Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበ30 የምርጫ ጣቢያዎች ነገ ድምፅ ይሰጣል

በ30 የምርጫ ጣቢያዎች ነገ ድምፅ ይሰጣል

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ባስፈጸመው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ መስጠት እንዲቆም ባደረገባቸው 30 የምርጫ ጣቢያዎች፣ ነገ ሐሙስ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምፅ እንደሚሰጥ ተገለጸ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ነገሌ የምርጫ ክልል በ139 የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ እንዲሰጥባቸው የታተሙ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች፣ የአንድ የግል ተወዳዳሪ ስምና ምሥል ሳይዙ በመታተማቸው፣ የግል ዕጩዋ ለቦርዱ ይኼንን በማስታወቃቸው የምርጫ ሒደቱ እንዲቆም መመርያ የተላለፈ ቢሆንም፣ ከ30 የምርጫ ጣቢያዎች በስተቀር ሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫውን አስፈጽመዋል፡፡

ቦርዱ ለምርጫ ክልሎች ያስተላለፈው መልዕክት በስልክ ግንኙነትና የኢንተርኔት መቆራረጥ ችግር መረጃው ለሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ሳይደርስ ቀርቶ፣ 109 የምርጫ ጣቢያዎች እንደተቀሩት የአገሪቱ የምርጫ ክልሎች ሁሉ ተሠልፈው ሲመርጡ መዋላቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

- Advertisement -

ነገር ግን በተመሳሳይ ቀን የግል ዕጩ ሆነው በምርጫ ክልሉ ከሦስት የብልፅግና ፓርቲ አባላት ጋር በመሆን የቀረቡት ዱሬ ቡዴ ጎበና፣ ምርጫው ለእሳቸው ተብሎ ከሚቋረጥና በድጋሚ ከሚከናወን ዕጩነታቸውን ይቅር ብለው ለቦርዱ አስታውቀው ነበር፡፡ ይሁንና በድምፅ መስጫው ቀን ቦርዱ ከዕጩዋ የተላከለት ደብዳቤ የእሳቸው መሆኑን ለማጣራትና ምርጫው እንዲቀጥል ውሳኔ ለመስጠት አጭር ጊዜ ስለሆነበት፣ በምርጫ ክልሉ ሥር የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በሙሉ ድምፅ መስጠት እንዲያቋርጡና የተላኩ ሰነዶች በሙሉ ታሽገው እንዲቀመጡ ወስኖ ነበር፡፡

ሆኖም በኋላ በተደረገ ማጣራትና ከግል ዕጩዋ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ለቦርዱ የተላከው ደብዳቤ የእሳቸው መሆኑ በመረጋገጡ፣ እሳቸውም ዕጩነታቸውን በመተዋቸው ሳቢያ ድምፅ የተሰጠባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ውጤቶች እንዲቆጠሩና እንዲመዘገቡ፣ እንዲሁም የተቀሩት 30 የምርጫ ጣቢያዎች ቦርዱ በሚወስነው መሠረት ቀን ተቆርጦ ድምፅ እንደሚሰጥ ተገልጾ ነበር፡፡ በወቅቱ በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች የሚደረገው የድምፅ መስጫ ቀን በቅርቡ እንዲደረግ መወሰኑ ተነግሮም ነበር፡፡

በዚህም መሠረት የምርጫ ቦርድ የኮሙዩኒኬሽን ከፍተኛ አማካሪ ወ/ሪት ሶልያና ሽመልስ ሰኞ ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል በሰጡት መግለጫ፣ የእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ መስጫ ቀን ሐሙስ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲሆን መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ ከቁጫ የምርጫ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች ውጤት በማዳመር ላይ አቤቱታ በማቅረባቸውና በአካባቢው ሪፖርት በተደረገ የፀጥታ ችግር ሳቢያ፣ በምርጫ ክልል ደረጃ የሚደረገው የምርጫ ማዳመር ሥራ ሙሉ ለሙሉ በምርጫ ክልሉ እንዳይደረግ እንዲታደግ ተወስኖ ነበር፡፡ በዚህ የምርጫ ክልል ሥር የሚገኙ ሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ውጤቶች ወደ ማዕከል መጥተው እንዲቆጠሩ እየተደረገ መሆኑም ተነግሯል፡፡

በዚህም ሳቢያ በአካባቢው የተወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወኪሎች፣ የምርጫ ክልሉ ኃላፊዎችና ማስተር አሠልጣኞች በተገኙበት ቆጠራ እየተከናወነ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት የምርጫ ክልሉ 86 የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት ቆጠራ በማዕከል እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ቦርዱ እነዚህና የሌሎች የምርጫ ክልሎች ውጤቶችን በማዕከል እየተቀበለና እያረጋገጠ የሚገኝ ሲሆን፣ ካሁን ቀደም የትራንስፖርትና የማዳመር ሥራ ጊዜ በመውሰዱ ምክንያት ውጤት ወደ ማዕከል ሳይመጣ ከዘገየባቸው 30 የምርጫ ክልሎችን ጨምሮ፣ ከሁሉም የምርጫ ክልሎች የምርጫ ውጤቶች ተጠቃለው ገብተዋል ተብሏል፡፡ ስለዚህም ቦርዱ የምርጫውን የተጠቃለለ ውጤት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እስካሁን 53 የፓርላማ መቀመጫዎችን ውጤት ቦርዱ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ካሸነፏቸው ሦስት መቀመጫዎች ውጪ ያሉ መቀመጫዎች በሙሉ ያሸነፈው ብልፅግና ፓርቲ ነው፡፡

የምርጫ ቦርድ ቅሬታ የቀረበባቸውን የምርጫ ክልሎች በመመልከት እስከ ሐሙስ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ውሳኔ እሰጣለሁ ያለ ሲሆን፣ አቤቱታ ከቀረበባቸው 165 የምርጫ ክልሎች መካከል በደቡብ 40፣ በኦሮሚያ ሁለት፣ በድሬዳዋ አንድ፣ በአፋር 21፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ስድስት፣ በአዲስ አበባ 23፣ በሲዳማ ስምንት፣ በአማራ 49 እና በጋምቤላ ሦስት የምርጫ ክልሎች ይገኙበታል፡፡

ቅሬታዎችን አደራጅቶና ሕጋዊ የሰነድ ቅርፅ አስይዞ ለማቅረብ ሦስት የሕግ ድርጅቶች ተቀጥረው፣ 30 ሰዎች በሦስት ቡድኖች ተከፍለው እየሠሩ እንደሚገኙም ወ/ሪት ሶልያና አስታውቀዋል፡፡

በፓርቲዎች እየቀረቡ ያሉ ቅሬታዎች፣ ‹‹በምርጫ ጣቢያዎች መግባት የማይገባቸው ሰዎች ገብተዋልና አስተዳደራዊ ውሳኔ ይሰጥልን፣ የምርጫ ማዳመር ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወኪሎች ሳይገኙ ተከናውኗልና እንደገና ቆጠራ ይከናወን፣ ወይም ውጤት ተሰርዞ ድምፅ በድጋሚ ይሰጥ›› የሚሉ እንደሚገኙበት ወ/ሪት ሶልያና አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...