች 107 በመቶ የሚደርስ ዕድገት ማስመዝገቡን ገልጿል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ አጠቃላይ አፈጻጸሙን በተመለከተ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ደርቤ አስፋው በሰጡት መግለጫ፣ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ሌላ በሁሉም የባንኩ የሥራ ዘርፎች ያሳየው አፈጻጸም ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ ውጤት እንዲያስመዘግብና ከታክስ በፊት 2.11 ቢሊዮን ብር እንዲያተርፍ አስችሎታል ብለዋል፡፡
የባንኩን አጠቃላይ አፈጻጸም በተመለከተ በአኃዝ አስደግፈው በሰጡት መግለጫ፣ በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችለው 107 በመቶ ዕድገት ያሳየው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሰጠው ብድር ነው፡፡
ባንኩ በተጠናቀቀው የ2013 የሒሳብ ዓመት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ፋይናንስ ያደረገው ወይም የሰጠው የብድር መጠን 8.29 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ እንደ አቶ ደርቤ፣ ይህ አፈጻጸም እስካሁን በመስኮት ደረጃ የዚህን ያህል ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያቀረበ እንደሌለ ያሳያል፡፡
በዚህ ዘርፍ የተሰጠው የብድር መጠን ባንኩ በቀደመው ዓመት ከሰጠው ብድር አንፃር ሲታይ የ107 በመቶ ዕድገት ማሳየት መቻሉ ነው፡፡ አምና ከወለድ ነፃ በሆነ መንገድ የሰጠው ብድር አራት ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ከዘንድሮው ጋር ሲነፃፀር ዕድገቱ ከፍተኛ የሚባል ሆኗል፡፡
ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያሰባሰበው የቁጠባ ገንዘብ መጠን በ87 በመቶ ዕድገት በማሳየት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 11.89 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በዚህን ያህል ደረጃ ከፍ ማድረግ የቻለው የአስቀማጮቹን ቁጥር 1.86 ሚሊዮን ማድረስ በመቻሉ ነው፡፡
በዚህ አገልግሎት ዘርፍ የተሰጠው ብድር ከፍተኛ የሚባልና አገልግሎቱ አዲስ ከመሆኑ አንፃር ተግዳሮት አልገጠማችሁም ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ደርቤ፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የቢዝነስ አዋጭነት በደንብ የሚታይ ነው፡፡ ደንበኞች ፋይናንሱን ፈልገው ሲመጡ ሥራቸው ያዋጣል አያዋጣም? የሚለው ታይቶ ብድሩ ተሰጥቷል፡፡ ከዚህ አንፃር የገጠመን ችግር የለም ብለዋል፡፡
በዚህ አገልግሎት ፋብሪካ ጭምር ፋይናንስ ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ደርቤ፣ ትልልቅ ፋብሪካዎች ሳይቀሩ ፋይናንስ በመደረጋቸው ከወለድ ነፃ የሰጡት ብድር ወይም ፋይናንስ ያደረጉት ገንዘብ ከፍተኛ ሊሆን መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ገንዘብን ሰብስቦ ማስቀመጥ ሸሪአውም የማይፈቅድ ስለመሆኑ አስታውሰው፣ ከሕዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ በቶሎ ፋይናንስ መደረግ ስላለበት በዚሁ መሠረት በመሥራታቸው ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ በተሰጠው መግለጫ ባንኩ ከፍተኛ እመርታ አሳይቶበታል የተባለው በአጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ያገኘው ውጤት ነው፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 72.69 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ተቀማጭ ገንዘብ ካሰባሰቡ ባንኮች መካከል አንዱ ያደርገዋል፡፡ ተቀማጭ ገንዘቡ በቀዳሚው ዓመት ከነበረው 45.51 ቢሊዮን ብር አንፃር ሲታይ በ27.18 ቢሊዮን ብር ወይም በ60 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ባንኩ ይህንን ያህል ጭማሪ ያለው የተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ የቻለው በሒሳብ ዓመቱ 1.4 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ቆጣቢዎችን ማፍራት በመቻሉና ከብር ለውጡ ጋር ተያይዞ በርካታ ዜጎች ገንዘባቸውን ወደ ባንክ በማምጣታቸው ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡
አቶ ደርቤም እንደገለጹት፣ ዘንድሮ በተለይ ትልልቅ የሚባሉት ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸው በከፍተኛ ደረጃ የጨመረ ሲሆን፣ ለዚህም የብር ኖት ለውጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡
ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠውን የብድር መጠን በ64 በመቶ ማሳደጉን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ አጠቃላይ የብድር ክምችቱ 56 ቢሊዮን ብር መድረሱን አመልክተዋል፡፡ አምና በተመሳሳይ ወቅት ባንኩ የነበረው የብድር ክምችት መጠን 34.21 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በ2013 ዓ.ም. ብቻ የሰጠው አዲስ የብድር መጠን 21.79 ቢሊዮን ብር በመሆኑ የብድር ክምችት መጠኑ 56 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡
