Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሃይ ባይ ያጣው የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ

እንደ ዋዛ የሚታለፉ አንዳንድ ነገሮች ውለው አድረው የአገርና የዜጎች ችግር ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ተፅዕኖዎች ጭምር ዜጎችን እያማረረ ያለው የኑሮ ውድነት የመፍትሔ ያለህ እያስባለ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ቅጥ እያጣ የመጣው የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ ደግሞ ሌላ ገጽታ እየያዘ ነው፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግር እንዴት ይፈታል? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ከባድ ቢሆንም፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ ቅጥ ያጣና ተቆጣጣሪ የሌለው ሆኖ መገኘት አጠቃላይ የዋጋ ንረቱን በእጅጉ ከፍ እያደረገው ነው፡፡

ዜጎች በገዛ አገራቸው ቤት ተከራይተው የመኖር መብታቸውን የሚጋፋ ተግባርም እየተፈጸመ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ እንደ ቀላል ነገር የሚታይ ያለመሆኑ እየታወቀ ትኩረት የተሰጠው ባለመሆኑ፣ ተከራዩ ላይ በወራት ልዩነት እንደተፈለገ የቤት ኪራይ ዋጋ እየተጨመረበት ነው፡፡ በዋጋ ንረት ያጎበጠው ሕዝብ ያለ ይሉኝታ እየተጨመረበት ያለው የቤት ኪራይ ኑሮን የበለጠ ጎምዛዛ እያደረገበት ነው፡፡

በተለይ ባለፉት ሁለትና ሦስት ወራት አከራዮች በዘመቻ የተነሱ እስኪመስል ድረስ፣ ‹‹የቤት ኪራይ ጨምሩ›› የሚለው ጥያቄያቸው ተከራዩን በእጅጉ እያማረረ ነው፡፡ የዋጋ አጨማመሩ ደግሞ ሥርዓት ያጣ፣ ወቅታዊውን ሁኔታ ያላገናዘበ ጭምር እየሆነ ነው፡፡ ከተከራዩ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለዳግም የቤት ኪራይ ጭማሪ ጥያቄ የሚመጡ አከራዮች ጉዳይ አንድ መላ ካልተፈለገለት ነገሩ አደገኛ ይሆናል፡፡ በተለይ በኮንዶሚኒየም አካባቢ ያለውን ሁኔታ በደንብ ከተገነዘብን ሆን ተብሎ የሚፈጸመው ሸፍጥ የአከራይና የተከራይ ጉዳይ በሕግ የታገዘ መሆን የሚገባው መሆኑን ነው፡፡

የቤት ኪራይ ዋጋ ከመተመን ጀምሮ፣ የዋጋ ጭማሪ በምን አግባብ መሆን እንደሚገባው ታምኖ ተረቆ የተቀመጠውን ሕግ ዞር ብሎ የሚያየው በመጥፋቱ የአከራይና የተከራይ ጉዳይ ሕግ አልባ እየሆነ ችግሩም ሥር እየሰደደ መጥቷል፡፡

የዜጎችን መብትና ግዴታንም መለየት እስኪያቅት ድረስ እየሆነም ነው፡፡ ቤት ማከራየት እንደ አንድ አገልግሎት በመሆኑ እንደፈለገ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ ተከራዮች ሕይወታቸውን ተረጋግተው እንዳይመሩ ከማድረጉም በላይ ነገሩን ሕግ የሌለበት አገር አስመስሎታል፡፡

ለዚህ ደግሞ አሁንም በኮንዶሚኒም ቤቶች አካባቢ የሚፈጸመው ደባ ምግባር የሌላቸው አከራዮች ከደላሎች ጋር በመመሳጠር የሚሠሩት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በየኮንዶሚኒየሙ ያሉ ጥበቃዎችም ቢሆኑ የዚህ ተባባሪ ሆነው ይታያሉ፡፡ ቤትህን በዚህን ያህል ዋጋ እናከራያለን ብለው በሰላም የተቀመጠውን አከራይ ጭምር እየቀሰቀሱ ዜጎችን የደላላ መጫወቻ እያደረጉ ነው፡፡