ባንኩ ከብድር አመላለስ አንፃር እንዴት ይመዘናል ለሚለውም ‹‹አንድን ባንክ ጤናማ የሚያስብለው የሰጠውን ብድር በአግባቡ ሲያስመልስ ነው›› ያሉት አቶ ደርቤ፣ በዚህ ረገድ ባንካቸው ጥሩ አፈጻጸም እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ የተበላሸ የብድር መጠኑ ከሁለት በመቶ በታች በመሆኑ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአምስት በመቶ አንፃር ሲታይም የተሰጠው ብድር በአግባቡ ማስመለስ መቻሉን ያሳያል ብለዋል፡፡
ነገር ግን በዓለም ላይም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የባንኮች ፈተና የሆነው ብዙ ማምረቻዎችና ተያያዥ ቢዝነሶች በኮቪድ-19 ምክንያት ብድር የማራዘም ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን ነው፡፡ በተለይ በአገልግሎት ዘርፍ የሆቴልና የቱሪዝም ዘርፍ በእጅጉ ተጠቃሚ ቢሆንም፣ ባንካቸው በዚህ ረገድ ብዙው ችግር ያልተፈጠረበት መሆኑን ነው፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ባንኩ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሰጠው ብድር አነስተኛ መሆኑ ከብድር አመላለስ ጋር በተያያዘ ችግር እንዳይገጥመው እንዳደረገም ገልጸዋል፡፡ ባንኩ ለብድር ካዋለው ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ ውስጥ ብልጫ ያለውን ብድር የሰጠው ለአገር ውስጥ ንግድ፣ ለማኑፋክቸሪንግና ለወጪ ንግድ ነው፡፡
የባንኩን ካፒታል ዕድገት በተመለከተ በተሰጠው ማብራሪያ፣ በ2012 መጨረሻ ላይ ሦስት ቢሊዮን ብር የነበረውን የተከፈለ ካፒታል በሦስት ዓመት ውስጥ ወደ አሥር ቢሊዮን ለማሳደግ በተወሰነው ውሳኔ መሠረት ዘንድሮ የተከፈለ ካፒታሉ 4.65 ቢሊዮን ደርሷል፡፡
ይህ አፈጻም ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው መመርያ መሠረት የተከፈለ ካፒታሉን አምስት ቢሊዮን ብር ለማድረስ የቀረው 350 ሚሊዮን ብር በመሆኑ ቀጣይ ሳምንት ይህንን ለማሟላት እንደሚችል አቶ ደርቤ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ 8.08 ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ይህ ገቢ ከዓምናው በ58 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡ ወጪው ደግሞ 5.9 ቢሊዮን ብር እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ አንፃር ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት 2.11 ቢሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉንም አቶ ደርቤ ገልጸዋል፡፡
ይህ የትርፍ መጠን በሒሳብ ዓመቱ ከግል ባንኮች ከፍተኛ ከሚባሉት አራት ባንኮች አንዱ ያደርገዋል፡፡
በ2013 ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ በ38 በመቶ ወይም የ1.53 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳየው በውጭ ምንዛሪ ግኝት ነው፡፡ በባንኩ መረጃ መሠረት፣ በ2013 የሒሳብ ዓመት ያገኘው የውጭ ምንዛሪ 343 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ አፈጻጸም ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ በ20 ሚሊዮን ዶላር ወይም በስድስት በመቶ ቀንሷል፡፡ ዓምና አሰጥቶ የነበረው 363 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡
ለቅናሹ ምክንያት የሆነው ኮቪድ-19 ነው ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ደርቤ፣ ኮቪድ-19 የውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ ተፅዕኖ ቢኖረውም፣ ባንኩ ዘንድሮ ከውጭ ምንዛሪ ያገኘነው ገቢ ከአምናው አንፃር ሲታይ መቀነሱ በኮቪድ-19ኝ ተፅዕኖ ብቻ ነው ለማለት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡
ምክንያታቸው ደግሞ ዘንድሮ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በመጨመሩ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በስድስት በመቶ መቀነሱ ኮቪድ ብቻ በፈጠረው ተፅዕኖ ነው እንዳይሉና የራሳቸውን አሠራር መፈተሽ እንደሚኖርባቸው ያመለከተ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ባንኩ መረጃ፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ የሀብት መጠን በ54 በመቶ አድጓል፡፡ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ የባንኩን አጠቃላይ የሀብት መጠን 81 ቢሊዮን ብር ማድረስ ተችሏል፡፡
ባንኩ ከሌሎች የግል ባንኮች አንፃር በተለየ የሚታይበትና አሁንም የቀጠለበት አንድ አፈጻጸም የባንኩ አስቀማጮችን ቁጥር የሚመለከት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከሁሉም የግል ባንኮች ከፍተኛ የሚባሉ የባንክ አስቀማጮች ያለው ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀጥሎ ከፍተኛ አስቀማጮች ያለው ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡ ዘንድሮም አዳዲስ 1.48 ሚሊዮን ደንበኞችን በማፍራት አጠቃላይ የባንኩ አስቀማጮን ቁጥር 7.73 ሚሊዮን አድርሷል፡፡
ባንኩ በአሁኑ ወቅት 469 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ ከነዚህ ቅርንጫፎች ውስጥ 77 በመቶዎቹ በገጠራማው የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ናቸው፡፡ ባንኩ 14,200 ባለአክሲዮኖች ሲኖሩት፣ 64 በመቶው ማኅበራት ናቸው፡፡ ከነዚህ ማኅበራት በሚሊዮን የሚቆጠር አባላት ያሉዋቸው እንዳሉም ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