አሁን ያለው የዋጋ ንረት እንቅልፍ የነሳው ተከራይ ተረጋግቶ እንዳይኖር አከራዮች ሰብዓዊ መብቱን እየነኩትም ይገኛል፡፡ ይህ እጅግ አሳዛኝ ተግባር መላ ካልተበጀለትና እንዳሻቸው ይሁኑ ብሎ ዝም ከተባለ ሥርዓት አልበኝነቱ ይጎላል፡፡ በየትኛውም አገልጋይና ተገልጋይ መካከል ያለው ግንኙነትም በዘፈቀደ ይሁን የሚባልበት ምክንያት የለምና ሕግ ያስፈልጋል፣ መተግበር አለበት፡፡ በአግባቡ ተከራዮችን የሚያስተናግዱ መብትና ግዴታቸውን የማያውቁ አከራዮች ቢኖሩም፣ አሁን አሁን ግን እነሱንም በመጫን ወዳልተፈለገ መንገድ እንዲሄዱ እየተደረገ መሆኑ ሲታሰብ የሁኔታውን አሳሳቢነት አንድንረዳ ያደርገናል፡፡   

ስለዚህ የአከራይና የተከራይን መብትና ግዴታዎች የያዘ እንዲሁም የቤት ኪራይ ተመንን በግልጽ ለማስቀመጥ ይረዳል የተባለው ረቂቅ ሕግ ዝም ብሎ አዋራ እየጠጣ ያለበት ምክንያት ለብዙዎቻችን እንቆቅልሽ ሆኗልና የሕግ ያለህ ማለት ተገቢ ነው፡፡

መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም፡፡ ሕጉ ለምን ተግባራዊ እንዳልሆነም መመርመር አለበት፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችም ምን እየሠሩ እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን፡፡

ረቂቁ ቀርቦለት የነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ቢሆን ይህ ረቂቅ የት ደረሰ? ብሎ ለምን እንዳልጠየቀም መልስ እንሻለን፡፡ ምክንያቱም ቤት የብዙ ተከራዮች ፈተና ሆኗልና ነው፡፡ መንግሥትም ችግሩን በመረዳት ረቂቅ አዋጁን ተመልክቶ ሕጉ እንዲወጣ ማድረግ ይጠበቅበታል የሚል ጥያቄ እንድናነሳ እያደረገን ነው፡፡

ብልሹ አመል ያላቸው አከራዮች እየፈጸሙ ያሉት ተግባር የሚፈጥረው ማኅበራዊ ቀውስ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ በተለይ በከተሞች አካባቢ መሠረታዊ ችግር እየሆነ ከመምጣት አልፎ መንግሥት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚገቡ አንገብጋቢ ችግሮች መካከል መያዝ አለበት፡፡

በእርግጥ እንዲህ ያለውን ችግር ለመፍታት ዘላቂ መፍትሔው የመኖሪያ ቤቶችን ግንባታ ማስፋፋትና አማራጮችን መጠቀም ነው፡፡ ይህ እስኪሆን ድረስ ግን ዜጎች መሄጃ የላችሁምና ቻሉት መባል የለባቸውም፡፡ እንዲህ ያለ ሰቀቀን ሥራንም በአግባቡ ለመሥራት፣ ልጆችንም አንድ ቦታ በተረጋጋ ሁኔታ ለማሳደግና ከለመዱበት ትምህርት ቤት ሳይርቁ እንዲማሩ ለማድረግ የቤት ኪራይ ዋጋ ላይ መመርያ ሊቀመጥ ይገባል፡፡  እንደዋዛ ዝም ተብሎ የሚፈጸሙ ያልተገቡ ተግባራትን በኋላ ለማስተካከል ይከብዳልና የአከራይና የተከራይ ሕግ ይፅደቅልን፡፡ የዜጎች መብትና ግዴታም በግልጽ ታውቆ አሠራራችን መስመር ይያዝ፡፡         

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት